ቅዱስ ሳዊሮስ በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ አንጾኪያ የተነሳ አባት ነው:: ወቅቱ መለካውያን (2 ባሕርይ ባዮች) የሰለጠኑበት እንደ መሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ያነሱበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ነበር:: በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስ በሥላሴ ፈቃድ ለቤተ ክርስቲያን የተነሳው:: ሊቃውንት "አንበሳ" ሲሉ ይጠሩታል::
ቅዱሱ ለተዋሕዶ ሃይማኖት ብዙ ሆኖላታል:: የመናፍቃን ጸር በመሆኑ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል:: ንጉሡን ዮስጢያኖስን (Justinian) ሳይቀር በይፋ ይገስጸው ነበርና ንጉሡ ሊገድለው ቆረጠ::
ሃይማኖቷ የቀና ንግሥቲቱ ታኦድራ ግን ይህንን ስትሰማ በሌሊት ወደ ሊቁ ሒዳ "እባክህን ሽሽ" አለችው:: እርሱ ግን "ሞት ለእኔ ክብር ነውና አልሔድም" ሲል መለሰላት:: አባቶችን ሰብስባ "ስለ ቤተ ክርስቲያን ስትል" ብለው ለምነው ወደ ግብጽ ሸኙት::
እርሱ እየሔደ ገዳዮቹ ያሳድዱት ገቡ:: መንገድ ላይ ቢደርሱበትም ተሰወረባቸው:: ለብዙ ቀናትም አብሯቸው ተጓዘ:: እነርሱ ተስፋ ቆርጠው ሲመለሱ እርሱ ግን ምድረ ግብጽ ደረሰ::
በምድረ ግብጽም የዽዽስና ልብሱን ትቶ የመነኮሳትን አሮጌ ልብስ ለብሶ ሕዝቡንና መነኮሳቱን አስተማረ: አጸና:: በየቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠራ::
አባቶች መነኮሳትም ማንነቱን ባወቁ ጊዜ ሰገዱለት:: ዶርታኦስ (ዱራታኦስ) በሚባል አንድ ደግ ሰው ቤትም በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ የካቲት 14 ቀን ዐርፏል:: ይህቺ ቀን ዕለተ ስደቱ ናት::
አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት የድንግል እመቤታችንን ጣዕሟን ፍቅሯን ያሳድርብን:: የአበውን ሃብትና በረከትም አይንሳን::
No comments:
Post a Comment