ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 9 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, March 19, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 9

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዘጠኝ በዚህች ቀን ተጋዳይ የሆነ ጽኑዕ አባት ቅዱስ_ኩትን አረፈ፣ የከበረ ቅዱስ_እንድርያኖስና_ሚስቱ_አውሳብዮስና_አርማ በሰማዕትነት አረፉ፡፡


መጋቢት ዘጠኝ በዚህች ቀን ተጋዳይ የሆነ ጽኑዕ አባት ኩትን አረፈ። እርሱም በሶርያ አገር ስሟ በንጣንዮስ ከምትባል ቦታ የሚኖር ነው። አባቶቹም ከዋክብትን ያመልኩ ነበር የአባቱ ስም ንስጣር የእናቱም ስም ቴዎድራ ይባላል።
በአደገ ጊዜም ወላጆች ሊአጋቡት ፈለጉ እርሱ ግን አልወደደም ግድ ብለው ያለውዴታው ሚስትን አጋቡት ሊገናኛትም አልፈለገም ስለ ሥጋ ድካም ወይም ስለ ጽድቅ ሳይሆን የሥጋ ፍትወትን ስለሚጠላት ነው እንጂ። ደናግልም እንደሆኑ ሁለቱ ሁሉ ከሚስቱ ጋራ በአንድነት ኖረ።
አምላክ ሆይ ወደ ዕውቀትህ ምራኝ በማለት ጸሎትና ምልጃን ያዘወትር ነበር። ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ለቆርኔሌዎስ እንደተገለጠ ተገልጦ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን አስተማረው ከሐዋርያትም ወደ አንዱ ሔዶ የክርስትና ጥምቀትን እንዲጠመቅ አዘዘው።
የሐዋርያት የስብከታቸው ወራት ነበረና ሒዶ ተጠመቀ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ሁሉ ሕጉን ሥርዓቱንም ሁሉ ተማረ መለኮታዊ ምሥጢርንም ተቀበለ። በየቀኑ ሁሉ የሐዋርያ ጳውሎስን ትምህርት ይሰማ ነበር የጽድቅን ሥራ መሥራትና ንጽሕና ለበጎ ሥራ መጠመድ ትጋት ቅንነት የዋህነት ጾም ጸሎት ሰጊድ በላዩ ተጨመረ። በእነዚህ ሁሉ የሚተጋ ሆነ እግዚአብሔርም አስደናቂ ተአምራቶችን እንዲአደርግ በርኲሳን አጋንንት ላይ ሥልጣንን ሰጠው።
በሚያደርገው ተአምራትም ወላጆቹን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደማመን ስቦ አስገባቸው ደግሞ ሚስቱንና ወላጆቿን አስገባቸው።
ከከሀድያን አንዱ ለሰይጣን ሊሠዋ ወደ ጣዖቱ ቤት በገባ ጊዜ ቅዱስ ኩትን አውቆ በሰይጣን ላይ ጮኸ እርሱ ሰይጣን እንጂ አምላክ እንዳልሆነ በሰው ፊት ያምን ዘንድ አዘዘው። ሰይጣንም እንዳዘዘው ራሱን ገለጠ በዚያ የነበሩ ሁሉም የቅዱስ ኩትን አምላክ አንድ እርሱ ብቻ ነው እያሉ ጮኹ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ።
ከዚህ በኋላ ከቀላውዴዎስ ቄሣር የተላከ መኰንን የቅዱስ ኩትንን ዜናውን በሰማ ጊዜ ወታደር ልኮ አስቀረበው ስለ ሥራውም ጠየቀው እርሱም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ መኰንኑም ጽኑ ግርፋት ገርፈው እንዲአሥሩት አዘዘ ይህንንም አደረጉበት።
የአገር ሰዎችም ቅዱስ ኩትንን አሠቃይተው እንዳሠሩት በሰሙ ጊዜ ሁሉም ወደርሱ ተራወጡ መኰንኑንም ሊገሉት ወደዱ መኰንኑም ሸሸ። ቅዱስ ኩትንንም ከማሠሪያው ፈትተው ከደሙም አጥበው ተሸክመው ወደቤቱ ወሰዱት ከዚያም በኋላ ብዙ ዘመናት ኑሮ የወደደውን እግዚአብሔርን አገልግሎ ደስ አሰኝቶ በፍቅር አንድነት አረፈ። ከዕረፍቱም በኋላ ቤቱን ቤተ ክርስቲያን አድርገው ሥጋውን በውስጥዋ አኖሩ ጌታችንም ከሥጋው ብዙዎች ታላላቅ ተአምራቶችን አሳየ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የከበረ እንድርያኖስና ሚስቱ አውሳብዮስና አርማ ሌሎች አርባ ሰዎችም በሰማዕትነት አረፉ።
እሊህንም ምርጦች ለረከሰ ከወርቅና ከብር ለተሠራ ጣዖት ማምለክን እምቢ ስላሉ የክብር ባለቤት ለሆነ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለስሙ ዐላውያን ጽኑ የሆነ ሥቃይን አሰቃዩአቸው።
ከዚህም በኋላ ራሶቻቸውን በሰይፍ ቆረጡ የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages