ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 15 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, February 22, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 15

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።



ቅድስት እንባ መሪና
ቤተ ክርስቲያን "እንቁዎቼ" ከምትላቸው ሴት ጻድቃን አንዷ ቅድስት እንባ መሪና ናት:: ጣዕመ ዜናዋ: ሙሉ ሕይወቷ: አስገራሚም: አስተማሪም ነው:: ቅድስቷ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብፅ ተወልዳ ያደገች ክርስቲያን ናት:: ወላጆቿ ከእርሷ በቀር ሌላ ልጅ የሌላቸው ሲሆን በአኗኗራቸውም ደግና ቅን ነበሩ::
ቅድስት እንባ መሪና ትክክለኛ ስሟ "መሪና" ነው:: ምክንያቱም "እንባ መሪና" የወንድ ስም ነውና:: ነገር ግን በወንድ ስም የተጠራችበት የራሱ ታሪክ አለውና እርሱን እንመለከታለን::
ቅድስት መሪና ገና ልጅ ሳለች እናቷ ማርያም ሞተችባት:: ደግ አባት አንድ ልጁን በሥጋዊም: በመንፈሳዊም ሳያጐድልባት አሳደጋት:: ዕድሜዋ አሥራ አምስት ዓመት በሆነ ጊዜ ወደ ፊቱ አቅርቦ "ልጄ! እኔ ወደ ገዳም ስለምሔድ አንቺን መልካም ባል ላጋባሽ::" አላት::
ቅድስት መሪናም "ነፍሰ ዚአከ ታድኅን: ነፍሰ ዚአየኑ ታጠፍእ - የአንተን ነፍስ አድነህ እንዴት የእኔን ትተዋታለህ? እኔም እመንናለሁ::" አለችው:: አባቷ የተናገረችው ከልቧ እንደሆነ ሲያውቅ "ልጄ! ገዳም ሁሉ በአካባቢው የወንድ ብቻ ነውና ስሚኝ::" አላት::
እርሷ ግን "አባቴ! ግዴለህም: ስሜን እንደ ወንድ ቀይረህ: አለባበሴንም ለውጥ::" አለችው:: (እንደ ወንድ ለበሰች ማለት ግን እንደ ዘመኑ ዓይነት እንዳይመስላችሁ አደራ!)
ከዚያ አባትና ልጅ ሃብት ንብረታቸውን ሸጠው ለነዳያን አካፈሉ:: በፍጹም ልባቸውም መነኑ:: በደረሱበት ገዳም ቅድስት መሪና በወንድ ስም "እንባ መሪና" በሚል ገባች:: ቀጣዩ ሥራዋ እንደ ወንዶች እኩል መስገድ: መጾምና መጸለይ ነበር::
ይህችን ቅድስት ልናደንቃት ግድ ይለናል:: ማንም በእርሷ አይፈተንም:: አያውቋትምና:: እርሷ ግን ወጣት ሆና: አንድም ሴት በሌለበት ገዳም ጸንቶ መቆየት በራሱ ልዩ ነው:: መልአካዊ ኃይልንም ይጠይቃል::
ተጋድሎዋ በጣም ስለ በዛ ወንድሞች መነኮሳት ይደነቁባት ነበር:: ጺም ስለሌላትና ድምጿ ቀጭን ስለሆነ አልተጠራጠሩም:: ምክንያቱም ጃንደረባ ናት ብለው አስበዋልና:: ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን አባቷ ታሞ ከማረፉ በፊት አበ ምኔቱን ጠርቶ "ወደ ከተማ ልጄን እንዳትልክብኝ: አደራ!" ብሎት ነበር::
ያም ሆኖ አንዳንድ መነኮሳት ቅሬታ በማንሳታቸው ወደ ከተማ ተላከች:: ችግሩ ለተልእኮ ባደሩበት ቤት አንድ ጐረምሳ ገብቶ የአሳዳሪውን ልጅ ከክብር አሳንሷት ሔደ:: ሲወጣም "ድንግልናሽን ያጠፋ ማን ነው? ካሉሽ ያ ወጣት መነኩሴ አባ እንባ መሪና ነው በይ::" አላት::
ከሦስት ወራት በኋላ የዚያች ዘማ ሴት ጽንስ በታወቀ ጊዜ ለአባቷ "አባ እንባ መሪና እንዲህ አደረገኝ::" አለችው::
አባት መጥቶ እየጮኸ መነኮሳትን ተሳደበ:: አበ ምኔቱ ግራ ተጋብቶ ቢጠይቀው "የአንተ ደቀ መዝሙር እንባ መሪና ልጄን ከክብር አሳነሳት::" አለው:: አበ ምኔቱ እውነት መስሎታልና ቅድስቲቱን ጠርቶ ቁጣና እርግማንን አወረደባት:: በዚያች ሰዓት ተንበርክካ አንድ ነገር ወሰነች::
"ሴት ነኝ" ብሎ መናገሩስ ቀላል ነው:: ግን ደግ ናትና የእነዛን አመጸኛ ሰዎች ኃጢአት ልትሸከም ወሰነች:: ቀና ብላ "ማሩኝ ወጣትነት ቢያስተኝ ነው?" አለቻቸው:: ተቆጥተው ዕለቱን እየገፉ ከገዳም አስወጧት:: ከባድ ቀኖናም ጫኑባት:: ከስድስት ወራት በኋላም የእርሷ ልጅ ነው የተባለ ሕፃን አምጥተው ሰጧት::
ይህኛው ግን ከባድ ፈተና ሆነባት:: እንዳታጠባው አካሏ በገድል ደርቁአል:: በዚያ ላይ ድንግል የሆነች ሴት ወተት የላትም:: ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት: የበጋውን ሐሩር: የክረምቱን ቁር ራሷ ታግሣ ለሕፃኑ ከእረኞች ወተት እየለመነች: እየመገበች ሦስት ዓመታት አለፉ::
በዚህ ጊዜ ወደ ገዳሙ ከከባድ ቀኖና ጋር ተመለሰች:: ሕፃኑን ስታሳድግ: ለገዳሙ ስትላላክ: ምግብ ስታዘጋጅ: ውኃ ስትቀዳ: የእያንዳንዱን ቤት ስታጸዳ ሰላሳ ሰባት ዓመታት አለፉ:: ሕፃኑም አድጐ ደግ መናኝ ወጣው:: (የቅድስቷ እጆች ያሳደጉት የታደለ ነው::)
በመጨረሻ ቅድስት መሪና (እንባ መሪና) ታማ ዐረፈች:: እንገንዛለን ብለው ቢቀርቡ ሴት ናት:: እጅግ ደንግጠው አበ ምኔቱን ጠሩት:: በዙሪያዋ ከበው እንባቸውን አፈሰሱ:: ጸጸት እንደ እሳት በላቻቸው:: ሥጋዋን በክብር ገንዘው: በአጐበር ጋርደው: በራሳቸው ተሸክመው ምሕላ ገቡ::
ሙሉውን ቀን "ስለ ቅድስት መሪና ብለህ ክርስቶስ ሆይ ማረን?" ሲሉ ዋሉ:: ድንገት ግን ከተባረከ ሥጋዋ "ይቅር ይበለን::" የሚል ድምጽን ሰምተው ደስ ብሏቸው ቀበሯት:: እነዚያ ዝሙተኞችም ከእርሷ ይቅርታን እስካገኙበት ቀን አብደው ኑረዋል::
ቅድስት ክርስጢና (ክርስቲና) ሰማዕት
በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን የተነሳችው ሰማዕቷ ቅድስት ክርስጢና ከዋና ሰማዕታት አንዷ ስትሆን በዓለማቀፍ ደረጃም ተወዳጅ ናት:: ከመነሻው የሃገረ ገዢ ልጅ ብትሆንም ቤተሰቦቿ ጣዖት አምላኪዎች ነበሩ:: አጥር አጥረው: በር ዘግተው: ከማንም ጋር ሳትገናኝ: ጣዖት እንድታጥን አደረጓት::
ወጣት በሆነች ጊዜ ግን ጣዖቱን ተመለከተችው: መረመረችው:: አምላክ እንዳልሆነም ተረዳች:: ወደ ምሥራቅ ዙራ "እውነተኛው አምላክ ራስህን ግለጽልኝ?" ስትል ጸለየች::
መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ክርስትናን በልቡናዋ አሳደረባት:: ቅዱስ መልአክም መጥቶ ሰማያዊ ሕብስትን መገባት::
ፈጥና ተነስታ አብርሃማዊት ቅድስት ጣዖታቱን ሰባበረች:: በዚህ አባቷ ተቆጥቶ (ርባኖስ ይባል) በዛንጅር (ሥጋን የሚልጥ: የሚቆርጥ ጀራፍ ነው::) አስገረፋት:: ንጽሕት ናትና ከአካሏ ደም ሳይሆን ጣፋጭ ማር ፈሰሰ::
በድጋሚ በእሳት ቢያቃጥላትም አልነካትም:: ድንገት ግን አባቷ ርባኖስ ተቀሰፈ:: ሌላ ንጉሥ መጥቶ በእሳትም: በስለትም አሰቃያት:: እሱንም መልዐክ ቀሠፈው:: ሦስተኛው ንጉሥ ግን ብዙ አሰቃይቶ: ጡቶቿንና ምላሷን አስቆረጣት:: በመጨረሻውም በዚህች ቀን ለእፉኝት (እባብ) አስነድፎ ገድሏታል::
የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ ለእነርሱ የሰጣቸውን ጽናት አይንሳን:: ከበረከታቸውም አብዝቶና አትረፍርፎ ያድለን::
ነሐሴ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት እንባ መሪና ገዳማዊት
2.ቅድስት ክርስጢና ሰማዕት
3.ቅዱስ ለውረንዮስ ሰማዕት
4.ሰላሳ ሺ ሰማዕታት (የቅድስት ክርስቲና ማኅበር)
5.አበው ቅዱሳን ሐዋርያት (ወላዲተ አምላክን ለመገነዝ በዚህ ዕለት ተሠብስበዋል::)
ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት
3.ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
"ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ:: ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ::"
(፩ጴጥ. ፫፥፫)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages