ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 8 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 16, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 8

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።



ነሐሴ ስምንት በዚች ቀን አልዓዛርና ሚስቱ ሰሎሜ እና ሰባቱ ልጆቻቸውም በሰማዕትነት አረፉ
ይህ ቅዱስ ከመምህራነ ኦሪት አንዱ ሲሆን የብሉይ ኪዳን ሰማዕታት ተብለው ከሚታወቁትም ዋነኛው ነው። የነበረበት ዘመንም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲሆን "ዓመተ መቃብያን/ ዘመነ ካህናት" ይባላል።
በወቅቱ ሰሎሜ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ይኖር የነበረው ቅዱስ አልዓዛር በኢየሩሳሌም ተወዳጅ ነበር። ሐረገ ትውልዱ ከአሮን ወገን ነውና በክህነቱ ተግቶ ያገለግል ነበር። በዚያ ላይ ሊቀ ካህንነትን በመመረጡ ሕዝቡን ይሠራ ያስተምር ያስተዳድር ነበር።
ቅዱስ አልዓዛር ከተባረከች ሚስቱ ሰሎሜ 7 ወንዶች ልጆችን አንኤም፣ አንጦኒኃስ፣ ዖዝያ፣ አልዓዛር፣ አስዮና፣ ስሙና መርካሎስን ወልዷልል። እነርሱንም በሥርዓት አሳድጐ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጐ ነበር:: በዚያው ዘመን በኢየሩሳሌም አካባቢ የሚኖሩ ስምዖን አልፍሞስና መባልስ የሚባሉ 3 እኩያን (ክፉ) ካህናት ነበሩ::
እነዚሁም ሕዝቡን ከማስቸገር: ፈጣሪን ከማሳዘን ቦዝነው አያውቁም ነበር:: የክፋታቸው መጨረሻ ግን የገዛ ሃገራቸውን ማጥፋት ሆነ::
ነገሩ እንዲህ ነው:- 3ቱም ተመካክረው የአልዓዛርን የሊቀ ካህንነት ቦታ ሊቀሙ ወስነው ወደ እርሱ ሔዱና እንዲህ አሉት። "ሹመት በተርታ ሥጋ በገበታ" ሲሆን ያምራልና እኛ በተራችን በወንበሩ ላይ እንቀመጥ።" እርሱ ግን "ሕዝቡን ጠይቃችሁ ተሾሙ" አላቸው። እነርሱም ሕዝቡን ጠርተው "ሹመት ይገባናል" ቢሏቸው ሕዝቡ መልሶ "አልዓዛርን የሾመው እግዚአብሔር ነውና እናንተም ከፈጣሪ ጠይቃችሁ ተሾሙ" አሏቸው።
በዚህ ጊዜ ሦስቱ እኩያን ተቆጡ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንደ ማይሰጣቸው ያውቃሉና። ወዲያው ግን ሦስቱም ከአካባቢው ጠፉ። ከኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ጨካኙ የግሪክ ንጉሥ አንጥያኮስ ሔዱ።
አንጥያኮስ ማለት "ቀኝ ዐይናችሁን ገብሩልኝ" የሚል ንጉሥ ነው። እርሱን "ኢየሩሳሌም ባለቤት የላትምና ሒደህ ውረራት" አሉት። "አጥሩ ጥብቅ ነው። በምን እገባለሁ?" ቢላቸው "እኛ በመላ እናስገባሃለን" አሉት። እርሱም 240,000 ሠራዊት አስከትቶ ወረደ።
እነርሱ ቀድመው ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው ያስወሩ ጀመር። "እናንተ ሹመት ብትነሱንም እኛ ግን አንጥያኮስን ያህል ንጉሥ በእሥራኤል አምላክ አሳምነን መጣን" እያሉ ይሰብኩ ገቡ። ቅዱስ አልዓዛር "አትስሟቸው በዚያም ላይ አሕዛብ የተቀደሰውን ምድር መርገጥ የለባቸውም" ብሎ ነበር። ነገር ግን አንዳንድ ችኩሎች አይጠፉምና ፈጥነው የከተማዋን በር ከፈቱት። ሠራዊቱን ደብቆ ትንሽ ራሱን የቆመ የመሰለው አንጥያኮስ በምክንያት በክፋትና በመላ ሁሉን ሠራዊቱን አስገባ። የሚገርመው በጊዜው የከተማዋ ሕዝብ 12 እልፍ (120,000) ሲሆን ንጉሡ ያስገባው ሠራዊት ግን 24 እልፍ (240,000) ሆኖ ተገኘ።
ወዲያው አንጥያኮስ ሕዝቡን ሰበሰበና አልዓዛርን ለብቻው ጠርቶ ተናገረው። "አንተ አምላክህን እንደምትወድ ሰምቻለሁ። አንተ የበጉን መስዋዕት በልተህ ለስዕለ ኪሩብ ሰግደህ ሕዝቡን ግን እሪያ (አሳማ) እንዲበላና ለጸፀሐይ እንዲሰግድ አድርግልኝ" አለው። ቅዱስ አልዓዛር መለሰለት "እግዚአብሔር የሾመኝኮ በጐ ሃይማኖትን ላስተምር እንጂ ለክፋት አይደለም። ለሕዝቤ የክፋት አብነት ፈጽሞ አልሆንም" አለው። ያን ጊዜ ንጉሡ በቅዱሱ ላይ ተቆጣ። "የምልህን ካላደረግህ ብዙ ግፍ ይደርስብሃል" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "የፈለግኸውን አድርግ" አለው።
በዚያን ጊዜ ንጉሡ የቅዱሱን ሚስትና 7 ልጆች እንዲያመጡለት አዘዘ። ቅዱሱ እያየ ከፊቱ ላይ 7ቱንም ልጆቹን በሰይፍ አስመታቸውና 7ቱም ወደቁ። ለአንድ አባት ይህ የመጨረሻው መራራ ፈተና ነው። አልዓዛር ግን ምን አንጀቱ በኀዘን ቢቃጠልም ከልጆቹ ለእግዚአብሔር አድልቷልና ቻለው ታገሠው።
በዚህ ለውጥ እንዳልመጣ ያየው ንጉሡ ሌላ ፍርድ ተናገረ። ቅዱሱንና ሚስቱን (ሰሎሜን) በፈትል ጠቅልለው በሠም ነከሯቸው። (ጧፍ እንደሚሠራበት መንገድ ማለት ነው)
አሁንም ግን ከአምልኮታቸው ፈቀቅ ባለማለታቸው ትልቅ ብረት ምጣድ ተጥዶ ሁለቱም ከነነፍሳቸው እንዲቃጠሉ ተደረገ። ቀጥሎም ሕዝቡን እንዲፈጁ አዋጅ ወጣ። በከተማዋ ከነበረው ሕዝብ 40,000 ያህሉ ተገደሉ።
40,000 ያህሉ ሲማረኩ 40,000 ያህሉን ደግሞ ይሁዳ የሚባል አርበኛ በር ሰብሮ ይዟቸው ሸሸ። "እንሾማለን እንሸለማለን" ብለው ሕዝባቸውን ያስፈጁ እነዚያ ካህናትም እግዚአብሔር ፈርዶባቸው እነርሱም ተገደሉ። ቅዱሱ የአልዓዛር ቤተሰብ ግን የክብርን አክሊል አግኝተዋል።
የእሥራኤል አምላክ ቸሩ እግዚአብሔር እንዲህ ካለው መከራ በኪነ ጥበቡ ይሰውረን። ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን።
ነሐሴ 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አልዓዛር ካህን (ሰማዕት)
2.ቅድስት ሰሎሜ ሰማዕት (ሚስቱ)
3."7ቱ" ቅዱሳን ሰማዕታት (ልጆቹ)
4.ቅዱስ አሞን ሰማዕት
††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages