ቅዳሜ - ቅዱሳት_አንስት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, April 23, 2023

ቅዳሜ - ቅዱሳት_አንስት



ቅዱሳት_አንስት_ይባላል፡- በዚህ ዕለት ቅዱሳት አንስት የክርስቶስን አካል ሽቶ ለመቀባት ጨለማ አቋርጠው ወደ መቃብር መምጣታቸውና ትንሣኤውንም ቀድመው ማየታቸው ይሰበካል።
ነገር፡ግን፥ከሳምንቱ፡በመዠመሪያው፡ቀን፡ያዘጋጁትን፡ሽቱ፡ይዘው፡ከነርሱም፡ጋራ፡አንዳንዶቹ፡ወደ፡
መቃብሩ፡እጅግ፡ማልደው፡መጡ።
ድንጋዩንም፡ከመቃብሩ፡ተንከባሎ፡አገኙት፥
ገብተውም፡የጌታን፡የኢየሱስን፡ሥጋ፡አላገኙም።
እነርሱም፡በዚህ፡ሲያመነቱ፥እንሆ፥ኹለት፡ሰዎች፡የሚያንጸባርቅ፡ልብስ፡ለብሰው፡ወደ፡እነርሱ፡ቀረቡ፤
ፈርተውም፡ፊታቸውን፡ወደ፡ምድር፡አቀርቅረው፡ሳሉ፥እንዲህ፡አሏቸው፦ሕያውን፡ከሙታን፡መካከል፡
ስለ፡ምን፡ትፈልጋላችኹ፧ተነሥቷል፡እንጂ፡በዚህ፡የለም።
የሰው፡ልጅ፡በኀጢአተኛዎች፡እጅ፡ዐልፎ፡ሊሰጥና፡ሊሰቀል፡በሦስተኛውም፡ቀን፡ሊነሣ፡ግድ፡ነው፡
እያለ፡ገና፡በገሊላ፡ሳለ፡ለእናንተ፡እንደ፡ተናገረ፡ዐስቡ።
ቃሎቹንም፡ዐሰቡ፥ከመቃብሩም፡ተመልሰው፡ይህን፡ዅሉ፡ለዐሥራ፡አንዱና፡ለሌላዎች፡ዅሉ፡
ነገሯቸው።
ይህንም፡ለሐዋርያት፡የነገሯቸው፡መግደላዊት፡ማርያምና፡ዮሐና፡የያዕቆብም፡እናት፡ማርያም፡ከነርሱም፡
ጋራ፡የነበሩት፡ሌላዎች፡ሴቶች፡ነበሩ።
ሉቃስ 24*1-10

ቅዱሳት አንስት ማለት ቅዱሳን ሴቶች ማለት ሲሆን በዚህም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ቀድመው የተመለከቱትን ቅዱሳን ሴቶችን የምናስብበት ዕለት ነው።
በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሰንበት (ቅዳሜ) ሕዝቡ ከአንዳንዱ በስተቀር ገበያ ስለማይገበያይባት ‹የቁራ ገበያ ፣ የገበያ ጥፊያ› ስትባል ፣ በቤተ ክርስቲያን ግን በዘመነ ሥጋዌው ክርስቶስን
=በገንዘባቸውና ጉልበታቸው ላገለገሉት፤
=በስቅለቱ ዋይ ዋይ እያሉ እስከ ቀራንዮ ድረስ ለተከተሉት ፤
=በትንሣኤው ዕለት በሌሊት ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው ለገሰገሱት፤
=በትንሣኤውም ጌታችን ከዅሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አንስት መታሰቢያ ኾና ‹ቅዱሳት አንስት› ተብላ ትጠራለች ማቴ. ፳፭25 ፥ ፩1 - ፲፩11 ፤ ሉቃ. ፳፫23 ፥ ፳፯27 - ፴፫33 ፤ ፳፬24 ፥ ፩1 - ፲10 ፡፡
በዕለተ ትንሣኤ ሌሊቱን ሲመላለሱ ያደሩ ሴቶች የድካማቸውና ጌታን የመሻታቸው ዋጋ መታሰቢያቸው ነው ። ይህች እለት አንስት አንከራ ተብላም ትጠራለች ፡፡ ''አንስት አንከራ'' ማለት ''የቅዱሳን ሴቶች አድናቆት'' እንደማለት ነው። ይህም መባሉ ሌሊት ሲመላለሱ ሁለት መላእክት አይተው ከብሩህነታቸው የተነሳ የተደነቁበትና በመቃብሩ ያለውን መዓዛ ትንሣኤ አሽትተው የተመሰጡበት ዕለት ስለሆነ እንዲሁም ድካማቸው ከንቱ እንዳልሆነ ለማጠየቅ ነው ።
አንድም ጌታችን አስቀድሞ ለእነርሱ ታይቶ ትንሣኤውን ያረጋገጠበት ስለሆነ እነርሱ ከአምላክነቱ ግርማ የተነሳ ረቡኒ ብለው ያደነቁበት ዕለት መታሰቢያ ነው።
አንድም በጠቅላላው ከሕማማቱ እስከ ትንሣኤው ብዙ የእንባ መሥዋዕት ያቀረቡ እናቶች የሚታሰቡበት ስለሆነ አንስት አንከራ ይባላል ።
በዚህ ዕለት:-
=የክርስቶስን አካል ሽቱ ለመቀባት ፍርሃታቸውን በክርስቶስ ፍቅር ለውጠው በጋለ ፍቅር አካሉን መፈለጋቸውን፥ =ወደ መቃብሩ ሲመላለሱ ማደራቸውን፥ =ማርያምም ትንሣኤውን ቀድማ ስለማየቷ፥
=ሴቶችም የመላእክትን ራእይ ስለ ማየታቸው፥ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች ። ማቴ. ፳፰28 ፥ ፩1 - ፲፭15 ፣ ማር. ፲፮16 ፥ ፩1 - ፰8 ፣ ሉቃ. ፳፬24 ፥ ፩1 - ፲፪12 ፣ ዮሐ. ፳20 ፥ ፩1 - ፲፰18 ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳት አንስት ጸሎት ይማረን!!!

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምሕሮ ቅዱሳት አንስት ብዛታቸው 36 ሲሆኑ ጌታን ተከትለው ግማሻቸው በጉልበት ፣ግማሻቸው ደግሞ በሚችሉት አቅም ከጌታችን ጋር ባደረበት እያደሩ በዋለበት እየዋሉ አገልግሎትን ፈጽመዋል ።በኋላም በጽርሐ ጽዮን ከሐዋርያት ጋር መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ለወንጌል መስፋፋት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ።
የ36ቱ ቅዱሳት አንስት ስም ዝርዝርና የመታሰቢያ ቀናቸው።
✔️
1. ኤልሳቤጥ፦የካቲት 16
2. ሐና ፦ መስከረም 7 ቀን
3. ቤርዜዳን ወይም ቤርስት፦ታህሳስ 10 ቀን
4. መልቲዳን ወይም ማርና፦ጥር 4 ቀን
5. ሰሎሜ፦ግንቦት 25 ቀን
6. ማርያም መግደላዊት፦ነሐሴ 6 ቀን
7. ማርያም እንተ እፍረት እህተ አልአዛር፦የካቲት 6 ቀን
8. ሐና ነቢይት፦የካቲት 20 እና ጥቅምት 6 ቀን
9. ማርያም እሞሙ ለደቂቀ ዘብዴዎስ፦ጥር 18 ቀን
10. ሶፍያ (በርበራ)፦ጥር 30 ቀን
11. ዮልያና (ዮና)፦ኅዳር 18 ቀን
12. ሶፍያ (መርኬዛ)፦ጥር 30 ቀን
13. አውጋንያን (ጵላግያ)፦ጥቅምት 11 ቀን
14. አርሴማ፦ግንቦት 11 ቀን
15. ዮስቲና፦ጥር 30 ቀን
16. ጤግላ፦ ነሐሴ 6 ቀን
17. አርኒ (ሶፍያ)፦ኅዳር 10 ቀን
18. እሌኒ፦ ጥር 29 ቀን
19. ኢዮጰራቅሊያ፦መጋቢት 26 እና ነሐሴ 2 ቀን
20. ቴዎክላ (ቴኦድራ)፦ጥር 4 ቀን
21. ክርስቲያና (አጥሩኒስ)፦ኅዳር 18
22. ጥቅሞላ (አሞና)፦ ጥር 30 ቀን
23. ጲስ፦ ጥር 30 ቀን
24. አላጲስ፦ጥር 30 ቀን
25. አጋጲስ፦ጥር 30 ቀን
26. እርሶንያ (አርኒ)፦ ጥር 30 ቀን
27. ጲላግያ፦ጥር 30 እና ጥቅምት 11 ቀን
28. አንጦልያ (ሉክያ)፦የካቲት 25 ቀን
29. አሞን (ሶፍያ)፦ጥር 15 አና ነሐሴ 3 ቀን
30. ኢየሉጣ፦ነሐሴ 6 ቀን
31. መሪና፦ሐምሌ 27 ቀን
32. ማርታ እህተ አልአዛር፦ጥር 18 እና ግንቦት 27 ቀን
33. ማርያም የማርቆስ እናት፦ጥር 30 ቀን
34. ሣራ (ሶፍያ) የይሁዳ እናት፦ጥር 30 ቀን
35. ዮሐና (ዮላና) የኩዛ ሚስት፦ታህሳስ 26 ቀን
36. ሶስና፦ ግንቦት 12 ቀን
የሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በረከታቸው ይደርብን

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages