ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 23 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, April 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 23

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሃያ ሦስት በዚች ቀን ታላቁ_ነቢይ_ዳንኤል አረፈ፣ የደብረ ሊባኖሱ አቡነ_ፊሊጶስ ፍልሰተ ዐፅማቸው በክብር ተከናወነ፡፡


መጋቢት ሃያ ሦስት በዚች ቀን የዮናኪር ሴት ልጁ የወለደችው ታላቅ ነቢይ ዳንኤል አረፈ። ናቡከደናጾርም ኢየሩሳሌምን በወረራት ጊዜ አባታቸው ዮናኪር አናንያን አዛርያንና ሚሳኤልን ሦስቱን ልጆቹን የልጁን ልጅ ዳንኤልንም ወሰዳቸው ከእንርሱም ጋር ከእስራኤል ልጆች ብዙ ሰዎች ተማረኩ ።
ይህም ዮናኪር የንጉሡ የኢዮአቄም ልጅ ነው። ኢሳይያስ ለሕዝቅያስ ንጉሥ ትንቢት እንደተናገረ የቤተ መንግሥቱንና የቤተ እግዚአብሔርን ዕቃ ሁሉ ናቡከደነጾር ወደ ባቢሎን ወሰደ።
ይህ ዳንኤል ያን ጊዜ በዕድሜው ታናሽ ነበር ፍጹም የሆነ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ የእግዚአብሔር መንፈስም አድሮበት በባቢሎን አገር ትንቢት ሲናገር ኖረ።
ምርኮ በሆነ በአራተኛው ዓመት ናቡከደነጾር የምታስፈራ ራእይን አየ ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ያቺን ሕልም ረሳት። በባቢሎን የሚኖሩትን ሁሉን ጥበበኞች ሰበሰባቸው ከእርሳቸውም ያቺን ራእይና ትርጓሜዋንም እንዲነግሩት ፈለገ እንርሱ ግን ያቺን ራእይና ትርጓሜዋን ሊያውቋት አልቻሉም።
የባቢሎንን ጥበበኞች ሁሉ እርሱንና ባልንጀሮቹ ሠለስቱ ደቂቅን ይገድሏቸው ዘንድ ንጉሥ አዘዘ። ዳንኤልም ይህን ነገር ሰምቶ የዘበኞችን አለቃ ስለ ምን እንዲህ ያለ ትእዛዝ ከንጉሥ ዘንድ ታዘዘ ብሎ ጠየቀው። እርሱም ንጉሥ ስለ አያት ራእይ ነው የባቢሎንና የግብጽ ጠቢባን ሁሉ እርሷን ራእዩን ትርጓሜዋንም ሊነግሩት አልተቻላቸውምና ብሎ መለሰለት።
ዳንኤልም የዘበኞቹን አለቃ እኔ ለንጉሥ ሕልሙን እንደምነግረውና ፍቺውንም እንደምተረጕምለት ስለ እኔ ንገርው እሊህንም ተዋቸው አለው ። ከዚህ በኋላም ዳንኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ባልንጀሮቹ ሠለስቱ ደቂቅም ከእርሱ ጋር የንጉሡን ሕልም ፍቺዋንም ይገለጥላቸው ዘንድ በአንድነት ማለዱ።
እግዚአብሔርም ገለጠላቸው ዳንኤልም ወደንጉሥ ገብቶ ሕልሙንና ፍችዋን ነገረው። ከእርሱ በኋላም ስለሚነሡ ነገሥታት ከእንርሱም ከየአንዳንዳቸው የሚሆነውንም ገለጠለት። የዳንኤል ቃል ናቡከደነጾርን ደስ አሰኘው በፊቱም ሰገደ ብዙ እጅ መንሻንም ሰጠው ታላቅ ክብርንም ሰጥቶ በባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው።
ከዚህም በኋላ ናቡከደነጾር ሌላ ሕልም አየ ያንንም ተረጐመለት እንዲህም ብሎ አስረዳው ስለታበይክ እግዚአብሔር ከሰው መካከል አውጥቶ ከአራዊት ጋራ በዱር ሰባት ዓመት ያኖርህ ዘንድ አለው። እንደ እንስሳም ሣር ትበላለህ ከሰባት ዓመትም በኋላ ወደ መንግሥትህ ይመልስሃል ፈ በማለት ይህም ተፈጸመበት።
ናቡከደነጾር ከሞተ በኋላ መልአክ በግድግዳ ላይ የጻፋትን ለልጁ ለብልጣሶር ተረጐመለት በቤተ እግዚአብሔር ዕቃ በጠጣ ጊዜ ጽሑፉ የተቆጠረ የተመጠነ የተመዘነ እንደሆነ ትርጓሜውም ዙፋኑንና መንግሥቱን እግዚአብሔር ለሌላ የሰጠው መሆኑን ገለጠለት። እንዲህም አለው ቢመዝንህ ጐደሎ ሆነህ አገኘህ መንግሥትህንም ለፋርስ አሳልፎ ሰጠ ትንቢቱም ተፈጸመች።
እግዚአብሔርም እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚነግሡትን ነገሥታት በራእይ አሳየው የሐሳዊ መሲሕንም መገለጥ አሳየው። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔርነቱን ክብር ልዕልናውን ጌትነቱን አሳየው። የክበር ባለቤት ክርስቶስን ወደ ዓለም መምጣቱን ትንቢት ተናገረ ሱባኤዎችንም ወሰነ እንዚያ ሱባኤዎችም በተፈጸሙ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ።
ክርስቶስ ይመጣል ይገድሉታልም ለኢየሩሳሌምም መዳኛዋ ይሆናታል ብሎ ትንቢት እንደ ተናገረ። የክብር ባለቤት ከሆነ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት በኋላ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ቤተ መቅደስም እንደሚፈርስ የተናገረው ትንቢት ሁሉ ተፈጸመ።
በባቢሎን አገርም ቤል የሚባል ጣዖት ነበረ ምግብንም ሁልጊዜ ዐሥራ ሁለት ጫን በሚፈጅ ቻል ዐሥራ ሁለት መስፈሪያ ስንዴ አርባ በግ ሰባት ፊቀን የወይን ጠጅ እያወጣጡ ይሰጡት ነበር። ንጉሡም ሁልጊዜ ይሰግድለታል ቤል ጣዖትም ከንጉሡ ቤት የሚሰጡትን የሚበላና የሚጠጣ ይመስለው ነበር ።
ንጉሡም ዳንኤልን ለቤል የማትሰግድ ለምንድን ነው አለው። ዳንኤልም ንጉሡን እኔስ ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ ፍጥረቱንም ሁሉ በሕያውነት ለሚያኖር አምላክ እንጂ የሰው እጅ ለሠራው ጣዖት አልሰግድም አለው።
ንጉሡም ቤል ሕያው ያልሆነ ይመስላሃልን በየነጋታው እንዲበላ እንዲጠጣ አታይምን አለው። ዳንኤልም በንጉሡ ሳቀበት ንጉሥ ሆይ ይበላል ይጠጣል እያሉ አያታሉህ ይህ ውስጡ ጭቃ ላዩ ናስ ነው ምንም ምን አይበላም አይጠጣም አለው። ንጉሡም ተቆጣ የጣዖቱንም ካህናት ጠራቸው እውነት ነውን ቤል አምላክ አይበላም አይጠጣምን አላቸው። ሁልጊዜ የምንሰጠውን በዕውነት ይበላል ይጠጣል አሉት።
ከዚህም በኋላ በመሸ ጊዜ ከጣዖቱ ዘንድ መብሉንና መጠጡን ሁሉ ንጉሡ እየተመለከተ ካህናቱ አስቀምጠው ወጡ። የጣዖቱ ካህናትም ከወጡ በኋላ ዳንኤል አመድ አምጡ ብሎ አዘዘ አመጡለትም። ንጉሡም ከዚያ ሁኖ እያየ በጣዖቱ ቤት ውስጥ ነሰነሰው። ንጉሡም በቁልፉ ከዳንኤል ጋር በአንድነት ቈለፉት አተሙትም ወደ ማደሪያቸውም ሔዱ። የጣዖቱ ካህናት ግን ከምድር በታች ውስጥ ለውስጥ መግቢያ ቀዳዳ ነበራቸው ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋራ በሌሊት በዚያ ገብተው በሉ ጠጡ በመጡበትም ተመለሱ።
በማግሥቱም ንጉሡ መጥቶ የጣዖቱን ቤት ከፈተ ራሱ ከአኖረው መብሎች ምንም አላገኘም ንጉሥም ቤል ሆይ ፈጣሪዬ ዳንኤልን ያሳፈርከው አንተ ገናና ነህ ብሎ ጮኸ። ዳንኤልም ሳቀ ለንጉሡም የወንዶችና የሴቶችን የልጆችንም ፍለጋቸውን በአመድ ላይ አሳየው። ንጉሡም የጣዖቱን ካህናት ይዞ መረመራቸው እነርሱም ውስጥ ለውስጥ ተሠውረው የሚገቡበትንና የሚወጡበትን ለንጉሡ አሳዩት። ያን ጊዜ ንጉሡ ተቆጥቶ የጣዖቱን ካህናት ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋራ ገደላቸው ጣዖቱንም ለዳንኤል ሰጠው። ዳንኤልም ሰበረው ምኲራቡንም አፈረሰ።
ከዚህ በኋላ ደግሞ የባቢሎን ሰዎች የሚአመልኩትና የሚሰግዱለት ታላቅ ዘንዶ ነበር ንጉሡም ዳንኤልን ይህንንስ አምላክ አይደለም ትለዋለህን እነሆ ሕያው ነው ይበላል ይጠጣል ናስ ነው ትለው ዘንድ አትችልምና ስገድለት እንጂ አለው።
ደንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔስ በሕያውነት ከሚኖር ከእግዚአብሔር በቀር ለሌላ አልሰግድም ግን ያለ ሰይፍና ያለ በትር ይህን ከይሲ እገድለው ዘንድ አሰነሰብተኝ አለው። ንጉሥም አሰናበትኩህ አለው።
ዳንኤልም ጠጉርና አደሮ ማር ወስዶ እንደ እንቁላልም አድበልብሎ በእሳት አጋለው በሞራም ጠቅልሎ ለከይሲው አጐረሰው በዋጠውም ጊዜ ሆዱ ተሰንጥቆ ሞተ ዳንኤልም የባቢሎን ሰዎች ሆይ አምላካችሁን ተመልከቱ አላቸው።
የባቢሎን ሰዎችም በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቆጡ ወደ ንጉሡም ተሰብስበው አይሁዳዊው ዳንኤል ነግሦአልን እነሆ ቤልን ሰበረው ካህናቶቹንም ገደላቸው ከዚያም ደግሞ ዘንዶውን ገደለው አሁን እርሱን ዳንኤልን እንድንገድለው ካልሰጠህን አንተን ቤተ ሰብህንም እንገድላለን አሉት።
ንጉሡንም እጅግ በአስጨነቁት ጊዜ ስለ ዳንኤል አዘነ ግን ዳንኤልን ሰጣቸው እነርሱም በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት በዚያም ሰባት ቀን ኖረ። ከረኀብ ጽናትም የተነሣ እንዲበሉት በሌላ ጊዜ የሚሰጧቸውን በእነዚያ ቀኖች ምንም ምን አልሰጧቸውም ነበር።
እግዚአብሔርም መልአኩን ወደ እንባቆም ላከው እርሱም በኢየሩሳሌም ውስጥ ለአጫጅዎች ምሳ ተሸክም ሲሔድ በራስ ጠጉሩ ተሸከመው። ወስዶም ዳንኤል በአለበት ጉድጓድ ውስጥ አኖረው። ዳንኤልም ተመግቦ እግዚአብሔርን አመሰገነው በዕንባቆምም ቃል ተረጋጋ በዚያችም ሰዓት እግዚአብሔር የላከው መልአክ ወደ አገሩ ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ አደረሰው።
በሰባተኛዪቱ ቀንም ስለ ዳንኤል እያለቀሰ ንጉሡ ወደ ጕድጓድ መጣ ዳንኤል ሙቶ አንበሶች የበሉት መስሎት ነበርና። ወደ ጕድጓዱም ሲመለከት ዳንኤልን አየው አንበሶችም እንደ ድመቶች እግሮቹን እየላሱ ከእግሮቹ በታች እጥፍጥፍ ብለው ተኝተው ነበር።
ንጉሡም እግሮቹን እስከሚልሱ እንደ ድመቶች አንበሶችን ያገረመለትና ያሰገዛለት የዳንኤል አምላክ ታላቅ ነው ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ። በዚያን ጊዜ ዳንኤልን ከጕድጓድ እንዲያወጡት እነዚያንም የዳንኤልን ጠላቶች ይዘው ለአንበሶች ወደ ጕድጓድ እንዲጥሉአቸው ንጉሥ አዘዘ ወዲያው እነዚያ አንበሶች በንጉሡ ፊት በሏቸው።
ዳንኤልም የእስራኤል ልጆች ወደ ኢየሩሳሌም እስከ ሚመለሱበት ጊዜ በባቢሎን ኖረ እርሷም ሰባ ዘመን ናት ከዚያም በኋላ በሰላም በፍቅር አረፈ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን የአቡነ ፊሊጶስ ፍልሰተ ዐፅማቸው በክብር ተከናወነ፡፡ የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ፊሊጶስ በተወለዱ በ15 ዓመታቸው በምናኔ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገቡ፡፡ ከብዙ ጊዜ አገልግሎትም በኋላ በአቡነ ተክለሃይማኖት እጅ መንኩሰው ከእርሳቸውም ዕረፍት በኋላ ሦስተኛ አበምኔት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከተወለዱት የመጀመሪያ ፓትርያርክ ሆነዋል፡፡ አባታቸው ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በመንፈቀ ኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነው ነበር፡፡ በመጀመሪያ የአቡነ ፊሊጶስን የጽድቅ ሕይወትና ሹመታቸውን በተመለከተ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድልና በራሳቸው በአቡነ ፊሊጶስ ገድል ላይ የተጻፈውን እንመልከት፡- ‹‹ክቡር አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ከዚህ ዓለም ተለይቶ የሚሄድበት ጊዜ ሲደርስ ‹ከአንተ በኋላ አንተን ተክቶ በዙፋንህ የሚቀመጥ ማነው?› አሉት፡፡ እርሱም ‹ብዙ ዘመን አይኖርም እንጂ ኤልሳዕ በእኔ ተተክቶ ይቀመጥ› አለ፡፡ ስለ ፊሊጶስ ግን አላነሳም፣ ኤልሳዕ ካረፈ በኋላ በእርሱ ተተክቶ አባት ይሆን ዘንድ ጌታችን የተሸለመ ፊሊጶስን እንደመረጠው ስም አጠራሩ ለልጅ ልጅ ዘመን እንደሚጸና ያውቅ ነበርና ስለዚህ ‹አልሳዕ በእኔ ተተክቶ አባት ይሁናችሁ› አለ፡፡ ክቡር አባታችንም በታላቅ ክብር ዐረፈ፡፡
አንድ ቀን አንድ ዲያቆን ዐረፈና ሬሳውን ገንዘው አጠቡት፣ ይቀብሩትም ዘንድ አስክሬኑን ይዘው ሲሄዱ በአልጋ ላይ ሳለ አስክሬኑ ተንቀሳቀሰ፡፡ የተሸከሙትም ደንግጠው መሬት ላይ አስቀመጡትና ከመግነዙ ፈቱት፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሦስት ጊዜ ተነፈሰ፡፡ ወንድሞችም ‹ምን እያልክ ነው?፣ ወዴትስ ነበርክ?› አሉት፡፡ ያ የከበረና የተመረጠ ዲያቆንም ‹ክቡር አባታችን ተክለሃይማኖት ‹ኤልሳዕ ወደኔ ይምጣ፣ ፊሊጶስ ስለ እኔ ተሹሞ በወንበሬ ይቀመጥ እርሱ ለብዙዎች አሕዛብ አባት ይሆናልና የክርስቶስንም መንጋ በጽድቅና በቅን ይጠብቃል› ብሎኛል› ብሎ ይህን ተናግሮ ተመልሶ ዐረፈ፡፡ ወንድሞችም ኤልሳዕ እንደልማዱ ጎኑን ሳያሳርፍ በወንበር ላይ እንደተደገፈ በሞት ማረፉን አላወቁም ነበር፡፡››
ወደ ጻድቁ የልጅነት ገድላቸው እንመለስና አቡነ ፊሊጶስ በእግዚአብሔር ተመርጠው የመንፈስ ቅዱስም ማደሪያ ሆነዋልና ገና በሕፃንነታቸው በተወለዱባት ሰላሌ ክፍለ ሀገር ዝማ በምትባል ልዩ ቦታ ውስጥ ሰይጣን በጠንቋይ ላይ አድሮ በነደደ በእሳት ውስጥ በመግባትና የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ በአካባቢው ራሱን ያስመልክ የነበረን ሰይጣን በእሳት ውስጥ እንዳለ በስመ ሥላሴ አማትበውበት አመድ አድርገውታል፡፡ በዚህ በአቡነ ፊሊጶስ ድንቅ ተአምር የጠንቋዩ ቤተሰቦችና የአካባቢው ሰዎችም አምነው ሊጠመቁ ችለዋል፡፡ ይህንንም ያደረገው ገና ሕፃን ሳለ ነው፡፡ መልአከ እግዚአብሔር ተገልጦለት የትውልድ መንደሩን ትቶ ወደ ግራርያ ሀገር ደብረ አስቦ ሄዶ ቅዱስ ተክለሃይማኖትን እንዲያገኝ በነገረው መሠረት አንድ ቀን ያህል ተጉዞ ተክለሃይማኖትን አገኛቸውና ባርከውት ከመነኮሳት ጋር እንዲያርፍ አደረጉት፡፡ ሦስት ዓመት እነርሱን በመልካም ሥራ ፍጹም ሆኖ ሲያገለግላቸው ከቆየ በኋላ ‹‹ሁሉም በአንድነት አሁን ልብሰ ምንኩስና ይገባዋል›› አሉ፡፡ ቅዱስ አባታችን ተክለሃይማኖትም የምንኩስናን ሥራ የሚያሠራ ቅድስናን ሰጠው፡፡
በሌላም ጊዜ ቅስናን ይቀበል ዘንድ ወደ ጳጳሱ ዘንድ ላኩት፡፡ አቡነ ፊሊጶስ በንጉሥ አምደ ፅዮን ዘመነ መንግሥት ሥጋቸው አልቆ አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ ሲገረፉ ደማቸው እሳት ሆኖ ገራፊዎቻቸውን ያሳደደ ቅዱስና ጻዲቅ አባት ናቸው፡፡ ንጉሥ አምደ ጽዮን በክፉ ጠንቋዮች ምክር ተታሎ ‹‹ያልወለደችህን የአባትህን ሚስት ብታገባ መንግሥትህ ትፀናለች›› ብለው ክፉ ምክርን መክረውት የእንጀራ እናቱን አገባትና ንግሥት አደረጋት፡፡ አቡነ ፊሊጶስም ይህን ሲሰሙ ነቢዩ ኤልያስ ንጉሡ አክአብንና አልዛቤልን በድፍረት እንደገሠጻቸው እርሳቸውም በቀጥታ ሄደው ንጉሡን ዘልፈው ገሠጹት፡፡ ወደ ንጉሡም ከመሄዳቸውም በፊት በዚህ ምክንያት ሰማዕት እንደሚሆኑ አውቀውት ነበርና ልጆቻቸውን ተሰናብተውና የሚተካቸውን ሰው ነግረዋቸው ነው የሄዱት፡፡ ንጉሡ አምደ ጽዮንም አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ አስገረፋቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውም መሬት ላይ እየተቆረሰ የወደቀውን ሥጋቸውን እያነሱ ለበረከት ወሰዱት፡፡ ደማቸውም እንደ እሳት ሆኖ ገራፊዎቻቸውን ያቃጥላቸው ነበር፡፡ 300 አንስራ ውኃ አምጥተው ከደሙ በወጣው እሳት ላይ ቢያፈሱትም የውኃው ብዛት እሳቱን ማጥፋት አልቻለም፡፡ ንጉሡም በፍርሃት ከዙፋኑ ላይ ወርዶ ሸሸ፡፡
የንጉሡ ጭፍሮች ግን በጋለ ማረሻ ጀርባና ግንባራቸውን ደረታቸውንም ተኮሷቸው፡፡ ኃፍረታቸውንም እንዳይሸፍኑ እጆቻቸውን ወደ ኋላ አስረው ራቁታቸውንም በከተማው ሁሉ ሲያዞሯቸው ዋሉ፡፡ ማታም ንጉሡ ‹ታስረው ለኖሩ ኃይለኛ ውሾች ስጡት› ብሎ በማዘዝ ውሾቹ እንዲቦጫጭቋቸው ቢያደርጉም ውሾቹ ግን ከእግራቸው ስር ሰግደዋል፣ እርሳቸውም በእግራቸው ባረኳቸው፡፡ አማካሪዎቹም ንጉሡን ‹‹ከዚህ መነኩሴ ጋር ምን አጨቃጨቀህ በግዞት አርቀህ ስደደው ብለው›› ብለው መክረውት ‹‹እስከ ቆርቆራ አገር አውጥታችሁ ወደ ትግሬ አገር ውሰዱት›› ብሎ አዘዘ፡፡ እርሳቸውም ንጉሡን ከ3 ዓመት በኋላ ትሞታለህ ብለው ትንቢት ነገረውት በወታደሮች ተወሰዱ፡፡ በግርፋት ብዛት የተቆረሰ ሥጋቸው ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡
ደማቸውም አስረው የሚወስዷቸውን የአንዱን ወታደር አንድ ስውር ዐይኑን ፈወሰለትና ወታደሮቹም አምነው ከእርሳቸው ጋር በዚያው ተሰደው መከራን ተቀብለዋል፡፡ እሳቸው በትግራይ ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ ሲያስተምሩ በትንቢታቸው መሠረትም ንጉሡ ከሦስት ዓመት በኋላ ሞተና ልጁ ነገሠ፡፡ ልጁም አባታችንን ከስደት መለሳቸውና ከተክለሃይማኖት መቃብር ደብረ አስቦ ገቡ፡፡ የነገሠውንም ልጅ አንድ ክፉ ሰው ‹‹ከአንድ በላይ ማግባት ትችላለህ፣ በገና ወቅትም ረቡዕና አርብን መጾም ተገቢ አይደለም›› ብሎ ስለመከረው ጳጳሱን ወደ ሀገራቸው ግብፅ እንዲሰደዱ ሲያደርግ አቡነ ፊሊጶስን ደግሞ ‹‹ረቡዕና አርብን በጠዋት ካልቀደስክ›› ብሎ ወደ ደራ ተሰደው እንዲሄዱ አደረገ፡፡ አባታችን በአጠቃላይ አምስት ጊዜ ተሰደው በትግራይ፣ በደራ፣ በዝዋይ ባሕረ ደሴት፣ በዳሞት ገማስቄ እና በወለቃ በስደት ቆይተዋል፡፡ ጳጳሱን አባ ሰላማን በአቃሊት ቅበረኝ ብለዋቸው በቃሬዛ አድርጎ ከጌርጌሳ ወደ አቃሊት ወሰዷቸው፤ እዚያም ሐምሌ 28 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰባት አክሊላት አቀዳጅቷቸዋል፡፡ዐፅማቸውም ከተቀበረ ከ140 ዓመት በኋላ በመጋቢት 23 ቀን ወደ ደብረ ሊባኖስ በክብር መጥቶ ዐርፏል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages