እግዚአብሔር በወዴት ይገኛል ቢሉ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, May 24, 2020

እግዚአብሔር በወዴት ይገኛል ቢሉ

እግዚአብሔር በወዴት ይገኛል ቢሉ


† በደዌ ደኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘዉ በሚማቅቁ፣አስታማሚና ጠያቂ አጥተዉ ዕለተ ሞታቸዉን በሚናፍቁ ምስኪን ህሙማን መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡
† የፍርቱና ጉዳይ ሆኖባቸዉ በባዶዉ አስፋልት ላይ ካርቶን አንጥፈዉ በሚተኙ ዝናቡ፣ ቁሩ፣ ዋዕዩ በሚፈራረቅባቸዉ፣ቆሻሻ ገንዳ ላይ ተንጠላጥለዉ የበሰበሰ ፍራፍሬን ቀለባቸዉ ባደረጉ፣ችጋር ጠንቶባቸዉ መማሪያ ክፍል ዉስጥ እንዳሉ በረሀብ በሚያሸልቡ የድሀ ድሀ ልጆች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡
† በግፈኞች ፍትህ ተንጋዶባቸዉ ባልዋሉበት እንደዋሉ፣ባልሰሩት እንደሰሩ ተደርገዉ በጨለማ እስር ቤት በተወረወሩ፣ብረት በተቆለፈባቸዉ የህሊና ታሳሪዎችና የህዝብ ጠበቆች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡
† በእኩይ ባሎቻቸዉ አካላዊም ሆነ ስነ ልቦናዊም ጥቃት በደረሰባቸዉ፣እጅግ የከበደዉን መከራ መቋቋም ተስኗቸዉ ቀኑ በጨለመባቸዉ እንዲሁም ቢጮሁ ቢጮሁ ሰሚ አጥተዉ ሌት ተቀን በሰቆቃ በሚባዝኑ አንስቶች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡
† ለዚህች ሀገር የሚችሉትን ሁሉ አበርክተዉ አቅማቸዉ ሲደክም ጉልበታቸዉ ሲከዳ ጧሪ ቀባሪ ጧሪ ቀባሪ በማጣት ቤታቸዉ በፈረሰባቸዉ እንዲሁም ለልመና እጅ በሰጡ አዛዉንት አባቶችና አሮጊት እናቶች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡ 
ታዲያ እነዚህን አካላት ሲራቡ በማብላት፣ሲጠሙ በማጠጣት፣ ሲታሰሩ በመጠየቅ፣ሲታረዙ በማልበስ፣ሲያዝኑ በማጽናናት ሲታመሙ በመንከባከብ በመርዳት ከጎናቸዉ ሆነን ችግራቸዉን ከተካፈልን ከእግዚአብሔር ጋር እንገናኛለን ምክንያቱም የእርሱ ቦታዉ እዚህ ነዉና ሁሌም በፍቅሩ ይጎበኘናል እኛ አናየዉ ይሆናል እንጂ እርሱ ይመለከተናል መሻታችንን ሁሉ ይፈጽምልናል የሚበልጠዉንም ያደርግልናል፡፡ኦ! ጌታ ሆይ ከአንተ ጋር መሆን እንዴት መባረክ ነዉ፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages