መልካም የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ይሁንልን። ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
በሕፃንነቱ ያለፈችውን የሰማዕትነት ጽዋ በሠላሳ ዓመቱ ተቀበላት፡፡ በመጨረሻም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ድንበር አታፍርሱ፤ ዋርሳ አትውረሱ” እያለ ንጉሡ ሄሮድስንና ሄሮድያዳን በመገሠፁ ምክንያት አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ የራስ ቅሉ ክንፍ አውጥቶ በዓለም እየተዘዋወረ ፲፭ አምስት ዓመት ወንጌልን አስተምሯል፡፡ የሰማዕትነቱ ዜናም እንዲህ ነበር፡፡
“የሄሮድያዳ ልጅ ንጉሥ ሄሮድስን በዘፈኗ በጣም አድርጋ ስላስደሰተችው እርሱም በተራው ሊያስደስታት ፈለገ፡፡ ‹እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ይሰጣት ዘንድ በሕዝቦቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት እንዳይከዳት በፅኑ ቃልኪዳን ማለላት፡፡” እንዲህም እያለ ‘የፈለግሽውን ጠይቂኝ፣ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁ ምን ላድርግልሽ?’ እያለ በመሐላ ባላት ጊዜ በእናቷ ምክር የዮሐንስን አንገት ቆርጦ ይሰጣት ዘንድ ለመነችው፡፡ ንጉሥ ሄሮድስም ይህን ልመና ከአፏ በሰማ ጊዜ ‹የፈለግሽውን እሰጥሻለሁ› ብሎ በሕዝቡ ፊት ስለማለ ለሰው ይምሰል አዘነ፣ ተከዘ፡፡ ኃዘኑም ስለ ዮሐንስ መሞት አይደለም፣ ዮሐንስን ሕዝቡ ይወደው ስለነበር እነርሱን ስለ መፍራቱና መሐላ ምሎ ከዳ እንዳይባል ነው እንጂ፡፡ ስለ ዮሐንስ አዝኖ ቢሆን ኖሮ ቀድሞውንም በግፍ እንዲታሰር ባላደረገው ነበር፡፡ ‹የለመንሽውን ሁሉ እሰጥሻለሁ› ብሎ ስለማለ ሄሮድስ የዮሐንስን አንገት እንድትቆረጥ አደረገ፡፡ መስከረም ፪ ቀን ሰማዕትነት የተቀበለበት ዕለት ነው፡፡
ከዚህ በኋላ ወታደሮች ሠይፍ ይዘው የዮሐንስን አንገት ይቆርጡ ዘንድ ወደ መኅኒ ቤት ሄዱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የሄሮድስ ጭፍሮች ሊገድሉት እንደመጡ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ስላወቀ ከጨለማው ቤት ውስጥ አንገቱን በመስኮት አውጥቶ እንደሚመቻቸው አድርጎ ጠበቃቸው፡፡ የሄሮድስን ቃል እንዳያቃልሉ ጭፍሮቹም የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስን አንገት ስለ መሐላው ቆረጡት፡፡ አስቀድሞ በሕፃንነቱ ስለጌታ ከተሰየፉት ሕፃናት መካከል በስደት ምክንያት ባይኖርም ከሠላሳ ዓመት በኋላ ግን እውነትን መስክሮ የሰማዕትነትን ጽዋ ተቀበለ፡፡ በመሐላ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ሄሮድስ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ባላስገደለው ነበር፡፡ ስካርና ዘፈን ከሚገኙበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፤ አለልክ መብላና መጠጣት ካለበት ቦታ እግዚአብሔርን መበደል፣ ማስቀየምና ማስቆጣት ይገኝበታል፡፡ ስካር ከሚገኝበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፡፡ ስካርና ዘፈን ከሚገኝበት ቦታ የእግዚአብሔር መቅሰፍት የፈጣሪያችን ቁጣና በቀል ይፈጸምበታልና፡፡ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ያስገደለው ዘፈን፣ ስካርና የዘማ ፍቅር መሆኑን ልብ በማለት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት:: ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለአሥራ አምስት ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች:: የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት) ዕለት ነው፡፡ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡
ስሞቹና ትርጉማቸው፡ ፍስሐ ወሐሴት፣ ጸያሔ ፍኖት፣ ቃለ ዓዋዲ… ይባላል፡፡
ዮሐንስ ማለት “እግዚአብሔር ጸጋ ነው” ማለት ነው፡፡ ትርጓሜ ወንጌልም መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና (ሉቃ.፩፥፲፬)፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ፣ በማሕጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት፣ በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ፣ እሥራኤልን ለንስሃ ያጠመቀ፣ የጌታችንን መንገድ የጠረገ፣ ጌታውን ያጠመቀና፣ ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው:: ስለዚሕም ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ነቢይ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕት፣ ጻድቅ፣ ካሕን፣ ባሕታዊ/ገዳማዊ፣ መጥምቀ መለኮት፣ ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)፣ ድንግል፣ ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)፣ ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)፣ መምሕር ወመገሥጽ፣ ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ) ብላ ታከብረዋለች::
ስለዮሐንስ የተሰጠ ምስክርነት፡ እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ በነብዩ በኢሳይያስ አስቀድሞ ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም፤ በምድረ በዳ የሚያስተምር የአዋጅ ነጋሪ ቃል ኢሳ. ፲፩ ፥ ፩ ተብሎ የተነገረለት ነው፡፡ ጌታችንም፡- “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? … ነቢይን? አዎን ይህ ከነቢይም ይበልጣል። (እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ) ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው፤ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ታላቅነት ተናግሯል (ማቴ.፲፩፥፱-፲፩)።
ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ ስለ ዮሐንስ ሲናገር “ወዝንቱ ውእቱ ማኅቶት ዘየኃቱ ወያበርህ – እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ” ነው ያለው (ዮሐ ፭፡፴፭)፡፡ ዮሐንስን የሚነድና የሚያበራ ፋና (መብራት) ብሎ ገለጸው፡፡ ይህን ለጨለማው ዓለም ታላቅ ብርሀን ነበረ፡፡ እርሱ ሰማዕትነትን እየተቀበለ (እየነደደ) ለሌላው አበራ፡፡ ፀሐይ በወጣ ጊዜ የፋናን ብርሀን የሚሻው እንደሌለ ጌታም ባስተማረ ጊዜ የዮሐንስን ትምህርት የሚሻው የለምና የዮሐንስን ትምህርት በፋና፣ የጌታን ትምህርት በፀሐይ መስሎ ተናገረ፡፡ በሌላም መልኩ ፋና ለመጣለት ነው የሚያበራው፡፡ ፀሐይ ግን ለሁሉም ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ዮሐንስ ያስተማረው ለመጣለት ሕዝብ ነው፡፡ ጌታ ያስተማረው ለሁሉም ነውና የዮሐንስን ትምህርት በፋና፣ የጌታን ትምህርት ደግሞ በፀሐይ መስሎ አስተማረ፡፡
የመልክአ ዮሐንስ መጥምቅ ፀሐፊም ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ “ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተ ነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ /ዮሐንስ ሆይ ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብም በጽድቁ ቢመኙም ሆነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም/” ሲል መስክሮለታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት ዕለት ነው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ሕይወቱና ትምህርቱ፣ ያደረጋቸው ድንቆችና ተአምራት፣ እንዲሁም እግዚአብሔር የሰጠው ቃል ኪዳንና ሰማዕትነቱ በገድሉ በሰፊው ተጽፏል፡፡ በዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር ክብሩን ለማስታወስ ያህል በጥቂቱ አቀረብን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከቱም ትጠብቀን፡፡አሜን!
ጌታችን አምላካችን መድኀኔዓለም ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ የሚል አስደናቂ ቃል ኪዳን ገብቶለታል፡🕊
፩. ‹‹ሰው ሁሉ ወደ ሥጋዊ ተግባርም ሆነ ወደ መንፈሳዊ ተግባርም ቢሆን ሲሄድ ‹ይህ የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ነው› ብሎ ቅጽሩን፣ ገራገሩን ቢሳለም የተሳለመው ሰው ቢኖር እኔ መንበረ መንግሥቴን አሳልመዋለሁ፡፡ የገድልህንም መጽሐፍ የተሳለመ ቢኖር እኔ መንበረ መንግሥቴን አሳልመዋለሁ፡፡››
፪. ‹‹…ከሚበላውና ከሚጠጣው ከፍሎ በስምህ ለነዳያን ለሰጠ ሥጋዬን ደሜን እሰጠዋለሁ፤ በሃይማኖት ፀንቶ፣ በምግባር ሠፍቶ ሥጋዬን ደሜን እንዲቀበል አደርገዋለሁ፤ ለሥጋዬ ለደሜ የሚያበቃ ሥራ እንዲሠራ አደርገዋለሁ፤ እስከ ሃምሣ አምስት ትውልድም ድረስ እምረዋለሁ፡፡››
፫. ‹‹ከቤተክርስቲያንህ የተቀበረውን ሰው ከመከራ ሥጋ፣ ከሲኦል እሳት አድነዋለሁ፤ እኔ ከተቀበርኩበት ኢየሩሳሌም ሄዶ ከእኔ መቃብር ውስጥ እንደተቀበረ አደርገዋለሁ፡፡››
፬. ‹‹ቤተክርስቲያንህ ከታነፀችበት፣ ስምህ ከሚጠራበት፣ መታሰቢያህ ከሚደረግበት፣ የተአምርህ ዜና ከሚነገርበት፣ የገድልህ መጽሐፍ ተነቦ ከሚተረጎምበት፣ እኔ በረድኤት ከዚያ እገኛለሁ፤ ከዚያ ቦታ አልለይም፡፡ የገድልህ መጽሐፍ ከሚተረጎምበት ቦታ አጋንንት አይደርሱም፤ ከዚያ ቦታ ሰይጣናት ይርቃሉ፡፡››
፭. ‹‹የገድልህ የተአምርህ መጽሐፍ የተነበበትን ውኃ እኔ እንደተጠመቅሁበት እንደ ማየ ዮርዳኖስ አደርገዋለሁ፡፡ የገድልህ መጽሐፍ በተነበበት ውኃ የተጠመቀበት ሰው ቢኖር የሰማንያ ዓመት ኃጢአቱን አስተሠርይለታለሁ፤ ወንዱን የአርባ ቀን፣ ሴቷን የሰማንያ ቀን ሕጻን አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ በተጠመቅሁበት ማየ ዮርዳኖስ እንደተጠመቀ ሆኖለት ከኃጢአቱ ይነጻል፡፡››
፮. ‹‹ሰውም ሆነ እንስሳ ቢታመም በጽኑ እምነት ይደረግልኛል ብሎ አምኖ ያለ ጥርጥር ውኃ አቅርቦ የገድልህን መጽሐፍ በላዩ ላይ አንብቦ የተነበበበትን ውኃ ቢታጠብበት ወይም ቢጠጣ ያለ ጥፋት ፈጥኖ ከደዌው ይፈወሳል፡፡››
፯. ‹‹የገድልህ መጽሐፍ የተነበበትን ማየ ጸሎት በቤቱ ውስጥ ቢረጭ ከዚያ ቤት በረከቴን እመላበታለሁ፤ ተድላን፣ ደስታን፣ ጥጋብን በዚያ ቤት አሳድራለሁ፤ እስከ ዘለዓለም ድረስ በቤቱ ውስጥ የእህል መታጣትና ረሀብ፣ የውኃ ጥማት፣ ተላላፊ በሽታ አይገባበትም፤ ፈጽሜም አላመጣበትም፡፡››
፰. ‹‹ደስ ብሎት በተድላ በደስታ በዓለህን ያከበረውን ሰው ሁሉ በቅዱሳን መላእክቶቼና በሰማያዊ አባቴ በአብ ማሕያዊ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ ፊት እኔ ደስ አሰኘዋለሁ፡፡ እነሆ እኔም ከበዓልህ ቦታ ላይ አልለይም፤ በዓልህንም ከሚያከብሩት ጋር እኔ አብሬያቸው እቀመጣለሁ፤ እስከ ሃምሣ አምስት ትውልድም እምረዋለሁ፡፡››
፱. ‹‹ለቤተክርስቲያንህ ዕጣን፣ ሻማ፣ ጧፍ፣ ልብሰ ተክህኖ፣ መጎናጸፊያ፣ መጋረጃ፣ ነጭ ስንዴ የሰጠ ሰው ቢኖር እስከ ሃምሣ አምስት ትውልድም ድረስ እምረዋለሁ፡፡››
፲. ‹‹ሥጋዬን ደሜን መቀበል ያልተቻለው ሰው ቢኖር ለመታሰቢያህ ዝክር ከተደረገው ፍርፋሪ ይቅመስ፣ ሥጋዬን ደሜን እንደተቀበለ እኔ አደርግለታለሁ፡፡ ፍርፋሪውን ባያገኝ እንጀራውና ዳቦው የተበላበትን ገበታ፣ ጠላው የተጠጣበትን ፅዋ በምላሱ ይላስ፣ እኔ ኢየሱስ ቃሌ የማያብለው ሥጋዬን ደሜን እንደተቀበለ አደርግለታለሁ፤ ስለ እምነቱ ሥጋዬን ደሜን ለመቀበል የሚያበቃውና እውነተኛውን ምግባር የጽድቅ ሥራ እንዲሠራ አደርገዋለሁ፡፡››
ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ ስለ ዮሐንስ ሲናገር ‹‹ዮሐንስ የሚያበራ መብራት ነበረ›› ነው ያለው፡፡ ዮሐ 5፡35፡፡ ዳግመኛም ክብሩን ሲገልጥለት "እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም" በማለት መስክሮለታል፣ (ማቴ 11:11፣ ሉቃ 7:28)፡፡ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
ምንጭ፦
፩) ደብረ መንክራት ሚጣቅ ቅዱስ አማኑኤል አንድነት ገዳም ያሳተመው የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ ገድል
፪) መጽሐፈ ስንክሳር፣ ትርጓሜ ወንጌል (ወንጌለ ሉቃስ)፣ ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ
Post Top Ad
Saturday, October 2, 2021
መስከረም ፪ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ በዓል ሰማዕትነቱና ዕረፍቱ፡
Tags
# ነገረ ቅዱሳን
Share This
About አትሮንስ ሚዲያ
ነገረ ቅዱሳን
Labels:
ነገረ ቅዱሳን
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Post Bottom Ad
Author Details
Templatesyard is a blogger resources site is a provider of high quality blogger template with premium looking layout and robust design. The main mission of templatesyard is to provide the best quality blogger templates which are professionally designed and perfectlly seo optimized to deliver best result for your blog.
No comments:
Post a Comment