ቅዱስ ቶማስ - አትሮንስ ሚዲያ

አትሮንስ ሚዲያ

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, April 15, 2020

ቅዱስ ቶማስ


ሥራ መሥራት የማይሰለቸው ታታሪ ሰራተኛ የሆነ አንድ ጎልማሳ ሰው ነበር:: ይህ ጎልማሳ ሰው አብዝቶ ኃጢአትን ይሰራ ነበር:: ከእለታት በአንዱ ቀን በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ እጅ የተባረከ እንጀራ ከሕዝብ ጋር አብሮ ተቀበለ:: ወደ አፉም ሊጨምረው በወደደ ጊዜ እጆቹ ደረቁ:: በዚህን ጊዜ አብረውት የነበሩት ሰዎች በነገሩ ተገርሙ ደነገጡም:: ወዲያውኑን ያዩትን ድንቅ ተአምር ለሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ነገሩት:: ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ነገሩን ከሰማ በኋላ ልጁን ጠርቶ ልጄ ሆይ የሆንከውን ነገር ሳታፍር ሳትፈራ እውነቱን ንገረኝ የ እግዚአብሔር ቸርነት በግልጽ ዘልፎሃልና አለው:: ያም ሰው ኃጢአቱን ያውቃልና ወዲያውኑ ከሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ እግር ስር ሰገደና እንዲህ በማለት ኃጢአቱን መናዘዝ ጀመረ:: እኔ መልካም ሥራ የሰራሁ መስሎኝ ክፉን ሥራ ሰርቻለሁ:: አንዲት ሴት ነበረች:: አስቀድሞ ወደ እርሷ እኔ እገባ ነበር:: አንተም በንጽሕና እንድንኖር አስተማርከን መከርከን ያች ሴት ግን ከ እርሷ ጋር እተኛ ዘንድ ኃጢአትን እሰራ ዘንድ ነዘነዘችኝ:: በነገሩ ተናድጄ ሰይፍ አነሳሁና አንገቷን ቀላኋት (አረድኳት) አለው:: ቅዱስ ቶማስም እንዴት እንዲህ ያለ ቁጣና የአውሬ የእንስሳ ሥራ ትሠራለህ? አለው:: ይህንን ነገር ለሚሰሙትም በሙሉ ውኃ ያመጡ ዘንድ አዘዛቸው:: እነሱም በፍጥነት ውሃውን ይዘው መጡ:: ቅዱስ ቶማስም በውሃው ላይ ጸለየ:: ጎልማሳውንም በ እግዚአብሔር ታምነህ እጆችህን ታጠብ አለው:: ቅዱስ ቶማስ የነገረውን አምኖ ሲታጠብም ዳነ:: ከዚህ በኋላ ቅዱስ ቶማስ ለጎልማሳው ሰው የዚያች ሴት አስከሬን የት ነው? ቦታውን ምራኝ ብሎ ጠየቀው:: ያም ጎልማሳ መርቶ ወደ ቦታው አደረሰው:: በደረሱም ጊዜ ቅዱስ ቶማስ በልጅቱ ላይ የደረሰውን ግፍና ጭካኔ አይቶ እጅግ አዘነ:: ወደ ውጭም አውጥተው በአልጋ ላይ ያኖሯት ዘንድ አዘዘ:: እነሱም ቅዱስ ቶማስ እንዳዘዛቸው አደረጉ:: እጁንም አንስቶ በላይዋ ጭኖ ጸለየ:: ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ጎልማሳውን ሂድ እጇን ይዘህ እኔ ቀድሞ በእጄ ገደልኩሽ አሁን ግን በሃይማኖት በእኔ እጅ ክርስቶስ ያስነሳሽ በላት አለው:: እሱም ቅዱስ ቶማስ እንዳዘዘው አደረገ:: እጇንም ይዞ ሳባት:: ፈጥናም ተነሳች:: ሐዋርያው ቅዱስ ቶምስን አየችው:: አልጋዋንም ትታ ከቅዱስ ቶማስ እግር ስር ሰገደች:: የልብሱንም ጫፍ ይዛ በአንተ ዘንድ አደራ ያስጠበቀኝ ባልንጀራህ ወዴት አለ? ብላ ጠየቀችው:: ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ወደ የት ደርሰሽ ነበር ንገሪኝ? አላት:: እርሷም አንተ ከእኔ ጋር እያለህ እንዴት ንገሪኝ ትለኛለህ? አለችው:: ያየሽውን ንገሪ አላት:: ከሥጋዬ በተለየሁ ጊዜ አንድ ልብሱ የቆሸሸ: ሽታውም የሚከረፋ: ጠቋራ ተቀበለኝ:: የ እሳት ጉድጓድና የ እሳት መንኮራኩር ወደ አለበት ቦታ ወሰደኝ:: ደግሞም እድፍንና ትልን የተመላ ጉድጓድን አየሁ:: ነፍሳትም በውስጡ ይንከባለላሉ:: በዚያም በምላሳቸው የተንጠለጠሉ አሉ:: በጸጉራቸውም የተንጠለጠሉ አሉ:: በእጆቻቸውም በእግሮቻቸውም የተንጠለጠሉም አሉ:: በላያቸውም ድኝ ይጤስባቸዋል ያስጨንቋቸዋልም:: ያ የሚመራኝም እኒህ ነፍሰ ገዳዮች: በዝሙት የረከሱ: ዘራፊዎች (ሌቦች): በሐሰት እየመሰከሩ አምላክን ሲያሳዝኑ የኖሩ: በእግዚአብሔር መንገድ ያልተመላለሱ: የእግዚአብሔርን ሕግ የጣሱ: የእግዚአብሔርን ሕልውና የካዱ: እነዚህ ሁሉ በንስሐ ያልተመለሱ ናቸው ስለዚህ እንደ ሥራቸው ይቀጣሉ አለኝ አለችው:: ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ከዚያ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይህች ሴት የምትለውን ሰማችሁ ከደቂቆች በፊት ሞታ ነበር በ እግዚአብሔር ቸርነት ተነሳች ያየችውን ነገረቻችሁ:: ይህች ሴት ያለችውን ሰማታችኋል ነገር ግን ያለው ስቃይ ይህ ብቻ አይደለም ነገር ግን ከዚህ የሚከፋ አለ:: እናንተም የኃጢአትን ሥራና ክፉ ሃሳብን ትታችሁ ወደ ፈጣሪያችሁ ወደ አምላካችሁ በፍጹም ልብ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ:; የተፈጠራችሁበት ዋና ዓላማ ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ነውና ከልባችሁ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ:: ትህትናን የዋህነትንና ፍቅርን ንጽሕናንም ጠብቁ ከ እግዚአብሔርም ዘንድ ጸጋን ትቀበላላችሁ አላቸው:: ክብር ይግባውና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም የተሰበሰው ሕዝብ በሙሉ አንድም ሳይቀር አመኑ:: ለድኆችም ምጽዋትን ሊሰጡ ብዙ ገንዘብ ሰብስበው አመጡ:: ለድኆች ምጽዋት መስጠት ለሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ልማዱ ነበርና:: ይህም ታላቅ ተአምር በየሃገሩ በተሰማ ጊዜ በተለያዩ በሽታ የሚሰቃዩትንና በአጋንንት የሚሰቃዩትን በሽተኞች በሙሉ አምጥተው በጎዳና (በመንገድ) ዳር አኖሯቸው:: ቅዱስ ቶማስም የእግዚአብሔርን ቸርነቱን ምህረቱን እያስተማሩ እነዚህን በሽተኞች በሙሉ በእግዚአብሔር ሃይል ፈወሳቸው አዳናቸው:: ወስብሐት ለእግዚአብሔር የእግዚአብሔር ቸርነቱና ምሕረቱ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነቱና ርህራሄዋ የቅዱሳን በረከታቸው ረድኤታቸው ጸሎታቸው አይለየን:: እግዚአብሔር አምላካችን በቅዱስ ቶማስ ጸሎት ይማረን በረከቱና ረድኤቱም አይለየን አሜን::

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages