ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 16 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, October 25, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 16

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_ያቃቱ አረፈ፣ የጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም እረድዕ የነበሩት #አቡነ_ኢያሱ_ዘጀር_ሥላሴ በዓለ ዕረፍታቸው ነው።


ጥቅምት ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ዘጠነኛ የሆነ ቅዱስ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ያቃቱ አረፈ።
ከርሱ በፊት የነበረ አባ ብንያሚን በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በዘመኑም ብዙ ችግር ደርሶበታል ስሙ ቴዎዶስዮስ የሚባል አንድ መለካዊ ሰው ነበረ እርሱም ወደ ደማስቆ ንጉሥ ወደ ዘይድ ሒዶ ብዙ እጅ መንሻ ሰጥቶ ለእስክንድርያ አገረ ገዥ ሁኖ ተሾመ።
ይህንንም አባት አባ ያቃቱን ሊአስጨንቀው ጀመረ በየዓመቱ ግብር ሰባት ሺህ የወርቅ ዲናር ከእርሱ እስከተቀበለ ድረስ እግዚአብሔርም እስከ አጠፋው ድረስ ይህን አባት እንዲህ አሠቃየው።
በዘመኑም የብዙዎች ቅዱሳን አባቶች አባት የሆነ የአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃዋ ተፈጸመ።
በአንዲት ሌሊትም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዚህ አባት ተገለጸለት ፍዩም በሚባል አገር በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ዮሐንስ የሚባል ጻድቅ ሰው መነኰስ እንዳለ ነገረው። ሕዝብን በማስተማርና በመምከርም ይረዳው ዘንድ መልእክተኞችን ልኮ እንዲአስመጣውም አዘዘው ሁለተኛም ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት እንደሚሆን ገለጠለት።
በዚያንም ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ሥራውንም ሁሉ አስረከበው ይህንንም አባት ከብዙ ድካም የሚያሳርፈው ሆነ በሹመቱ ወንበር ዐሥራ ዘጠኝ ዓመት ኑሮ ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።

አቡነ ኢያሱ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰሜን ሸዋ የተነሡ ሲሆን ምንኵስናቸውን ከደብረ ሊባኖሱ ከዕጨጌ አቡነ መርሐ ክርስቶስ እንደተቀበሉ ታሪካቸው ያስረዳል። ትውልዳቸው አምሐራ ሳይንት ሲሆን መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳምን የመሠረቱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው።
እርሳቸው የመሠረቱት ጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳም በግራኝ ወረራ ሳይወድም ስለቀረ ጥንታዊነቱን እንደጠበቀ ስለሚገኝና ታላቅ የበረከት ቦታ የቅዱሳን መናኸሪያ ስለሆነ ብዙዎች ነገሥታት ገዳሙን እየሔዱ ተሳልመው በረከት አግኝተውበታል። የአቡነ ኢያሱን ገድላቸውን ከአቡነ ሀብተ ማርያም ገድል ጋር ጣልያናዊው ራይኔሪ በሀገሩ ሮም እንዳተመው ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ጽፈዋል። (0s valdo Raineri, Atti di Habta Māryam (†1497) e.di Iyasu (†1508), Santi Monaci Etiopici, Roma 1990 (Or ChrA 235), 165-265.)
የጻድቁ በዓለ ዕረፍታቸው ጥቅምት 16 በገዳሙ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን ስለ ጻድቁ ገድል በዝርዝር ተጽፎ አላገኘንም፣ ይልቁንም አቡነ ኢያሱ ስለገደሙት ታላቁ ጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳም ነው በብዛት የሚነገረው።
አቡነ ኢያሱ ጀር ስላሴ ከመምጣታቸውም በፊት አስቀድመው በአቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም፣ በደብረ ሊባኖስ እና በሌሎችም ገዳማት እየተዘዋወሩ በተጋድሎ ሲቀመጡ ‹‹ቦታኸ ይኸ አይደለም›› ተብለው በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ነው ወደ ጀር ሥላሴ የመጡት። ወደ ቦታው ከመምጣታቸው በፊት አካባቢው ባእድ አምልኮ የተስፋፋበት ነበር፣ ነገር ግን ጻድቁ ሕዝቡን ክርስትናን አስተምረው ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሰውታል። የምንኵስናን መሠረት ጥለውበታል። የአቡነ ኢያሱ የዕረፍታቸው ቦታ ደብረ ሊባኖስ ቢሆንም መታሰቢያቸው በመራቤቴ በሚገኘው አስደናቂ ገዳማቸው ይታሰባል። በገዳሙ በክብረ በዓሉ ወቅት ታቦት አይወጣም፣ ከበሮ አይመታም። ምክያቱም ፍጹም የጸሎት የጽሞና ቦታ ስለሆነ ነው።
መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር ቅድስት ሥላሴ አቡነ ኢያሱ ገዳም በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ አስደናቂ ሲሆን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በደንቢ ግራርጌ ቀበሌ ጀር በሚባል ስፍራ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው። ገዳሙ ከአዲስ አበባ 137 ኪ.ሜ ከደብረ ብርሃን 91 ኪ.ሜ ከለሚ ከተማ 4 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ከጥንት ጀምሮ ስዉር ገዳም ሆኖ የቆየ ነው። ገዳሙ በ1495 ዓ.ም በዐፄ ናኦድ ዘመነ መንግሥት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ጻዲቁ አቡነ ኢያሱ ወደዚህ ቦታ መጥተው መሥርተውታል። በጅረት ታጂቦ ስለሚገኝ ነው ጀር ሥላሴ የተባለው። የክብር ባለቤት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ አስመልክቶ ከመሠረታቸው ገዳማት አንዱ ነው። አቡነ ኢያሱም በገዳሙ በሚገኘው አንድ ትልቅ ዋርካ ሥር ቆመው ይጸልዩ እንደነበር አባቶች ያስረዳሉ። አሁንም ድረስ ዋርካው በሥፍራው ላይ ሕያው ማስረጃ ሆኖ ይገኛል።
ገዳሙ ከአቡነ ኢያሱ ዕረፍት ከዘመናት በኋላ በግራኝ አህመድ ወረራ ጥቃት ደርሶበት መነኰሳቱም ተበታትነው ለ247 ዓመት ጠፍ ሆኖ ከቆየ በኋላ በ1747 ዓ.ም አቡነ ዮሴፍ የተባሉት ጻድቅ በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ከአምባሰል ተነሥተው መጥተው ገደሉን ቦርቡረው ቅኔ ማሕሌት፣ ቅድስትና ቅዱሳንን ያሟላ ቤተ መቅደስ በማነጽ ዳግም ገዳሙን በማቅናት የቀደመውን የአባቶችን ታሪክ ማስቀጠል ችለዋል። በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት ቅርሶቹና ነዋየ ቅዱሳቱ አደጋ እንዳይደርስባቸው አባቶች ሰብስበው በስውር ከቀበሩ ከረጅም ጊዜ በኋላ የቀበሩበት ቦታ ጠፍቶባቸው ነበር ነገር ግን የወንዙ ውኃ አቅጣጫውን ቀይሮ ሽቅብ ፈስሶ ቅርሶቹ ያሉበትን ቦታ አመላክቷል።
መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር ቅድስት ሥላሴ አቡነ ኢያሱ ገዳም የበርካታ መናንያን አበው በኣት ከመሆኑም ባሻገር የወንዶች ብቻ ገዳም ሲሆን መናንያኑ ከአራዊት ጋር ተስማምተው የሚኖሩበት ነው። ዙሪያው በገደል የተከበበ ሲሆን ወደ ገዳሙ ለመውረድ የዕንጨት መሰላልን ተጠቅሞ መጓዝ ግድ ይላል። ወደ ገዳሙ መግቢያ የሚያስወርደው መሰላል ደቡብ ወሎ ከሚገኘው ከታላቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም መግቢያ ጋር ይመሳሰላል። የመሰላሉ ርዝመት ከ15 ሜትር በላይ ይሆናል።
ገዳሙ ከእግዚአብሔር ጋር በሱባዔ ለመገናኘት ፍጹም ጸጥታ የሰፈነበት ከመሆኑም በላይ ረድኤተ እግዚአብሔር ያለበት ቅዱስ ቦታ ነው። ዋሻው የሚከፈተው ዐቢይ ጾም ላይ እና በእመቤታችን የፍልሰታ ጾም ወቅት ነው። በዋሻው ውስጥ ሱባዔ የሚያዘው በደረቅ ሽምብራ ቆሎ እና በአንድ ኩባያ በሶ ብቻ ነው። አባቶች በኣት ዘግተው ጾመ ፍልሰታን፣ ጾመ ነቢያትን፣ ጾመ ሐዋሪያትን በይበልጥ በምነና ሕይወት የሚያሳልፉበት የበረከት ገዳም ነው።
በጀር ሥላሴ የሚገኘው ታሪካዊ ታላቅ ተራራ በልበሊት ኢየሱስን ግራኝ አሕመድ ሲያቃጥል ሁለት በወርቅ የታነጹ አብያተ ክርስቲያናት በፍቃደ እግዚአብሔር እንደሰወረ አባቶች ይናገራሉ። ይኸም ጥንታዊና ታሪካዊ ተራራ አሁንም በቦታው የሚገኝ ሲሆን በዋሻው ውስጥ የክብር ባለቤት ጌታችን በስደቱ ወራት ከእናቱ ድንግል ማርያም፣ ከዮሴፍና ከሰለሜ ጋር ለጥቂት ጊዜ የተቀመጠበት ሲሆን አቡነ ዜና ማርቆስና አቡነ ተክለ ሃይማኖትም በምነና የተጋደሉበት ታላቅ ዋሻ ነው። ዋሻው እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ውስጥ ለውስጥ የሚያስኬድ ሲሆን በውስጡ ከ40 በላይ አብያተ ክርስቲያናት እንደተሰወሩበት አባቶች ይናገራሉ።
በግራኝ አሕመድ ወረራ ወቅት የግራኝ ሠራዊት አብያተ ክርስቲያናቱን እናጠፋለን ብለው ሲመጡ በተኣምራት ሰምጠው እንደጠፉ አባቶች ያስረዳሉ። አዛዦቹንም በዋሻ ውስጥ የሚገኙት ወፍ የሚያህሉ ተርቦች ነድፈው ጨርሰዋቸዋል። እነዚያ ተርቦች አሁንም ድረስ በገዳሙ ውስጥ ያልተፈቀደ ነገር ሲደረግ በመናደፍና በመከልከል ዋሻውን የሚጠብቁ ሲሆኑ አንዱ ተርብ ከነደፈ ሕይወት ሊያጠፋ እንደሚችል የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ። ከዚኸም በላይ ዋሻው በነብርም ይጠበቃል።
ገዳሙ ባለብዙ ቃልኪዳን ሲሆን ብዙ ስውራን አበው ዛሬም የሚኖሩበት ትንቢታቸው የማይነጥብ ብዙ ግሁሳን የከተሙበት ነው። ስውራኑ አበው ዛሬም እግዚአብሔር ለፈቀደለት ሰው ይገለጣሉ። ደገኞቹ የኢትዮጵያ ቀደምት ነገሥታት የገዳሙን ክብር በመረዳት ቦታው ድረስ በመሔድ በረከት ይቀበሉ ነበር። ዳግማዊ ምኒሊክ ለጀር ሥላሴ ገዳምና ለገዳማውያኑ አለኝታ ስለነበሩ በገዳሙ የታሪክ መዝገብ ስማቸው ዘወትር ይነሳል። ግርማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ቦታውን ይንከባከቡት የነበረ ሲሆን ለገዳሙ መርጃ የሚሆን አዲስ አበባ ላይ የሚከራይ ቤት አሠርተው በኪራዩ ገቢ ገዳሙ እንዲጠቀም አድርገው ነበር። በአካልም ገዳሙ ድረስ በመሔድ በረከትን ይቀበሉ ነበር።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages