ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 11 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, April 20, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 11

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም



ሚያዝያ ዐሥራ አንድ በዚች ዕለት የከበረችና የነጻች እመሜኔት ታዖድራ አረፈች። ይቺም ቅድስት ከእስክንድርያ አገር ከታላላቆች ባለጸጎች ወገን ናት። ወላጆቿም ክርስቲያኖች ናቸው። እነርሱም ዋጋው ብዙ በሆነ በወርቅና በብር ያጌጡ የከበሩ ልብሶችን አሠሩለት ከእርስዋ በቀር ልጅ ስለሌላቸው ሊአጋቡአት እነርሱ ያስባሉና።
እርሷ ግን የምንኲስና ልብስ ለብሳ በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ልትጋደል ትወዳለች መከራ መስቀሉንም ልትሸከም ትወድ ነበር የዚህን የኃላፊውን ሠርግ አልፈለገችም። ከዚህም በኃላ የወላጆቿን ዕቃ ገንዘብ ወስዳ ለሚሸጥላት ሰጠችው ለድኆችና ለምስኪኖች መጸወተች በቀረውም ከእስክንድርያ ውጭ በስተምዕራብ አብያተ ክርስቲያናትን አነፀች።
ወደ እስክንድያው ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ አትናቴዎስም ሔዳ ራሷን ተላጭታ ከእርሱ ዘንድ መነኰሰች። ከደናግል ገዳማትም ወደ አንዱ ገብታ በገድልም ተጸምዳ ጽነዕ ገድልን ተጋደለች አምላካዊ ራእይንም ታይ ዘንድ ተገባት መላእክትን ታያለችና የሰይጣናትንም ሥራቸውን ለይታ ታውቃለችና ለሠሩ የታሰቡትን የምታውቅበትና የምትፈትንበት እውቀት ተሰጣት።
ቅዱስ አትናቴዎስም በእርሷ ፈጽሞ ደስ ይለው ነበር ወደርሱም ይጠራታል እርሱም ሊጎበኛት ወደርሷ ይሔዳል ኀሳቧንም ትገልጥለታለች እርሱም የጠላት ደያብሎስን ወጥመዱንና ምትሐቱን ያስገነዝባታል። ከመንበረ ሢመቱ ከእስክንድርያ በአሳደዱትም ጊዜ ብዙዎች ድርሳናትን ጽፎ ላከላት።
ይቺም ቅድስት እጅግ እስከአረጀች ድረስ ኖረች በመንፈሳዊ ተጋድሎም የጸናች ናት እርስዋ ከአምስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ተምራለችና። እሊህም እለ እስክንድሮስ አትናቴዎስ ጴጥሮስ ጢሞቴዎስና ተዎፍሎስ ናቸው።
እንዲህም ብለው ጠየቋት ሰው ተርታ ነገር ቢናገር ዝም በል ሊሉት ወይም እንዳይሰሙት ጆሮአቸውን መክደን ይገባልን እንዲህም ብላ መለሰች ምንም ምን ሊሉት አይገባም ነገሩ ደስ እንዳላቸው ሆነው ዝም ይበሉ እንጂ ሰው ማዕዱን በፊትህ ቢያኖር በላይዋም በጎ የሆነና ብላሽ የሆነ ምግብ ቢያኖር ይህን ብላሹን ከእኔ ዘንድ አርቀው አልሻውም ልትለው አይቻልህም መጥፎውን ትተህ ከምትፈቅደው ትበላለህ እንጂ ያለ ትሕትና ያለ ጾምና ጸሎት ሰይጣንን ድል የሚነሣው የለም።
መላ ዕድሜዋም መቶ ዓመት ሆኖዋት በሰላም።
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages