መስከረም ፭ ቀን ጻድቁ አቡነ መልከ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

መስከረም ፭ ቀን ጻድቁ አቡነ መልከ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ

ጻድቁ አቡነ መልከ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ _______________________________ የአቡነ መልክአ ክርስቶስ አባት ጣዕመ ክርስቶስ፡ እናታቸው አውጋንያ ይባላሉ፡፡ እነርሱም ልጅ አልነበራቸውምና የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ይማጸኑ ነበር ነገር ግን ‹‹የተባረከ ፍሬ የማትሰጠን ከሆነ ልጅ አትስጠን›› እያሉም ይጸልዩ ነበር፡፡ ጣዕመ ክርስቶስና አውጋንያ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ሕጉን ዘወትር የሚጠብቁ፣ ለተቸገሩ የሚራሩ ናቸው፡፡ የተራቡትን በመመገብ የታረዙትን በማልበስ የበረቱ በመሆናቸው ዘወትር ከቤታቸው ድኆች አይጠፉም ነበር፡፡ የቅዱሳኑን ልመና የተቀበለ አምላክ የእነርሱንም ልመናቸውን ሰምቶ የተባረከ ልጅ አቡነ መልክአ ክርስቶስን ሰጣቸው፡፡ አባታችን በምድረ ኢትዮጵያ ሳርካ በሚባል ቦታ ሰኔ 26 ተፀንሶ መጋቢት 27 ቀን ተወለደ፡፡ ዕድሜውም ለትምህርት ደርሶ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሲማር ከዕለታት በአንድ ቀን ከሕፃናት ጋር ሲጫወት እመቤታችን ተገልጻለት ‹‹ልጄ ከእንግዲህ አንተ የምትጫወተው ከቅዱሳን መላእክት፣ ከጻድቃንና ከሰማዕታት ጋር ይሁን›› አለችው፡፡ እርሱም ዘወትር ጸሎትን መጸለይ ጀመረ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ስለገለጠለት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ወድያው አጠናቀቀ፡፡ ከዚኽም በኋላ አቡነ መልክአ ክርስቶስ ገና በለጋ ዕድሜው ስለ ጌታችን መስክሮ ሰማዕት ይሆን ዘንድ በመመኘት በዘመኑ ሰማዕታት ሰማዕትነትን ከሚቀበሉባቸው ቦታዎች ቢሔድም ሰማዕትነት ለእርሱ አልተፈቀደለትም ነበር፡፡ ወደ ወግዳ እና ምድረ ሰርማት የሚባሉ ቦታዎች ቢሔድም የተመኘውን ሳያገኝ ቀረ፣ በዚኽም ጊዜ ቃል ከሰማይ ወደ እርሱ መጣና ‹‹ወዳጄ መልክአ ክርስቶስ ሆይ! ሰማዕትነት ክፍልህ አይደለም ይልቁንም እንደ አብርሃም የብዙሃን አባት የሕፃናትና የደካሞች መጠጊያ ትሆናለህ›› አለው፡፡ ከዚኽም በኋላ ጻድቁ በመንዝ፣ በጎንደር፣ በመቄት፣ በዳውንት፣ በላስታ፣ በዋድላና በሌሎቹም ቦታዎች ተዘዋውሮ የከበረች ወንጌልን በመስበክ ድዉያንን በመፈወስ ብዙ አገልግሏል፡፡ መንዝ ሪቅ በሚባል ቦታ አቅም የሌላቸውን በዕድሜም የገፉትን እናቶችንና አባቶችን ውኃ በመቅዳት ምግብ በማብሰል ዕንጨት በመሸከም አገለገላቸው፡፡ እንግዶች ሲመጡ እግራቸውን አጥቦ ያሳርፋቸዋል፡፡ ሥራዎችን በሚሠራ ጊዜም ከአንደበቱ ጸሎት አይቋረጥም ነበር፡፡ በእንዲህ ያለ ምግባር ዐሥር ዓመት ካገለገለ በኋላ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ከሆነው ከአቡነ አኖሬዎስ ቤተ ክርስትያን ደብረ ጽጋጃ አባ ጴጥሮስ በተባለ መምህር እጅ መነኰሰ፡፡ አባ ጴጥሮስም አቡነ መልክአ ክርስቶስን ካመነኰሰው በኋላ ወደ ቀደመ ቦታው ሔዶ በዚያ ያሉትን በክህነቱ እንዲያገለግላቸው እንዲያመነኵሳቸው መስቀል ሰጥቶ ሸኘው፡፡ እርሱም ተጨማሪ 12 ዓመት አገልግሏቸው በአጠቃላይ 22 ዓመት ሲሞላው የእግዚአብሔር ጸጋ የበዛላት ወለተ ጽዮን ስታርፍ ፍትሐት አድርሶ ከቀበራት በኋላ ወደ ሌላ ቦታ በመሔድ የእግዚአብሔር መልአክ እየመራው ዳውንት ደረሰ፡፡ በዳውንት አጽፍት ሚካኤል ዘጠኝ ዓመት አገልግሎ ብዙዎችን አመነኰሰ፡፡ ከዚያም ወደሌላ ቦታ እንዲሔድ እግዚአብሔር ነግሮት ለሔድ ጉዞ ሲጀምር ድንጋዮች ዕፅዋቶች ከነበሩበት ተነሥተው ይከተሉት ጀመር፣ እርሱ ግን በሥልጣኑ በቦታቸው እንዲወሰኑ አዘዛቸው፡፡ ወደ ዋድላ በመሔድ በሰለልኩላ በየጭራ በሐዲስ አምባ እና በደብረ ዳሪት አቡነ አሮን ተመላልሶ ወንጌልን ሰበከ ድዉያንን ፈወሰ ብዙዎችንም አመነኰሰ፡፡ ከዚህም በኋላ ዐብይ ጾምን ወደ ጎንደር ሔዶ ሱባኤውን በዚያ ከቆየ በኋላ ወደ ሰለልኩላ ተመለሰ፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያምና የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል ታቦታት አብሮ ይዞ ስለነበር ሀገሩ እንዲባረክ በሰላልኩላ የቅዱስ ሚካኤልን ቤተ ክርስትያን ሠርቶ ታቦተ ሚካኤልን አስገብቶ አከበረ፡፡ ዛሬም ድረስ በዋድላ ሰለልኩላ ሚካኤል በሰለልኩላ ቅዳሴ መገኛነቱ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል፡፡ አባታችንም ጥቂት ጊዜ በሰለልኩላ ሚካኤል እንደቆየ እመቤታችን ‹‹…ይህ ስፍራህ አይደለምና ወደ ደብረ አብ ደብረ ወለድ ደብረ መንፈስ ቅዱስ ሒድ›› አለችው፡፡ በተነገረው ቦታም ተወስነው የሚጸልዩ ሦስት ደገኛ መነኰሳት አባቶች ‹‹በቶሎ ወደዚህ ና፣ በዚህ አንተ የብዙዎች አባት ትሆናለህ›› ብለው ወደ አቡነ መልክአ ክርስቶስ መልእክት ላኩበት፡፡ አባታችንም ከዳውንት ወደ ግሸቅ መሔጃ መንገዱ ላይ መንኳክ ማርያም ደርሶ አደረ፤ ጸሎት አድርሶ ቦታዋን ቢባርካት ጠበል ፈለቀ፤ የገዳም ሥርዓትንም ሠራላት፡፡ ዛሬም ድረስ አባታችን ያፈለቀው ጠበል ብዙ ተኣምራት እያደረገ ምስክር ሆኖ በቦታው ላይ አለ፡፡ አቡነ መልክአ ክርስቶስ የእመቤታችንን ታቦት ይዞ በሽሎ የሚባል ወንዝ ሲደርስ እንደ ሱራፌል ቀንና ሌሊት ሳያስታጉሉ የሚያመሰግኑ ሥዉራን ቅዱሳን በደብሩ እንዳሉ አስተዋለ፡፡ እመቤታችን እየመራችው በደብሩ አናት አድርሳው ‹‹ይህ ቦታህ ይሁን፣ ስሙም ግሸቅ ይባል፣ ታቦቴንም በቀኝህ አኑር›› አለችው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ልጄ ገዳመ አስቄጥስን፣ ገዳመ ሲሐትን እንደባረከ ይህን ገዳምህንም ይባርክልህ፤ ማህበረ መቃርስ ወማኅበረ ጳኩሚስ፣ ማኅበረ ሖር ወአባ አብሎ፣ ደብረ ኮኖብዮስ እና ሌሎችንም እንድባረከ ይባርክልህ፤ ከአንተ የሚወለዱ አንዱስ እንኳን አይጠፋም፤ በገዳምህ የተቀበረ አይጠፋም›› አለችው፡፡ አባታችንም ገዳሙን ግሸቅ ካደረገ በኋላ ገዳማዊ አንድነቱ እየጠነከረ በመምጣቱ በደብሩ ዙሪያ የነበሩ ክፉዎች ‹‹ቦታችንን ሊቀሙን ነው›› ብለው በማሰብ ክፋትን ማድረግ ጀመሩ፡፡ በድንግልና ራሳቸውን ጠብቀው ከዓለም የተለዩ ደናግል መነኰሳት ሴቶቹን በማየት እንዲፈተኑ ተንኮል አስበው መነኰሳት አባቶች ውኃ ከሚቀዱበት ማይ ዘአጋም ከተባለ ምንጭ ሴቶች ልጆቻቸውን መላክ ጀመሩ፡፡ መነኰሳቱም በዚህ አዝነው ውኃ ሳይቀዱ በመመለስ ለአቡነ መልክአ ክርስቶስ የሆነውን ሲነሩት ‹‹ልጆቼ ይህን ቦታ እመቤታችን ነች የሰጠችኝ፣ ‹አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የፈቀዱልህ ቦታህ ነው፣ ለአንተና ለልጆችህ ለዘለዓለም ማደርያ ርስትህ ይሁን፣ ወገን የሌላቸው ታማሚዎች ስምህን በመዘከር ከመከራ ይዳኑ› ብላ ተናግራ ሰጥታኛለች፤ እግዚአብሔር ለኛ ካለው ያድርገው ለእነርሱ ካለው ይሁን ብሎ ሱባኤ ይዞ እናትና ልጅን ለመነ፡፡ የአካባቢው ሰዎችም እግዚአብሔርን አሳዝነዋልና ከእነርሱ ውስጥ ብዙዎች በሕማም በደዌ ተመቱ፤ ብዙ ሰው መሞት ሲጀምር ቀሪዎቹ ከገዳሙ ክልል ሸሽተው ወጡ፡፡ በዚህም ጊዜ የአቡነ መልክአ ክርስቶስ ዝና በመላው ኢትዮጵያ ደረሰ፡፡ ዳግመኛም አባታችን ‹‹…የኤርትራን ባሕር ከፍለህ ሕዝብህን ያሻገርኽ፣ እንዳይርባቸው በበረሓ መና ያወረድኽ፣ እንዳይጠሙ ከዓለት ውኃ ያፈለቅኽ አምላክ ሆይ! ዛሬም አንተ ነኽና ውኃ አፍልቅልኝ›› ብሎ ቢማጸን በግሸቅ ተራራ ላይ ውኃ ፈለቀለት፡፡ በገዳሙ የነበሩ ሁሉ ከእርሷ ተጠምቀው ጠጥተው ተፈወሱ፡፡ የጎንደሩ ንጉስ አድያም ሰገድ ኢያሱ ሙያተኞችን ልኮ በግንብ አሰራት፡፡ የአጼ ኢያሱ ልጅ ልዑል ሰገድ ተክለ ሃይማኖትም ውሃ የሚቀዱበት በቅሎ ሰጥቷቸዋል፡፡ ማኅደረ ክርስቶስ የሚባል ክፉ ጠላት በብዙ ፈተና የሚያሠቃየው የአቡነ መልክአ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር በደብሩ ነበር፡፡ አቡነ መልክአ ክርስቶስም በጸሎቱ ክፉ ጠላትን ድል አደረገለት፡፡ ‹‹ልጄ አይዞህ አትፍራ ጽና›› ይለው ያበረታው ነበር፡፡ ከዚኽም በኋላ በጎንደር ዙሪያ ብዙ መነኰሳት ሰማዕት በሚሆኑበት ዘመን ማኅደረ ክርስቶስ ለአባታችን በራእይ ያየውን ነገረው፤ ‹‹አንተ ሰማዕት ለመሆን ሒድ፣ አቡነ መልክአ ክርስቶስ ግን አይሔድም፣ ብዙ ሥራ ከፊቱ አለ፣ ብዙዎችን ወደ መንግስተ ሰማያት ይጠራልና›› ተብያለው በማለት የተነገረውን መልእክት አስረዳው፡፡ አባታችንም ‹‹የነብያትን መንገድ ያቀና ሰማዕታትን በፈተና ሁሉ ያጸና አምላክ መንገድህን ያቅናልህ ያስፈጸምህ›› ብሎ ልጁን መረቀውና ሰማዕትነት ወደሚቀበልበት ቦታ ሰደደው፡፡ ማኅደረ ክርስቶስም ወደ ንጉሥ ወታደሮች ዘንድ ቀርቦ ስለ ሃይማኖቱ መስክሮ አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ የክብር አክሊልን ተቀዳጀ፡፡ አንገቱንም በሰይፍ ከቆረጡት በኋላ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ራስ የሰማዕቱ ማኅደረ ክርስቶስ ራስ መዝሙረ ዳዊት መኃልየ ሰሎሞን ውዳሴ ማርያም ዘመረች፡፡ ተአምር መስከረም ፭ በዓመታዊ የዕረፍት በዓላቸው ታስበው የሚውሉት ኢትዮጵያዊው ታላቅ ጻድቅ አቡነ መልክአ ክርስቶስ ያደረጉት ታላቅ ተአምር ይህ ነው፣ ለጻድቁ እንደ ሰው እየተላላከ ከበሸሎ ወንዝ ውኃ እየቀዳ ወደ ገዳማቸው የሚያመጣላቸው አንድ አህያ ነበራቸው፡፡ አህያውም ሰው ሳይጭነው ባዶ እንስራ ወደ ወንዙ ወስዶ በተአምር ውኃው በእንስራ ሲሞላለት ሳያጋድል ይዞ ሩቅ መንገድ ተጉዞ ከአባታችን ገዳም ይደርሳል፡፡ ነገር ግን በአንደኛም ቀን ይህንን አገልጋይ አህያቸውን ጅብ በላባቸው፡፡ አቡነ መልክአ ክርስቶስም በአህያቸው ፈንታ ጅቡን ፯ ዓመታት ውሃ አስቀድተውታል፡፡ ቅዱሳኑ አቡነ መልክአ ክርስቶስ እና አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ በአንድ ዘመን አብረው የኖሩ ሲሆን ኹለቱ ቅዱሳን የቅርብ ወዳጆችም ነበሩ፡፡ ገድላቸው እንደሚናገረው አቡነ መልክአ ክርስቶስ ከግራኝ አህመድ የ15 ዓመት ጥፋት በኋላ የቅዱስ ያሬድን የቅዳሴ ዜማ ትምህርት ጠብቆ ለትውልድ በማበርከት እጅግ የጎላ ድርሻ አላቸው፡፡ አቡነ መልክአ ክርስቶስ ዐቢይ ጾም ሲገባ ብዙ ጊዜ ብቻውን ሱባኤ ይይዛል፡፡ በዐቢይ ጾም ወቅት ከዕለታት በአንደኛው ቀን በግሸቅ ማርያም ሳለ ክፉ ጠላት በከባድ ረኀብ ፈተነው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝኖ ሲጨነቅ ክብርት እመቤታችን ተገጻለት ‹‹ሰላም ለአንተ ይሁን ወዳጄ መልክአ ክርስቶስ›› አለችው፤ ዳግመኛም ‹‹ስለምን ትተክዛለህ? አይዞህ ጽና…›› ብላ በልጇ ቸርነት ሰማያዊ ኅብስት መገበችው፡፡ አባታችንም ይህን ምሥጢር ለልጁ ለአባ ሚካኤል ከነገረው በኋላ ‹‹እስከምሞት ድረስ ይህን ለማንም አትንገር፣ በኋላ ግን እንደፈቃድህ›› አለው፡፡ ቅዱሳን ከውዳሴ ከንቱ ለመሸሽ ሲሉ በሕይወት እያሉ በጎ ሥራቸውን መደበቅ ልማዳቸው ነው፡፡ እረፍታቸው የአቡነ መልክአ ክርስቶስ የዕረፍቱ ቀን በደረሰ ጊዜ በጽኑ ደዌ ታመመ፡፡ ከመረጣቸው ጋር ቃልኪዳን ያደረገ መድኀኔዓለም ለአቡነ መልክአ ክርስቶስም እንዲሁ አደረ፡፡ ‹‹…ድካምህን ተቀብያለሁ፣ በእጅህ የመነኰሱ፣ በመስቀልህ የተባረኩ፣ ከሩቅ አንተን ብለው ደጅህ የመጡ፣ በስምህ መታሰቢያህን የሚያደርጉትን ሁሉ የልባቸውን በጎ መሻት እፈጽምላቸዋለሁ፤ በደላቸውን ሳልመለከት ጸጋ በረከትን እሰጣቸዋለሁ፤ የወዳጆችህን ትውልድ እስከ 15 ትውልድ እምርልሃለሁ›› ብሎ ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ መስከረም 5 ቀን በዕለተ ቀዳሚት በ86 ዓመታቸው ነፍሳቸው ከሥጋው ተለየች፡፡ ከመቃብራቸውም ላይ ሕሙማን የሚፈወሱበት ድንቅ ድንቅ ተኣምራትን የሚያድርግ ጠበል ፈለቀ፡፡ አቡነ መልክአ ክርስቶስ ለአገልግሎት ሲጓዙ በመንገድ ላይ ከሞተ 900 ዓመት የሞላውን ሰው ዐፅም አግኝነተው ወደ እግዚአብሔር ጸልየው በመስቀላቸው ባርከው ከሞት አስነሥተውታል፣ ከሞት የተነሣውም ሰው ኢአማኒ ስለነበር ጻድቁ አጥምቀው ለክርስቶስ መንግሥት አብቅተውታል፡፡ የአቡነ መልክአ ክርስቶስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን አሜን። (ምንጭ፡-ገድለ አቡነ መልክአ ክርስቶስ)

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages