ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 2 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, April 14, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 2

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ሁለት በዚህችም ቀን የቃይናን ልጅ የቅዱስ_መላልኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ ቅዱስ_ክርስትፎሮስ በሰማዕትነት አረፈ።


ሚያዝያ ሁለት በዚህችም ቀን የቃይናን ልጅ የመላልኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ መላልኤልም መቶ ስልሳ አምስት ዓመት ኖረ ያሬድንም ወለደው።
መላልኤልም ያሬድን ከወለደው በኃላ ሰባት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። የመላልኤልም መላ ዘመኑ ሁሉ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ዓመት ነው። ቅዱስ መላልኤልም ሚያዝያ ሁለት ቀን በእሑድ ዕለት ሞተ በማከማቻም ውስጥ ቀበሩት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_ክርስቶፎሮስ (ሐዋርያና ሰማዕት)
በዚችም ቀን ፊቱ እንደ ውሻ የሆነ ቅዱስ ክርስትፎሮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ ሰውን ይበሉ ከነበሩ ሰዎች ሀገር ነው በጦርነትም ማረኩት አባቱም በሐዋርያ ማትያስ እጅ ያመነ ነው። በማረኩትም ጊዜ ቋንቋቸውን አያውቅም ነበር የክብር ባለቤት ወደሆነ እግዚአብሔርም ማለደ ቋንቋቸውንም ገልጦለት እንደርሳቸው ተነሰገረ የክርስቲያን ወገኖችን የሚያሠቃዩአቸውንም ገሠጻቸው የጦር ሠራዊቱንም የሚመራ መኰንን ጽንዕ ግርፋትን ገረፈው። ቅዱስ ክርትፎሮስም መኰንኑን የጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዙ ኃይሌን ባትይዘኝና ባታስታግሠኝ አንተና ሠራዊትህ ከእኔ እጅ ባልዳናችሁ ነበር አለው።
መኰንኑም ስለ ርሱ ወደ ንጉሥ ላከ ከእርሱ የሆነውንም ነገረው። ንጉሡም ወደ ርሱ እንዲያመጡት ሁለት መቶ ወታደሮችን ላከለት እርሱም ያለ መፍራት ያለ ማፈግፈግ አብሮአቸው ሔደ። በእጁ በትር ነበረች በላይዋ በጸለየ ጊዜ በቀለችና አበበች። እነዚያ ወታደሮች ተርበው የሚበሉት እንጀራ በአጡ ጊዜ ቅዱስ ክርስትፎሮስ ጸለየ በእነርሱ ዘንድ እንጀራ በዝቶ ተትረፈረፈ እጅግም አድንቀው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። አባ ጳውሎስ እጅ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ።
ወደ ንጉሡም ፊት በደረሱ ጊዜ ንጉስ ዳኬዎስ ሊያስፈራውና ሊሸነግለው ጀመረ ደግሞ እጅግ መልከ መልካም የሆኑ ሁለት አመንዝራ ሴቶችን ወደርሱ ሰደደ እነርሳቸው እንደሚያስቱትና በኀጢአት እንደሚጥሉት አስቧልና። እርሱ ግን ገሠጻቸው አስተማራቸውም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በደማቸው ምስክር ሁኑ። እንዲሁም እነዚያ ሁለት መቶ ወታደሮች በንጉሡ ፊት በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ራሶቻቸውንም በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነትንም በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
ቅዱስ ክርስትፎሮስም ንጉሡን አንተ የሰይጣንን ሥራ የምትቀበል ማደሪያው የሆንክ ብሎ ዘለፈው ንጉሡም ተቆጥቶ በትልቅ ብረት ምጣድ ውስጥ እንዲጨምሩትና ከበታቹ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ። እንዲሁም አደረጉበት ነገር ግን ከጉዳት እንዳሰቡት ምንም የደረሰበት የለም። ጤነኛ ሆኖ ሰዎችን አስተማራቸው እንጂ። እጅግም አድንቀው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። ቅድሱንም ከእርሷ ሊአወጡት ወደዚያች ብረት ምጣድ ቀረቡ ንጉሡም አንገቶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘ የሕይወት አክሊልንም ተቀበሉ። ከዚያም በኃላ ታላቅ ደንጊያ በአንገቱ አንጠልጥለው ከጥልቅ ጉደረጓድ እንዲጨምሩት ንጉሡ አዘዘ በጨመሩትም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በጤንነት አወጣው። ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ ንጉሡ አዘዘ። ቅዱሱም በእግዚአብሔር መንግስት የድል አድራጊነትን አክሊል ተቀዳጀ፡፡
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages