ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 18 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, September 29, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 18

 

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም አስራ ስምንት በዚህች ቀን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ #አቡነ_ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር፣ የደብረ ጽጋጉ #አቡነ_አኖሬዎስ፣ ሰማዕቱ #ቅዱስ_መርቆሬዎስ_ካልዕ#የአቡነ_ያዕቆብ_ግብፃዊ ዕረፍታቸው ነው። ዳግመኛም ይህች ዕለት ሐዋርያው #ቅዱስ_ቶማስ በሕንድ አገር ድንቅ ተአምር ያደረገባት ዕለት ናት፣ኢትዮጵያዊቷ #ቅድስት_ጸበለ_ማርያም ዕረፍቷ ነው። ፡፡

መስከረም ዐሥራ ስምንት በዚች ቀን ወንጌልን የሚሰብክ የሃይማኖት መምህር አባታችን ኤዎስጣቴዎስ አረፈ ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ክርስቶስ ሞዓ የእናቱ ስም ስነ ሕይወት ይባላል ሁለቱም ደጋጎች እግዙአብሔርን የሚፈሩና በሕጉ ጸንተው የሚኖሩ ነበሩ።
ከዘህም በኋላ በከበረ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል አብሣሪነት ይህን ቅዱስ ወለዱት ስሙን የጌታ ጥብቅ ብለው ሰየሙት ። በአደገም ጊዜ የዳዊትን መዝሙርና የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍትን አስተማሩት ።
ከዚህም በኋላ የእናቱ ወንድም አባ ዘካርያስ ወደአለበት የመነኰሳት ገዳም ወሰዱት ። አባ ዘካርያስም የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዳደረችበት አውቆ የምንኩስናን ሥርዓት አስተምሮ የመላእክትን አስኬማ አለበሰው ። ከገድሉ ጽናት የተነሣ በገዳም ያሉ አረጋውያን እስኪያደንቁ ድረስ በጾም በጸሎት የተጠመደ ሆነ እርሱ በጥበብና በዕውቀት የጸና ነውና ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ዲቁና ተሾመ የዲያቆናት አለቃ እንደሆነ እስጢፋኖስም ለቤተ ክርስቲያን አገለገለ ።
ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋር ተገለጠለትና ሰላምታ ሰጠው በንፍሐትም መንፈስ ቅዱስን አሳደበረት እንዲህም አለው ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ ሆይ እኔ ከእናትህ ማሕፀን መረጥኩህ ያለ ፍርሀትና ድንጋፄ ወንጌልን ለብዙዎች ሕዝቦች ትሰብክ ዘንድ ከኢትዮጵያ እስከ አርማንያ ድረስ መምህር አደረግሁህ አንተን የሰማ እኔን ሰማ አንተን ያልሰማ እኔን አልሰማም ጌታችንም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ ።
ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስም ወደ ጳጳስ ሒዶ ቅስና ተሾመ የወንጌልንም ሃይማኖት ይሰብክ ዘንድ ጀመረ ብዙ ሰዎች ወደ ርሱ እስቲሰበሰቡ ድረስ በእርሱም እጅ መንኩሰው ደቀ መዛሙርትን ሆኑት ከእርሳቸውም ታላቁ አባ አብሳዲ ነው ።
ብዙዎችንም የከፋች ሥራቸውን አስትቶ ከክህደታቸው መለሳቸው ትምህርቱም በሀገሩ ሁሉ ደረሰ በመላ ዘመኑም የሰንበታትና የበዓላት አከባበር የጸና ሁኖ ተሠራ ከሐዋርያትም ሕግና ሥርዓት ወደቀኝም ሆነ ወደ ግራ ሁሉም ፈቀቅ አላሉም ።
ወደ ኢየሩሳሌምም ሁለት ጊዜ ሔደ እግዚአብሔርም በእጆቹ የዕውራንን ዐይኖች በማብራት አንካሶችንና ጎባጦችን በማቅናት አጋንንትን በማስወጣት ቁጥር የሌላቸው ተአምራትን አደረገ ።
ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ፈቃድ ለመሔድ በአሰበ ጊዜ ልጆቹን ሰብስቦ የመነኰሳትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ከመናፍቃንም ጋር እንዳይቀላቀሉ አማፀናቸው ። ልጁ አብሳዲንም በእነርሱ ላይ ሾመውና ወደ ኢየሩሳሌም ሰንበትን እያከበረና የክርስቶስን ሃይማኖት እያስተማረ ሔደ ። ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚንም ደርሶ ከእርሱ ቡራኬ ተቀበለ የሃይማኖትንም ነገር ተነጋገሩ ዳግመኛም ከከበሩ ቦታዎች በመሳለም በረከትን ተቀበለ በዮርዳኖስም ተጠመቀ ።
ከዚያም ወደ አርማንያ ሔደ ወደ ኢያሪኮ ባሕርም ሲደርስ በመርከባቸው ያሳፍሩት ዘንድ መርከበኞችን ለመናቸው በከለከሉትም ጊዜ ዓጽፉን በባሕሩ ላይ ዘረጋ በቅድስት ሥላሴ ስም በላዩ ባረከ ራሱንም በመስቀል ምልክት አማተበ እንደ መርከብም ሁኖለት በላዩ ተጫነ ሁለት መላእክትም ቀዛፊዎች ጌታችንም እንደ ሊቀ ሐመር ሆኑለት ። ከባሕሩም ግርማ የተነሣ እንዳይፈሩ ልጆቹን አጽናናቸው ። ግን እንዲህ አላቸው ልጆቼ በልባችሁ ቂምንና ሽንገላን እንዳታኖሩ ተጠበቁ ለኔ ግን ከእናንተ አንዱ አንደ ሚጠፋ ይመስለኛል ይህን ሲናገር ልቡ የቂም የበቀል ማከማቻ ስለሆነ ወዲያውኑ አንዱ ከእነርሱ መካከል ሠጠመ ።
በእግዚአብሔርም ፈቃድ ባሕሩን ተሻግሮ ወደ አርማንያ ከተማ ደርሶ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር ተገናኘ ሰገደለትም ከእርሱም ቡራኬን ተቀበለ ሊቀ ጳጳሱም በአየው ጊዜ ታላቅ ደስታን ደስ አለው በፍቅርም ተቀበለው ።
አባታችን ኤዎስጣቴዎስም ሁሉም በትመህርቱ አንድ እስከሆኑ ድረስ የአርማንያን ሰዎች ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው የሠሩትን ሥርዓት እያስተማራቸው ኖረ ።
ከዚህም በኋላ ዕረፍቱ ሲደርስ ክብር ይግባውና ጌታችን ተገለጠለትና ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ቃል ኪዳንን ሰጠው ። በአረፈም ጊዜ ጳጳሳትና ካህናት በታላቅ ክብር ገንዘው በሰማዕቱ በቅዱስ መርምህናም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀበሩት ። ከሥጋውም ብዙ ተአምራት ተገለጡ ።

በዚችም ቀን የደብረ ጽጋግ መምህር አባ አኖሬዎስ አረፈ።
"አኖሬዎስ ትልቁ" መባላቸው "ትንሹ አኖሬዎስ" በሚል ስያሜ የተጠሩ ሌላ ጻድቅ አሉና ነው፡፡ ይኸውም ታላቁ አቡነ አኖሬዎስ አባታቸው ዘርዐ ሃይማኖት ወይም ዘርዐ አብርሃም እናታቸው ደግሞ ክርስቶስ ዘመዳ ይባላሉ፡፡ አቡነ አኖሬዎስ ታላቁ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ ሕፃን ሞዐ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ አቡነ ዜና ማርቆስና አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር እነዚህ ሁሉም የወንድማማቾች ልጆች ናቸው፡፡
እነኚህ ደጋግ ቅዱሳን በእናትም የእኅትማማቾች ልጆች ናቸው፡፡ ማለትም የአኖሬዎስ ታላቁ እናት ክርስቶስ ዘመዳ፣ የሕፃን ሞዐ እናት ትቤ ጽዮን፣ የንጉሡ የዐፄ ይኮኖ አምላክና የማርያም ዘመዳ እናት እምነ ጽዮን እኅትማማቾች ናቸው፡፡ እነዚህም ሦስቱ እኅትማማቾች (እምነ ጽዮን፣ ትቤ ጽዮንና ክርስቶስ ዘመዳ) መድኃኒነ እግዚእ የሚባል አንድ ወንድም አላቸው፡፡ እርሱም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት እናት የቅድስት እግዚእ ኀረያ አባት ነው፡፡ ማርያም ዘመዳም አቡነ ዜና ማርቆስንና ማርያም ክብራን ወልዳለች፡፡ ማርያም ክብራም ትንሹን አኖሬዎስን ወልዳለች፡፡ ታላቁ አቡነ አኖሬዎስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በኋላ ወደ ትግራይ በመሄድ ፀዓዳ ዓንባ ከተባለ ቦታ ገዳም መሥርተዋል፡፡
ግብፃዊው አቡነ ያዕቆብ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የደብረ ሊባኖሱን እጨጌ አቡነ ፊልጶስን አስጠርተው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት “ኢትዮጵያ በአንድ ጳጳስ መወሰን የለባትም፡፡ ስለዚህ ዐሥራ ሁለት አበው መርጠን ክርስትና ይስፋፋ” ብለው ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል፣ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያን መርጠው ሀገረ ስብከት ተሰጥቷቸው ለሐዋርያዊ ተልእኮ ተሠማሩ፡፡ እነዚህ ዐሥራ ሁለቱን ንቡራነ ዕድ ለስብከተ ወንጌል በመላዋ አገሪቱ ሲሠማሩ ለአቡነ አኖሬዎስ እንደ ግብጦን የተባለ ቦታ ደረሳቸው፡፡ ይህም ቦታ ከግንደ በረት እስከ ባሌ ያለውን አገር ያካትታል፡፡ እርሳቸውም ሰባት ታቦታት ይዘው በመሄድ አብያተ ክርስቲያናት ተክለው ክርስትናን አስፋፍተዋል፡፡ በአካባቢው ስብከተ ወንጌልን ካስፋፉ በኋላ ባርጋባን የተባለ የአካባቢው ሰው ተአምራታቸውንና ትምህርታቸውን ተመልክቶ በጽጋጋ ገዳም እንዲመሠርቱ ስለነገራቸው አቡነ አኖሬዎስ በጽጋጋ ገዳም መሥርተዋል፡፡
ይህ የአቡነ አኖሬዎስ ገዳም ደሴ ዙሪያ በጽጋጋ የሚገኝ ሲሆን ከደሴ ወደ መካነ ሰላም በሚወስደው መንገድ በ12 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ገዳሙ የተመሠረተው በ1317 ዓ.ም በንጉሥ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ አቡነ አኖሬዎስ በጽጋጋ ገዳማቸው እያሉ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን በክፉዎች ምክር ተታሎ የአባቱን ሚስት በማግባቱ ጻድቁ እንደ ዮሐንስ መጥምቅ ንጉሡን ስለገሠጹት ታስረው ወደ ወለቃ ተጋዙ፡፡ ንጉሡ ሲሞት ሠይፈ አርዕድ ነግሦ የተጋዙት በሙሉ እንዲመለሱ ስላወጀ አቡነ አኖሬዎስም ወደ በዓታቸው ጽጋጋ ተመለሱ፡፡ አቡነ አኖሪዎስ በነገሥታቱ ፊት ቆመው የወንጌልን ሕግ በመመስከራቸው እየታሰሩ ምድረ ጸወን ወደምትባል አገር (ይህውም ደቡብ ወሎ ቦረና የምትገኝ ናት) እንዲሁም ዝዋይ ደሴ ገማስቄ ግድሞ (ባሌ አካባቢ) ወደ ተባለው አገር ተጋዙ፡፡ ለብዙ ዓመታት ገዳም መሥርተው ቆይተው ወደ ጥንት በዓታቸው ተመልሰው ጽጋጋ መጥተው በገዳማቸው ብዙ ተጋድለው በ1471ዓ.ም በዚሁ በጽጋጋ ገዳማቸው ነው ያረፉት፡፡
በኋላም ወደ አሩሲ በመሄድ ኢስላሞችን አስተምረዋል፡፡ ብዙ ተአምራት ያደረጉላቸው ሲሆን መንደራቸውንም ያማረ መንደር ብለው ሰይመውላቸዋል፡፡ የአሩሲ ኢስላሞች እጅግ ያከብሯቸውና ይወዷቸው ነበር። ከአክብሮታቸውም የተነሣ አቡነ አኖሬዎስን ‹‹ኑር ሁሴን›› እያሉ ይጠሯቸው ነበር፡፡ ጻድቁ በአሩሲ ቆመው የጸለዩበት ቦታ ዛሬም ድረስ ተከብሮ ይኖራል፣ ሶፍ ዑመር ዋሻ ተብሎ የሚጠራው ታሪካዊ ዋሻ የአቡነ አኖርዮስ በዓት መሆኑ በታሪክ የሚታወቅ ሐቅ ነው፣ ይህም በገድለ ተክለ ሃይማኖትና በድርሳነ ቅዱስ ዑራኤል ላይ በሰፊው ተጠቅሷል፡፡ ጻድቁ በኢቲሳ 21 ዓመት ቆመው ሲጸልዩ ብርሃን ተተክሎ ይታይ ነበር፡፡ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትልቅ ቃልኪዳን ከተቀበሉ በኋላ መስከረም 18 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡

በዚች ቀን በከሀዲው ዮልያኖስ እጅ ሌላው ቅዱስ መርቆሬዎስ በሰማዕትነት አረፈ እርሱም አስቀድሞ ክርስቲያን የነበረ ነው ። የታላቁ ቈስጠንጢኖስ ልጅ ሁለተኛው ቈስጠንጢኖስ በሞተ ጊዜ የቈስጠንጢኖስ እኅት ልጅ ዩልያኖስ ነገሠ እርሱ ግን ጣዖታትን አመለከ ሰገደላቸውም የክርስቲያን ወገኖችንም አሠቃያቸው ብዙዎችም በእርሱ እጅ በሰማዕትነት አረፉ ።
የንጉሡም የልደቱ ቀን በሆነች ጊዜ የሳቅ የሥላቅ የሆኑ ተጫዋቾችን ሰበሰባቸው ይህ ቅዱስ መርቆሬዎስም ቁጥሩ ከእሳቸው ጋር ነበር ካህናት በቤተክርስቲያን እንደሚያደርጉት በክርስትና ሥርዓት እንዲጫወት ይህን መርቆሬዎስን ከሀዲው ንጉሥ አዘዘው እንዳዘዘውም በክርስትና ሥርዓት ሁሉ ተጫወተ ታላቅም ሳቅና ሥላቅ ሆነ።
ሁለተኛም በክርስትና ጥምቀት ሥርዓት ሊጫወት ጀመረ በመስቀል ምልክት አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያለ በውኃው ላይ አማተበ ። ያን ጊዜም መለኮታዊ ብርሃን በውኃው ውስጥ ወረደ እግዚአብሔርም የልቡናውን ዐይን ገልጦለት ያንን ብርሃን አየው ልብሱን ጥሎ ራቁቱን ወደ ውኃው ወርዶ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያለ ተጠመቀ ።
ከዚህም በኋላ ወጥቶ ልብሱን ለበሰ በንጉሡም ፊት ቆሞ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ ንጉሡም በርሱ ላይ ተቆጣ እንዲህም ብሎ አስፈራራው ለእኔ በመታዘዝ ለአማልክት ዕጣንን ካላሳረግህ ታላቅ ሥቃይን አሠቃይሃለሁ ትእዛዜን ከተቀበልክ ግን እኔ ብዙ ገንዘብ ሰጥቼህ እጅግ አከብርሃለሁ ።
ቅዱስ መርቆሬዎስም የዚህን ዓለም ገንዘብ ሁሉና መንግሥትንም ብትሰጠኝ ጌታዬ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም ብሎ መለሰለት ። ያን ጊዜም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ንጉሡ አዘዘና ቆረጡት በሰማያዊት መንግሥትም የማይጠፋ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ ።

በዚችም ቀን መስተጋድል የሆነ ግብጻዊ ሊቅ ያዕቆብ አረፈ። ወላጆቹም ደጎች ምእመናን ነበሩ ይህንንም ቅዱስ አገልጋይ ሊሆን ለእግዚአብሔር ሰጡት ። ትምህርቱንም በአደረሰ ጊዜ በእስክንድርያ ወደ አለ ገዳም ወላጆቹ ወሰዱት ለአበ ምኔት አባ ገብርኤልም ሰጡት ። እርሱም ተቀብሎ የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሁኖ ሳለ አመነኰሰው ።
ከዚህም በኋላ ሃያ ዓመት ሲሆነው ለተጋድሎ ከመምህሩ ጋር ወደ በረሃ ወጡ ከፍታ ያላት ግንብንም አግኝተው አባ ገብርኤልና አባ ያዕቆብ ከላይዋ ላይ ወጡ ። ከዚያም የውኃ ጉድጓድ አለ ከዚያም ጉድጓድ ውኃ እየቀዱ በገንዳዎች ላይ ያፈሳሉ የዱር እንስሶችም ሁል ጊዜ እየመጡ ከገንዳው ውኃ ይጠጣሉ አባ ያዕቆብም ያልባቸዋል ወተታቸውንም አይብ አድርጎ ከመምህሩ ጋር ይመገባሉ ።
አባ ገብርኤልም በአረፈ ጊዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ ዐሥራ ሁለት ገዳማውያን መጡ በጾምና በጸሎትም በመትጋት የእንስሶቹን ወተት በመመገብ ከእርሱ ጋር ተቀመጡ ለገዳሙ የሚያስፈልገውን ግን ነጋዴዎች ሥንዴን ከሩቅ ያመጣሉ ።
ለዕለታትም በአንዲቱ ዕለት እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ አባ ሙሴ ጸሊምን ብናየው ከእርሱም ብንባረክ እንወድ ነበር። ሰይጣንም በሰማ ጊዜ በመፋቀራቸው ቀንቶ በሙሴ ጸሊም አምሳል በክንፍ እየበረረ መጣ ሽማግሌ ስሆን ከቦታዬ ለምን አናወጻችሁኝ አላቸው ። እነርሱም የሕይወትን ቃል ከአፍህ ልንሰማ ከአንተም በረከትን ልንቀበል እንወዳለን አሉት ደግሞ ኑሮአችሁ እንዴት ነው አላቸው ። እነርሱም ለዱር እንስሶች በገንዳ ላይ ውኃን እንደሚቀዱ ውኃውንም ሊጠጡ ሲመጡ እንደሚአልቧቸውና ሁል ጊዜ በየማታው ከወተታቸው እንደሚመገቡ ነገሩት ።
ሰይጣንም እንዲህ አላቸው የአዘዝኳችሁን ትሰማላችሁን አላቸው አዎን እንሰማሃለን አሉት ። ዳግመኛ እንዲህ አላቸው የእንስሶቹን ወተት አትጠጡ እናንተ መነኰሳት ስትሆኑ አታምጡአቸው ጾምን ግን በየአርባ ቀን ጹሙ የዳዊትንም መዝሙር አትጸልዩ እርሱ በዐመፅ የኦርዮን ሚስት ነጥቋልና። እርሱንም ገድሎታልና ጥቅም የሌለው ብዙ ነገርንም መከራቸው እነርሱም እርሱ እንደ አባ ሙሴ መስሏቸው ይመልሱለት ነበር ።
ከዚህም በኋላ ሰይጣን እንደሆነ ለሊቅ ያዕቆብ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘበው ደቀ መዛሙርቱንም የቁርባን ቅዳሴ እንዲቀድሱ አዘዛቸውና ሥጋውንና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ ሰይጣን መሆኑን ለልጆቹ መነኰሳት ነገራቸው ።
ሁለተኛም በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አምሳል ወደርሳቸው መጣ ከእርሱም ጋር በኤጲስቆጶሳት አምሳል አሉ ። በደረሰም ጊዜ በላያቸው ተኰሳተረ ከዚህ ልትኖሩ ማን ፈቀደላችሁ ብሎ አወገዛቸው ሊቅ ያዕቆብም አይቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እጆቹን ዘርግቶ ጸሎትን አደረገ ። ወዲያውኑ ሰይጣን ተበተነ ግን መፈታተኑን አሁንም አልተወም በሚአስፈራ ዘንዶ አምሳልም ወደ አባ ያዕቆብ የሚመጣበት ጊዜ አለ ። በንጉሥ አምሳልም ደም ግባታቸው በሚያምር ደናግል አምሳልም በአሞራዎችና በቁራዎች አምሳልም ሁኖ በጥፍሮቻቸው ፊቱን እየነጩ በእንዲህ ያለ ፈተና ሰባት ዓመት ተፈተነ ከዚህም በኋላ ትዕግሥቱንና ድካሙን እግዚአብሔር አይቶ መብረቅን ልኮ ሰይጣንን ቀጥቅጦ በተነው ያዕቆብ ሆይ ከአንተ የተነሣ ወዮልኝ በጸሎትህ አቃጠልከኝ እያለ ሸሸ ።
ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና እግዚአብሔር አብዲን ወደሚባል ገዳም እንዲሔድ ሊቅ ያዕቆብን አዘዘው ። እርሱም ለልጆቹ መነኰሳት ይህን ነገራቸው ከዚያም ግንብ ውስጥ እንዲኖሩ አማፀናቸው ።
እርሱ ግን ብቻውን ወደ ኢያሪኮ ባሕር ዳርቻ ሔደ መርከብንም በአጣ ጊዜ በባሕሩ ሞገድ ላይ ባረከ ገብቶም ወደ ተርሴስ አገር እስከ ገባ ድረስ በባሕሩ ላይ እንደ ደረቅ ምድር ሔደበት ።
በሀገሩ ጥጋጥግ አልፎ ሲሔድ በትል የተከበበ ቁስለኛ ሰው አገኘና ሊቅ ያዕቆብ ስምህ ማነው ብሎ ጠየቀው እርሱም ስሜ እንጦኒ ነው አባቴም ለባለ መድኃኒቶች ብዙ ገንዘብ ሰጠልኝ ሊፈውሱኝ አልቻሉም ። መምህር ያዕቆብም ስለ ደዌው ተከዘ ጸሎትንም አድርጎ ሁለመናውን በመዳሰስ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ጤነኛ ሁን አለው ወዲያውኑ ዳነ ደቀ መዝሙሩም ሁኖ ተከተለው ።
ከዚህም በኋላ ከረድኡ ጋር ሲጓዝ ሀገረ ዐምድ ደረሱ የንጉሥ አንስጦስን ልጅ እየአበደ ራሱን በደንጊያ ሲደበድብ አገኙት እርሱን መያዝም የሚችል አልነበረም። ሊቅ ያዕቆብም ይዞ ያመጣለት ዘንድ ረድኡን አዘዘው በአቀረበለትም ጊዜ በከበረ መስቀል ምልክት አማተበበትና ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሰውዬው ወጥቶ እንዲሔድ ሰይጣንን አዘዘው ። ያን ጊዜም በጥቁር ባርያ አምሳል ወጣ የንጉሡም ልጅ በከበረ ሊቅ ያዕቆብ ጸሎት ዳነ አባቱና ወገኖቹ ሁሉ በታላቅ ደስታ ደስ አላቸው ንጉሡም ለከበረ ሊቅ ያዕቆብ ብዙ ገንዘብ ሊሰጠው ወደደ እርሱ ግን አይሆንም አለ ምንም ምን አልተቀበለም ።
ክብር ይግባውና በእግዚአብሔርም ትእዛዝ አብዲን በሚባል አገር የገዳም አበ ምኔት ከሆነ ከአባ በርሳቦ ጋር ተገናኝተው በአንድነት ተጓዙ በጒዞ ላይም እያሉ እንጦኒ በሆድ ተቅማጥ በሽታ ታመመና በሦስተኛው ቀን አረፈ ቀበሩትም።
ስሟ አውርሳ ከሚባል አገር በደረሱ ጊዜ የአገረ ገዥውን ልጅ ታሞ አገኙት በሊቅ ያዕቆብም ጸሎት ዳነ መኰንኑም ልጁ እንደ ዳነ አይቶ በታላቅ ደስታ ደስ አለው እስከ ዕለተ ሞቱ ረድዕ ይሆነው ዘንድ ለከበረ ያዕቆብ ልጁን ሰጠው የልጁም ስም ፍቁር ነው ።
ወደ ሊቅ በርሳቦ ገዳምም በቀረቡ ጊዜ መነኰሳቱ ተቀበሏቸው በብዙ ምስጋናም እየዘመሩ አስገቧቸው በዚያችም አገር ጎን የታነፀ የጣዖት ቤት አለ ስሙ ሰሚር የሚባል የፋርስ ንጉሥ በየዓመቱ እየመጣ ለጣዖታት በዓልን ያከብራል የከበረ ሊቅ ያዕቆብም መነኰሳቱን እንዲህ አላቸው እነሆ የፋርስ ንጉሥ እንደመጣ ሰምታችኋል የክብር ባለቤት ስለ ሆነ ክርስቶስ ስለ ስሙ ኑ ደማችንን እናፍስስ ።
መነኰሳቱም በዚህ ምክር እየተስማሙ ሳሉ የንጉሡ ጭፍሮች ወደዚያ ገዳም ደረሱ መነኰሳቱንም ጥቁር ልብስን ለብሰው አዩአቸውና እናንተ ምንድን ናችሁ ከአምልክትስ ማንን ታመልካለችሁ አሏቸው ። ቅዱሳን መነኰሳትም እንዲህ አሏቸው እኛ ከሰማያት የወረደውን በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው የሆነ የሕያው እግዚአብሔርን ልጅ ክብር ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመልከዋለን ጭፍሮችም ወደ ንጉሥ አቀረቧቸው ።
በደረሱም ጊዜ የክብር ባለቤት በሆነ በክርስቶስ ስም በንጉሡ ፊት ታመኑ ንጉሡም ሀገራቸውን መረመረ አባ በርሳቦም የእኔና የወንድሞቼ መነኰሳት አገራችንም ሮም ነው አለ ። አባ ያዕቆብም የእኔ አገር ግብጽ ነው አለ ንጉሡም የአባ ያዕቆብን ቃል ሰምቶ ሊገድለው አልፈለገምና ብቻውን ገለል እንዲያደርጉት አዘዘ ። ከግብጽ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን ስላለው መነኰሳቱን ግን ደማቸው እስቲፈስ ገርፈው ከእሥር ቤት እንዲጥሏቸው አዘዘ የእግዚአብሔርም መልአክ ፈወሳቸው ።
በማግሥቱም ጤነኞች ሁነው በአገኛቸው ጊዜ ብዙ ሀብት እንደሚሰጣቸው ተስፋ ሰጣቸው እነርሱ ግን ቃሉን አቃለሉ ። ንጉሡም በወይን መርገጫ ውስጥ በማስረገጥ በግርፋት ጥርሶችን የእጆችንና የእግሮች ጥፍሮችን በማውለቅ ሰባት ቀኖችም ያህል አፍንጫን፣ ከንፈርን፣ ጆሮዎችን በመቆረጥ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ ።
በስምንተኛውም ቀን ራሶቻቸውን ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ መምህራቸው ሊቅ በርሳቦም እየአንዳንዱን ለሰያፊ ከሰጣቸው በኋላ ዐሥሩ መነኰሳት ተቆረጡ የንጉሡ የፈረሶች ባልደራስ ያን ጊዜ ለቅዱሳኑ የወረዱትን አክሊሎች አየ ትጥቁንም ፈትቶ ጥሎ ክብር ይግባውና በጌታችን ክርስቶስ ታመነ እርሱንም አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት መምህር በርሳቦም ልጆቹ ከተቆረጡ በኋላ አንገቱን ዘርግቶ ሰያፊውን የታዘዝከውን ፈጽም አለው ያን ጊዜም ሰያፊው ቆረጠው ምስክርነታቸውንም ነሐሴ ሃያ ስምንት ቀን ፈጸሙ።
ንጉሡም ሥጋቸውን በእሳት እንዲአቃጥሉ አዘዘ ምድርም ተከፍታ ሥጋቸውን ሠወረች ንጉሡም አፍሮ ወደ አገሩ ሊሔድ ወደደ ። ያን ጊዜም አባ ያዕቆብ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ከሰማይም ከጠቆረ ደመና ጋርና ከሚከረፋ በረድ ጋር እሳት በንጉሡ ላይ ዘነመ ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ተቃጥሎ ጠፋ ከእነርሱ አንድ እንኳ አልቀረም ።
የዚያች አገር ሰዎችም በሰሙ ጊዜ ሁሉም ወጥተው ፈረሶቻቸውንና ዕቃዎቻቸውን ገንዘባቸውንም ወሰዱ ወደ ሊቅ ያዕቆብም አምጥተው እሊህን ገንዘቦች ለምትሻው ሥራ ውሰድ አሉት ። እርሱም አልተቀበላቸውም ግን በሰማዕታት መቃብር ላይ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ አዘዛቸው ቤተ ክርስቲያኒቱም እስከ ዛሬ አለች ።
ከዘመናትም በአንዲቱ አገር ቸነፈር ሆነ ወደ ሊቅ ያዕቆብ እንዲጸለይላቸው ላኩ እርሱም ሰምቶ እጅግ አዘነ ማዕጠንትም ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ረጅም ጸሎት ጸለየ ዕጣንንም አሳረገ ። ከዚያም ወጥቶ መልእክተኞችን አትፍሩ አትጨነቁ በሰላም ሒዱ አላቸው ። በደረሱም ጊዜ አገሪቱን ጤነኛ ሁና አገኟት ደስ ብሏቸው የሊቅ ያዕቆብን አምላክ አመሰገኑት ።
ዳግመኛም ለከበረ ሊቅ ያዕቆብ ዳንኤል የሚባል ረድእ ነበረው ደግሞ ለቅዱስ ያዕቆብ ወዳጁ የሆነ አገር ገዥ አለ ለአገረ ገዥውም ወደ ቅዱስ ያዕቆብ ከአባቷ ጋር የምትመጣ ብላቴና አለችው ረዱን ዳንኤልን በኃጢአት ልትጥለው ፈለገችው እምቢ ባላትም ጊዜ ከአባቷ አገልጋይ ፀነሰችና በሊቅ ያዕቆብ ረድእ አመካኘችበት አባቷም ሰምቶ መምህር ያዕቆብንና ደቀ መዝሙሩን ሊገድል ሔደ በጒዞ ላይም ሳለ በላዩ ከሰማይ መብረቅ ወርዶ ዐይኖቹን አሳወረው ።
የመኰንኑም ልጅ ከወለደች በኋላ ወደ ከበረ መምህር ያዕቆብ በጉባኤ መካከል ሕፃኑን አባትህ ማን እንደሆነ ትናገር ዘንድ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዝሃለሁ አለው ። ሕፃኑም አባቴ የእናቴ የአባቷ አገልጋይ እገሌ ነው አለ የተሰበሰቡትም ሕዝብ ሰምተው አደነቁ የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ።
ከዚህም በኋላ ዕረፍቱ ሲቀርብ ደቀ መዝሙሩን እንዲህ ብሎ አዘዘው ከዚህ ዓለም የምለይበት ጊዜ ደርሷል በምሞትም ጊዜ ከአባ በርሳቦና ከልጀቹ ጋራ ቅበረኝ ይህንንም ብሎ በሦስተኛው ቀን አረፈ መላእክትም ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ነፍሱን በክብር አሳረጉ ።

በዚችም ቀን የከበረ ሐዋርያ ቶማስ በሕንደኬ አገር ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ሆነ ። ቶማስም በሕንድ አገር ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ለመሔድ በተነሣ ጊዜ ወደዚያች አገር መግባትን እንዴት እችላለሁ ብሎ አሰበ ። ይህንንም ሲያስብ እነሆ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለትና አትፍራ ቸርነቴ ከአንተ ጋር ትኖራለችና አለው።
ወዲያውኑ ከሕንደኬ የጎና ነጋዴ አቤኔስ መጣ ጌታችንም ምን ትሻለህ አለው ነጋዴውም ሐናፂ የሆነ ባሪያ እሻለሁ አለ። ጌታም ይህን ባሪያዬን ገዝተህ ውሰድ እርሱ አናፂ ነውና አለው ከዚህም በኋላ በሦስት ወቄት ወርቅ ሸጠው እንዲህም ብሎ ጻፈለት የጠራቢ ዮሴፍ ልጅ የሆነ ባሪያዬን ለጎና ነጋዴ ለአቤኔስ ሸጨዋለሁ።
ከዚህም በኋላ አቤኔስ ቅዱስ ቶማስን ተረክቦ ወደ አገሩ ወሰደው ወደ ከተማውም በቀረቡና በደረሱ ጊዜ የእንዚራና፣ የመሰንቆ፣ የዛጉፍ፣ የእምቢልታ ድምፅ ሰምተው ይህ ምንድን ነው አሉ።
ሰዎችም ንጉሥ ለሴት ልጁ ሠርግ አዘጋጅቷል ወደ ንጉሡ ሠርግ ያልሔደውን እንዲቀጡት ንጉሥ አዟል አሏቸው። ይህንን ሰምተው አቤኔስና ቅዱስ ቶማስ ወደ ሠርጉ ሔዱ ሁሉም ሲበሉና ሲጠጡ ሐዋርያ ቶማስ ምንም አልቀመሰም በዚያም ዕብራዊት የሆነች አዝማሪ አለች ። በሠርጉ ምሳ ላይ ከሚያገለግሉ ውስጥ አንድ ሰው ሐዋርያ ቶማስን በጥፊ ፊቱን ጸፋው ሐዋርያውም በዕብራይስጥ ቋንቋ ይቺን እጅ ውሾች ሲጎትቷት አያታለሁ አለ አዝማሪዋም ብቻዋን ሰማችው።
ይህም በጥፊ የመታው ውኃ ሊቀዳ ወደ ውኃ ጉድጓድ ወረደ አንበሳም መጥቶ ገደለውና በታትኖ ተወው አንድ ውሻም የቀኝ እጁን ይዞ ወደ ምሳ መካከል ወሰዳት ከዚያ ያሉትም ማን ነው የሞተ አሉ ሰዎችም ይህን እንግዳውን በጥፊ የመታው ያ አሳላፊ ነው አሏቸው። አዝማሪዋም በሰማች ጊዜ ወደ ሐዋርያው ሒዳ በአጠገቡ ቁማ በጥፊ የመታችኝን እጅ ውሾች ሲጎትቷት አያታለሁ ሲል እኔ ስምቼዋለሁ አለች በዚያ ያሉትም ሁሉ ይህን ሰምተው አደነቁ።
ይህም ነገር በንጉሡ ዘንድ በተሰማ ጊዜ ንጉሡ ወደ ሐዋርያው መጥቶ ዛሬ አጋብቻታለሁና ና በልጄ ላይ ጸሎት አድርግ አለው። ሐዋርያው ቶማስም ወደ ጫጒላ ቤት ገብቶ ስለ ሙሽሮቹ ወደ ጌታችን ጸለየ የሃይማኖትንም ቃል አስተምሮ ባረካቸው በሐዋርያውም ቃል አመኑ ። ጌታችንም ደግሞ በቶማስ አምሳል ተገልጦላቸው እርሱም ሃይማኖትን አስተማራቸው እነርሱም አመኑበት ጽምረታቸውንም ትተው ድንግልናቸውን ጠበቁ ንጉሥም ክብር ይግባውና በጌታችን ክርስቶስ አመነ ።

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት ጸበለ ማርያም ዕረፍቷ ነው።
እናታችን ቅድስት ጸበለ ማርያም፡- ቅድስት ጸበለ ማርያም ትውልዷ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ቀሐ አካባቢ ነው፡፡ ወላጆቿ አባቷ እንድርያስና እናቷ መስቀል ክብራ ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያስተማሩ በሃይማኖት በምግባር ኮትኮተው አሳደጓት፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ተከስተ ብርሃን የተባለ ደገኛ ባሕታዊ ወደ አባቷ ቤት መጥቶ ባደረበት መንፈስ ቅዱስ ኀይል የቅድስት ጸበለ ማርያምን ጸጋ አወቀ፡፡
ለወላጆቿም ‹‹ይኽቺ ልጅ ወደፊት ነፍሳት የሚድኑባት የከበረች ትሆናለች›› ብሎ በእርሷ ላይ ትንቢት ተናገረ፡፡
ቅድስት ጸበለ ማርያም ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ ወላጆቿ በጋብቻ ሕግ እንድትወሰን ፈለጉ፡፡ ነገር ግን ቅድስት ጸበለ ማርያም ‹‹ቅዱስ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር አጭቶኛልና ፈጣሪዬን በድንግልና ለማገልገል ተስያለሁ›› በማለት ተቃወመቻቸው፡፡ ወደ አንድ ደገኛ ባሕታዊም ዘንድ ሄዳ በጸሎቱ ከዚህ ነገር እንዲያድናት ተማጸነችው፡፡ እርሱም ፈቃደ እግዚአብሔርን በጸሎት ከጠየቀላት በኋላ ማድረግ የሚገባትንና ወደፊት የሚገጥማትን ሁሉ ነገራት፡፡ እርሷም ለዕጣን እንዲሆን ጌጧን ሁሉ አውጥታ ሸጠችና ‹‹መሥዋዕቴን አሳርግልኝ›› ብላ ለባሕታዊው ሰጠችው፡፡ እርሱም ከጸለየላት በኋላ የጸሎቱን ምላሽ ነገራት፡፡
ወለጆቿም ያለፈቃዷ በሕግ ቢያጋቧትም ቅድስት ጸበለ ማርያም ግን በሌሊት ማንም ሳያያት ከጫጉላ ቤት ወጥታ ሄዳ በልዳው ፀሐይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ወደተሠራች ቤ/ክ ሄዳ እያለቀሰች ጸሎት አደረገች፡፡ እመቤታችንም ከሚካኤል ወገብርኤል እንዲሁም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተገለጠችላትና እንዲጠብቋት ነገረቻቸው፡፡ ቤተሰቦቿም እንዳያዝኑባት ፈርታ ተመልሳ ወደ ባሏ ዘንድ ብትገባም ባሏ በግብር እንዳያውቃት መላእክቱ ይጠብቋት ነበር፡፡ ባሏንም ሰውነቷ እንደእሳት ያቃጥለው ነበር፡፡ እርሱም አእምሮውን ከሳተ ከ3 ቀን በኋላ ሲነቃ የደረሰበትን ለቤተዘመዶቹ ባስዳቸው ጊዜ ‹‹ከገዳም የመጣች ከሆነች ለእኛ ልትሆን አይገባም›› አሉና አስጊጠውና ሸልመው መልሰው ወደ ቤተሰቦቿ ላኳት፡፡
አባቷም ዳግመኛ ወደባሏ እንድትመለስ በማስገደድ ብዙ አሰቃቂ ግርፋት ቢገርፋትም በተአምራት ምንም እንዳላገኛት ሆነች፡፡ ከዚኽም በኋላ ወጥታ ወደ ምድረ በዳ ሄደች፡፡ ወደ ገዳምም ሄዳ ዋሻ ውስጥ ገብታ ስትጸልይ አድራ አረፍ ስትል ነብር መጥቶ የእግሯን ትቢያ ይልሳት ነበር፡፡ ከዚያም ወጥታ ንህበት ወደሚባል ሀገር መጥታ ቶማስ ከሚባል መነኩሴ ጋር በታላቅ ተጋድሎ ኖረች፡፡ ቆማ ስትጸልይ እንባዋ መሬቱን ያርስ ነበር ነገር ግን ሰው እንዳያውቅባት አፈር በላዩ ትጨምርበታለች፡፡ በአንድ ዕለትም በቤ/ክ ቆማ ስትጸልይ በሁለቱ ማዕዘን የተቀበሩ ምውታን ሲጮኹ ሰማቻቸው፣ እነርሱ ግን በሲኦል ነበሩ፡፡ ጩኸታቸውንም በሰማች ጊዜ በእንባዋ ላይ እንባን በጸሎቷም ላይ ጸሎትን ጨምራ ስለእነርሱ ለመነች፡፡ ስለእነርሱም ሱባኤ ያዘች፡፡ በባሕርይው ቸርና ይቅርባይ የሆነ ልዑል እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ
እነዚያን ነፍሳት ማረላት፡፡
ቅድስት ጸበለ ማርያም በምግባርና በትሩፋት በጾም በጸሎት ጸንታ ከኖረች በኋላ የምንኩስና ቀንበርን ትሸከም (በመንናኔ ትኖር) ዘንድ በብሕትውና ወደሚኖረው ታላቁ አባት ወደ አቡነ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ ዘንድ ሄደች፡፡ እርሱም ማኅሌተ ጽጌን ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር የደረሰው ነው፡፡
አቡነ ገብረ ማርያምም ካስተማራትና በኋላ አመነኮሳትና ስሟን ‹‹ጸበለ ማርያም›› ብሎ ሰየማት፡፡ ከዚኽም በኋላ ተጋድሎዋን እጅግ በማብዛት ትሕርምትን ገንዘብ አደረገች፡፡ ከዕንጨት ፍሬዎች ውጭ የማትመገብ ሆነች፡፡ በተቀደሰችው የጌታችን 40 ጾም ወራት ግን ከሰንበት በቀር እርሱንም ፈጽሞ አትቀምስም፣ እስከ ፋሲካም ድረስ ከበዓቷ ስለማትወጣ ማንም አያያትም ነበር፡፡ ከመነኮሰችም ጊዜ ጀምሮ በጎኗ ተኝታ አታውቅም፡፡ ባመማት ጊዜም ተቀምጣ ታንቀላፋ ነበር፡፡ በውርጭ ቅዝቃዜ መከራን እየተቀበለች በባሕር ውስጥም ቆማ እየጸለየች ታድራለች፡፡ በስግደቷም በቀን እስከ 8 እልፍ ትሰግድ ነበር፡፡ ከወንድሟ ቶማስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ተማረች፡፡ የዮሐንስን ወንጌልና የራእዩን መጽሐፍ ዘወትር በማንበብ ትጸልያለች፡፡ የእመቤታችን በዓል በሆነ ጊዜ አርጋኖን ውዳሴዋን በቀን ሦስት ጊዜ ታነባለች፣ አንቀጸ ብርሃንንም በየሰባቱ ጊዜ ትጸልያለች፡፡ የዳዊትንም መዝሙር በፈጸመች ጊዜ የጌታችንን መከራ ግርፋት እያሰበች ራሷን ሺህ ጊዜ ትገርፋለች፡፡ ዳግመኛም አገዛዛቸው መልካም ይሆን ዘንድ ስለ ጳጳሱና ስለ ንጉሡ አንድ አንድ ሺህ ጊዜ፣ ስለ መነኮሳትም ሺህ ጊዜ፣ ስለኃጥአንም ሺህ ጊዜ ራሷን ትገርፋለች፡፡ ዳግመኛም ነጭ ዕጣን በእጇ ይዛ ሰባት ቀን እስኪሆን ድረስ ዕንባዋን ታፈስበታለች፣ ያም ነጭ ዕጣን ከዕንባዋ ብዛት የተነሣ ጥቁር ይሆናል፡፡ በዓል በሚሆንበት በሰባተኛው ቀን አስቀድማ ዐውቃ በመሠዊያ ያሳርገው ዘንድ ያን ዕጣን ለቄሱ ትሰጠዋለች፡፡ እግዚአብሔርም እንደሱራፌል የጽናሕ መዐዛና እንደኪሩቤል ዕጣን ሽታ አድርጎ ከቄሱ እጅ ሲቀበል በግልጽ ታያለች፡፡
ቅድስት እናታችን እሾህ ያለው የብረት ዛንዠር በወገቧ ትታጠቃለች፡፡ በወገቧና በጭኖቿ ያሰረችው ርጥብ የላም ቁርበት ከአጥንቶቿ ጋር ይጣበቃል፡፡ በደረቀም ጊዜ ሥጋዋ እየተቆራረጠ ይወድቃል፣ በምድርም ውስጥ ትቀብረዋለች፡፡ አምስት ጊዜም እንደዚህ እያደረገች ራሷን ጎዳች፣ ከዳነም መልሳ ታቆስለዋለች፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ተገለጠላትና ‹‹ወዳጄ ጸበለ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን›› አላት፡፡ ዳግመኛም ‹‹በእንዲህ ያለ የቁስል መከራ መሠቃየት ይበቃሻል›› ካላት በኋላ ተሰወረ፡፡ እርሷ ግን ሰባት ጊዜ እስኪሆናት ድረስ ይህንን አደረገች፡፡ በዚህም ጊዜ ሥጋዋ እጅግ ታመመ፡፡ ሥጋዋ እንደ ድንጋይ ደርቆ ቢቀር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንደተላለፈች ዐውቃ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተወች፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ቅድስት ጸበለ ማርያም እየጸለየች ሳለ የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቆሰለ ችግረኛ ደሃ ሰው ተመስሎ ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገልጦ ወደ እርሷ በመምጣት ቁራሽ እንጀራ ለመናት፡፡ እርሷም ፈጥና ይዛ መጥታ ሰጠችው። እንጀራውንም ተቀብሎ ሲያበቃ ‹‹በመንገድ ብዛት ደክሜአለሁና በጀርባሽ አዝለሽ ትሸኚኝ ዘንድ እወዳለሁ›› አላት፡፡ እርሷም ለድሆች አዛኝ ናትና አዝላው የድንጋይ መወርወሪያ ያህል እንደወሰደችው ቁስሉ ይድን ጀመር፡፡ ወዲያውም ቁስሉ ድኖ ምንም እንዳላገኘው ፍጹም ደህነኛ ሰው ሆነ፡፡ ያንጊዜም ፊቱ እንደፀሐይ አበራ፣ ሁለንተናውም ተለወጠ፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን ከጀርባዋ ወርዶ በፊት ለፊቷ ቆመና ‹‹የከበርሽ አገልጋዬ ጸበለ ማርያም ሆይ! ምን እንዳድርግልሽ ትወጃለሽ?›› አላት፡፡ እርሷም ከድንጋጤዋ የተነሣ እንደበድን ሆና መሬት ላይ ወደቀች፡፡ ጌታችንም አበረታትና እጇን ይዞ አነሣትና ‹‹የልብሽን መሻት ለምኚኝ›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹አምላኬ ሆይ ! በፊትህስ ሞገስ ካገኘሁ በሲኦል ያሉ ነፍሳትን ይቅር
በላቸው›› አለችው፡፡ በዚኽም ምክንያት በጌታችን ቸርነትና በእርሷም አማላጅነት ብዙ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ፡፡ ጌታችንም ሰላምታ ሰጥቷት በክብር ዐረገ፡፡
ዳግመኛም ጌታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ሦስት በትሮችን ሰጥቷት በእነርሱ እየተመረኮዘች እስከሲኦል ድረስ ትሄድና ነፍሳትን ታወጣና ታስምር እንደነበር ራሷ ተናገረች፡፡ ዳግመኛም ስትናገር ‹‹ሰማያውያን ብዙ ስሞች አወጡልኝ፣ ‹የወይን ፍሬ› እያሉ ይጠሩኛል፣ ‹የበረከት ፍሬ› የሚሉኝም አሉ፣ ‹የገነት ፍሬም› ይሉኛል›› አለች፡፡ ዳግመኛም ከልዑል ዘንድ ብዙ ጸጋዎች እንደተሰጣት በሕይወት ሳለች ለአንደ ደገኛ ቄስ ነገረችው፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት እመቤታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገለጠችላትና ‹‹ስሜን የተሸከምሽ ጸበለ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን›› አለቻት፡፡ እመቤታችንም ብዙ ምሥጢርን ከነገረቻት በኋላ ጡቶቿንም አጠባቻትና በጸጋ የከበረች አደረገቻት፡፡ በስሟም ብዙ ተአምራትን የምታደርግ ሆነች፡፡
ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም ከነቢያት፣ ከሐዋርያትና ከሰማዕታት ዕድል የተሰጣት እናት ናት፡፡ እንደነቢያት የሚመጣውን ሁሉ እንዳለፈ አድርጋ ትናገራለች፡፡ ዳግመኛም የትምህርታቸውን ፍለጋ ስለተከተለችና ለሕጋቸው ስለተገዛች ከሐዋርያት ጋር ዕድል ተሰጣት፡፡ ሦስተኛ ግድ ሳይሏት በፈቃዷ ስለተቀበለቻቸው ግርፋቶቿና ስላገኛት መከራ የሰማዕታት ዕድል ተሰጣት፡፡ ከደናግል መነኮሳትም ዕድል ተሰጣት መነኩሲትም ድንግልም ናትና፡፡ ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም መልካም የሆነውን ተጋድሎዋን ከፈጸመችና ጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ከገባላት በኋላ በሰላም ዐርፋለች፡፡ እንደ ንግሥት ዕሌኒም የሞቷን መስቀል ተሸክማ ተጠብቆላት ወዳለ ተስፋዋ በክብር ሄደች፡፡ ዕረፍቷ መስከረም 18 ነው፡፡ ጥር 18ም ዓመታዊ በዓሏ ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages