ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 12 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, April 20, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 12

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ዐሥራ ሁለት በዚህችም ዕለት የመላእክት አለቃ ቅዱስ_ሚካኤልን እግዚአብሔር ወደ ነብዩ_ኤርምያስ ላከው፣ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አባ_እለእስክንድሮስ አረፈ።


ሚያዝያ ዐሥራ ሁለት በዚህችም ዕለት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን እግዚአብሔር ወደ ነብዩ ኤርምያስ ላከው፡፡ ጠባቡና ረግረግ ከሆነ እሥር ቤት ሴዴቅያስ ንጉሥ በአሠረው ጊዜ የንጉሡ ባለሟልና የጭፍራ አለቃ የሆነው አቤሜሌክ አወጣው።
ያንጊዜም የኢየሩሳሌምን ጥፋት እንዲያይ መራራ ምርኮንም እንዳይቀምስ ኤርምያስ ነብይ መረቀው እንዲሁም ሆነ። ስሳ ስድስት ዓመትም ተኝቶ ኖረ ከእርሱ ጋራ ወይንና በለስ ነበረ አልተለወጠም የእስራኤል ልጆች ከምርኮ እስቲመለሱ በለሱንም ከደብዳቤ ጋራ ወደ ኤርምያስ ባቢሎን አገር ላከው።
ስለዚህም የዚህን የከበረ መልአክ ሚካኤልን በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን መታሰቢያውን እንድናደርግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አባ እለእስክንድሮስ አረፈ። ይህ ቅዱስም አስቀድሞ በቀጰዶቅያ አገር ኤጲስቆጶስነት ተሹሞ ነበር። እርሱም የከበሩ ቦታዎችን ተሳልሞ በረከት ተቀብሎ ወደ አገሩ ሊመለስ አስቦ ኢየሩሳሌም መጣ።
በኢየሩሳሌምም ስሙ በርኪሶስ የሚባል መቶ ዐሥር ዓመት የሆነው ጻድቅ ሰው ነበረ ሹመቱንም ሊተው ይወድ ነበረ ወገኖቹ ግን አልለቀቁትም።
ቅዱስ እለእስክንድሮስም ሥራውን ፈጽሞ ወደ አገሩ ቀጰዶቅያ ሊመለስ በፈለገ ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ የሚል ቃል እነሆ ከሰማይ አሰማ። ወደ እገሌ በርውጡ አስቀድሞ የሚገባውንም ይዛችሁ በላያችሁ ኤጲስቆጶስነት ሹሙት። ያን ጊዜም ሲወጡ አባ እለእስክንድሮስን አገኙትና ያዙት። እርሱም እኔ የቀጰዶቅያ ኤጲስቆጶስ ነኝ የክብር ባለቤት ክርስቶስ በእነርሱ ላይ የሾመኝን መንጋዎቼን ልተው አይቻለኝም አላቸው።
እነርሱም ከሰማይ ስለሰሙት ስለዚያ ቃል ስለርሱም እንደአመለከታቸው ነገሩት። ይህ ነገር ከእግዚአብሔር እንደሆነ በተረዳ ጊዜ ለበዓሉም የተሰበሰቡ አባቶች መከሩት ቃላቸውንም ተቀበለ ወደ ሀገሩ ቀጰዶቅያም እንዲህ ብሎ መልእክት ጽፎ ላካት። ይቅርታ አድርጉልኝ በእኔ ላይ አትዘኑ በእናንተ ላይም ኤጲስቆጶስ በእኔ ፈንታ ሹሙ እናንተም የተፈታችሁ ናችሁ ያቺን መልእክትም ከእርሱ ጋራ አብረው ከመጡ ከቀጰዶቅያ ሰዎች ጋራ ላከ።
ከዚህም በኃላ እየተራዳው አምስት ዓመት ያህል ከአባ በርኪሶስ ጋራ ኖረ። ከዚህም በኃላ ሽማግሌው አባ በርኪሶስ አረፈ። አባ እለእስክንድሮስም መንጋውን ተረክቦ እንደ ሐዋርያት በመልካም አጠባበቅ ጠበቃቸው። ከሀዲ መክስምያኖስም በነገሠ ጊዜ ይህን አባት ይዞ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ አሠቃየው። ከዚያም በላዩ የሚያደርግበትን እስከሚያስብ ድረስ አሠረው፡፡ ጌታችንም ይህን ከሀዲ ፈጥኖ አጠፋው፣ ወገኖቹም ይህን አባት እለእስክንድሮስን ከእሥር ቤት አወጡት።
ገርድያኖስም በነገሠ ጊዜ ጸጥታና ሰላም ሆነ ከክርስቲያን ወገኖች ላይም ጥቂት ወራት መከራው ጸጥ አለ። ገርድያኖስም በሞተ ጊዜ በርሱ ፈንታ አማኒ የሆነ ፊልጶስ ነገሠ። እርሱም በክብር ባለቤት በጌታችን ስለሚአምን በክብር ባለቤት በጌታ ክርስቶስ ሰም የታሠሩትን ምእመናንን ፈታቸው እጅግም አከበራቸው ይህም አባት በጸጥታ ኖረ።
ከዚህም በኃላ ከሀዲ ዳኬዎስ ተነሣ ፊልጶስንም ገድሎ መንግሥቱን ወሰደ ክርስቲያኖችንም እጅግ አሠቃያቸው ይህንንም አባት ያዘው ብዙዎችንም የቤተ ክርስተያን ሊቃውንት ጽኑ ሥቃይም አሠቃያቸው። ይልቁንም ይህን አባት አብዝቶ አሠቃየው ጽኑ ግርፋትንም ገርፎ ስለት በአላቸው በትሮች የጐኑ ዐጥንቶች ተሰብረው ወደሆዱ እስቲገቡ አስመታው።
ከዚህም በኃላ እስከ እሥር ቤት ጐትተው በዚያ እንዲጥሉት አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት።እግዚአብሔር ለመረጣቸው ያዘጋጀውን መንግሥተ ሰማይ እስከ ወረሰ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ እስከ ሰጠ ድረስ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየታመነ በዚያ ወድቆ ኖረ በጸሎቱ የምትገኝ በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages