"የራስን የሥራ ድርሻ ጠንቅቆ ካለማወቅ የሚመነጭ ድፍረት የተሞላበት ተግባር የህግና የሥርዓት ባለቤት ከሆነች የቤተ ክርስቲያን ልጆች የማይጠበቅ ነው" የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ዛሬ መስከረም ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ፡፡
ጉባኤው በየዓመቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤያትን ተከትሎ ህግና ሥርዓትን ያልጠበቁ አቤቱታዎች፣ የተቃውሞና የድጋፍ ሰልፎች እንዲሁም አድማዎችን በማካሔድ ቤተ ክርስቲያንን እና ቅዱስ ሲኖዶሱን የማይመጥኑ ተግባራትን በተመለከተ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተለይም የጥቅምቱን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መቃረብን ተከትሎ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኙ አንዳንድ አድባራትና ገዳማት በኩል ከህግና ሥርዓት ውጪ የሆኑ የድጋፍና የተቃውሞ አድማዎች እየተካሔዱ መሆናቸውን ጉባኤው ደርሶበታል ተብሏል።
በተጨማሪም ይህ አይነቱ ድርጊት ከቤተ ክርስቲያን ክብር ጋር የማይሄድ፣ ቤተ ክርስቲያንን የማይመጥን፣ የራስን የሥራ ድርሻ ጠንቅቆ ካለማወቅ የሚመነጭ ድፍረት የተሞላበት ተግባር የህግና የሥርዓት ባለቤት ከሆነች የቤተ ክርስቲያን ልጆች የማይጠበቅ ነው ሲል ገልጿል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ህግ ሠርታ እና ሥርዓት ዘርግታ ሥራዎችን የምታከናውን ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሚከናወኑ ሹመትና ሽረቶች ሁሉ በሥርዓትና በህጋዊ መንገዶች እንጂ በአድማ፣ በድጋፍና በተቃውሞ ፊርማዎች ተጽእኖ እንዳልሆነ ግልጽ መሆን ይኖርበታል በማለትም አሳስቧል።
ስለሆነም በቅዱስ ሲኖዶስ የአገልግሎት ድርሻ ገብቶ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ፊርማ የቤተ ክርስቲያንን ክብር የማይመጥን ተግባር በመሆኑ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው ታውቆ በዚህ ዙሪያ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጉባኤው ወስኗል።
በዚህም ካህናት፣ ሠራተኞችና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር የማይመጥን ድርጊት ከሚፈጽሙ ወገኖች ራሳቸውን በማራቅ አገልግሎታቸውን በተረጋጋና በሰከነ መንገድ እንዲያከናውኑ አሳስቧል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አንዳንድ አድባራት እና ገዳማት የሚከናወኑ የሰበካ ጉባኤያት ምርጫዎች በህግና በስርዓት መከናወን ሲገባቸው ከቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ ቃለ ዓዋዲ ውጭ ምርጫዎች እየተካሔዱ ከመሆኑም በላይ የአገልግሎት ጊዜያቸው የተጠናቀቀ የሰበካ ጉባኤ አባላትም በቀላጤ ደብዳቤ የአገልግሎት ጊዜያቸው ሲራዘም ይታያል።
ስለሆነም የጥቅምት ፳፻፲፭ ዓ.ም ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል ተለዋጭ መመሪያ እስከሚሰጥ ድረስ አድባራትና ገዳማቱ በቃለ ዓዋዲው መሰረት የሰበካ ጉባኤ ምርጫ የሚካሔድበትን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንዲቆዩ ሲል በጉባኤው ተወስኗል። ዘገባው የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment