አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሚያዝያ ዐሥር በዚች ቀን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ_ሳሙኤል_ዘቆየጻ ልደታቸው ነው፣ የታላቁ አባት የአባ ዕብሎ ረድእ ቅዱስ_ይስሐቅ አረፈ፣ ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ_ገብርኤል አረፈ።
ሚያዝያ ዐሥር በዚህች ቀን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ ሳሙኤል ዘቆየጻ ልደታቸው ነው፡፡ ሀገራቸው ትግራይ ቆየጻ ከተባለው ቦታ ነው፡፡
አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ካመነኮሷቸው ከሰባቱ ከዋክብት ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ ይህ ጻድቅ በተለየ ሁኔታ በሊቅነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ከ5 ሺህ በላይ ተከታይ መነኮሳት ነበሯቸው፡፡ 120 የሐረግ ሥዕላት ያሉት ትርጓሜ ወንጌል በ4 ዓምድ አድርገው በብራና ላይ ጽፈው እንደ አይሁድ 70ው ሊቃውንት እሳቸውም 70 እውቅ የሀገራችንን ሊቃውንት ሰብስበው እጅግ ትልቁን ትርጓሜ ወንጌል በጉባኤ አስወስነዋል፡፡
በጉባኤውም ካስወሰኑ በኋላ ወስደው ከሙታን መቃብር ላይ ቢጥሉት 211 ሙታን ተነሥተው ነአምን በአምላከ ጻድቃን ወሰማዕታት በጸሎተ ሳሙኤል ተንሣዕነ ብለው መስክረዋል። ወንጌላቸውንም በሊቃውንት ሲያጽፉ ቀለሙን ቅዱሳን መላእክት ያመጡላቸው ነበር፡፡
ጻድቁ ባረፉ ጊዜ 5 ነብሮች መጥተው መቃብራቸውን ቆፍረው ቀብረዋቸዋል፡፡ ትልቁ ገዳማቸው በትግራይ ክፍለ ሀገር እንዳ ሥላሴ ቆሪሮ ወረዳ ውስጥ ይገኛል፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን የታላቅ አባት የአባ ዕብሎ ረድእ ቅዱስ ይስሐቅ አረፈ። ይህም ቅዱስ ይህን ዓለም ተድላ ደስታውን ምቾቱን ጣዕሙን ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወጥቶ መነኰሰ ። ለአባ ዕብሎም ረድእ ሁኖ ሃያ አምስት ዓመት ሲያገለግለው ኖረ።
ሥጋውም እሰኪደርቅ ድረስ ጹኑዕ ተጋድሎን ተጋደለ ። ከሰውነቱም ሥጋዊ ፍላጎትን ሁሉ አጠፋ ባሕርዩ ቀንቶለት ኖረ በጸሎትና በቅዳሴም ጊዜ ጸጥታን አጸና ። የቍርባን ቅዳሴ ጸሎትም እስኪፈጸም ሁለት እጆቹ የኋሊት ታሥረው ራሱን አዘንብሎ እያለቀሰ ይቆማል።
ከቅዳሴም በሚወጣ ጊዜ በዚያች ዕለት ከሰው ወገን ከማንም ጋራ አይገናኝም በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜ ከአንተ ጋራ መነጋገር ከሚፈልግ ሰው ጋራ ለምን አትነጋገርም ብለው በጠየቁት ጊዜ እንደሚገባ ለሁሉ ጊዜ አለው ብሎ መለሰ ።
ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ በረከት ከርሱ ሊቀበሉና በጸሎቱም ሊማጻኑ መነኰሳት ወደርሱ ተሰበሰቡ። ከሰው ለምን ትሸሻለህ ብለው ጠየቁት እርሱም ከሰይጣን እንጂ ከሰው የምሸሽ አይደለም አንድ ሰው መብራት እያበራ በነፋስ ውስጥ ቢቆም መብራቱ የሚጠፋ አይደለምን? እንዲሁ እኛም በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜ ልባችን ብሩህ ሁኖ ሳለ ከሰው ጋራ ተገናኝተን እርስበርሳችን በተነጋገርን ጊዜ ልባችን ይጨልማል ብሎ መለሰ።
ይህም አባት መልካም ገድሉን ፈጽሞ በገድሉም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው ጊዜ ጌታችንም ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ድካም ሊአሳርፈው ወደደ። ጥቂትም ታሞ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ገብርኤል አረፈ። ይህም ቅዱስ የምስር አገር አለቆች ከሆኑት ከልጆቻቸው ውስጥ ነው። በግብጽ ባለች በቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያንም ዲቁና ተሾመ ዐዋቂና ጥበበኛም ስለሆነ ጸሐፊ ሁኖ ብዙዎችን መጽሕፍቶች ጻፈ የሚበዙትንም በዐረብና በቅብጥ ቋንቋ ተረጐመ። ከመሆኑ በፊት ሁሉን አይቶ በመንፈስ ቅዱስ የሚናገር የእግዚአብሔር ጸጋ በላዩ ያደረች ሶርያዊ አባ ዮሴፍ የሚባል አንድ አረጋዊ ሰው ነበረ።
አረጋውያን መነኰሳትና ኤጲስቆጶሳት ወደርሱ ተሰብስበው ለዚች ለከበረች የሊቀ ጵጵስና ሹመት ማን እንደሚሻል ይገልጥላቸውና ይነግራቸው ዘንድ ለመኑት።
እርሱም የታሮይክ ልጅ አንድ ሰው አለ ብሎ መለሰላቸው ምልክቱንም አመለከታቸው መነኰሳቱና ኤጲስቆጶሳቱም በዚህ ወደው ተስማሙ ከዓመተ ሰማዕታትም በስምንት መቶ ዓመት የካቲት ሃያ አንድ ቀን ይዘው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።
ወደ አስቄጥስ ገዳምም በሔደ ጊዜ መታመንን ጨመረ ይቺም በባስልዮስ ቅዳሴ ፍጻሜ ከመለኮቱ ጋር አንድ ሆነ የምትል ናት። መለኮቱ ከትስብእቱ ተጨመረ ብሎ እንዲህ እንዳያስብ መነኰሳቱ ስለፈሩ እኛስ ልማዳችን እንዲህ አይደለም አሉት። ከብዙ ምርምርም በኋላ ይች ቃል ከሚከተላት ያለ መለያየት ያለ መጨመርና ያለ መደባለቅ ከሚለው ጋራ ተሰራች በበጎ አቀባበልም ተቀብለዋት እስከዚች ቀን ጻንታ ኖረች።
በሹመቱ ወራትም ብዙዎች በጎ ሥራዎች ተሠሩ ሙታንን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳይቀብሩዋቸው በውግዘት ከለከለ ሁለተኛም ዕቁባቶችን በእነርሱ ዘንድ ያኖሩትን አውጥተው እንዲሰዱ አወገዘ ።
ይህም አባት ስለሙታን ርስትና ስለሌሎች ሥራዎች የሕግና የሥርዓት መጽሐፍን ደረሰ፡፡ ከቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትም ብዙዎችን ተረጐመ፡፡ በዘመኑም ኃምሳ ሦስት ኤጲስቆጶሳትንና ብዙ ካህናትን ሾመ፤ ነገረ ግን ከእርሳቸው አንድ አላድ እንኳ አልተቀበለም።
የግብጽ ንጉሥም በግፍ ከእርሱ ገንዘብ ሽቶ አሠቃየው እንዲጠባበቁትም ሰላዮችን በላዮ አኖረ። ጸሐፊዎችና ሹሞች ከሕዝቡም ታላላቆች ከሕዝቡም ሆነ ከአብያተ ክርስቲያናት ወይም ከገባሬዎች ምንም ምን እንዳልወሰደ በአወቁ ጊዜ ስለዚህ ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር ሰብስበው ስለርሱ ለንጉሡ ሰጡት ።
የዕረፍቱም ጊዜ ሲቀርብ እግዚአብሔርም ትሩፋቱንና ጽድቁን ለሰው ሊገልጽ ወደደ ጥቂትም ታመመ ብዙ ካህናትና መነኰሳትም ወደ ርሱ እንደ መጡ በሌሊት ራእይ አየ። እነርሱም ወንጌሎችን መስቀሎችንና ማዕጠንቶችን በእጆቻቸው ይዘዋል። እንዲህም አሉት እኛ ልንጐበኝህ መጣን ከዓመትም ፍጻሜ በኋላ ወደአንተ ተመልሰን መጥተን ከእኛ ጋራ እንወስድሃለን ። በነቃም ጊዜ ከእርሱ ዘንድ ላሉ መነኰሳትና ኤጲስቆጶሳት ለካህናትም እንዴት እንዳየ ነገራቸው ከደዌውም ዳነ።
ከዓመት ፍጻሜም በኋላ ጥቂት ታመመ አስቀድመው ወደርሱ መጥተው የነበሩትን ካህናትና መነኰሳት ደግሞ አያቸው፤ ሰላምታም ሰጡት ። ከእንርሱም ጋራ ደስ አለው በዚያን ጊዜም ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጥቶ በሰላም አረፈ፡፡ በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ዓሥራ አራት ዓመት ከኖረ በኋላ ነው።
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment