=============
መስቀል ቤዛችን መስቀል ኃይላችን መስቀል የነፍሳችንም መዳኛ ነው።
“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፤” /፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲፰/ተብሎ እንደተነገረ የእግዚአብሔር ኃይሉ የተገለጠበት ኃይለ እግዚአብሔር ክርስቶስ የማዳን ሥራውን የፈጸመው በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ነው። በመሆኑም የጌታችን ቅዱስ ሥጋው የተፈተተበትና ክቡር ደሙም የፈሰሰበት መስቀል ስለ ክርስቶስ የከበረ ነው። ለምሳሌ የሆሳዕና አህያ በተጓዘችበት ጐዳና ሁሉ የተነጠፈላትና የተጐዘጐዘላት ስለ ክርስቶስ የከበረች በመሆኗ ነው። /ማቴ. ፳፩፥፰/። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የከበረውና የማዳን ኃይሉም የተገለጠበት መስቀል፥ ወልድ ዋህድ ብለን በኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ለምናምን ሁሉ ዲያብሎስን የምንቀጠቅጥበት ኃይላችን ነው። ምክንያቱም ጌታችን አስቀድሞ “እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤” ተብሎ እንደተነገረ ዲያብሎስን የቀጠቀጠው በመስቀሉ ነውና። /ዘፍ. ፫፥፲፭/። ይህንን በተመለከተ በብሉይ ኪዳን ዘመን የተፈጸመ ምሳሌ አለ። የነቢያት አለቃ ሙሴ እጆቹን በመስቀል አምሳል ግራና ቀኝ ዘርግቶ በሚጸልይበት ጊዜ እስራኤል ኃይል አግኝተው ጠላቶቻቸውን ድል አድርገዋል። እኛም እስራኤል ዘነፍስ የምንባል ምዕመናንም ጠላቶቻችንን አጋንንትን በኃይለ መስቀሉ ድል እናደርጋቸዋለን። የአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል አባት ቅዱስ ያዕቆብም እጆቹን ባመሳቀለ ጊዜ ኃይል አግኝቶ በዮሴፍ ልጆች ላይ በረከትን አሳድሯል። /ዘፍ. ፵፰፥፲፫-፳/። እኛም በመስቀሉ ኃይል በረከተ ሥጋንና በረከተ ነፍስን እናገኛለን።
ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ግን ፊት በቀራንዮ ድል የሆነበትን፥ ኋላም እንደ ቀራንዮ ዕለት ዕለት የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ በሚፈተትባት በቤተ ክርስቲያን ድል የሚሆንበትን መስቀል ከእጃችን ለማስጣል ያልሞከረው ሙከራ የለም። ለልማዱም “እንጨት አይደል? ለምን ትሳለሙታላችሁ? ለምንስ ትሰግዱለታላችሁ?” እያሰኘ ነው። ይሁን እንጂ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኃይል ይታመናል እንጂ “ይህ እንጨት ነው፥ ይህም ጨርቅ ነው፥ ይህ ደግሞ ውሃ ነው፤” ተብሎ አይጠረጠርም። ለምሳሌ፦
በትረ ሙሴ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ብዙ ተዓምራት አድርጋለች፤ /ዘፀ. ፬-፲፬/
የኤልያስ መጐናጸፍያ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ዮርዳኖስን ከአንዴም ሁለት ጊዜ ለሁለት ከፍላለች፤ /፪ኛ ነገ. ፪፥፯-፲፬/
ፈለገ ዮርዳኖስ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ንዕማንን ከለምጹ ፈውሳዋለች፤ /፪ኛ ነገ. ፭፥፩-፲፬/
በዘይት /በቀንዲል/ ላይ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦ በሽተኞች ተፈውሰዋል፤ /ማር. ፮፥፲፫፣ ያዕ. ፭፥፲፬/
የቤተሳይዳ መጠመቂያ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ዓይነ ስውሩ ብርሃን አግኝቶባታል፤ /ዮሐ. ፱፥፩-፲፪/
ቅዱስ ጳውሎስ የልብሱ ቁራጭ ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ብዙ በሽተኞች ፈውስ አግኝተውባታል፤ ከአጋንንት ቁራኝነትም ተላቀውባታል፤ /የሐዋ. ፲፱፥፲፩-፲፪/
ቅዱስ ጴጥሮስ ጥላው ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦባት ከመንገድ ዳር የወደቁ በሽተኞች ሁሉ ተፈውሰውባታል። /የሐዋ. ፭፥፲፭-፲፮/። ስለሆነም ስለመስቀሉ ያልሆነ ነገር እየተናገርን ከመስቀሉ ባለቤት ከክርስቶስ እንዳንጣላ መጠንቀቅ አለብን። ምክንያቱም መስቀልን መጥላት የክፉ ትንቢት መፈጸሚያ መሆን ነውና። ይህንንም በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ አላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው /ገሃነመ እሳት ነው/፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው /አይጾሙም/፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው፤” ሲል ተናግሯል። /ፊል. ፫፥፲፰-፲፱/።
እንግዲህ ነቢዩ ዳዊት “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው። ወዳጆችህ እንዲድኑ፤” ብሎ አስቀድሞ በትንቢት እንደተናገረ፥ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዲያብሎስ ቀስት /ጦር/ እናመልጥና እንድን ዘንድ በደሙ ቀድሶና አክብሮ የሰጠንን ምልክት መስቀልን አጥብቀን መያዝ አለብን። /መዝ. ፶፱፥፬-፭/። እንደ ቅዱስ ጳውሎስም “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት /ዓለም በእኔ ዘንድ ሙት ከሆነበት/ እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት /እኔም በዓለም ዘንድ ሙት ከሆንኩበት/ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።” እያልን በመስቀሉ መመካት አለብን። /ገላ. ፮፥፲፬/። መስቀልን በምልክትነቱ ብቻ የሚቀበሉት ሰዎች አሉ፤ ለእኛ ግን፥ መድኃኒታችን፥ የሚያድነን፥ ቤዛችንና መስቀል ኃይላችን የነፍሳችንም መዳኛ ነው።
Post Top Ad
Saturday, October 2, 2021
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Post Bottom Ad
Author Details
Templatesyard is a blogger resources site is a provider of high quality blogger template with premium looking layout and robust design. The main mission of templatesyard is to provide the best quality blogger templates which are professionally designed and perfectlly seo optimized to deliver best result for your blog.
No comments:
Post a Comment