ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 18 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, April 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 18

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዐሥራ ስምንት በዚች ቀን ቅዱስ_ኤስድሮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ የጻድቁ አባታችን አቡነ_እጨጌ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡


መጋቢት ዐሥራ ስምንት በዚች ቀን የሰማዕት ቅዱስ ፃና ጓደኛው የከበረ ኤስድሮስ በሰማዕትነት አረፈ። ፃና ግን ፈርማ በሚባል አገር ለአገረ ገዥው ከጦር ሠራዊቱ ውስጥ ወታደር ነበር እርሱም ከደቅስያ ሰዎች ወገን ነው ከበግ ጸጕር ልብሶችን ለሚሠራ ለኤስድሮስ ወዳጁ ነው።
ሁለቱም ሠርተው ከሚያገኙት ለድሆችና ለችግረኞች ይመጸውታሉ። በአንዱት ሌሊትም ከእርሷ ጋር አክሊሎች ያሉ ድንግል ሴት በራሳቸው ላይ ስታኖረው ሁለቱም ራእይን አዩ። ከእንቅልፋቸውም በነቁ ጊዜ ያዩትን እንዴት እንዳዩ ተነጋገሩ። ምስክሮቹ ሊሆኑ የጠራቸው እግዚአብሔር እንደሆነ አውቀው እጅግ ደስ አላቸው።
ከዚያም ተነሥተው ሒደው ወደ መኰንኑ ደረሱ ቅዱስ ፃናም ትጥቁን ፈትቶ በመኰንኑ ፊት ጣለው ሁለቱም በጌታችን በክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ማመናቸውን ገለጡ። መኰንኑም ነገራቸውን ሰምቶ አሥረው ይደበድቧቸው ዘንድ አዘዘ እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ አዳናቸው።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደእስክንድርያ ቅዱስ ፃናን ላከው ቅዱስ ኤስድሮስን ግን በዚያው ተወው ከጥቂት ቀኖችም በኋላ የእስክንድርያው መኰንን ቅዱስ ፃናን ወደ ፊርማ ከተማ መለሰው። ሁለቱ ቅዱሳንም ተገናኙ በመገናኘታቸውም ደስ ብሎአቸው በላያቸው በየአንዳንዳቸው የደረሰውን መከራ ተነጋገሩ።
ዳግመኛን በቅዱስ ኤስድሮስ ዐዘቅትን ይቆፍሩለት ዘንድ በዐዘቅቱም ውስጥ እሳትን አንድደው ቅዱስ ኤስድሮስን እንዲጨምሩት መኰንኑ አዘዘ። ቅዱሱም ጥቂት እስቲጸልይ ይታገሡት ዘንድ ወታደሮቹን ለመናቸው ወደ ጌታችንም ነፍሱን ይቀበል ዘንድ ለሥጋውም ያስብ ዘንድ ጸለየ።
ከዚያም ወደ እሳቱ ጕድጓድ ቀረበ ወደ እሳቱም ውስጥ ጨመሩት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ በሥጋውም ላይ ምንም ጕዳት አልደረሰም መልኩም አልተለወጠም። የቅዱስ ፃና እናትም ከሚወደው ጓደኛው ስለመለየቱ ታለቅስለት ነበር በዚያም ሥጋውን ተሸክመው ወሰዱ የስደቱም ወራት እስቲፈጸም በመልካም ቦታ አኖሩት።
ቅዱስ ኤስድሮስም ምስክር ሁኖ በሞተ ጊዜ የቅዱስ ፃና እናት ብዙ መላእክት የቅዱስ ኤስድሮስን ነፍስ ይዘው በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ሲያሳርጓት አየች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#አቡነ_እጨጌ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ (ፍልሰተ ዐፅማቸው)
ዳግመኛም በዚህች ቀን የጻድቁ አባታችን አቡነ እጨጌ ዮሐንስ ዘጠገሮ ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡ ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ተወለዱ፡፡ አባታቸው ድላሶር እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል፡፡ ወላጆቻቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡ አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ ‹‹በምን አውቀኸኝ ነው?›› ብላ አቅፋ ሳመችውና ‹‹ከእንግዲ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 ትኖራለህ›› ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡
ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዮሐንስ ለክርስቶስ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ 50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኃላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኩስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በድብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ አባ ዩሐንስ ወደ ተዘጋቸላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኃላ ይገኛል፡፡
ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው፡፡ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል፡፡ በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል፡፡ እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል። ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡
አባታችን በታላቀ ተጋድሎ ሣሉ ሰይጣን የሀገሩን ሰዎች በጠላትነት እንዲነሡባቸው አደረገ፡፡ ሰዎቹም አባታችንን እንዴት እንደሚያጠፏቸው ይማከሩ ጀመር፡፡ ሊገድሏቸው ፈልገው ቅድስናቸው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ፈሩ፡፡ ከዚኽም በኋላ ‹‹ለምን ከመንደራችን ከወንድ ያረገዘች ሴት ፈልገን እሳቸው አስረገዟት ብለን በሐሰት እንከሳቸው?›› ብለው ተማከሩ፡፡ ብዙ ወርቅና ብርም ለአንዲት ሴት ሰጥተው በሐሰት ከእርሱ አርግዣለሁ ብላ እንድትመሰክር አደረጓት፡፡ አባታችንም በሕዝብ ፊት በሐሰት ተከሰሱ፡፡ ጻድቁም ‹‹አንቺ ሴት ከእኔ ነው ያረገሽው?›› አሏት እርሷም ‹‹አዎ ከአንተ ነው ልትክድ ነው እንዴ?›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝነው ‹‹በአንቺና በእኔ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ›› ሲሉ ያች ሴት ወዲያው ለሁለት ተሰንጥቃ ሞተች፡፡ የአገሩ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ አባታችንም ምድሪቱን እረገሟት፡፡ ‹‹የተዘራው ዘር አይብቀልብሽ፣ የተተከለው አይፅደቅ፣ ብርድና ውርጭ ይፈራረቅብሽ›› ብለው እረግመዋት በደመና ተጭነው ወደ ሰሜን ጎንደር እስቴ ጉንደ ተክለተሃማኖት ሔዱ፡፡
አቡነ ዮሐንስ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እየተዘዋወሩ ያስተማሩ ሲሆን ከቅድስናቸው የተነሣ በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 የኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በይፋት ጠገሮ በዓለ ወልድ፣ በአፋር አዘሎ፣ በመንዝ ፍርኩታ ኪዳነምሕረት፣ በደብረ ሊባኖስ፣ በጉንደ ተክለ ሃይማኖት በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ አባታችን ከሰማይ መስቀል የወረደላቸው ሲሆን ዛሬም በገዳማቸው የሔደ ሰው በወረደው በእጃቸው መስቀል እየተዳበሰ ቆመው በጸለዩበት ባሕር በጠበላቸው ይጠመቃል፡፡
በተጨማሪም ይይዙት በነበረውም መቋሚያቸው በመዳበር በረከትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቆመው ከጸለዩበት ባሕር ውስጥ ደረቅ አሸዋ ይወጣል፡፡ አባ ዮሐንስ 500 ዓመት ከኖሩ በኋላ እረፍተ ዘመናቸው ሲደርስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከ15 ነቢያት፣ ከ12 ሐዋሪያት፣ ሄሮድስ ያስፈጃቸው ከመቶ አርባ አራት ሺ ሕፃናት፣ ከአብርሃም ከይስሐቅ፣ ከያዕቆብ ጋር ሁሉንም ነገደ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ‹‹ስምህን የጠራ ገዳምህን የረገጠ፣ መባ የሰጠ፣ ቤተ ክርስትያንህን የሠራ ያሠራ የረዳ፣ ገድልህን የሰማ ያሰማ ያስተረጎመ፣ መታሰቢያን ያደረገ እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለው፤ ንስሀ ሳይገባ አይሞትም፣ ልጅ መውለድ ባይችል እኔ ልጅ እሰጠዋለሁ፤ ገድልህን በቤትህ ያስቀመጠ እርኩስ መንፈስ፣ ክፉ አጋንንት ቸነፈር ወባ መልአከ ጽልመት አይነካውም፡፡ በገዳምህ መነኩሴ ቢቀበር በሰማይ ክንፍ አበቅልለታለሁ፤ አይሁድም አረማዊም ያላመነ ያልተጠመቀ በገዳምህ መጥቶ ቢያርፍ ይቅር እልልሃለሁ፣ እንደ መቃብሬ ጎልጎታ እንደተቀበረ አድርጌ እቆጥርልሃለሁ›› የሚል ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
ቅዱስ አባታችንም በ500 ዓመታቸው ሐምሌ 29 ቀን ዐርፈው በጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚገኘውን ይህንን ገዳም ጻድቁ ራሳቸው ናቸው የመሠረቱት፡፡ ነገር ግን የገዳሙን ስያሜ በአባታቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም አድርገውታል፡፡ አቡነ ዮሐንስ ካረፉ በኋላ በእርግማናቸው መሠረት በመንዝና በይፋት ብርዱ ድርቁ ስለበዛባቸው አንድ ብቁ ባሕታዊ ከበዓታቸው ወጥተው ‹‹በሐሜታችሁ ምክንያት እጨ ዮሐንስ ስለረገማችሁ ነው የእርሱን ዐፅም ካላመጣችሁ ብርዱ ውርጩ ድርቁም አይጠፋላችሁም›› አሏቸው፡፡ ሕዝቡም አባታችን በጉንድ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሩ ከ134 ዓመት በኃላ በቅዱሳን እየተመሩ ሄደው በሌሊት ግማሽ ዐፅማቸውን አምጥተው በሀገራቸው አምጥተው ስላስቀመጡ ብርዱና ውርጩ በመንዝ እየቀነሰላቸው መጥቷል፡፡ ዛሬም በሀገሩ ብርዱና ውርጭ ሲበዛ የጻድቁን ታቦት ሲያወጡ ውርጩ ይጠፋል፡፡ ጠገሮ በሚባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘው ጠበላቸው እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ግማሽ ዐፅማቸውን ከጉንደ ተክለሃይማኖት አምጥተው አርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ በላይ በፍሩክታ ኪዳነምሕረት መጋቢት 18 ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡
ምድሪቷም ተባረከች፣ የዘሩትንም አበቀለች፣ ውርጩም ብርዱም ቀነሰ፣ ዝናብ አልዘንብ ሲል ወይም ሰብል የሚጨርስ አንበጣ ሲመጣ ታቦታቸው ወጥቶ ምህላ ይያዛል ወድያውም መቅሰፍት ይርቃል፣ ዝናብም ይዘንባል፡፡ ጻድቁ ደመናን፣ ጨረቃንና ፀሐይን በእጃቸው እየያዙ ይጸልዩ ነበር፡፡ በጠገሮ፣ በአዘሎ፣ በፍርኩታና በሌሎቹም ታላላቅ ቦታቦዎች ላይ በእያንዳንዱ ገዳም ሃምሳ ሃምሳ ዓመት በጸሎት ኖረው በአጠቃላይ በ500 ዓመታቸው ነው ያረፉት፡፡ ዐፅማቸው መንዝ ከአርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ ፍርኩታ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages