ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, September 29, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 19

 

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ያለ ደም ማፍሰስ ሰማዕት የሆነ የአርማንያ #ሊቀ_ጳጳሳት_ቅዱስ_ጎርጎርዮስ ከዐዘቅት የወጣበት መታሰቢያው ነው፣ የከበረ #ገዳማዊ_ቂርቆስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው እና የኢትዮጵያ ንጉሥ የናዖድ ልጅ የከበረችና #የተባረከች_ሮማነ_ወርቅ የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው።


መስከረም ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ቀን ያለ ደም ማፍሰስ ሰማዕት የሆነ የአርማንያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ከዐዘቅት የወጣበት መታሰቢያው ነው።
ይህም በንጉሥ ድርጣድስ ዘመን በአርማንያ አገር ራሱን ባሪያ አድርጎ ይኖር ነበር። ይህም ንጉሥ ከሀዲ ነበርና ዕጣን ሊዐሳርግ ወደ ጣዖቱ ቤት ሲገባ ቅዱስ ጎርጎርዮስን ጠርቶ ለአማልክት ዕጣን እንዲአሳርግ አዘዘው። ቅዱሱ ግን የንጉሡን ትእዛዝ አልሰማም ስለዚህም እጅግ ጽኑዕ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው በእሳትም አቃጠለው ከዚህም በኃላ ጥልቅ ከሆነ ጉድጓድ ውስጥ ጣለው በዚያም ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ።
በንጉሡ አዳራሽ አቅራቢያም አንዲት አሮጊት ነበረች እርሷም እንጀራ እየጋገርሽ ቅዱስ ጎርጎርዮስ በውስጡ ከአለበት ጉድጓድ ሁል ጊዜ ጣይለት የሚላትን ራእይ አየች። ይችም አሮጊት እንዲህ እያደረገች እንጀራንም እየጣለችለት እስከ ዐሥራ አምስት ዓመት ፍጻሜ ኖረች።
በዚያም ወራት ይህ ንጉሥ ድርጣድስ ደናግሎችንና ቅድስት አርሴማን ገድሎ ሥጋቸውም በተራራ ላይ ተጣለ። ሰይጣንም በንጉሥ ድርጣድስ ላይ ተጫነ እግዚአብሔርም የተፈጥሮ መልኩን ለውጦ እንደ እሪያ አደረገው እንዲሁም ከቤተ መንግሥት ሰዎች ብዙዎቹን ሰይጣን ተጫነባቸው በቤተ መንግሥት ውስጥ ታላቅ ኀዘንና ጭንቀት ሆነ።
የንጉሡ እኅት ግን በሌሊት ራእይ ጎርጎርዮስን ከጉድጓድ ውስጥ ካላወጣችሁት አለዚያ አትድኑም እንደሚላት ሰውን አየች ለወገኖቿም ነገረቻቸውና እንርሱም ሒደው ቅዱስ ጎርጎርዮስን ከጎድጓድ አወጡት በዚያን ጊዜም ቅዱሳት ደናግልን ሥጋቸውን ገንዞ በመልካም ቦታ አኖራቸው ከዚያም በኃላ ንጉሡንና ቤተሰቦቹን ሁሉንም ረወሳቸው። ዜናውም ሁሉ በዕረፍቱ ታኅሣሥ ዐሥራ አምስት ቀን ተጽፎአል።

በዚህችም ቀን በሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ዘመን የሆነ የከበረ ገዳማዊ ቂርቆስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
ይህም ቅዱስ ሰው ከከሀዲው ንጉሥ ከመርቅያን በሸሸ ጊዜ በከፍተኛ ተራራ ላይ በብቸኛነት ተቀመጠ በውስጡም አራዊት የኖሩበታል ምግቡንም ከእግዚአብሔር ለመነ አጋዘንም በየሦስት ቀን ወደርሱ እንድትመጣ ወተቷንም እንዲጠጣ አዘዘለት በእንዲህ ያለ ሥራም ዐሥር ዓመታት ኖረ።
የተረገመ ሰይጣን ግን በተጋድሎው በቀና ጊዜ በየአይነቱ በሆነ ፈተና ሊፈትነው ጀመረ ያስፈራው ዘንድ በጥቁር ባሪያ አምሳል የሚመጣበት ጊዜ አለ ደግሞም በብዙ ሠራዊትና በፈረሰኞች አምሳል ሁነው ይዘው ያሥሩታል በጅራፍም ገርፈው በእግሮቹ ይጎትቱታል ሰይጣናት እንደሆኑ በአወቀ ጊዜ በመስቀል ምልክት በላያቸው ሲአማትብ ያን ጊዜ ሸሹ።
በአንዲትም ዕለት በሌሊት ሲሰግድ በታላቅ ከይሱ አምሳል በአንገቱ ላይ ተንጠለጠለና በፊቱ ውስጥ ሊተነፍስበት ፈለገ ያን ጊዜም ከእግዚአብሔር ርዳታን ለመነ መልአኩን ልኮ አዳነው።
የዕረፍቱም ጊዜ ሱቀርብ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ሒዶ ሥራውን ሁሉ ነገረው ከዚህም በኃላ ወደ በዓቱ ተመለሰ ሊቀ ጳጳሳቱም መገነዣውን እንዲያዘጋጁ ሦስት ኤጲስቆጶሳትን ወደርሱ ላከ ወደ በዓቱም በሔዱ ጊዜ ታሞ አገኙት ነፍሱም ከሥጋው በምትወጣ ጊዜ ለመነገር የማይቻል ታላቅ ክብርን ተመለከቱ በበዓቱም ውስጥ ቀበሩት።

በዚህችም ቀን የከበረችና የተባረከች ሮማነ ወርቅ የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው።
ይህቺ ቅድስት እናት ኢትዮጵያዊት ናት። የንጉሥ ልጅ ስትሆን አባቷ አፄ ናዖድ እናቷ ደግሞ እሌኒ (ወለተ ማርያም) ይባላሉ። ወንድሟ ደግሞ አፄ ልብነ ድንግል ይባላሉ።
በቤተ መንግስት ውስጥ ብታድግም መንፈሳዊነቷ የገዳም ያህል ነበር። መጾምና መጸለይን የምትወድ ድኆችንና ችግረኞችን የምትጐበኝ እና ከተባረከ ትዳሯም ቅዱስ ላዕከ ማርያምን አፍርታለች። አብያተ ክርስቲያናትን ከማነጽ ባለፈ የነዳያን እናትም ነበረች። በክርስትናዋ ፈጣሪዋን ደስ አሰኝታ በዚህ ቀን ዐርፋለች።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages