ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 7 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, February 16, 2024

ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ 7

 እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የጽንሰት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ቁጽረታ (ጽንሰታ) ለማርያም
ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ መድኃኒት፤ የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል::
ስለ ምን ነው ቢሉ:-
ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው:: አንድም ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ ናትና እንዲህ ይላሉ::
"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ::"
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው::"
(መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. 1:9, መኃ. 4)
ይሕች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል::
የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ(አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር::
ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::
የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::
ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ: በማኅጸኗ ስትደርስ አየ::
እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::
በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::
እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ"
"ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ::
(ቅዳሴ ማርያም)
ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ መታሰቢያ ናት:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ በዚህች ቀን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልጶስ ይዟቸው ሔደ:: በዚያም ጌታ ከእነሱ ራቅ ብሎ ተቀምጦ ነበርና የማይሰማቸው መስሏቸው እርስ በእርስ ይከራከሩ ገቡ::
የክርክራቸው መነሻ ደግሞ ጌታችን ነበር:: የዋሃን (ገና ምሥጢርን ያልተረዱ) ነበሩና አንዱ ተነስቶ "ኤልያስ ነው": ሌላኛው "ሙሴ": ሦስተኛው "ኤርምያስ ነው" በሚል ተከራከሩ:: ቅዱስ ጴጥሮስ ለብቻው ቆሞ ነበርና ጠርተው "ሃሳባችንን አስታርቅልን:: ለአንተስ ማን ይመስልሃል?" አሉት::
አረጋዊው ሐዋርያም ተቆጣቸው:: "እናንተ እንደምታስቡት እርሱ ከነቢያት አንዱ ሳይሆን "እግዚአ ነቢያት-የነቢያት ፈጣሪ ነው" አላቸው:: ወዲያውም ጌታ ጠርቷቸው ወደ እርሱ ቀረቡ::
ቸር አምላክ "ለምን ተጠራጠራችሁኝ" ብሎ መገሰጽ ሲችል እንዳይደነግጡ ጥያቄውን በፈሊጥ አደረገ:: "የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?" አላቸው:: እነርሱም በልባቸው ያለውን የሌላ አስመስለው ተናገሩ::
ጌታችን "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ጸጥ አሉ:: ገና ሃይማኖታቸው አልጸናም ነበርና:: በዚያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ተነስቶ "አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው-አንተ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ ነህ" አለው:: (ማቴ. 16:16)
ይህች ቃል የክርስትና ሃይማኖት መሠረት ናትና ጌታችን "አንተ ዓለት (መሠረት) ነህ" ብሎ የቤተ ክርስቲያንን በዚህ እምነት ላይ መመስረት ተናገረ:: ለቅዱስ ጴጥሮስም "መራሑተ መንግስት-የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ (ሥልጣን)" ተሰጠው::
ሊቀ ሐዋርያትነትንም ደረበ:: ዛሬ ለበርካቶቹ የጸነነባቸው ይሔው እምነት ነው::
ኢየሱስ ክርስቶስን "አምላክ ወልደ አምላክ:
ወልደ ማርያም:
አካላዊ ቃል:
ሥግው ቃል:
ገባሬ ኩሉ:
የሁሉ ፈጣሪ"ብለው ካላመኑ እንኳን ጽድቅ ክርስትናም የለም::
አፄ ናዖድ ጻድቅ
ሃገራችን ኢትዮጵያ ምስፍና ከክህነት: ንግሥናን ከጽድቅ ያጣመሩ ብዙ መሪዎች ነበሯት:: ከእነዚህ አንዱ ደግሞ አፄ ናዖድ ናቸው:: ጻድቁ ንጉሥ የነገሡት ከ1487 እስከ 1499 ዓ/ም ሲሆን ለእመቤታችን በነበራቸው ልዩ ፍቅር ይታወቃሉ:: ካህን እንደ ነበሩም ይነገራል::
ዛሬ ሁላችን የምንወዳትን ጸሎት (ሰላም ለኪ: እንዘ ንሰግድ ንብለኪ . . .)
የደረሷት እርሳቸው ናቸው:: ትልቁን መልክአ ማርያምም ደርሰዋል:: ይህ መልክእ ጣዕሙ ልዩ ነው::
የጻድቁ ንጉሥ ሚስት (ማርያም ክብራ): ልጆቻቸው (አፄ ልብነ ድንግልና ቡርክት ሮማነ ወርቅ) እጅግ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩ:: ንጉሡ አፄ ናዖድ ከባለሟልነት የተነሳ ድንግል ማርያምን "እመቤቴ ስምንተኛው ሺ መቼ ይገባል? ጊዜውስ እንዴት ያለ ነው?" አሏት::
እመ ብርሃንም በአካል ተገልጻ የዘመኑንና የሰውን ክፋት ነገረቻቸው:: ንጉሡም አዝነው "እመቤቴ! ከዛ ዘመን አታድርሺኝ" አሏት:: በዚህ ምክንያት የስምንተኛው ሺህ ዘመን መስከረም 1 በ1500 ዓ/ም ሊገባ እርሳቸው ነሐሴ 7 ቀን በ1499 ዓ/ም ዐርፈዋል::
ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የድንግል እናቱን ጣዕም: ፍቅር: የቅዱስ ጴጥሮስን ሃይማኖትና የአፄ ናዖድን በረከት ያሳድርብን::
ነሐሴ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በዓለ ጽንሰታ ለእግዝእትነ ማርያም
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ገብርኤል መበሥር
4.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
5.አፄ ናዖድ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
6.ቅዱስ ዮሴፍ ጻድቅ (ወልደ ያዕቆብ-ልደቱ)
7.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት
ወርኀዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)
"መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው:: ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል::
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! በአንቺ የተደረገው ድንቅ ነው . . .
ሰው እናታችን ጽዮን ይላል::" †††
(መዝ. ፹፮፥፩-፮)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages