ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ ያለው ሐሙስ - አዳም ( አዳም ሐሙስ) - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, April 20, 2023

ከጌታችን ትንሣኤ በኋላ ያለው ሐሙስ - አዳም ( አዳም ሐሙስ)አዳም የመጀመሪያ ሰውና የሰው ሁሉ አባት ነው፤ በ፮ኛው ቀን የተፈጠረ የሰው ሁሉ ምንጭ ስለሆነ የሰው ዘር ሁሉ ከእርሱ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ዕለት ለአዳም የተሰጠው የተስፋ ቃል ስለመፈጸሙ፤ (ዘፍ. ፫÷፲፭) አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለመውጣቱ ይታሰብበታል፡፡ ክርስቶስ በተነሳበት በአምስተኛው ቀን ሐሙስ አዳም ይባላል፤ ጌታችን አዳምን ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ቃል ገብቶለት እንደነበር በቀሌምንጦስ ተጽፏል፡፡
አዳምና ሔዋን በገነት ፯ ዓመት ከቆዩ በኋላ ትእዛዙን በመተላለፋቸው ከኤደን ገነት አስወጣቸው (ኩፋ.፬፥፲፮፤ዘፍ.፫፥፳፫) «ብዙ ተባዙ» ያለው ቃል እንዳይቀር በምድር ላይ ወርደው ልጆችን ወለዱ ይላል፡፡ የተወለዱትም ልጆችም በቁጥር ፷ እንደሆኑ (፩መቃ. ፳፰፥፮) የተወለዱት ልጆች ደጎችና ክፉዎች እንደ ነበሩ በአቤልና በቃየል ታውቋል፤ (ዘፍ. ፬፥፰)፤ አዳም በዚህ ዓለም ፱፻፴ ዓመት ኑሮ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፵፻፭፻፸ ሚያዚያ ፮ ዐርፏል፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን ከትንሣኤ በኋላ ያለው ሐሙስ “አዳም ሐሙስ” ይባላል፡፡ በዚህ ዕለት ክብር ይግባውና በገነት ዛፎች መካከል “አዳም አዳም” እያለ ይመላለስ የነበረው “የእግዚአብሔር ቃል” ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለው" በማለት የገባውን ቃል ኪዳን መፈጸሙንና አዳምና ልጆቹም በጌታችን ትንሣኤ ነጻ መውጣታቸውን እናስባለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ ህግንና ነቢያትን ለመሻር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ” እንዳለ (ማቴ 5፡17) “እንደ እግዚአብሔርም መልካምና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ” ስለማይፈልግ ነው የሚለውን የዲያቢሎስን የማታለያ ቃል ሰምተው አምላክነትን ሽተው የሳቱትን አዳምንና ልጆቹን (ዘፍ 3፡5) ሊያድን ቃል በገባላቸው ቃል መሠረት ከእነርሱ ንጹህ ዘር ሆና ከቀረች (ኢሳ 1፡9) ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ፍጹም ሰው ሆኖ አድኖታል፡፡ በሞት ባርነት ተይዞ ለነበረ የሰው ልጅም ሰው ሆኖ በሞቱ ሞትን ድል በመንሣት በትንሣኤው ይህንን የሰውን ትንሣኤ በማረጋገጥ የገባለትን ኪዳን ፈጽሟል፡፡

ውድ ክርስቲያኖች!!! የክርስቶስ ትንሣኤ ለአዳም የተገባለት ቃል ኪዳን የተፈጸመበት ብቻ ሳይሆን የነቢያት ትንቢትና የሐዋርያት ትምህርት እንዲሁም የእምነታችንም አማናዊነት የተረጋገጠበት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ክርስቶስ ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት” ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ (1ቆሮ 15፥13) በትንሣኤው ወደ ሕይወት የመራን አምላካችን ስሙ ይመስገን!!!

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages