ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ ያለው አርብ - ቅድስት ቤተ ክርስቲያን - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, April 21, 2023

ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ ያለው አርብ - ቅድስት ቤተ ክርስቲያን"ከዚህ በኃላ የሞትን ስልጣን አጠፋ ዲያቢሎስንና ኃይሉን ሻረ የብረት መዝጊያዎችን ሰበረ ሲዖልን በዘበዘ የጣዖት ቤቶችን አፈረሰ የምህረትን በር ከፈተ ይህችውም በደሙ የከበረች ቤተ ክርስቲያን ናት " ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎድስዮስ

በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ስለመመስረቷ ይሰበካል፡፡ ክርስቶስ ስለ እርሷ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ቤዛ ሆኖ በደሙ አንጽቶ በትንሣኤው ድል ሰጥቶ እንዳከበራት ይነገራል
ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ላይ
" ዕፀ መስቀል በአይሁድ እጅ ተተከለ፤ ቤተ ክርስቲያንም በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ተሠራች የእግዚአብሔር በግ በሰቃዮች እጅ በዕፀ መስቀል ላይ ተሠዋ፤ የበረከት ማዕድ ለምእመናን ተዘጋጀ፤ መድኃኒታችን ተወጋ፣ የቤተ ክርስቲያን ደጃፎቿ በሙሽራዋ ደም ተቀቡ" እንዳሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ እንደመሠረታት ለማሰብ ይሄን የስሙነ ትንሣኤ አምስተኛ ቀን ዕለተ አርብን ቤተ ክርስቲያን ብለው አባቶቻችን ሰይመዋታል
አርብ ለክርስቶስ የመከራ የስቅለት ቀን እንደነበረች ቤተ ክርስቲያንም ሙሽራዋ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ በመከራ ውስጥ እንደምትቆይ ለማሳየት ይሄን ዕለት ቤተ ክርስቲያን ተብሏል
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዝማሬው "የምናገረውን አውቅ ዘንድ እግዚአብሔር የጥበብ አንደበትን ይስጠኝ፤ አቤቱ ቃሌን አድምጥ፤ አቤቱ የቤተ ክርስቲያንን ሕጓን ሥርዓቷን አውቅ ዘንድ ግለጥልኝ፤ ወደ እርሷ ፈጽሞ የሚገሠግሥ ሁሉ አይደክምም፤ እርሷ እንግዳ ተቀባይ ናትና " እንዳለ ቢጠብቁት ሕይወትን የሚሰጥ ሕግ እና ሥርዓቷን አውቀን እንኖር ዘንድ ከደካማችን እና ኃጢአታችን በቃለ እግዚአብሔር እና በንስሐ ወደ ምታድሰን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንገስግስ ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages