የጌታችን ልደት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, April 15, 2020

የጌታችን ልደት


የጌታ ልደት...
 
“ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ” (እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም ዐማኑኤል ትለዋለች) ኢሳ 7፡14 የጌታን ልደት ከማየታችን በፊት ጌታችን ለምን ሰው ኾነ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይገባናል፤ ይኸውም ሰው ያረገው በቸርነቱ ብዛት ለአዳምና ለሔዋን በገባው ቃል መሠረት ነው፤ ይኸውም አዳምና ሔዋን ጌታ አትብሉ ያላቸውን ዛፍ በልተው ከገነት ከተባረሩ በኋላ አዳም የቤተ ፈት ልማድ አላገኘውም፤ ቤተ ፈት በዚኽ ጊዜ እበላ እጠጣ፤ በዚኽ ጊዜ ተድላ ደስታ አድርግ ነበር ብሎ ያዝናል፤ ርሱ ግን ፈጣሪዬ አትብላ ያለኝን ዕፀ በለስን በልቼ በደልኍ ብሎ በኀጢአቱ ፲፬ ሱባዔ ፺፰ ዓመት መሪር ልቅሶን አለቀሰ

‹‹ወአልቦቱ ካልዕ ኅሊና ላዕለ ኀጢአቱ ዘእንበለ ብካይ ወላህ›› እንዲል መቅድመ ወንጌል ያን ጊዜ ‹‹በአንተና በሴቲቱ መኻከል በዘርኽና በዘርዋም መኻከል ጠላትነትን አደርጋለኍ›› ሲል የተናገረውን የተስፋ ቃል በማጒላት ‹‹ወእምድኅረ ኀሙስ መዋዕል ወመንፈቀ መዓልት እምሕረከ ወእሣሃለከ በብዝኀ ሣህልየ ወምሕረትየ፤ ወእወርድ ውስተ ቤትከ ወአኀድር ውስተ ከርሥከ ወበእንቲኣከ ኦ አዳም እትወለድ ከመ ሕፃን ወበአንቲኣከ ኦ አዳም አሐውር ውስተ ምሥያጥ፤ ወበእንቲኣከ እጸውም ፵ መዓልተ ወ፵ ሌሊተ፤ ወበእንቲኣከ እትዌከፍ ወእትዔገሥ ሕማማተ ወበእንቲኣከ እሰቀል ዲበ ዕፀ መስቀል›› (በፍጹም ይቅርታዬ ከዐምስት ቀን ተኩል በኋላ በፍጹም ምሕረቴ ይቅር እልኻለኍ፤ ወደ ቤትኽም ወርጄ በባሕርይኽ ዐድራለኍ፤ አዳም ሆይ ስለ አንተ እንደ ሕፃን እወለዳለኍ፤ ስለ አንተ ወደ ገበያ እኼዳለኍ፤ ስለ አንተም አርባ ቀን አርባ ሌሊት እጾማለኍ፤ ስለ አንተ መከራ መስቀልን በትዕግሥት አቀበላለኍ፤ ስለ አንተም በዕንጨት መስቀል ላይ እሰቀላለኍ)ብሎ ተስፋውን ነግሮታል (መጽሐፈ ቀሌምንጦስ፣ ፫መቃ ፬፥፳፫-፳፬፤ ዕዝ ሱቱ ፬፥፩፤ ሲራ ፳፬፥፮፤ ገላ ፬፥፬)

አዳም በ፭ቀን ተኩል ያለውን የተስፋ ቃል እንደሱ አቈጣጠር መስሎት ዐምስት ቀናትን ጠብቋል፤ ኋላ ግን ዘመኑ ፭ሺሕ፭፻ መኾኑን ተረድቶ ይኽነን ተስፋ በመትከፈ ልቡናው ይዞ ይኖር ነበር፤ ዛሬ ነጋዴ ሥንቁን ይዞ እየበላለት ከዚኽ እስከዚያ ያደርሰኛል እያለ በተስፋ እንዲጓዝ፤ አዳምም በዐጸደ ሥጋ በዐጸደ ነፍስም ሳለ ፈጣሪዬ እንዲኽ ብሎኛል ይምረኛል፤ እያለ ተስፋውን አጽንቶ ሲጠባበቅ ኖረ፤ ይኽነን ተስፋውን ለልጆቹ አስቀድሞ ነግሯቸዋልና ልጆቹ አንዱ ሲቀበር አንዱ ሲወለድ፤ የአካላዊ ቃል ከድንግል ማርያም ተወልዶ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ዓለምን የማዳኑ ምስጢር እየተገለጸላቸው ፭ሺሕ፭፻ ዘመን እስኪፈጸም ትንቢት እየተናገሩ ሱባዔ እየቈጠሩ ኖረዋል (ማቴ ፲፫፥፲፯፤ ዮሐ ፭፥፵፮፤ ፰፥፶፮፤ ዕብ ፩፥፩-፪፤ ፩ዮሐ፩፥፩-፪)፡፡

5550 የተባለው ዘመንም ሲተነተን
ከአዳም↔ኖኅ መርከብ ═ 2256
ከኖኅ መርከብ ↔ እስከ መገናኛዋ ድንኳን ═1852
ከመገናኛዋ ድንኳን ↔ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ ═ 480
ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ ↔ መቅደሰ ዘሩባቤል ═ 510
ከመቅደሰ ዘሩባቤል ↔ ልደተ ክርስቶስ ═ 403
በአጠቃላይ ═5501 ይኽም ዘመን ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ በመባል ይታወቃል፡፡

ስለ መሲሕ የተነገሩ ተስፋዎች አበው፤ አራቱ ዐበይት ነቢያት 12ቱ ደቂቅ ነቢያት በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝተው የወልደ እግዚአብሔርን ሥጋን መዋሐድ በትንቢት አስተምረዋል፡፡

ከእነዚኽ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለጌታ በአበው ነቢያት በትንቢት የተነገሩ፤ ጌታችን ፈጽሟቸው በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ከተጻፉት ውስጥ ከእመቤታችን እንደሚወለድ (ዘፍ 3፡15 ↔ ማቴ 1፡20፤ ገላ 4፡4)

በድንግልና ስለመወለዱና ስሙ ዐማኑኤል እንደሚባል (ኢሳ 7፡14፤ ሕዝ 44፡2 ↔ ማቴ 1፡22-23)

በቤተልሔም ስለመወለዱ (ሚክ 5፡2 ↔ ማቴ 2፡1-6፤ ሉቃ 2፡4-6) መሲሕ

ከአብርሃም ወገን ስለመወለዱ (ዘፍ 12፡3፤ 22፡18 ↔ ማቴ 1፡1፤ ሮሜ 9፡5)

ጌታችን ከነገደ ይሁዳ እንደሚወለድ (ዘፍ 49፡10 ↔ ሉቃ 3፡33፤ ዕብ 7፡14) በመኾኑም በተነገረው ትንቢትና በተቈጠረው ሱባኤ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት የተፀነሰው አምላክ 9ወር ከ5 ቀን ሲፈጸም ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና በቤተልሔም ተወለደ፡፡

በዜና አበው ትምህርት ፸፻፴፮ መጻሕፍት እንደጻፈ የሚነገርለት ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የአምላክ ከቅድስት ድንግል መወለድ የርሱን የባሕርይ አምላክነት የርሷን ወላዲተ አምላክነት የሚገልጽ መኾኑን በልደት መጽሐፉ ላይ ተንትኖ ሲገልጸው

“When He had accomplished the full measure of nine months, the begetter of Adam…” (የዘጠኙን ወራት ሙሉ ስፍራ በፈጸመ ጊዜ የአዳም ወላጅ (አስገኚ) የኾነው ርሱ በትክክለኛው ወግ መሠረት ለመወለድ ፈቀደ፤ ርሱም አዳምን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ሊጽፈው በፈለገ ጊዜ ሕዝብ በሕዝብ ቈጠራ መዝገብ ይመዘገብ ዘንድ ትእዛዝ ወጣ (ሉቃ ፪፥፩)፤ ትእዛዛቱ አንድ ላይ ተጣመሩ፤ አንዱ ከላይ ከከፍታ እና ሌላኛው ከታች ከጥልቁ ምክንያቱም የኹለቱ ስፍራዎች ነገሥታት ሕዝብ ሊቈጥሩ ነበርና ቄሳር በሰብኣዊ ቈጠራ መዝገብ ሰዎችን ይጽፋል (ይመዘግባል)፤ ወልድ ግን ደቂቀ አዳምን በሕይወት መዝገብ ውስጥ ያትማል (መዝ ፹፯፥፮)፤

አንደኛው ሰዎችን ለራሱ ባለ ዕዳ አድርጎ የሚያስገዛበትን መንገድ ይቀይሳል ሌላኛው ግን ባለዕዳዎቹን ይቤዣቸው ዘንድ ያውጠነጥናል፤ መልእክታቸው ግልጽ የኾኑ የኹለቱ ነገሥታት መጻሕፍት (መዛግብት) ተገናኙ ምክንያቱም ንጉሡ በምድር፤ ወልድም በሰማይ ስሞችን መዝግበዋልና ያ የሕዝብ ቈጠራ የመዠመሪያው ጉዳይ ነበር፤ አንዳች ዐዲስ ነገር የሰው ዘር ላይ የተከሠት ይመስል በተገለጡ ነገሮች ውስጥ ምስጢር የኾኑ ነገሮች ይገለጣሉ፤ በሚታዩ ነገሮች ውስጥም ስዉር ነገሮች ይበሠራሉ፤ አእላፍ ሰዎች ወደ ባርነት ይበልጥ እየቀረቡ ባለበት ጊዜ አርነታቸው ዳግም በልዑሉ አምላክ ታተመ፤ እያንዳንዱ ሰው ስሙን በየራሱ አገር ውስጥ መመዝገብ እንዳለበት ትእዛዝ ተላለፈ (ሉቃ ፪፥፫)

ስለዚኽም ለአዳም ርሱ (ክርስቶስ) ስሙን (የአዳምን ስም) በዔዴን ውስጥ መዘገበለት፤ አገሩ ርሷ ናትና በበረከት ምድር፣ በወገኖች ኹሉ መዲና አምላኩ ስሙን ጻፈለት በቀደምት አገሩ በወገኖቹ መኻከል ርሱ ስሙን ጻፈለት፤ እና ይኽ ምልክት ከሰማይ በተላከ ጊዜ ይኽ በምድር ይፈጸም ዘንድ ቄሳር አዘዘ፤ እያንዳንዱ ሰው ወደ ከተማው እና ወደ የሰፈሩ (መንደሩ) ይመለስ ዘንድ የመመለስ ምሳሌ ሊኾን፤ ምክንያቱም የተሰደደው ርሱ ወደ ዔዴን ይመለስ ዘንድ ነበርና፤ ትእዛዙ በይሁዳ ምድር ላይ የሚገዛ ስለነበር፤ ኹሉም ሕዝብ በቈጠራው ተመዝግበው ነበርና ተቈጣጣሪዎች ወደ ማርያም እጮኛ ወደ ዮሴፍም መጡ፤ ርሱም ይኼድና በዳዊት ከተማ ስሙን ያስመዘግብ ዘንድ ርሱም የድንግልና ውበት ምላት የኾነቺው ርሷን እየመራ መጣ፤ በትእዛዙ መሠረት ስሙን ይጽፍ ዘንድ ወጣ፤ በዚያ ያበራ ዘንድ ንጉሡ ወደ ነገሥታት ከተማ ወጣ በልደቱ የሰውን ዘር በሕይወት መዝገብ ውስጥ ይጽፈውም ዘንድ፤ ብላቴናዪቱ ድንግል በንጹሕ ማሕፀኗ ውስጥ የነገሥታትን ንጉሥ ተሸከመችው ተጉዛም ከዮሴፍ ጋር ወደ ኤፍራታ ወጣች (ሚክ ፭፥፪)

እነርሱም ወደ ንጉሡ ምድር በደረሱ ጊዜ ርሱ የራሱ የኾነውን ዐወቀ እናም ይገባና በራሱ ግዛት ይቀመጥ ዘንድ ራሱን አዘጋጀ፤ ልጇን መውለድ ነበረባትና ብላቴናዪቱን እናት ጊዜ ወሊድ ኾነላት ምክንያቱም የሕፃናት ሠሪ የመወለጃው ጊዜ ደርሶ ነበርና፤ ርሱ የዳዊትን ከተማ ዐወቃት እናም ገብቶ በርሷ ዐደረ የርሱ አባት በንጉሡ ማደሪያ ይከብር ዘንድ፤ ነገር ግን በቤተልሔም ለእናቱ ምንም ስፍራ ስላልነበረ የዐለታት መጠለያ ወደኾነው ዋሻ (በረት) ገብተው በዚያ ተቀመጡ፤ ድኾቹ ባለጠጋውን ርሱን ይዘው ወደተውሶ መኖሪያ ቤት ገቡ ትሑታኑ ከኀያሉ ጋር በባዶ ስፍራ ውስጥ ተቀመጡ፤ ወጣቲቱ በግ የአንበሳ ደቦሉን ለመውለድ ጉልበቷን ዐጠፈች (ዘፍ ፵፱፥፱)፤ ያዕቆብ በበረከቱ ውስጥ ስለ ርሱ የጻፈውን ኀያሉን ለመውለድ (ዘፍ ፵፱፥፰‐፲፪)፤ ወጣቲቱ ርግብ በድንግልናዋ ውስጥ ጋደም አለች ወጣቱን ንስር ታላቁን ንጉሥ በታናሽ ዋሻ ውስጥ ልትወልደው፤ የተወደደችው ጊደር በወጣትነቷ ውስጥ ጋደም አለች (መዝ ፷፰፥፴፩፤ ኢሳ ፯፥፳፩‐፳፪)፤

በኀጢአተኞች ፈንታ መሥዋዕት የኾነውን የሠባውን በሬ (ኮርማ) ልትወልደው፤ የሕፃናት አባት (አስገኝ) ራሱን በአካለ ሥጋ ወለደ ርሱም ከማሕፀን ወጣ የድንግልና ማኅተም ግን ምንም ሳይኾን (ሳይነካ) ቀረ፤ የርሱ ልደት መለኮታዊም ሰብአዊም ነው (ቅድመ ዓለም ከአብ፤ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን) የርሱ ተአምር (ድንቅ) ወሰን የለሽ በመኾኑ ምክንያት የሚመረመር አይደለም፤ ርሱ የባሕርይ አምላክ ነው ማሕፀን በድንግልና ወግ ወልዶታልናል ርሱ ሰው ነው ምክንያቱም ማሕፀን በአካለ ሥጋ ወልዶታልና፤

ርሱ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው (ብቸኛ) ያ ሕፃን ነው፤ እውነተኛው ወልድ፤ ፍጹም እና ድንቅ ከአብ የተወለደ፤ ከመላእክት የተሰወረ፤ ሰዎች የሚሰግዱለት፤ ከመለኮታዊ ባሕርይ እና በሰውነት የተወለደው አንድያ ልጅ አንድ ነው (አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው)፤ የግርማዊ (የአብ) ልጅ የማርያምም ልጅ አንድ አዳኝ፤ ከልዑሉ እና ከዳዊት ሴት ልጅ፤ አንድ የኹሉ ጌታ ከእሳት ሕያዋንና እና ከሥጋውያን፤ አንድ ኀያል፤ በመለኮት ባሕርዩ የተሰወረ፤ በሰውነቱ የተገለጠ፤ እና ርሱን ይመረምር ዘንድ ለማን ይቻለዋል?፤ በመለኮታዊ ባሕርዩ የተሰወረ እና በአካለ ሥጋነቱ የተገለጠ፤ በነገሮች ኹሉ ውስጥ ድንቅ፤ ርሱ እሳትን ለብሷል፤ በመጠቅለያ ጨርቅም ተጠቅልሏል፤ ግን ደግሞ ከመታወቅ በላይ ነው፤ በዙፋን ላይ ተቀምጧል እንዲኹም በግርግም ተኝቷል፤ ግን ደግሞ አይመረመርም

በኪሩቤል ዠርባ ላይ ተቀምጧል እንዲኹም ጉልበቶች ተሸክመውታል፤ እናም በዚያ ምክንያት ርሱ ታላቅ ነው፤ ርሱ የተፈጠሩ ፍጥረታትን ያላውሳቸዋል እንዲኹም ርሱ አካለ ሥጋን ተውሕዷል እናም እነርሱ ድንቁን ይናገራሉ፤ ርሱ ወገኖችን ያኖራቸዋል ርሱ እንዲኹም ወተት ይጠባል፤ ርሱን ይረዳው ያውቀው ዘንድ ማን ይችላል?፤ ርሱ ዝናብን ያዘንባል፤ ርሱ ደግሞ ጡት ይጠባል፤ እናም ድንቁን ተመልከቱ ርሱ ልዑል እና አስፈሪ ነው፤ ርሱም የሚቀኝለት ነው፤ እነሆ ድንቁ፤ ሰማይ ለርሱ እጅግ ያንሰዋል እናም ርሱ መኖሪያን ፈለገ፤ እነሆ እንዴት ያለ ጸጋ ነው! ሱራፌል ራሳቸውን ይሸፍናሉ (ይጋርዳሉ)፤ ዮሴፍ ይሰግዳል አንዳች ድንቅ በዚኽ አለና፤ ሥልጣናት ተዘርግተዋል ሰዎችም ደካሞች ናቸው፤ ያስተውል ዘንድ ግን ማን ይችላል?) በማለት አስተምሯል፡፡

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በማሕፀነ ማርያም ከተከናወነው አንሥቶ በልደት እስከኾነው ታላቅና አስደናቂ ምስጢርን በመጽሐፈ ምስጢር ላይ ሲገልጸው “ወሶበ ይቤላ መልአክ መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ተቀደሰት በርደተ መንፈስ ቅዱስ ለከዊነ እመ አምላክ ...” (መልአክ መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል ባላት ጊዜ የአምላክ እናት ለመኾን በመንፈስ ቅዱስ ተለየች ይኽም ካንቺ የሚወለደው ቅዱስ ነው የልዑል ልጅ ይባላል ሲላት ያን ጊዜ ከርሷ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾነ አስተዋለች (ሉቃ ፩፥፴፭)፤ ኅሊናዋን ወልድ ከአባቱ ጋር ወዳለበት ወደ ጽርሐ አርያም አሳረገች፤ ርሱም ዝቅ ብሎ ከሰማያት ወረደ ራሱንም በማሕፀኗ ውስጥ አሳደረ (ዮሐ ፩፥፲፬)፤

ዳግመኛም ድንግል መልአኩን እንዳልኸኝ ይኹንልኝ አለችው ያን ጊዜ ቃል ከርሷ ሥጋን ተዋሐደ (ሉቃ ፩፥፴፰)፤ አይታ እንዳትደነግጥ ተመልክታም እንዳትፈራ ሰው በኾነ ጊዜ ከርሱ ጋር አራቱን እንስሳውን አላመጣም በሰማይ ሥርዐት የተጠበቁ ሰማያውያኑን በዚያ ተወ (ራእ ፬፥፮-፱)፤ በዚኽም ለቅዱሳን መላእክት የሚረባ ምድራዊት ሥርዐትን ሠራ (ሉቃ ፪፥፲፫)፤ በዚያ በአባቱ ቀኝ አለ በዚኽም በእናቱ ማሕፀን ውስጥ አለ፤ በዚያ ብቻውን የማይታይ ኀይል ነው በዚኽም የማይዳሰስ ኀይል ከሥጋው ጋር የሚዳሰስ ኾነ፤ በዚያ ተሸካሚዎቹ እሳት የተሣለባቸው አራቱ እንስሳ ናቸው (ሕዝ ፩፥፬-፳፮) በዚኽም ተሸካሚዎቹ ለሰውነት መንገድ የተገቡ አራቱ ጠባይዐት ናቸው፤

በዚያ ያለ እናት አባት አለው (መዝ ፪፥፯፤ ዳን ፯፥፲፫-፲፬) በዚኽም ያለምድራዊ አባት እናት አለችው (ሉቃ ፪፥፯)፤ በዚያ ገብርኤል በፍርሀት ይቆማል (ሉቃ ፩፥፲፱) በዚኽም ገብርኤል በሐሤት የምሥራችን ይናገራል (ሉቃ ፩፥፳፮)፤ በዚያ በጽርሐ አርያም የሚደነቅ ከማይታይ አብ የመወለድ ምስጋና አለው በዚኽም በቤተልሔም ከድንግል መወለድ ምስጋና አለው (ሉቃ ፪፥፩-፯)፤ በዚያ ከሰማያውያን ካህናት በወርቅ ማዕጠንት የዕጣኑን መዐዛ ይቀበላል (ራእ ፰፥፫-፬) በዚኽም ወርቅንና ከርቤን ዕጣንንም ከሰብአ ሰገል ተቀበለ (ማቴ ፪፥፲፩)፤ በዚያ ኪሩቤልና ሱራፌል ከግርማው የተነሣ ይንቀጠቀጣሉ በዚኽም ማርያም ዐቀፈችው ሰሎሜም አገለገለችው፤ በዚያ የመብረቅ ብልጭልጭታ በፊቱ ይገለባበጣሉ የእሳትም ወላፈን ከአዳራሹ ይወጣል (ሕዝ ፩፥፲፫) በዚኽም አህያና ላም በትንፋሻቸው አሟሟቁት (ኢሳ ፩፥፫)፤

በዚያ የእሳት ዙፋን አለ በዚኽም የደንጊያ በረት አለ፤ በዚያ የእብነ በረድ የሰማይ ንጣፍ አለ በዚኽም የላሞች መጠጊያ በረት አለ፤ በዚያ የትጉሃን ሥፍራ በሰማያት ያለች ኢየሩሳሌም አለችው በዚኽም የእንስሳት ጠባቂዎች ማደሪያ በኣት አለው (ሉቃ ፪፥፯)፤ በዚያ ርዝማኔ የማይታወቅ የዳንኤል ብሉየ መዋዕል አባት አለው (ዳን ፯፥፲፫-፲፬) በዚኽም የዓመቶቹ ቊጥር በሰው ልጅ ዐቅም መጠን የኾነ ሽማግሌ ዮሴፍ ተሸከመው …

የአምላክን ልጅ ሰው መኾኑን በዓል እናድርግ የተሸከመችውን ማሕፀን እናመስግን፤ ላቀፉት ጉልበቶች እንስገድ፤ ላሳደጉት ጡቶች እንዘምር፤ የዳሰሱትን እጆች እናመስግን፤ ለሳሙት ከንፈሮች እናሸብሽብ፤ ከእረኞች ጋር ምስጋናን እናቅርብ፤ ከሰብአ ሰገልም ጋር እጅ እንንሣ፤ እንደ ዮሴፍ እናድንቅ እንደ ሰሎሜም እናገልግል በተኛበት በረት እንስገድ፤ በተጠቀለለበት በረት እንበርከክ፤ ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና ይኹን በምድርም ሰውን ለወደደ እንበል (ሉቃ ፪፥፲፬)፤ እግዚአብሔር ሰው ኾነ የሰው ልጅ ሴት ልጅም የእግዚአብሔር እናት ኾነች፤ ለርሱ ምስጋና ይኹን ለርሷም ስግደት ይገባል ለዘላለሙ አሜን ይኹን) በማለት በጥልቀት ገልጾታል፡፡

ይኸው የቤተ ክርስቲያን ሊቅ በድጋሚ በሰኞ አርጋኖን መጽሐፉ ላይ “ሥርዐተ ሰማይ ከማሁ ተሠርዐ በዲበ ምድር፤ ቤተልሔም ተመሰለት ከመ ሰማይ ህየንተ ፀሓይ ዘየዐርብ ሠረቀ በውስቴታ ፀሓየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኢየዐርብ ወዘዘልፈ ያበርህ ዲበ ቅዱሳን …” (የሰማይ ሥርዐት በምድር ላይ ተሠራ፤ ቤተልሔምም እንደ ሰማይ ተመሰለች፤ በሚጠልቅ ፀሓይም ፈንታ በቅዱሳን ላይ ዘወትር የሚያበራ ኅልፈት ጥልቀት የሌለበት አማናዊ ፀሓይ ኢየሱስ ክርስቶስ በውስጧ ወጣ (ሚልክ ፬፥፪)፤ ከብርሃኑ ጒድለት መምላትን የማያፈራርቅ በጨረቃ ፈንታ የድንግልናዋ ምስጋና ዘወትር የማይጐድል በኹሉ የመላ በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባለች የተመረጠች ድንግል ማርያም ተገለጠች (መሓ ፮፥፲)፤ በክዋክብት ፈንታም የብርሃን መላእክት ታዩ (ሉቃ ፪፥፲፫)፤ በዚኽ ማኅበር እኖር ዘንድ ከጥበብ ሰዎች ጋራ እጅ እነሣ ዘንድ (ማቴ ፪፥፲፩)፤ ከእረኖችም ጋራ አገለግል ዘንድ (ሉቃ ፪፥፲፮-፲፰)፤ ከሰሎሜም (ከአዋላጂቱ) ጋራ አደንቅ ዘንድ ከመላእክትም ጋራ አመሰግን ዘንድ፤ በዚኽ ማኅበር አንድነት እንድኖር ማን በአደለኝ?፤ የተጨነቁትን የሚያድን የተስፋ ቈረጦች ተስፋ፤ የተዳደፉትን የሚያነጻ የሙታን ሕይወት የተኛበትን በረት እጅ እነሣ ዘንድ ማን ባደለኝ? ይቅርታን የምታሰጥ ብላቴና የረድኤት ክንፎቿ ጥላ ይነካኝ ዘንድ ማን ባደለኝ? ምሕረትን የምታሰጥ ብላቴና ጫማዋን እሸከም ዘንድ ማን ባደለኝ?፤ ብርሃንን ላስገኘች ብላቴና በኼደችበት እከተላት ዘንድ ማን ባደለኝ?) በማለት የእናትና የልጅን ነገር በጥልቀት ሃይማኖታዊ አገላለጽ ገልጾታል፡፡

የመናፍቃን መዶሻ የተባለው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያም የአምላክ እናትነቷን በእናትና በልጅ መኻከል ያለውን መለያየት የማይችል ፍጹም ፍቅርን ሲገልጸው

“O my beloved, ye God-fearing people, open ye the ears of your hearts,…” (የምወድዳችኊ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሕዝቦች ሆይ የልቡናችኹን ዦሮዎች ከፍታችኊ የሴቶችን ኹሉ ንግሥት፣ በርሷም ውስጥ የአብ ልጅ በታላቅ ክብር የኖረ የእውነተኛዋን ሙሽራ የእግዚአብሔርን እናት ክብሯን ስሙ፤ መጥቶ በማሕፀኗ ለዘጠኝ ወራት ኖረ ስለእኛ መዳን በቤተ ልሔም ውስጥ ወለደችው በመናኛ የመታቀፊያ ኩታ ጨርቅ ጠቀለለችው፤ በከብቶች ማደሪያ በረት ውስጥ አኖረችው፤ እንስሳትም ርሱን ተመልክተው ዐውቀውት ተገዙለት (እስትንፋሳቸውን ገበሩለት) (ሉቃ ፪፥፮-፯)፤ ቅድስት ድንግል ማርያምም የቀኝ ክንዶቿን ዘርግታ በእጆቿ አንሥታ በግራ ክንዶቿ ውስጥም እንዲያርፍ አደረገችው፤ አንገቶቿን ሳታዞር በመቅረቷም ጸጉሮቿ በላዩ ላይ እንዲያርፉ ኾኑ፤ ልክ የባሕርይ አባቱ እንዳደረገው ርሷም አፉን ስማ በጉልበቶቿ ላይ አሳረፈቻቸው፤ ዐይኖቹን ወደ ፊቷ አዞራቸው እጆቹንም ዘርግቶ ጡቶቿን በመሳብ ከመና ይልቅ በጣም ጣፋጭ የነበረውን ወተቷን ባፉ ውስጥ ጨመራቸው፤ ጣእሙም ከኖኅ የመሥዋዕት ሽታ ጣዕም የበለጠ ለርሱ ጣፋጭ ነበረ (ዘፍ ፰፥፳-፳፩) ከንጹሓት ጡቶች ወተትን እየጠባ “የእኔ እናት” ብሎ ይጠራል…እግዚአብሔር ማርያምን “እናቴ” እያለ በመጣራት አፎቿን ሲስማት ኑና ተመልከቱ፤ ርሷም ኹልጊዜ አፉን እየሳመች “ጌታዬና ልጄ” እያለች ትጠራዋለች፤ ታመልከዋለች፤ ጡቶቿንም ስትመግበው ራሷን ለክብሩ ወደርሱ ታስጎነብሳለች፤ ርሱም እንደ ዐምድ ሲቆም “ጌታዬ እና ልጄ” በማለት ታመልከዋለች፤ እናም ከእነዚኽ ነገሮች በኋላ እጆቹን በመያዝ በመንገድ ላይ ይዛው ስትጓዝ “የኔ ጣፋጭ ልጅ ትንሽ ተራመድ” እያለች ልክ ሌሎች ልጆች ኹሉ መኼድ እንደሚማሩት ኹሉ በእግሩ እንዲኼድ ታስተምረዋለች፤ የባሕርይ አምላክ ክርስቶስም ያለምንም ችግር ተከትሏት ይጓዛል፤ በትናናሽ ጣቶቹም ይይዛት ነበር፤ በየመኻሉም በመቆም በርሱ ፍጥረታት ኹሉ እንደተያዙ እንደተንጠለጠሉ ርሱም በእናቱ ሸማዎች ላይ ይንጠላጠላል ፍጥረት በመላ በርሱ የተያዙ የሚኖሩት ርሱ ወደ ፊቷ ይመለከታል፤ ወደ ሰውነቶቿ አስጠግታ አጥብቃ ዐቅፋው በክንዶቿ ወደ ላይ አንሥታ ትሸከመዋለች፤ እናንተ ሴቶች ሆይ በመላ ኑና ከርሷ መወለድ የመረጠው እግዚአብሔር ፊቶቹን አንሥቶ ሲስማት ተመልከቱ፡፡ አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ ተራመጂ ተራመጂ፤ ማርያም ተመልከቺ ንጉሥ ክርስቶስ ባንቺ ላይ ዐርፏል፣ ንጉሥ ክርስቶስ ካንቺ ጋር ነው በክንዶችሽም ውስጥ ተቀምጧል፤ አብ ራሱ ይኽነን ሥራ ሠርቷል (ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ልጁን በመላክ)፤ ወልድ ራሱ የአንቺን ሥጋ ነሥቷል፤ መንፈስ ቅዱስም ከአንቺ አይለይም፤ መላእክት ይሰግዱልሻል ከንጽሕናሽ የተነሣ ርሱ ወዶሽ ከአንቺ ተወልዷልና፤ ከሴቶች ኹሉ አንቺን መርጦ ጌታችን ከአንቺ ጋር ኖሯልና) በማለት ትክክለኛውን የቤተ ክርስቲያን የእውነት ትምህርትን አጒልቶ አስተምሯል፡፡

በድንግልና የኾነው ልደት ፅንሱና በግብረ መንፈስ ቅዱስ የኾነ የእግዚአብሔር ልጅ ሲፀነስ የእናቱን ማኅተመ ድንግልና ሳይጥስ እንደኾነ ኹሉ ሲወለድም አለወጠውም፤ ክብር ይግባውና ልዑል እግዚአብሔር በኢሳይያስ 7፡14 እና በሕዝቅኤል በምዕ ፵፬፥፩-፪ ላይ የእናቱን የዘላለማዊ ድንግልናዋን ነገር በትንቢት አናግሮላታል፡፡

ከዚኹ ጋራ የዘላለማዊ ድንግልናዋ ምሳሌ የሚኾኑ በርካታ ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሲኖሩ በተጨማሪም የኅቱም ድንግልናዋ ምሳሌ የሚኾኑ የሊቃውንት ምሳሌዎች አሉ፤ ይኸውም የእያንዳንዱ ሰው መልክ በሰው የዐይን ብሌን ውስጥ ገብቶ ይታያል፤ ኹለተኛም ፀሓይ የመስኮት መስታዮትን ሳትሠነጥቅ ወደ ቤት ውስጥ ገብታ ትታያለች፤ ሦስተኛም የእያንዳንዱ ሰው አምሳለ መልክእ መስታዮትን ሳይሰብር (ሳይሰነጥቅ) በውስጡ ይታያል፤ ዐራተኛም ግንባራችንን ሳይሰነጥቀው ወዛችን (ላባችን) ይወጣል፤ እነዚኽ ግዙፋን እንኳን የርቀት ሥራ ሲሠሩ ረቂቅ ዘእምረቂቅ የኾነው የባሕርይ አምላክ አካላዊ ቃል ክርስቶስም የእናቱን የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅተመ ድንግልናዋን ሳይጥስ እንደተፀነሰ ኹሉ ዳግመኛም ማኅተመ ድንግልናዋን ሳይለውጥ በኅቱም ድንግልና በቤተ ልሔም ተወልዷል፤ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳኢ ይኽነን ሲያስረዳ “ተወልደ እምድንግልና እንዘ ኅቱም ድንግልናሃ ከመ ልደተ ንጻሬ ዐይን ወከመ ልደተ ሐፍ እምገጽ፤ ወከመ ልደተ መልክእ እመጽሔት” (ከዐይን ንጻሬ፣ ከግንባር ወዝ ሳይሰነጥቀው፣ ከመስታዮት አምሳለ መልክእ ሳይሰብረው እንዲወለድ ጌታም ማኅተመ ድንግልናዋን ሳይፈታ በኅቱም ድንግልና ተወለደ) በማለት ምሳሌውን እንደ ወርቅ አንከብሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ አስቀምጦታል፡፡

አምላካችን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ፀንሳው በኅቱም ድንግልና እንድትወልደው ትንቢት ሲያናግርላት ምሳሌም ሲያስመስልላት ምስጢሩ ግን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንደገለጸው ነው፤ ይኸውም ሊቁ በሃይማኖተ አበው ላይ “ወሶበሂ ወለደቶ ዐቀበ ድንግልናሃ ዘእንበለ ርኲስ ከመ በፅንሳ መንክር ትኩን መራሂተ ለሃይማኖት ዐባይ ...” (በወለደችውም ጊዜ ድንግልናዋን ያለመለወጥ አጸና፤ ድንቅ በሚኾን ፅንሷ ለደገኛው ሃይማኖት መሪ ትኾን ዘንድ፤ ጣዖት የሚያመልክ ወይም አይሁዳዊ በውኑ ክርስቶስ እንደ ሰው ኹሉ ያለ ሰው ነውን? ወይስ ከሰው ኹሉ ርሱ ይበልጣል? ብሎ ቢጠይቀኝ አዎን ከሰው ኹሉ ርሱ ይበልጣል ብዬ እመልስለታለኊ፤ ለቃል ምስክር ከምትኾን ከድንግል በኅቱም ድንግልና መወለዱን ምስክር አድርጌ እናገራለኊ) በማለት እንዳስተማረው ርሷ ስትወልደው ማኅተመ ድንግልናዋ አለመለወጡ ሰው ኹኖ ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ፤ ርሷ “ድንግል ወእም” (ድንግልም እናትም) እንደምትባል፤ ርሱም “አምላክ ወሰብእ” (አምላክም ሰውም) ሲባል የመኖሩ የሃይማኖት ምስክር ናትና በእውነት ርሱ የባሕርይ አምላክ እናቱም ወላዲተ አምላክ እንደ ኾነች ለማጠየቅ በኅቱም ድንግልናዋ ፀንሳ በኅቱም ድንግልናዋ ወልዳዋለች፡፡

በዚኽም ወልድ ዋሕድ አካላዊ ቃል ክርስቶስ ኹለት ልደታት ብቻ አሉት 1) ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት አካል ዘእም አካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ (ማቴ 3፡17፤ ማቴ 17፡5-7) 2) 5,500 ዘመን ሲፈጸም ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለአባት (ማቴ 1፡19-23፤ ሉቃ 1፡27-38፤ 2፡7)

በተጨማሪም ጌታችን ልደቱን በዘር በሩካቤ ያላደረገው ያለ ዘር ያለ ሩካቤ ያደረገው ለኹለት ምክንያቶች ሲኾን
፩ኛ/ በኹለተኛው ልደት ቀዳማዊዉን ልደት ለመግለጽ ነው ይኸውም ፭ሺሕ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ ዘር ያለ አባት መወለዱ፤ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት መወለዱን ያስረዳልና፤ “ልደት ቀዳማዊ ተዐውቀ በደኀራዊ ልደት” እንዲል
፪ኛ/ በተጨማሪም ጌታ ልደቱን በዘር በሩካቤ አድርጎት ቢኾን ኖሮ መናፍቃን ዕሩቅ ብእሲ ነው አንጂ የባሕርይ አምላክ አይደለም ባሉ ነበርና በእውነት የባሕርይ አምላክ እንደ ኾነ ለማጠየቅ ጌታችን ልደቱን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ያለ ዘር ያለ ሩካቤ አድርጎታል፤ ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ይኽነን ሲገልጽ “ሶበሰ ወፅአ እምትድምርተ ሰብሳብ ዘከማየ ብዙኀን እምተሐዘብዎ ወእምሐሰውዎ” (እንደ እኔስ በዘር በሩካቤ ተወልዶ ቢኾን ብዙ ሰዎች ዕሩቅ ብእሲ ባሉት ነበር፤ አምላክነቱንም በካዱ ነበር) ብሏል፡፡

ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና የተወለደው ዐማኑኤል የመላእክት ፈጣሪ ነውና መላእክት አመስግነውታል፤ እውነተኛ እረኛ ነውና እረኞች ከመላእክት ጋር በኅብረት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ” (በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን በምድርም ሰላም ኾነ ለሰው በጎ ፈቃድ) (ሉቃ 2፡14) በማለት ዘምረዋል፡፡

የእንስሳት ፈጣሪ ነውና ላምና አህያ እስትንፋሳቸውን ገብረውለታል (ኢሳ 1፡3)፤ የነገሥታት ንጉሥ ነውና ሦስቱ ነገሥታት ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ ገብረውለታል፡፡ በልደቱ ሕይወትን ለሰጠን ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ለተወለደው ለአምላካችን ለለዐማኑኤል ክብር ምስጋና ይኹን አሜን
.
 በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ</div>

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages