ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, May 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 19

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምሚያዝያ ዐሥራ ዘጠኝ በዚች ቀን የአርማንያ ሰው የፋርስ ኤጲስቆጶስ የከበረ ስምዖን በሰማዕትነት አረፈ ከእርሱም ጋር መቶ ሃምሳ ሰማዕታት።
ይህም ቅዱስ ትከሻ ነቃይ የተባለ የሐርመዝ ልጅ በሳቦር ግዛት ውስጥ ይኖራል። ይህም ሳቦር ሌላውን ንጉሥ ድል በሚያደርግ ጊዜ አሥሮ ትክሻውን ይመዝዘዋልና ትከሻ ነቃይ ተባለ። ይህም ከሀዲ ለጣዖት እንዲሰግዱ እያስገደደ ምእመናንን በጽኑዕ ሥቃይ አሠቃያቸው።
ይህም የከበረ አባ ስምዖን ለንጉሥ ሳቦር መልእክት ጽፎ ላከለት። እንዲህ የሚል የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ደሙ የዋጃቸው ከሰው ተገዢነት ድነዋል የክብር ባለቤት የክርስቶስ ተገዢ ናቸውና። ስለዚህ ተገዢ መሆን ከተሠራው ሕግ አብዝቶ መገበርም አይገባቸውም። የሕያው እግዚአብሔርን ሕግ ለለወጡ ከሀድያን አይገዙም። ስለ እርሳቸው ደሙን በአፈሰሰ በክብር ባለቤት በክርስቶስ ስም እንዲሞቱ እነርሱ ይመርጣሉ።
ንጉሥ ሳቦርም ይህን መልእክት በአነበበ ጊዜ በዚህ አባት ላይ እጅግ ተቆጣ በሁለት ሰንሰለትም አሥሮ በእሥር ቤት ጣለው በዚያም ሃይማኖታቸውን ክደው ሰማይን ያመለኩ እነርሱም በሌላ የታሠሩ ብዙ እሥረኞችን አገኘ።
ይህ ቅዱስም ገሠጻቸው አስተማራቸው እነርሱም ተጸጽተው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው መሰከሩ ራሶቻቸውንም ቆረጡአቸውና የሕይወት አክሊልን ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ ይህን አባት ወደ ምስክርነት ሸንጎ አቀረቡት ከእርሱም ጋራ መቶ ሃምሳ ሰዎች አሉ እነርሱም አንገታቸውን እስከ ቆረጡአቸውና አክሊል እስከ ተቀበሉ ድረስ ያጽናናቸው ነበር።
ከእርሳቸውም አንዱ ሰይፍን ከመፍራት የተነሣ ደንግጦ ሃይማኖቱን ሊክድ ወደደ በዚያ ከቆሙት አንዱ አትደንግጥ የሰይፍ በትር ዓይንህን ከሸፈንክ ምንም አይደለም ጽና። ከሰማዕታት ጋራ ተቆጥረህ ከክብር ባለቤት ክርስቶስ ጋራ ለዘላለም ነግሠህ ትኖራለህ ብሎ አጽናናው። እንዲሁም አደረገ የሕይወት አክሊልንም ተቀበለ።
ስሙ ባሴቅ የተባለ ያንን ያጥናናውን ሰው ከሰሱት ንጉሡም አስቀርቦ ምላሱን አስቆረጠው። ቆዳውንም አስገፈፈውና ነፍሱን አሳለፈ የድል አክሊልንም ተቀበለ። ከዚህ በኋላም የከበረ ስምዖንን ወደ እርሱ አቅርቦ ለአማልክት ስገድ ያለዚያ በጽኑ ሥቃይ አሠቃይሃለሁ አለው። ቅዱሱም ትእዛዙን አልሰማም ሥቃዩንም አልፈራም ያን ጊዜም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዝዞ ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ።
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages