ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 3 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, April 14, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 3

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ ሦስት በዚች ቀን የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የከበረ አባት አባ_ዮሐንስ አረፈ፣ የከበረ አባት በእስክንድርያ ለተሾሙ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባ አንደኛ የሆነ አባ_ሚካኤል አረፈ፣ ክርስቲያናዊ ነጋዴ ቅዱስ_መርቄ አረፈ።


ሚያዝያ ሦስት በዚች ቀን የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የከበረ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ የኦሪት ምሁራን የሆኑ አዋቂዎች ነበሩ የኦሪትን ሕግ ትምህርቶችንም እያስተማሩት አሳደጉት።
ክርስቲያኖችን በጸና ልቡና የሚከራከራቸውና የሚጣላቸው ነበር መጻሕፍትን አዘውትሮ ከመመርመሩ የተነሣ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም እንደመጣና ሰውም እንደሆነ በሞቱም ዓለምን እንደአደነ አመነ። እርሱም የባሕርይ አምላክ እንደሆነ አምኖ በኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ በአባ ዮስጦስ እጅ ተጠመቀ ዲቁናም ሾመው ከዚያም በኢየሩሳሌም ሀገር ኤጲስቆጶስነት ለመሾም እስቲገባው ድረስ በበጎ ስራና በዕውቀት አደገ።
ኤልያስ የሚባለው እንድርያኖስም በነገሠ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ሀገር የፈረሰውን ሕንፃ ሁሉ እንዲያንፁና በስሙ ኤልያስ ተብሎ እንዲጠራ አዘዘ። ከዚህም በአይሁድ ምኲራብ ደጃፍ ላይ ታላቅ ግምብ ሠሩ ከከበረ ድንጊያም ሠሌዳ ሠርቶ በላዩም ስሙን ኤልያስን ጽፎ በመግቢያው አኖረው በዘመኑም ኢየሩሳሌም አሕዛብንና አይሁድን ተመላች ሠለጡኑባትም።
ክርስቲያኖችም ሊጸልዩ ወደ ጎልጎታ ሲመጡ በአዩአቸው ጊዜ አሕዛብ ይከለክሉአቸው ነበር በዚያ ዝሁራ በሚባል ኮከብ ስም መስጊድ ሠርተው ነበርና። ስለዚህም ክርስቲያኖችን በዚያ እንዳያልፉ ይከለክሏቸው ነበር።
በዚህም አባት ላይ ከአሕዛብ ታላቅ መከራና በምድር ላይም ጐትተውታልና አጐሳቁለውታልና እርሱም ነፍሱን ወደርሱ ይቀበል ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው ጌታም ልመናውን ሰምቶ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ደግሞ የከበረ አባት በእስክንድርያ ለተሾሙ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባ አንደኛ የሆነ አባ ሚካኤል አረፈ። ይህ አባት ከታናሽነቱ ጀምሮ የምንኲስና ልብስ ሊለብስ ወደደ በአስቄጥስ ገዳም በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን መንኲሶ እስከ ሸመገለ ድረስ በዚያ ኖረ።
በብዙ መነኰሳትም ላይ አበ ምኔት ሆኖ ተሾመ በዘመኑ ሁለየ መልካም ተጋድሎ በመጋደል እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። በወንጌላዊው ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጵጵስና ለመሾም እስቲገባው ድረስ ፍጹም ተጋድሎ በመጋደል ደከመ።
ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ገብርኤል በአረፈ ጊዜ የወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ያለ ሊቀ ጳጳሳት አራት ወር ኖረ ለዚች ሹመት የሚሻል ሲመረምሩና ሲመርጡ ብዙ ደከሙ። ከብዙ ድካምም በኃላ ሦስት የገዳም ሰዎችን መርጠው ስማቸውን በሦስት ክርታስ ጻፉ የክብር ባለቤት የጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንም ስም በአንዲት ክርታስ ጽፈው እየአንዳንዳቸውን አሽገው በመሠዊያው ውስጥ አኖሩአቸው። ቸር ጠባቂ ይሾምላቸው ዘንድ ኤጲስቆጶሳቱና ካህናቱ እስከ ሦስት ቀን እየጸለዩና እየቀደሱ እግዚአብሔርን በመማለድ ኖሩ።
ከሦስት ቀኖችም በኃላ አንድ ታናሽ ብላቴና ጠርተው ከእነዚህ ከሦስቱ ስሞች አንዱን አንሥተህ ስጠን አሉት። ያም ብላቴና የዚህን አባት የአባ ሚካኤል ስም ያለበትን ያንን ክርታስ አወጣ። ሁሉም እግዚአብሔር እንደመረጠው አውቀው ይገባዋል ይግባዋል ይገባዋል እያሉ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት እርሱም በሹመቱ ላይሆኖ እንደሚገባ በመልካም አመራር ሥራውን መራ።
የሚጽፍለትም ጸሐፊ መረጡለት ስለ ምእመናን አጠባበቅና ስለማስተማር ወደ ሀገሮች ሁሉና ወደ ኤጲስቆጶሳቱ መልእክትን ይልክ ነበር። እርሱም ከኃጢአታቸው ተመልሰው ንሰሐ እንዲገቡ ሕዝቡን ይመክራቸውና ይገሥጻቸው ነበር እግዚአብሔርን ይፈሩት ዘንድ።
ንጽሐ ነፍስ ንጽሐ ልቡና ያለው ሆነ የዚህን አለም ጣዕም ያለውን ምግብ አይሻም አይመኝም ክብሩንም ቢሆን ወይም ጥሪቱን ድኆችንና ችግረኞችን አስቦ ይመጸውታቸው ነበረ እንጂ፡፡ ከእነርሱ የሚተርፈውንም ለቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ ያደረገው ነበር። ይህ አባት ሙሉ ዓመት አልኖረም ከዚያ የሚያንስ ነው እንጂ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ዳግመኛ ክርስቲያናዊ ነጋዴ መርቄ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከአንጾኪያ ሰዎች ወገን ነው ጉዝፋርም ጣዖት የሚያመልክ ከሀዲ ነው ከሃይማኖት በቀር በምንም በምን አይለያዩም። ከዕለታትም በአንዲቱ መርቄና ጉዝፋር ነበግዱድ ወደሚባል አገር ለንግድ ሒደው ሰው በሌለበት በበረሀ ውስጥ አምስት ቀን ተጓዙ ክርስቲያናዊ መርቄም ባለጸጋ ነው ከእርሱ ጋርም አርባ ልጥረ ወርቅ ነበረ።
በጐዳና በጉዞ ላይም እያሉ ለሞት የሚያደርስ ደዌን መርቄ ታመመ ከዚያም ራሱን አጽናንቶ እንዲህ ብሎ ጻፈ። "ከባሪያህ ልጅ ከባሪያህ መርቄ ለእኔ ያለ በጥቁር በቅሎ የተጫነ አርባ ልጥረ ወርቅ ለአንተ ይሁን ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሄር ልጅ የክብር ባለቤት ሆይ ስለ በደሌ ይቅር ብለኸኝ መንግሥተ ሰማያትን ትሰጠኝ ዘንድ ለልጆቼ ለሚስቴም ወይም ለዘመዶቼ አይሁን ብዬአለሁ።"
ይቺን ደብደቤ ጠቅልሎ ወዳጄ ጉዝፋርን ጠራው የሚለውን ሁሉ ያደርግለት ዘንድ አማለው። ከዚያም በምሞትበት ጊዜ አትንካኝ ግን ይህን አርባ ልጥረ ወርቅ እንደተጫነ ከበቅሎው ጋራ ወስደህ የክብር ባለቤት ለሆነ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በእጁ ስጠው። ለልጆቼ እንዳትሰጥ ከእርሱ በቀር ለማንም ቢሆን አትስጥ አለው።
ጉዝፋርም እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ ራስህ ሞቶ ተነስቶ ወደ ሰማይ ወጣ የምትል አይደለምን እኔ ወደ ሰማይ ወጥቼ ልሰጠው እችላለሁን። መርቄም እንዲህ አለው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒድ ራሱ ወደ አንተ ይመጣል እጅ በእጅ ስጠው።
ከዚህ በኃላ መርቄ ለመሞት ሲቃረብ ራቀወ ብሎ በመቀመጥ ጉዝፋር መሞቱን ይጠብቅ ነበር።ወደርሱም መላእክት የብርሃን ልብስ ይዘው ሲወርዱ አየ ከእርሳቸውም ጋራ ጻድቃን ሰማዕታት አሉ ዳዊትም በመስንቆ ያመሰግን ነበር መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በስጋው ላይ ሦስት ጊዜ ዞረ ያንጊዜም የመርቄ ነፍስ ከሥጋዋ ተለይታ ወደ ሰማይ እንዲህ ባለ ሁኔታ ዐረገች።ሁለት አንበሶችም መጡ ምድሩንም ቆፍረው ቀበሩት።
ጉዝፋርም ተነሣ የመርቄንም ወርቅ ጭኖ ስለአየው ሁሉ እያደነቀ ሔደ።አንጾኪያም በደረሰ ጊዜ የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳዳሪ ቀሲስ ታዴዎስን አግኝቶ መርቄ እንዳለው ነገረው።ቀሲስ ታዴዎስም ሊረከበው ወደ ጉዝፋር ሔደ።ግን የክብር ባለቤት ከሆነ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለማንም አልሰጥም ወዳጄ መርቄ እንዳማለኝ እጅ በእጅ እሰጠዋለሁ እንጂ ብሎ ከለከለው።
ከዚያም ሒዶ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ግቢ ገባ።ቀሲስ ታዴዎስም ደጁን ከፈተለት የተጫነውንም ወርቅ አውርዶ በፊቱ አኑሮ በዚያ ቆመ። ከሌሊቱ እኩሌታ ላይ እንደ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰማ። ታላቅ ብርሃንም ወጣ ጌታችንም ከሰማይ ወርዶ በመሠዊያው ላይ ተቀመጠ መላእክትም ከእርሱ ጋር አሉ።
ከመላእክትም አንዱ ከሀዲ ጉዝፋር ከዚህ ለምን ቆምክ አለው። እርሱም ወዳጁ መርቀፀ ለክብር ባለቤት ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ለሌላ እንዳይሰጥ ብሎ እንዳማለው ነገረው። መልአኩም የክብር ባለቤት የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ ነውና ና ስገድ አለው።
ጉዝፋርም ሰገደ ደብዳቤውንም ሰጠው። እየተንቀጠቀጠም የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አመንኩብህ አለ። ጌታም ያንን ወርቅ ይመዝኑት ዘንድ አዘዘ። አርባ ልጥርም ሆነ ጉዝፋርንም ከቀሲስ ታዴዎስ ዘንድ እንዲጠመቅ አዘዘው። ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር ተጠመቀ የተጠመቁትም ሰባ አምስት ነፍስ ሆኑ።
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡
(የበዓታ ለማርያም ምስል ወርኃዊ በዓሉን እንጂ ከላይ ዜና ሕይወታቸው የተጠቀሰው ቅዱሳን ጋር የማይገናኝ መሆኑን አሳውቃለሁ።)

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages