ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 22 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, October 2, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 22

ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 21

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ሁለት በዚህች ቀን የፋርስ ንጉሥ የሳቦር ልጆች #የከበሩ_ኮቶሎስና_እኅቱ_አክሱ#የከበረ_ዮልዮስ በሰማዕትነት ያረፉበት መታሰቢቸው ነው።

መስከረም ሃያ ሁለት በዚች ቀን የፋርስ ንጉሥ የሳቦር ልጆች የከበሩ ኮቶሎስና እኅቱ አክሱ በሰማዕትነት አረፉ።
ለቅዱስ ኮቶሎስም ጣጦስ የሚባል ክርስቲያን ወዳጅ አለው ይህም ንጉሥ ሳቦር እሳትን የሚያመልክ ነው ብዙዎች ምእመናንን ስለሚያሠቃያቸው ክብር ይግባውና የክርስቶስን ስም ይጠራ ዘንድ በዚያ ወራት የደፈረ የለም።
ይህም ጣጦስ በአንዲት አገር ላይ ገዥ ነበር እርሱ ክርስቲያን እንደሆነ በንጉሡ ዘንድ ወነጀሉት። ንጉሡም ስለርሱ የተነገረው እውነት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያረጋግጥ ዘንድ ሌላውን መኰንን ወደርሱ ላከ። ሁለተኛም ክርስቲያንን ያገኘ እንደሆነ ጽኑዕ ሥቃይ እንዲያሠቃይ አዘዘው።
የንጉሥ ልጅ ኮቶሎስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ወዳጁ ጣጦስ ወደአለባት ወደዚያች አገር ሔደ ያ መኰንንም በደረሰ ጊዜ ጣጦስን በንጉሥ እንደ ወነጀሉት እንዲሁ ክርስቲያን ሁኖ አገኘው በዚያን ጊዜም የእሳት ማንደጃ ሠርተው ጣጦስን እንዲአቃጥሉት አዘዘ ቅዱስ ጣጦስ ግን በመስቀል ምልክት በእሳቱ ላይ አማተበ እሳቱም የኋሊት ተመልሶ ጠፋ።
ኮቶሎስም ይህን ተአምር በአየ ጊዜ እጅግ አድንቆ ጣጦስን ወንድሜ ሆይ ይህን ሥራይ እንዴት ተማርክና አወቅህ አለው። ጣጦስም ይህ ከሥራይ አይደለም ክብር ይግባውና ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ይህ ድንቅ ተአምር እንጂ ብሎ መለሰለት።
ኮቶሎስም እኔ በክርስቶስ የማምን ከሆንኩ እንደዚህ ልሠራ እችላለሁን? አለው ጣጦስም እንዲህ ብሎ መለሰለት በእርሱ ካመንክበት ከዚህ የሚበልጥ ተአምራት ታደርጋለህ።
በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ኮቶሎስ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ በዚያን ጊዜም ነበልባሉ እጅግ ከፍ ከፍ እስከሚል እሳቱን አነደዱ ቅዱስ ኮቶሎስም ቀረብ ብሎ በእሳቱ ላይ በመስቀል ምልክት አማተበ እሳቱም ወደ ኋላ ዐሥራ ሁለት ክንድ ተመለሰና ጠፋ።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ ንጉሥ ሳቦር ከመኰንኑ ከጣጦስና ከልጁ ከኮቶሎስ የሆነውን ሁሉ ጻፈ ንጉሡም ሰምቶ ጭፍራ ልኮ አስቀረባቸው የቅዱስ ጣጦስንም ራሱን በሰይፍ ቆረጠውና የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ።
ልጁን ቅዱስ ኮቶሎስን ግን ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየውና ደግሞ እንዲአሠቃየው ለሌላ መኰንን ሰጠው እርሱም ብዙ ካሠቃየው በኋላ አሠረው። እኅቱም አክሱ ወደ እሥር ቤት ወደርሱ መጣች ወደ ቀድሞ ሥራው እንዲመለስ ትሸነግለው ዘንድ አባቷ ልኳታልና። እርሱ ግን እኅቱን ገሠጻት መከራት የቀናች ሃይማኖትንም አስተማራት ያን ጊዜም ከስኅተቷ ተመልሳ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነች።
ከዚህም በኋላ ወንድሟ ቅዱስ ኮቶሎስ ወደ አንድ ቄስ ላካት እርሱም የክርስትና ጥምቀትን በሥውር አጠመቃት። ወደ አባትዋም ተመልሳ እንዲህ አለችው አባቴ ሆይ ለእኔና ለወንድሜ ለኮቶሎስ የሆነው ላንተ ቢደረግልህ ይሻልሃል ክብር ይግባውና ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ ከፈጠረ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለምና።
ይህንንም ነገር አባቷ ከእርሷ በሰማ ጊዜ በእርሷ ላይ እጅግ ተቆጥቶ ነፍሷን በእግዚአብሔር እጅ እስከ ሰጠች ድረስ ጽኑዕ ሥቃይን እንዲአሠቃዩአት አዘዘ በዚህም ምስክርነቷን ፈጽማ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለች።
ወንድሟን ቅዱስ ኮቶሎስን ግን በፈረሶች ጅራት ውስጥ አሥረው በተራራዎች ላይ አስሮጧቸው ሥጋውም ተቆራርጦ ተበተነ ነፍሱንም በፈጣሪው እጅ ሰጠ። የቀረ ሥጋውንም ወደ ሦስት ቆራርጠው የሰማይ ወፎች ይበሉት ዘንድ በተራራ ላይ ጣሉት በእንደዚህም ሁኔታ ምስክርነቱን ፈጽሞ የሕይወት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ወታደሮችም ሲመለሱ የሰማዕታትን ሥጋ ይወስዱ ዘንድ በሀገር አቅራቢያ ያሉ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን እግዚአብሔር አዘዛቸው እነርሱም በሌሊት ሔደው የቅዱሳን ሰማዕታትን ሥጋቸውን ወስደው በታላቅ ክብር ገነዙአቸው እንደ በረዶም ነጭ ሁነው አግኝተዋቸዋልና። የመከራው ወራትም እስቲፈጸም ድረስ በመልካም ቦታ አኖሩአቸው።
ከዚያም በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ተሠርታላቸው የቅዱሳን ሥጋቸውን በዚያ አኖሩ ከሥጋቸውም ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

በዚችም ቀን የከበረ ዮልዮስ በሰማዕትነት ያረፈበት መታሰቢያው ነው። ይህም ቅዱስ አቅፋሐስ ከሚባል አገር ነው ክብር ይግባውና ጌታችንም ስለ ቅዱሳን ሰማዕታት ለሥጋቸው እንዲአስብ ገድላቸውንም እንዲጽፍ ሥጋቸውንም ገንዞ እየአንዳንዱን ወደ ሀገራቸው እንዲልክ ያቆመው ነው።
እግዚአብሔርም በመኳንንቱ ልብ መታወርን ስለ አመጣ ለሰማዕታት ይህን ያህል በጎ ሥራ ሲሠራ ምንም ነገር አይናገሩትም ስለ ጣዖት አምልኮም አያስገድዱትም ነበር። ጽሕፈትም የሚያውቁ ሦስት መቶ አገልጋዮች አሉት እነርሱም የሰማዕታትን ገድላቸውን እየተከታተሉ ይጽፋሉ።
በመሠቃየትም ሳሉ ሰማዕታትን ያገለግላቸዋል በቊስላቸውም ውስጥ መድኃኒት ያደርግላቸዋል ሰማዕታትም ይመርቁታል እንዲህ ብለውም ትንቢት ይናገሩለት ነበር። አንተም ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደምህ ይፈስ ዘንድ አለህ ከቅዱሳን ሰማዕታትም ጋራ ትቈጠራለህ።
የከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ የግዛቱ ዘመን በተፈጸመ ጊዜ ዮልዮስን ከቅዱሳን ሰማዕታት ከቁጥራቸው አንድ ሊአደርገው ወዶ ቅዱሳን ሰማዕታትም ትንቢት እንደተናገሩለት በመኰንኑ ፊት ስለ ከበረ ስሙ ይታመን ዘንድ ለግብጽ አገር ደቡብ ወደሆነች ወደ ገምኑዲ ወደ መኰንኑ አርማንዮስ እንዲሔድ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዘዘው።
ወዲያውኑ ተነሥቶ ሔደ ከዚያም ደርሶ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ታላቅ ሥቃይን ብዙ ጊዜ አሠቃየው እግዚአብሔርም ያለ ጥፋት በጤና ያነሣው ነበር። ከዚህም በኋላ ምድር አፍዋን ከፍታ ጣዖታቱን ትውጣቸው ዘንድ ቅዱስ ዮልዮስ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ወዲያውኑ አፍዋን ከፍታ ሰብዓ ጣዖታትን መቶ ሠላሳ የሆኑ ካህናቶቻቸውን ዋጠቻቸው።
በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ዮልዮስን አምጥተው ለአማልክት በግድ እንዲአሰግዱት መኰንኑ አዘዘ ጣዖታቱን ግን ከካህናቶቻቸው ጋር ጠፍተው አገኙአቸው በዚያ ያሉ ሕዝቦችም ይህን አይተው እጅግ አደነቁ። ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አመኑ መኰንኑ አርማንዮስም ጣዖታቱ ከካህናቶቻቸው ጋር እንደ ጠፉ በአየ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ። ከቅዱስ ዮልዮስም ጋር ወደ አትሪብ ሔደው በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመኑ የአትሪብ መኰንን ግን ቅዱስ ዮልዮስን እጅግ ጭንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው ክብር ይግባውና ጌታችንም ያለ ጥፋት ያነሣው ነበር።
በአንዲት ዕለትም የጣዖቶቻቸው በዓል በሆነ ጊዜ በሽልማት ሁሉ ሸለሙአቸው በመብራቶችና በሥዕሎችም ዘንባባም አስጌጧቸው በማግሥቱም መጥተው በዓላቸውን ለማክበር በዋዜማው አዘጋጅተው የጣዖታቱን ቤቶች ዘግተው ወደ ቤታቸው ገቡ። ቅዱስ ዮልዮስም ጣዖታቱን ያጠፋቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ለመነ በዚያን ጊዜም ጌታችን መልአኩን ልኮ የጣዖታቱን ራሶቻቸውን ቆረጠ ፊቶቻቸውንም በፍም አጠቆረ ሽልማታቸውንና ዘንባባውን የጣዖቱን ቤት ሥርዓት ሁሉ አቃጥሎ አጠፋ።
ማግሥትም በሆነ ጊዜ ለአማልክቶቻቸው እንደ ልማዳቸው በዓልን ሊአከብሩላቸው በከበሩ ልብሶች ተሸልመው ሲመጡ ተጐሳቁለው ጠፍተው አዩአቸው የጣዖቶቻቸውን ድካማቸውን አወቁ። እንዲህም አሉ አማልክቶቻችን ራሳቸውን ማዳን ያልቻሉ እኛን ያድኑ ዘንድ እንዴት ይችላሉ ይህንንም ተናግረው ከአትሪብ መኰንን ጋር በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት አመኑ።
ከዚያም ደግሞ ቅዱስ ዮልዮስ ጡዋ ወደሚባል አገር ሔደ ከርሱም ጋር የገምኑዲ መኰንንና የአትሪብ መኰንን አሉ የጡዋ መኰንን ወደ ሁነ ወደ እስክንድሮስ ቀርቦ በፊቱ ክብር ይግባውና በጌታችን ስም ታመነና እንዲህ አለው ገድሌን ፈጽምልኝ ራሴንም እንዲቆርጡ እዘዝና የምስክርነት አክሊልን ተቀብዬ ወደ ክብር ባለቤት ወደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድሔድ። እስክንድሮስም እኔ አላሠቃይህም በአንተ ላይም ምንም ክፉ ነገር አላደርግም አለው።
ቅዱስ ዮልዮስም አምስት መቶ የሚሆኑ አገልጋዮቹን ሰይፎቻቸውን መዝዘው እስክንድሮስን እንዲአስፈሩት አዘዛቸው በዚያንም ጊዜ በእስክንድሮስ ላይ ተነሥተው ለክብር ባለቤት ክርስቶስ ምስክሮቹ እንሆን ዘንድ የሁላችንም ራሶቻችንን እንዲቆርጡ ካላዘዝክ እኛ እንገድልሃለን አሉት።
ዳግመኛም ርኵስ መንፈስ እንዲጫንበት ቅዱስ ዮልዮስ አዘዘው ወዲያውኑ በመኰንኑ በእስክንድሮስ ላይ ተጫነበት በዚያንም ጊዜ ራሶቻቸውን ይቆርጧቸው ዘንድ በጽሑፍ አዘዘ ሁሉንም ቅዱሳን ሰማዕታትን ቆረጧቸው።
እሊህም ቅዱስ ዮልዮስ፣ ልጁም ቴዎድሮስ፣ የከበረ ወንድሙ ዮንያስ፣ አምስት መቶ አገልጋዮቹ የገምኑዲና የአትሪብ መኰንኖች ብዙዎች ሕዝቦችም የሁሉም ቁጥራቸው አንድ ሺህ አምስት መቶ ነው። በዚያች ቀን ከቅዱስ ዮልዮስ ጋር በሰማዕትነት የሞቱ ናቸው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
የቅዱስ ዮልዮስን የልጁንና የወንድሙን ሥጋ አንሥተው ወደ እስክንድርያ አገር አደረሱ እርሱ በውስጧ ነዋሪ ሁኖ ነበርና ትውልዱ ግን አቅፋሐስ ከሚባል አገር ነው በአማረ ቦታ ውስጥም አኖሩአቸው። ከዚያም በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያንን ሠሩላቸው ከእርሳቸው ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተደረጉ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages