ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 13 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, June 21, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ 13

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሰኔ ዐሥራ ሦስት በዚህችም ዕለት ለከበረ መልአክ አዲስ የምሥራች ነጋሪ ለሆነ ለመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል በዓልን አደረጉለት፣ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አባ ዮሐንስ አረፈ፣ ከአዳም አራተኛ ትውልድ የሆነ የኄኖስ ልጅ የቃይናን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።


የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል
ሰኔ ዐሥራ ሦስት በዚህችም ዕለት ለከበረ መልአክ አዲስ የምሥራች ነጋሪ ለሆነ የመላእክት አለቃ ገብርኤል በዓልን ያደርጉለት ዘንድ መምህራን በግብጽ አገር ለክርስቲያን ወገኖች ሥርዓት ሠሩላቸው።
ይህ የከበረ መልአክ የእስራአል ልጆች ከሰይጣን እጅ ስለመዳናቸውና ከምርኮም ስለ መመለሳቸው ነቢዩ ዳንኤል ወደ እግዚአብሔር በሚጸልይና በሚማልድ ጊዜ አስቀድሞ የተገለጠለትና ስለ ድኅነታቸውና ስለ ቤተ መቅደስም መታነፅ የነገረው ነውና።
ዳግመኛም ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ መምጣትና መገደል ስለ ቤተ መቅደስም መፍረስ ከዚያም በኋላ ስለ ሐሳዊ መሲሕ መምጣት ነገረው። ለመድኀን መምጣትም በሱባዔ የወሰናቸው ዘመናት በተፈጸሙ ጊዜ ይህ የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ወደ ቅድስት ድንግል ወደ እመቤታችን ማርያም መጣ ዓለምን ስለ ማዳን የእግዚአብሔር ልጅ ከእርሷ ሰው ስለመሆኑ ነገራት።
ስለዚህም የበዓላቶቹን መታሰቢያ እንድናደርግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘዙን። እኛም ከጠላታችን ሰይጣን እጅ ያድነን ዘንድ ለመንግሥቱም የተዘጋጀን ያደርገን ዘንድ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ስለ እኛ እንዲማልድ እንለምነው።
ልዕልና ችሎታም ገንዘቡ ለሆነ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም
በዚህች ቀን የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አባ ዮሐንስ አረፈ። ይህም ቅዱስ በቅዱስ አባ ኢላርዮንና በታላቁ አባ ኤስድሮስ ገዳም በታናሽነቱ መነኰሰ ከአባ ኤጲፋንዮስ ጋራም በገድል በመጠመድ ታላቅ ተጋድሎ ተጋደለ የደግነቱ የተጋድሎውና የትሩፋቱ ዜናም በቦታው ሁሉ ተሰማ።
ከዚህም በኋላ ኤጲፋንዮስ በቆጵሮስ ሀገር ኤጲስቆጶስነት ከተሾመ በኋላ እርሱን መርጠው በኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስነት ሾሙት። ይህ አባት በሹመት በነበረ ጊዜ ሰይጣን በገንዘብ ፍቅርና በዚህ ዓለም ክብር አሳተው ብዙ ገንዘብ ሰብስቦ ለማዕዱ የሚመገብበት የወርቅና የብር ሣህን አሠርቶ ነበርና ለድኆችና ለምስኪኖችም መራራትን ተወ ምንም የእንጀራ ቁራሽ አይሰጣቸውም ነበር።
ቅዱስ ኤጲፋንዮስም በሰማ ጊዜ የቀድሞውን ተጋድሎውንና የዓለም መናኒነቱን ፍቅሩንም አስታውሶ እጅግ አዘነ ከቀድሞ ጀምሮ በመንፈስ ወንድሙና ወዳጁ ነበርና። ስለዚህም ብፁዕ ኤጲፋንዮስ ከቆጵሮስ ተነሥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አባ ዮሐንስ መጣ አባ ዮሐንስን በጥበብ ከስሕተት ያድነው ዘንድም ክብር ይግባውና የጌታችን መቃብር ባለበት ቤተ መቅደስ ለመስገድ እንደመጣ አመካኘ።
በተገናኙም ጊዜ አባ ዮሐንስ አባ ኤጲፋንዮስን ወደ ቤቱ አስገብቶ ማዕድ አዘጋጀለት በማዕድም ላይ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ሣህኖችን አኖረ አባ ኤጲፋንዮስም በልቡ አዘነ ለድኆችና ለምስኪኖች ርኃራኄ እንደሌለውም አየ።
ከዚህም በኋላ ከእርሱ ዘንድ ወጥቶ በኢየሩሳሌም ካሉ ገዳማት በአንዱ አደረ። ምክንያትም አዘጋጀ ይህም እንዲህ ነው ወደ አባ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ መልእክተኞችን ላከ ወንድሜ ሆይ ከቆጵሮስ አገር ሽማግሌዎችና የሕዝቡ መምህራን ወደ እኔ መጥተዋልና በእነርሱ ፊት ታከብረኝ ዘንድ ከወርቅና ክብር የተሠሩ የማዕድ ዕቃዎችን ይመገቡባቸው ዘንድ እንድትልክልኝ እሻለሁ እርሱም ላከለት።
ያን ጊዜም አባ ኤጲፋንዮስ ዕቃዎቹን ወስዶ ሸጣቸው ዋጋቸውንም ለድኆችና ለምስኪኖች መጸወታቸው። ከዚህም በኋላ በተገናኙ ጊዜ አባ ዮሐንስ አባ ኤጲፋንዮስን የላኩልህን የማዕድ ዕቃዎቼን መልስ አለው እርሱም እሺ አለው እንዲሁም ሁለተኛና ሦስተኛ ጊዜ ነገረው አባ ኤጲፋንዮስም እሺ አለው።
በአንዲት ዕለትም ክብር ይግባውና የጌታችን መቃብር ካለበት ቤተ መቅደስ ሲወጣ አገኘው ያን ጊዜም ያዘውና ገንዘቤን እስከምትሰጠኝ አልለቅህም አለው አባ ኤጲፋንዮስም ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ጸለየ በዚያን ጊዜም የአባ ዮሐንስ ዐይኖቹ ታወሩ።
ያን ጊዜም ይቅር ብሎት ዐይኖቹን ይገልጥለት ዘንድ እያለቀሰ ወደ አባ ኤጲፋንዮስ ማለደ እርሱም መጸጸቱን አይቶ አንዲቱን ዐይኑን ገለጠለት እንዲህም አለው ነፍስህን ታስብ ዘንድ አንዲቷ ዐይንህ ዕውርት እንደሆነች ትቶልሃል። ገሠጸውም እነሆ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቀድሞ ድካምህን ብርታትህንና ተጋድሎህን አስቦ ራራልህ ከስሕተትም አዳነህ አለው።
የማዕድ ዕቃዎችንም እኔ እንደሸጥኳቸውና ስለ አንተ ለድኆችና ለምስኪኖች እንደ መጸወትኳቸው ዕወቅ አንተ በገንዘብ ፍቅር መጠመድህንና የቀድሞውን መልካም ሥራህን መተውህን ብሰማ ነው እንጂ ከቆጵሮስ ወደ ኢየሩሳሌም አልመጣም ነበር።
ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ ቅዱስ ዮሐንስ ከእንቅልፍ እንደነቃ ሆነ በርኅራኄም መንገድ ሔደ ያለውንም ጥሪቱን ሁሉ ሰጠ ምንም ምን አላስቀረም። ልብሶቹንም ለተራቆቱ ሰጠ በሞተ ጊዜ አንድ አላድ ከዚያም በታች ከእርሱ ዘንድ እስከ አልተገኘ ድረስ ሰጠ።
ጌታችንም የመፈወስ ሀብትን ሰጠው ብዙዎች ድንቆችንና ተአምራቶችን አደረገ ከተቀደሰ ዘይት እየቀባ ፊታቸውንም አዳኝ በሆነ በመስቀል ምልክት እያማተበ ደዌ ያለባቸውን ሁሉ አዳናቸው። መልካም ተጋድሎውን ፈጽሞ ክብር ይግባውና ጌታችንን አገልግሎ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
አባታችን ቃይናን
በዚችም ቀን ከአዳም አራተኛ ትውልድ የሆነ የኄኖስ ልጅ የቃይናን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ቃይናንም መቶ ሰብዓ ዓመት ኖረ መላልዔልንም ወለደው መላልዔልንም ከወለደው በኋላ ሰባት መቶ አርባ ዓመት ኖረ ሴቶች ልጆችና ወንዶች ልጆችንም ወለደ። የቃይናን መላ ዘመኑ ሁሉ ዘጠኝ መቶ ዐሥር ነው ከዚያም በኋላ አረፈ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን። በረከታቸውም ትድረሰን፤ የከበረ መልአክ ገብርኤል የረድኤቱ ኃይል ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ ሰኔ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages