እነሆ_የታረዘው_ሰው_ምስክርነት
#ደጉ አባታችን ሊቀ ብርሃናት ሐዋዝ ተበጀ በተቸገርሁበት ጊዜ ጸድቀውብኛል። “ታርዤ አልብሳችሁኛልና” ማቴ 25:35 ይህ የከበረ የጌታ ቃል በአባታችን እንደተፈጸመ በፍጹም ልቤ አምናለሁ።
#ሊቅነትን ከደግነት ጋር የተካኑት ትልቁ አባታችን ማረፋቸውን ስሰማ በአልጋዬ ላይ ስቅስቅ ብዬ አልቅሻለሁ። ዕንባዬ በቀላሉ መፍሰስ ካቆመ ሰነባብቷል። ሞት በዚህ ዘመን ብርቅ አይደለምና ማልቀስ አቁሜአለሁ። ደረቅ ሆኛለሁ። የአባታችንን ማረፍ ስሰማ ግን የተቸገርሁበትን ዘመን እያሰብሁ፣ በችግሬ ጊዜ የደረሱልኝን አባቴን እየናፈቅሁ ሆድ ባሰኝና አነባሁ።
#በ1995 ዓ.ም ከክፍለ ሀገር አዲስ አበባ እንደገባሁ ይዘውኝ የመጡ መርጌታ ያገለግሉ የነበረበት ደብር ፈረንሳይ አቦ (አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ) ቤተክርስቲያን ነበር። ከአንድ ሳምንት በላይ ከእሳቸው ጋር እንድቆይ አልተፈቀደልኝም ነበርና እንጦጦ መንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን የቅኔ ቤተ ጉባኤ ስላለ እዚህ ተጠጋ ብለው ከክፍለ ሀገር ያመጡኝ መምህር ከቅኔ መምህሩ መርጌታ አክሊሉ መኮንን ጋር አስተዋውቀውኝ መቃብር ቤት ከተማሪዎቹ ጋር ተቀላቀልሁ። መርጌታ አክሊሉ መኮንን አዴት ከተማ ውስጥ ሲጓዙ በጠራራ ፀሐይ መከላከያ በኮማንድ ፖስት ምክንያት ከገደላቸው ሦስት ዐራት ዓመት እንደሆናቸው ሰምቻለሁ። በብዙ የረዱኝ ባለውለታዬ ነበሩ። ነፍሳቸውን ይማርልኝ። የዚህ ዘመን የግፍ ሰለባ ከሆኑት አንዱ እሳቸው ናቸው። ባሰብኋቸው ቁጥር ሁሌም አዝናለሁ።
#በጊዜው እኔ የምፈልገው በዲቁና ተቀጥሮ ማገልገል ነበር። ምክንያቱም ውስጠዘ ቅኔና ደብር ዓባይ ቅዳሴ ከአንድም ሁለት ቦታ ላይ በደንብ ተምሬ፣ የአቋቋም ትምህርቴን አቋርጬ ነው አዲስ አበባ የገባሁት። ስለዚህ ስመጣ ዓላማዬ ተቀጥሮ ማገልገል ነበር። ፈተናው ግን ቀላል አልነበረም።
#አዲስ አበባ የገባሁት ዐቢይ ጾም አካባቢ ስለነበር ሌሊት ሰዓታት ቁሜ አድራለሁ፣ ጧት ስብሐተ ነግህ ከመርጌቶቹ ጋር እቆማለሁ፣ ቀን አስቀድሳለሁ....የየቀን ውሎዬ ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነ።
#በዚህ ጊዜ ነበር ዛሬ በሥጋ የተለዩንን፣ የደብሩን አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት ሐዋዝ ተበጀን የመተዋወቅ ዕድል የገጠመኝ። ሊቀ ብርሃናት የታወቁ የድጓ መምህር ናቸው። ዋሸራ የማዕበል ፈንቴ ቅኔ አስነጋሪ እንደነበሩ በጆሮዬ ነግረውኛል። ጽላሎ ከእመይቴ ገላነሽም እንደተማሩ ሰምቻለሁ። ብቻ ግን ሊቁ ከማኅሌት በፍጹም አይለዩም። ዐቢይ ጾም እሁድ እሁድ መወድሱ ለእሳቸው ይሰጣቸዋል። ታዲያ ደጉ አባታችን ለእኔ “ነዪ ተቀኚ” ብለው መልሰው መወድሱን የቅኔ ዳረጎት በተደጋጋሚ ሳምንት የቅኔ መምህራኑ ባሉበት ይሰጡኛል። አቤት ደስታዬ! ባዩኝ ቁጥር “ኧረ እንዲያው ይህንን ልጅ ጎንደር አቋቋም ቤት ጥሎልኝ የሚመጣ ሰው ባገኘሁ። እንዴት ያለው ልጅ ከተማ ገብቶ ተበክሎ ሊቀር ነው” ይሉኝ ነበር። አለቃው ፊት ቅኔ ማድረግ ለቋሚ ሠራተኛነት የታጨሁ እየመሰለኝ በትኩስና ለጋ ዕድሜዬ ቅኔ ማኅሌቱን እነሰነስበት ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እሳቸው ቅኔ ሲያደርጉ “ዲበ ነዪ ተመሪ” ይሉኛል። አቤት እንዴት ደስ ይለኝ እንደነበር!
#ብዙ ሳልቆይ ስንት ዓመት ደጅ የጸኑ ዲያቆናት ባሉበት የተወሰኑ ካህናት አገልግሎቴን አይተው ቅዳሴ መቀደስ እንዲፈቀድልኝ ለሊቀ ብርሃናት ሐዋዝ ጠየቁልኝና ተፈቀደልኝ። #የመጀመሪያው_ትልቅ_ውለታ_ይህ_ነው። ወዳጆቼ ለአንድ ደጅ ጠኚ ቅዳሴ መግባት ማለት ደስታውን በቃላት ልገልጽላችሁ አልችልም። ማይክራፎኑን ጨብጬ “ተንሥእ” ያልሁኝ እለት ምድርን የገዛሁ ያህል ተሰምቶኝ ነበር። ሐሙስ ግንቦት 26-1996 ዓ.ም አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተወዳድሬ አልፌ ቤቴል ደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እስከምመደብ ድረስ “ሰላም ለልብከ፣ ቅሩበ ኲልያት ምንታዌ....ውስተ መቅደስከ ረስየኒ ሠርዌ።” የሚለውን በየቀኑ ደጋግሜ እጸልየው ነበር።
#እንድቀድስ ለአለቃው ሊቀ ብርሃናት ሐዋዝ ተበጀ ያስፈቀዱልኝና ትልቁን ኃላፊነት የወሰዱት የዚያን ጊዜው መምህር ምሥራቅ ናቸው። ተያዥ እሆነዋለሁ ብለው ያስፈቀዱልኝ እሳቸው ናቸው። ከዚያም ተቀናቃኝና ከሳሽ እስኪነሳብኝ ድረስ ለትንሽ ወራት ቀደስሁ። መምህር ምሥራቅ ደግና ርኅሩህ፣ ትጉህ አገልጋይ ናቸው። የምለብሰው ባጣሁበት ጊዜ ብዙ ልብስ አልብሰውኛል። የእሳቸውን ውለታ በሌላ ቀን እተርከዋለሁ። መምህር ምሥራቅ ዕድሜና ጤና ይስጥልኝ። ውለታ መላሽ ያድርገኝ።
#ከትንሽ ወራት በኋላ በየአቅጣጫው ከአቅሜ በላይ ምቀኛ ተነሳብኝና ቅዳሴ እንዳልገባ ተከለከልሁ። አንድ እንደእኔ ደጅ መጥኚያ ፈልጎ እዚያው የነበረ ጥጋበኛ ደጀጠኚ መርጌታ ከቅኔ መምህሩ ጋር ተነጋግሮ ከመቃብር ቤቱ አስወጣኝና በረንዳ ላይ ወደቅሁ ለወራት በረንዳ መተኛት ጀመርሁ። ከመቃብር ቤት እንድወጣ የተደረግሁበት ወቅቱ ክረምት ስለነበር የአሁኑ የቁስቋም ደወል ቤት ያን ጊዜ በመሠራት ላይ ነበር። እናም ከዝናብና ከጅብ ለመዳን ሌሊት የሳር ፍራሼን ፉካው ውስጥ እያስገባሁ፣ ቀን ቀን ጽዱ ሥር ፍራሼን እያነጠፍሁ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ ፍለጋ በእግሬ በየቀኑ እመላለስ ነበር። ከሀገረ ስብከቱ ወደ ማታ ስመለስ ኩርቱ ፌስታሌን ይዤ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ጀምሬ ቁስቋም ድረስ እንደ ክፍለ ሀገሩ "በእንተ ስማ ለማርያም" እያልሁ ለአንድ ዓመት ቁራሽ ለምኛለሁ።
#አንድ ቀን ከማድርበት ፉካ ውስጥ ወጥቼ ጸጉሬን ስታጠብ ያ ከመቃብር ቤት ያባረረኝ ጥጋበኛ መርጌታ “አንተ እዚህ ምን ታደርጋለህ? ከዚህ አካባቢ ጥፋ አላልሁህም ብሎ በዱላ ቀጠቀጠኝ። በዚህ ጊዜ ከአሜሪካ ኤምባሲ አንዳንድ ጊዜ ብቅ ይሉ የነበሩ ፖሊሶች ድንገት ሲደበድበኝ አይተው በካልቾ አነሡልኝ። ለምን እንደመታኝ ጠየቁኝ። በዝርዝር አስረዳኋቸው። በግፍ ከመቃብር ቤት ተባርሬ የምተኛበትንና ዝናም ጠብጠብ የሚልበትን ፉካ አሳየኋቸው። በዚህ ጊዜ አለቃውን ማግኘት እንፈልጋለን ብለው ወደ ሊቀ ብርሃናት ሐዋዝ ተበጀ ቢሮ ወሰዱኝ።እሳቸውም ያለሁበትን ሁኔታ አያውቁም ነበርና እጅግ አዝነው “ከዚህ ፉካ ውስጥ ፍራሽህን አውጣና መቃብር ቤቱ ግባ” አሉኝ፣ “ማንም እንዳይነካው” ብለው ማስጠንቀቂያ ሰጥተውልኝ ሄዱና ለተወሰነ ጊዜ በሰላም መኖር ጀመርሁ። #ቁጥር ፪ (#ሁለት) #ታላቅ_ውለታ።
#ከጥቂት ወራት በኋላ ያለ የሌለኝን ልብሴን አጥቤ ውጭ ላይ እንዳሰጣሁት ሌባ ጥርግርግ አድርጎ ወሰደብኝና ያለ መቀየሪያ ልብስ ቀረሁ። በነገራችን ላይ እንደዚያ ያሰቃዬኝ የነበረው መርጌታ ቅዳሴ ቤት እያለሁ ውዷ እናቴ በውድ ዋጋ አሠርታ ያለበሰችኝን ቢጫ ፎጣ ጋቢ ልብስ ነበር። ይህንን ውድ ጋቢ ልብስ ይህ መርጌታ ሲቸገር አይቼ ግማሹን ነጥዬ የሰጠሁት ሰው ነው።
ኮቱ በጣም ያምር ነበር። ለእኔ በጣም ስለረዘመኝ ለዚያ ላሰቃየኝ መርጌታ ሰጠሁት። አይ ልጅነት፣ ቂም በቀል የለ፣ ምን የለ!
በዚህ አጋጣሚ ከዚህ መርጌታ ጋር አሁን ሳይሆን እዚያው ያን ጊዜ ነው የታረቅነው። ምናልባት ይህንን ጽሑፍ ካነበብኸው እንዳይከፋህ አደራ። የምተርከው ታሪክ ስለሆነ ብቻ ነው።
#ስለ_ሊቀ_ብርሃናት_ሐዋዝ_ተበጀ ብዙ የምተርከው መልካም ነገር ነበር ምን ዋጋ አለው አንባቢ እንዳላሰለች ትቼዋለሁ። እጅግ ሲበዛ ደግ ናቸው። ሊቅነትና ትኅትና ገንዘባቸው ናቸው። የማይለወጥ፣ የማይናወጥ፣ የማይበርድ፣ የማይቀየር መንፈሳዊነትን ከእሳቸው አይቼባቸዋለሁ። ተምሬባቸዋለሁ።
#በሕይወቴ ውስጥ ከማልረሳው ብሎም ከማስታውስላቸውና ሁልጊዜም ትዝ ከሚለኝ ነገር አንዱና ለአንባብያን መናገር የምፈልገው ነገር አለ። በተለይ ይህንን ታሪክ ስነግራችሁ ገጠር ተምራችሁ ያደጋችሁ ሊቃውንት ትረዱኛላችሁ። በገጠር የዜማ መምህራኖቻችን ማታ ማታ ውዳሴ ማር በዜማ ቆመው ያደርሱ ነበር። እኛም ከበን አብረን እናደርስ ነበር። ሊቀ ብርሃናት ሐዋዝ ተበጀ ማታ ማታ ከዘራ መቋሚያቸውን ይዘው ከቤታቸው ወደሚያስተዳድሩባት ደብር እንጦጦ ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን በስተምሥራቅ በኩል ይገባሉ። ከዕቃቤቱ በስተቀኝ በኩል ሆነው ውዳሴ ማርያም እያደረሱ ይሄዱ ነበር። እኔ ሳውቅ ይህ አዲስ አበባ ውስጥ የተለመደ ነገር አይደለም። እንኳን አለቆች መርጌቶችም ውዳሴ ማርያም በዜማ የሚያደርሱ አይመስለኝም። ሊቁና ደጉ አባታችንን ግን ከልጅነታቸው እስከ ዕረፍት ቀናቸው ይህንን አድርገው፣ መልካም አርአያ ሆነው ዛሬ ከዚህ ክፉ፣ ዕረፍት-አልባ ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ሄደዋል።
#ደጉና ርኅሩኁ፣ ሊቁና መንፈሳዊው አባቴ ተራቁቼ አልብሰውኛልና ለቸሩ መድኃኔዓለም ይህንን ምስክርነት ሰጥቻለሁ። ማመልከቻዬንም ፈጣሪያችን ችሎት አስገብቻለሁ። እርስዎ ለእኔ ያደረጉት ጌታ ለእርሱ እንደተደረገ አድርጎ እንደሚቆጥረው ያስተማረን እርሱ ነው። እናም ጌታም በቃሉ ታማኝ ነውና “አንተ የአባቴ ቡሩክ ና፥ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀልህን መንግሥት ውረስ።” ማቴ 25:34 እንዳለዎት በፍጹም ልቤ አምናለሁ።
#ሁልጊዜ እንደፎከርሁ አንድ ነገር ሳላደርግልዎ በመሄድዎ የማይረሳ ቁጭት ጥለውብኛል። አዝናለሁ። ደግነትዎን ለካህኑ የመንፈስ ብቻ ሳይሆን የሥጋ ልጅዎ ቀሲስ መዝሙር ሐዋዝ ደጋግሜ ነግሬው ነበር። ምናልባት ከተቆጠረልኝ እርሱን አግኝቼ ምስጋና የማቀርብ ይሆናል።
#ደጉ አባታችን #ሊቀ_ብርሃናት_ሐዋዝ ደጉ ሣምራዊ መድኃኔዓለም ከደግጋጎቹ ጋር በዕቅፉ ያሳርፍልን።
#ለጓደኛዬ ልጃቸው ቀሲስ መዝሙር ሐዋዝ ተበጀ እና ለመላው ቤተሰቡ፣
#ለእንጦጦ መንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናን መጽናናትን እመኛለሁ።

No comments:
Post a Comment