ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 4 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, October 13, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 4

 ጥቅምት_4

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት አራት በዚች ቀን #ቅዱስ_ባኮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ #ቅዱሳን_ነገሥታት_አብርሃ_ወአጽብሓ ያረፉበትም ዕለት ነው፣ ሐዋርያው #ቅዱስ_ሐናንያ በሰማዕትነት ዐረፈ፣ #አቡነ_በርተሎሜዎስ ዕረፍታቸው ነው፡፡


ጥቅምት አራት በዚህች ቀን የቅዱስ ሰርጊስ ባልንጀራ ቅዱስ ባኮስ በከሀዲ ንጉሥ አንጥያኮስ እጅ በሰማዕትነት አረፈ።
ይህም እንዲህ ነው እሊህን ቅዱሳን ከሀዲው ንጉሥ መክስምያኖስ በያዛቸው ጊዜ እነርሱ ወታደሮች ነበሩና ትጥቃቸውን ቆርጦ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው ከዚህም በኋላ ወደ ሶርያ አገር ወደ ንጉሥ አንጥያኮስ ሰደዳቸው። እርሱም ቅዱስ ሰርጊስን አሠረው ቅዱስ ባኮስን ግን ሰቅለው እንዲደበድቡት በአንገቱም ከባድ ደንጊያ አንጠልጥለው ከኤፍራጥስ ወንዝ ከባሕር እንዲጥሉት አዘዘ ንጉሡም እንደ አዘዘ እንዲሁ አደረጉ።
እግዚአብሔር ግን የቅዱስ ባኮስን ሥጋ ጠብቆ ወደ ወደብ አደረሰው በዚያ ወደብ አቅራቢያም በገድል ተጠምደው የሚኖሩ የአንደኛው ስሙ ማማ የሁለተኛው ባባ የሚባሉ ባሕታውያን አሉ። ለእሊህ ወንድሞችም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጠላቸውና ሒደው የቅዱስ ባኮስን ሥጋ ወደ በዓታቸው እንዲወስዱ አዘዛቸው።
በዚያንም ጊዜ መልአክ እንዳዘዛቸው ሔዱ የቅዱስ ባኮስንም ሥጋ አገኙ በአጠገቡም አንድ ቀንና አንድ ሌሊት ሲጠብቁት የነበሩ አንበሳና ተኵላ አሉ እነርሱም ከሰው ሥጋና ከእንስሳ በቀር የማይመገቡ ሲሆኑ ግን ከልዑል አምላክ ዘንድ ስለታዘዙ ነው። እሊያ ቅዱሳንም የቅዱስ ባኮስን ሥጋ ወሰዱ በታላቅ ክብር እያመሰገኑ እስከ በዓታቸውም አድርሰው በዚያ ቀበሩት።



ዳግመኛም በዚህ ቀን ቅዱሳን ነገሥታት አብርሃ ወአጽብሓ ያረፉበት ነው። አባታቸው ታዜር እናታቸው ሶፍያ (አህየዋ) ይባላሉ፡፡ መንትዮች የሆኑት እነዚህ ቅዱሳን የተወለዱት ጌታችን በተወለደባት ዕለት በታኅሣሥ 29 ቀን 312 ዓ.ም ነው፡፡ በታላቁ አባት በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እየተማሩ አድገው በእሳቸው እጅ በ330 ዓ.ም መጋቢት 29 ቀን ተጠመቁ፡፡ በእነርሱም ጊዜ አማናዊው ጥምቀትና ቁርባን መጣልን፡፡ በሀገራችን 154 አብያተ ክርስቲያናትን ያሠሩ ሲሆን 44ቱ ፍልፍል ናቸው፡፡ በተለይም ገርዓልታ ያለው ቀመር ዓርባዕቱ እንስሳ ፍልፍል ቤተ መቅደስ በሩ በራሱ ጊዜ ይከፈታል ይዘጋል እንጂ ሰው አይከፍተውም አይዘጋውም፡፡
አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን በአክሱም ሲኖሩ ከሳምንቱ ቀናት ውስጥ ቅዳሜና እሁድ ብቻ የዛፍ ቅጠሎችን ከመመገብ በቀር ሌላ ምግብ ባለመመገብ በታላቅ ተጋድሎ ይኖሩ ነበር፤ አህልም አይቀምሱም፤ በየቀኑም አምስት ሺህ ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡ በእርሳቸውም የተጋድሎ ዘመን ደጋግ የሆኑ ቅዱሳን ነገሥታት አብርሃና አጽብሓ ነገሡ፡፡
ነገሥታቱም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃንን እጅግ በጣም ይወዷቸው ነበር፡፡ አባታችንም በእንዲህ ዓይነት ተጋድሎ ሲኖሩ ከዕለታት በአንደኛው ቀን የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክ ለአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ተገልጣላቸው ‹‹ዲቁናና ቅስናን መቀበል ይገባሃል፣ ለጵጵስና ተዘጋጅ፣ እግዚአብሔር ይህችን ከፍ ያለችውን ማዕረግ ሰጥተሃልና የልጄ ወዳጅ ሆይ በጸሎትህና በልመናህ በስብከትህም የኢትዮጵያ ሰዎች ሁሉ ይድናሉ፣ በእጅህ ጥምቀትንና ሥጋ ወደሙን ይቀበላሉ›› አለችው፡፡ ጌታችንም እንዲሁ ተገልጦላቸው ‹‹ወደ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አትናቴዎስ ሄደህ ከፍ ያችውን ማዕረግ ተቀብለህ የኢትዮጵያን ሰዎች አጥምቅልኝ፣ ነቢዩ ዳዊት ስለ እነርሱ ‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች› ብሎ ተናግሯልና›› አላቸው፡፡ ነገሥታቱ አብርሃንና አጽብሓ ነገረ ክርስቶስን እያሰቡ ስለ ጥምቀት ልጅነት ይጨነቁ ነበር፡፡ ከሊቀ ካህናቱም ጋር በዚህ ጉዳይ ሲጨዋወቱ ሊቀ ካህናቱ ስለ አቡነ ሰላማ ነገሯቸው፡፡ ነገሥታቱም አቡነ ሰላማን አስጠርተው ስለነገረ ክርስቶስ ምሥጢር እንዲያስረዷቸው ጠየቋቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ይወለዳል ካሉበት ጀምሮ የልደቱን፣ የትምህርቱን የጥምቀቱን፣ የስቅለቱን፣ የሞቱን፣ የትንሣኤውንና የእርገቱን ነገር ሌላውንም ሁሉ ተንትነው አስተማሯቸው፡፡ ሐዋርያትም በጌታ ተሾመው ዓለምን ዞረው ማስተማራቸውን እንዲሁ ተረኩላቸው፡፡ ነገሥታቱም ይህንን በሰሙ ጊዜ እጅግ ደስ ብሏቸው ፍሬምናጦስን ‹‹ወንድማችን ሆይ! ይህን ሥርዓት በሀገራችን እንድታስፋፋ›› አሏቸው፡፡ አባታችን ግን ‹‹ለዚህ የሚያበቃ ሥልጣን ያለው እንጂ ለእኔ አይቻለኝም›› አሉ፡፡ ነገሥታቱም ‹‹ይህን የሚችል ማነው?›› ብለው ቢጠይቋቸው ‹‹በእስክንድርያ ጳጳሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን የሚሾም አባት አለ አሏቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ነገሥቱ ወደ እስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቅዱስ አትናቴዎስ ደብዳቤ በመጻፍ ‹‹አባታችንና መምህራችን ሆይ! የምንጠይቅህን እሺ በጀ በለን ይኸውም ወደ ጽድቅ ጉዳና የሚመራንን ጳጳስ ሹምልን›› በማለት ብዙ ወርቅና ብር ገጸ በረከት አስይዘው ከብዙ ሊቃውንት ጋር ፍሬምናጦስን ወደ እስክንድርያ ላኳቸው፡፡
ከዚህም በኋላ አባታችን ከነገሥታቱ አብርሃና አጽብሓ ጋር ተማክረው ወደ እስክንድሪያ ሄደው በቅዱስ አትናቴዎስ እጅ በአገራችን ላይ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ታኅሳስ 18 ቀን ተሾሙ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ከሾሟቸውና ከመረቋቸው በኋላ ለአቡነ ሰላማና አብረውት ለነበሩ ሊቃውንት መጻሕፍተ ብሉያትን፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትንና ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ታቦተ ማርያምን፣ ታቦተ ሚካኤልንና ታቦተ ገብርኤልን አስይዘው ለነገሥታቱም ደብዳቤ ጽፈው ከብዙ ገጸበረከት ጋር በታላቅ ክብር ሸኟቸው፡፡ ቅዱሳን የሚሆኑ ሁለቱ ነገሥታትም አቡነ ሰላማ ከእስክንድርያ ተሾመው መምጣቸውን በሰሙ ጊዜ ‹‹የኢትዮጵያ ሰዎች ሁላችሁ እስከ 40 ቀን ተሰብሰቡ›› ብለው አዋጅ አስነገሩ፡፡ አባታችንንም በደብረ ሲናም ሄደው አገኟቸውና ከዚያች ቀን ጀምሮ ሕዝቡም ሁሉ እስከ 40 ቀን ድረስ ተጠመቁ፡፡ በዚያችም ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያች በደብረ ሲና አገር ላይ ወረደና ሕዝቡን ሁሉ ባረኮ ተመልሶ ሲያርግ ከአባ ሰላማ በቀር ያየው አልነበረም፡፡ ወደ አክሱምም ሄደው ቅዱሳን ነገሥታቱም የአድባራት ሁሉ የበላይ የምትሆን የቅድስት ጽዮንን ቤተ ክርስቲያን በወርቅና በዕንቊ ሠሯትና አባ ሰላማ ባርከው ቀደሷት፡፡ ታቦተ ጽዮንም ከድንኳን ወጥታ ማንም ካህን ሳይሸከማት አብርሃና አጽብሓ ወዳሠሩላት ቤተ መቅደስ ራሷ በመንፈስ ቅዱስ ገብታ ተገኘች፡፡
አባታችን በእመቤታችንም በዓለ ዕረፍት ጥር 21 ቀን በውስጧ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀድሱ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በግራ በቀኝ እየተራዷቸው እርሳቸውም ከምድር ሦስት ክንድ ከፍ ብለው ሥርዓተ ቅዳሴውን ፈጽመው ለነገሥታቱና ለሕዝቡም ሁሉ አቆረቧቸው፡፡ የዚያን ዕለትም እጅግ ታላቅ በዓልን አደረጉ፡፡
እነዚህም ቅዱሳን ነገሥታት ትምህርተ ወንጌልን እየሰጡ በአክሱም ቤተ መንግሥታቸው ሳሉ ከዕለታት አንደኛው ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ በአክሱም ‹‹ማይ ኰኩሐ›› በሚባል ተራራ ላይ ቁሞ አብርሃ ወአጽብሓን ጠርቶ ‹‹በዚህች ቦታ ላይ ቤተ መቅደሴን አንጹልኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ቦታው ባህር ላይ ነው በየት እናንጽልህ?›› አሉት፡፡ ጌታችንም በጥበቡ ከገነት ጥቂት አፈር አምጥቶ በባሕሩ ላይ ቢበትንበት ባሕሩ ደርቆ ሜዳ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን ‹‹ቤተ መቅደሴን በዚህ ሥሩ›› ብሏቸው ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ጌታችንም በቆመባት ዓለት ላይ የእግሩ ጫማ ቅርጽ እስከ አሁን ሳይጠፋ በግልጽ ይታያል፡፡ ቦታውም ከዚያ ወዲህ ‹‹መከየደ እግዚእ›› እየተባለ ይጠራል፡፡
አብርሃ ወአጽብሓ ከመንግሥት አስተዳደሩ ጋር ክርስትናንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በመላ ኢትዮጵያ በማዳረስ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል፡፡ ካህናትንና ዲያቆናትን ይዘው በመላ ኢትዮጵያ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ ሕዝቡን ሁሉ እያስተማሩ፣ ሃይማኖትን እያጸኑ፣ ሥርዓተ ጥምቀትን እያስፋፉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል፡፡ በሀገራችን በአራቱም አቅጣጫ ወንጌልን አስፋፍው ሕግ ሠርተዋል፡፡ የከበሩ ቅዱሳን ነገሥት አብርሃ ወአጽብሓ በእንዲህ ዓይነት ግብር ጸንተው በመኖር እግዚአብሔርንም ሰውንም አገልግለው ለሀገራችንም ብርሃን አብርተውላት ነው ያለፉት፡፡
ታላቁ አብርሃ በ364 ዓ.ም ጥቅምት 4 ቀን እሁድ ዕለት ዐረፉ፡፡ ከ13 ዓመት በኋላ ታናሹ አጽብሓ በ379 ዓ.ም ጥቅምት 4 ቀን ዐረፉ፡፡ ልደታቸውም ሆነ ሞታቸው አንድ ቀን ነው-የዕረፍታቸው ዓመቱ ይለያይ እንጂ፡፡ የተቀበሩበት ቦታም አንድ ነው፡፡ የንግሥና ስማቸው ኢዛናና ዛይዛና ይባላል፡፡


በዚችም ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሐዋርያ ቅዱስ ሐናንያ በሰማዕትነት አረፈ ። ይህም ቅዱስ በሐዋርያት እጅ ለደማስቆ አገር ኤጲስቆጶስነት ተሾመ እርሱም ክብር ይግባውና ጌታችን በደማስቆ ጐዳና ተገልጦለት ለወንጌል ትምህርት በጠራው ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን ያጠመቀው እርሱ ነው ።
እርሱም አስቀድሞ ለግብሪል ወገኖች አስተማረ ብዙዎች በሽተኞችን አዳናቸው ብዙ ሰዎችንም ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት መለሳቸው ።
ከዚህም በኋላ ስሙ ሉቅያኖስ የሚባል መኰንን ያዘው በምድር ላይ ደሙ እንደውኃ እስከሚፈስ ድረስ ገረፈው ጐኖቹንም በብረት በትሮች ሠነጣጠቀ ደረቱንም በእሳት መብራቶች አቃጠለ ። ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ አውጥተው በደንጊያ ይወግሩት ዘንድ አዘዘ በዚህም ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ።


ዳግመኛም በዚህች ቀን አቡነ በርተሎሜዎስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ልጆች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ ያመነኮሷቸውና የሾሟቸውም እርሳቸው ናቸው፡፡ የቆባ፣ የጠጠርና የኮረም ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመው በብዙ ድካም አገልግለዋል፡፡ ጻድቁ ደብረ ሊባኖስን የሚያጥኑበት ተራቸው በወርሃ ጳጉሜ ነበር፡፡
ወሎ ራያ ውስጥ ያለችውን ጥንታዊቷንና ባለታሪኳን ደብረ ዘመዳን የመሠረቷት ይህ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ሁልጊዜ ሰዓታትና ማኅሌት በማይታጎልባት በዚህች ጥንታዊ ገዳም ውስጥ ትገኛለች፡፡ እጅግ በርካታ ቅርሶችም ይገኙባታል፡፡ በአካባቢዋም ዘብ ሆነው የሚጠብቋት በርካታ የዱር አራዊት ይገኛሉ፡፡ ጻድቁ በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ ኖረው በሰላም ዐርፈዋል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages