አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ከዚህም በኋላ ያ ሰው እኔ በአባ መቃርስ ገዳም በነበርኩ ጊዜ ስጸልይ የሊቀ ጵጵስና ሹመት ለሚካኤል ይገባዋል ለዚች ሹመት የሚሻል እሱ ነውና የሚል ቃልን ከሰማይ ሰማሁ አላቸው፡፡ ሁሉም ስለ ትሩፋቱ ተናገሩ ስለ እርሱም ተስማምተው ከገዳሙ ወደ እስክንድርያ ሊያመጡት ከመስር ገዥ ዘንድ ደብዳቤ አጽፈው ያዙ።
ሊያመጡትም ሲሔዱ ስለ ገዳሙ አገልግሎት ከሽማግሎች መነኰሳት ራር ወደ ጋዛ ከተማ ሲመጣ በመንገድ አገኙት ይዘውም አሠሩት። ወስደውም በመስከረም ወር በዐሥራ ሰባት ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ያቺም ዕለት በጌታ ደም የከበረ መስቀል በዓሉ የሚከበርባት ናት።
ይህም የሆነው ከዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በኋላ የሐሚድ ልጅ እልሲድ በሚገዛበት ዘመን ነው። በሹመቱ ወራትም መርዋን አልጋዲን ነገሠ። የእስክንድርያም አገር ሰዎች ከጥቂት ካፊያ በቀር ብዙ ዝናብ ሳይዘንብላቸው ብዙ ዓመታት ኖሩ። በዚያች እርሱ በተሾ መባት ቀን በሁለተኛውም በሦስተኛውም ብዙ ዝናብ ዘንቦላቸው እጅግ ደስ አላቸው።
በዚህም አባት ዘመን በክርስቲያን ወገኖች ላይ ታላቅ መከራ ደረሰ ከምእመናንም ብዙዎች ሸሹ የክብር ባለቤት ክርስቶስንም የካዱት ሰዎች ቁጥራቸው ሃያ አራት ሺህ ሆነ። ለዚህ ነገር ምክንያት የሆነውን ከእርሱ እግዚአብሔር እስከአጠፋው ድረስ ይህ አባት ስለዚህ በታላቅ ኀዘን ውስጥ ነበር።
ዳግመኛም በዚህ አባት ዘመን ለመለካውያን ቆዝሞስ ሊቀ ጵጵስና ተሹሞ ሳለ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ ክርስቶስ ተዋሕዶ ከዚህ አባት ከአባ ሚካኤል ጋራ ተከራክሮ ይህ አባት አባ ሚካኤል እንዳስረዳው አመነ።
እንዲህም ብሎ በእጁ ጻፈ የክብር ባለቤት ክርስቶስ ከተዋሕዶ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት ቄርሎስ እንደተናገረ የመለኮቱና የትስብእቱ አንድ ባሕርይ በመሆን ጸንቶ ይኖራል ሲል ኤጲስቆጶሳቱም እንዲሁ ከተዋሕዶ በኋላ ስለ ክርስቶስ የተለያዩ ሁለት ባሕርያት ሁለት ገጻት አሉት ይሉ ዘንድ የሚገባ አይደለም ሲሉ ጻፉ።
ሐዋርያትም በሰበሰቧት በከበረች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአንድነት ጸንተው ሊኖሩ ተስማሙ። ከዚህም በኋላ ከእስክንድርያ ሰዎች መለካዊ የሆነ ስሙ አንስጣስዮስ የሚባል ሰው በላያችው ጥፋትን አመጣ እርሱ ኤጲስቆጶስነት እንዲሾሙት ሽቶ አልሾሙትምና ስለዚህ ወደ እስላሞች ንጉሥ ሒዶ በአባ ሚካኤል ነገር ሠራበት ከዐመፀኞች ነገሥታትም ብዙ መከራ ደረሰበት። ጽኑዕ የሆነ ሥቃይም አሠቃዩት ብዙ ግርፋትም ገረፈው ለረጂም ጊዜ በእግር ብረት አሠሩት። አንገቱንም በሰይፍ ሊቆርጡ ወደ መኰንኑ አቅርበውት ነበር ስለ መንጋዎቹም ጥበቃ እግዚአብሔር አዳነው።
ዳግመኛም በመርዋን አልጋዲ ዘመነ መንግሥት የሙሴ ልጅ በሆነ በንጉሥ አገልጋይ አደባባይ በታላቅ ሥቃይ አሠቃዩት። መኰንኑም ገንዘብ እንዲሰጠው ሽቶ ሊቀ ጳጳሳቱን አባ ሚካኤልን አሠረው ሰዎችም መጥተው ዋስ ሁነው አወጡት። ምጽዋትም ጠይቆ ለመኰንኑ ብዙ ገንዘብ አምጥቶ እንዲሰጠው ወደ ላይኛው ግብጽ ወሰዱት።
ይህ አባትም ወደ ላይኛው ግብጽ በሔደ ጊዜ በዚያ ብዙ ተአምራትን አድርጎ የክብር ባለቤት ክርስቶስን የካዱትን ምእመናን ብዙዎቹን ወደቀናች ሃይማኖት መልሶ አስገባቸው።
የኢትዮጵያ ንጉሥም ይህን አባት የእስላሞች መኳንንት እንዳሠቃዩት በሰማ ጊዜ ፍጹም ኀዘንንም አዘነ። መንፈሳዊ ቅናትንም ቀንቶ ወደ ግብጽ አገር ዘምቶ ከላይኛው ግብጽ ደረሰ፡፡ ከርሱ ጋርም መቶ ሺህ ፈረሰኞች አርበኞች መቶ ሺህ በበቅሎ የተቀመጡ አሁንም በግመል የተቀመጡ መቶ ሺህ አርበኞች ወታደሮች ነበሩ ብዙ አገሮችንም አጠፉ ብዙዎችንም ማረካቸው።
የግብጽ ንጉሥም ይህ ሁሉ የሆነው ስለ ሊቀ ጳጳሳቱ ስለ አባ ሚካኤል እንደሆነ ዐውቆ ከእሥራቱ ፈጥኖ ፈታው ታላቅ ክብርንም አከበረው እንዲሁም የክርስቲያንን ወገኖች ሁሉ እጅግ አከበራቸው።
ከዚህም በኋላ ለኢትዮጵያ ንጉሥ ደብዳቤ ጽፎ ይልክ ዘንድ ወደ አገሩም እንዲመለስ ያዝዘው ዘንድ የግብጽ ንጉሥ ይህን አባት አባ ሚካኤልን ለመነው። ይህም አባት ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥ እርሱንና መኳንንቱን መሳፍንቱንና ሠራዊቱን እየባረከና እየመረቀ ደብዳቤ ጽፎ ላከ ።እንዲህም አለው እነሆ በአንተ ምክንያት ከእሥራትና ከዽቃይ ሁሉ እግዚአብሔር አድኖናልና አሁን ወደ አገርህ በሰላም በፍቅር ተመለስ ስለ እኔና ስለ ክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ስለ ደከምክ መልካም ዋጋህን እግዚአብሔር በመንግሥተ ሰማያት ይስጥህ።
የኢትዮጵያ ንጉሥም የዚህን አባት የሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤልን ደብዳቤ በአነበበ ጊዜ ፈጥኖ ተነሥቶ ወደ አገሩ በሰላም በፍቅር አንድነት ተመለሰ።
አባ ቆዝሞስና ወገኖቹም ከሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋራ በተስማሙ ጊዜ አባ ቆዝሞስ በውዴታው ለምስር ኤጲስቆጶስ ሁኖ ተሹሞ ከዚህ አባት ከአባ ሚካኤል ስልጣን በታች ሆነ። ይህም አባት መልካም ተጋድሎውን በፈጸመ ጊዜ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ሔደ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የቅዱሱም አማልጅነቱ በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ይሁን አሜን።
No comments:
Post a Comment