የ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርከ መክፈቻ መልዕክት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, October 23, 2022

የ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርከ መክፈቻ መልዕክትጥቅምት ፲፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
*ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት
ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ
ስብከት ሊቀ ጳጳስ፡-
* ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና
ጸሐፊ እና በሰሜን አሜሪካ የኒዮርክ እና
አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፡-
*ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ
አባላት፡- 

 
በአጠቃላይ በዚህ መንፈስ ቅዱሳዊና ሐዋርያዊ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፡-
የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉ ስለሆነች ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለመምከርና ለመወያየት ስለ ሰበሰበን ቅዱስ አምላካችን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡
“ወሑሩ ባሕቱ ኀበ አባግዕ ዘተኃጒላ እምቤተ እስራኤል" ነገር ግን ከቤተ እስራኤል ወገን ወደ ጠቦት በጎች ሂዱ” [ማቴ፲፥፮፡]
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሥጋ ሰብእ እንዲገለጥ ያደረገው ዓቢይ ምክንያት፣ የጠቦትን በጎች ለመፈለግ እንደሆነ ከሚያስረዱ ትምህርቶች አንዱ ይህ የጌታችን አስተምህሮ ነው ፡፡
የጌታችን አገላለፅ ለጊዜው ቤተ እስራኤልን ብቻ የሚመለከት ቢመስልም በዚያ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ግን አልነበረም፡፡
ይህም “ወብየ ካልአትኒ አባግዕ እለ ኢኮና እምዝንቱ ዐፀድ ወኪያሆንሂ ሀለወኒ ኣምጽኦን ዝየወይሰምዓኒ ቃልየ ወይከውና አሐደ መርዓተ ለአሐዱ ኖላዊ፡-"ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛልድምፄንም ይሰማሉ። አንድም መንጋ ይሆናሉ"እረኛውም አንድ ብሎ ባስተማረው ትምህርት ይታወቃል፡፡
ከዚህ አንፃር ቤተ ክርስቲያን የቆመች በዚህ ዓለም ለሚገኙ በጎች ሁሉ እንደሆነ እንገነዘባለን" ግልገሎቼን ጠብቅ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን ጠብቅ በማለት በቅዱስ ጴጥሮስ በኩል የነገረንም ይህንን የሚያስረግጥ ነው"እኛም በየጊዜው የምናካሄደው ሐዋርያዊ ሲኖዶስ ይህንን አደራ ለመወጣት ነው፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በረጅሙ ታሪኳ ለሕዝባችንና ለሀገራችን ብዙ መልካም ነገርን አውርሳለች& በአንጻሩ ደግሞ ብዙ የተጋድሎ መከራን ተጋፍጣለች፡፡
በዘመኑ ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችን ዙርያ መለስ አካሏ በተቃራኒ ነገር የተከበበ ቢሆንም፣ እጅግ በሚያስገርምና በሚያስደንቅ ሁኔታ ራሷን በመከላከል እስካሁን ዘልቃለች።ይህንን ዓለምን ያስደነቀ ታሪኳን የማስጠበቅና የማስቀጠል ኃላፊነት አሁንም በቅዱስ ሲኖዶስና በምእመናኗ ጫንቃ ላይ ያረፈ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ያሉ አሉታዊ ገጽታዎችን በንቃት ማየት፣ መከታተልና መፍትሔንበበበ እያስቀመጡ መስራት የዚህ ዓቢይ ጉባኤ ኃላፊነት መሆኑ ላፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡
ጌታችን “አንሥኡ አዕይንቲክሙ ወነጽሩ በሐውርቲክሙ” ብሎ እንዳስተማረን በውስጥም፣ በውጭም በዙርያ ጥቀቀምጥም ሁሉ እየሆነና እየተቃጣ ያለው ፈተና በአጠቃላይ፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ስጋት ላይ እንዳይጥል በጋራም ሆነ በተናጠል በንቃት መከታተል ያስፈልጋል፡፡
ሁሉም እንደሚመሰክረው ቤተ ክርስቲያናችን በሰው ሀብትም ሆነ በምጣኔ ሃብት ባላት ዓቅም በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ክፍለ አህጉር ብሎም በኦሪየንታሉና በምሥራቁ ኦርቶዶክስ ጭምር በግምባር ቀደም ወይም በመጀመሪያ የምትቀመጥ ናት፡፡
ይህንንም ደማቅ ታሪክ በዓለም የታሪክ መዝገብ ለማስመዝገብ የበቃችው ቤተ ክርስቲያናችን ባላት የረጅም ጊዜ ታሪክ በምድረ አፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ የክርስትና ሃይማኖትን ህላዌ ለማስከበርና ዘላቂ ለማድረግ በፈጸመችው ጠንካራና ውጤታማ ተጋድሎ የተገኘ ነው፡፡
ይህ ለሦስት ሺሕ ዘመናት ተጠብቆ የዘለቀውን የተጋድሎ ደማቅ ስኬት በዙሪያችን ሆነው በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ እይታ የሚመለከቱ ብዙ ናቸው፡፡
ይህንን ልዩ ሃብታችንና ታሪካችን አደንዛዥ በሚመስል ስልተ ሂደት እንዳንነጠቅ ጠንክረን መስራት ይገባናል& የቤተ ክርስቲያናችን ሰብአዊና ቁሳዊ ሀብታችንን አደራጅተን፣ አቀናጅተንና አዘምነን ለአጠቃላይ የሃይማኖታችን ጥበቃ ማዋል ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ቤተ ክርስቲያናችን የሃይማኖት፣ የቀኖና፣ የባህልና የሥርዐት እንከን የላትም በአስተዳደር ስልታችን ግን ገና ብዙ እንደሚቀረን ግልፅ ነው::
በመሆኑም ይህንን እውነት ከልብ ተቀብለን፣ ከዛሬ ጀምሮ ካሁን በፊት ከነበረው ይበልጥ ዛሬ ዘመኑ በሚጠይቀው ጥበብ የሀብታችን ተጠቃሚ ለመሆን፣ የሕዝበ ክርስቲያኑን ጥያቄ ለመመለስ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችንን ህልውና በቀጣይነት ዋስትና ባለው ድልድይ ለማሸጋገር በሐቅና በሐቅ በርትተን የምንሰራበት ጊዜ መሆን አለበት፡፡
ታድያ የምንመኘውና የምናልመው ሁሉ እውን ሊሆን የሚችለው ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ባለው የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር መልካም አስተዳደርን ስናሰፍን እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ መልካም አስተዳደር ካልተረጋገጠ እያኮረፈንና እየተወን ከሚሄድ በቀር ፍልሰተ ምእመናንን ማስቆምና ስንዝር የሚያህል ዕድገትን ማስመዝገብ አንችልም፡፡
ስለዚህ ቀጣዮቹ ዓመታት ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም አቅጣጫ መልካም አስተዳደርን የምታረጋግጥባቸው ዓመታት እንዲሆኑ በመወሰን የማስፈጸም ኃላፊነቱን መውሰድ አለብን፡፡
በሌላ በኩል መልካም አስተዳደር ያለ ፍትሕና ያለ ልማት የትም ሊደርስ አይችልምና ፍትሕ ይሰፍን ዘንድ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት በሀገር ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ ስራ እንዲጀምር ያላሰለሰ ጥረት ብናደርግ፣ የልማትን ጉዳይ በተመለከተም የቤተ ክርስቲያናችንን የሃብት ምንጮች አጥንቶ፣ ለይቶና የትግበራ ሂደታቸውን አመላክቶ የሚያቀርብልን ከፍተኛ ባለሙያዎች ያሉበት ግብረ ኃይል በማቋቋም ወደ ግዙፍ የልማት መርሐ ግብር ብንሸጋገር፣ የምእመናን ጥበቃና አገልግሎትም በተመሳሳይ ሁኔታ ልዩ ስልት እና ጥበብ ተቀምጦለት ምእመናንን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የምንጠብቅበትንና የምናበዛበትን የትኲረት አቅጣጫ ብናስቀምጥ፣ በአጠቃላይ ዳር እስከ ዳር እየተናበብን በመስራት ፈጣን ዕድገት የምናስመዘግብበትን ስልት ብንቀይስ፣ እግዚአብሔርና ምእመናን ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሹትን ማሟላት እንችላለን፡፡
ስለሆነም ጉባኤያችን በነኝህ ዙርያ በስፋትና በጥልቀት መክሮበት ወደ ተግባር ቢሸጋገር መልካም ነው እንላለን፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ሌላው በዚህ ዓቢይ ጉባኤ ትኲረት ሰጥተን መነጋገር ያለብን የሀገራችንን የሰላም ጉዳይ በተመለከተ ነው።መቼም ቤቱ እየተቃጠለ ዝም ብሎ የሚያይ ሰው ይኖራል ብለን አናስብም። ዛሬ የሁላችን ቤት የሆነች ሀገር በሰላም እጦት ከባድ ችግር ውስጥ ናት፡፡
በዚህ አስከፊ ጦርነት ሰውም፣ ንብረትም ቤተ ክርስቲያንም ክኛ እየተጐዱ ነው።እነዚህ ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገራችን ምርጥ ቤቶች ናቸው& ቤቶቹ ተቃጥለው ይለቁ ወይስ ምን እናድርግ;ነው ጥያቄው መልሱ ከቤቱ ቢሆን ምርጫችን ነው።ለማንኛውም ግን ቤተ ክርስቲያናችን ነገ የምትነቀፍበት፣ እኛም የምንገመገምበትና የምንተችበት ታሪክ አስቀምጠን እንዳናልፍ በብርቱ ልናስብበት ይገባል::
ከዚህ አኳያ የሀገራችንን ችግር የመፍትሔ አቅጣጫ በቅንነት፣ በገለልተኝነት፣ በማእከላዊነት እና በአቃፊነት መንፈስና እንደዚሁም፣ ሰላምንና አንድነትን፣ ዕርቅንና ይቅርታን ማእከል ባደረገ መንፈስ ብናየው ለቤተ ክርስቲያንም ለእኛም ይበጃል፡፡
በመጨረሻም
በሀገር ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነትና እሱን ተከትሎ ያንዣበበው የስጋት ደመና ወደ ባሰ ጥፋት እንዳይወስደን የሀገራችን ችግሮች በሙሉ በሰላማዊ ውይይት ይፈቱ ዘንድ የሚመለከታቸው ሁሉ ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ፣ በጦርነቱም ሆነ በድርቁ ምክንያት በረሃብና በበሽታ እየተጐዱ ላሉ ልጆቻችንም የምግብና የሕክምና አቅርቦት እንዲያገኙ ይደረግ ዘንድ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እያስተላለፍንና ቤተ ክርስቲያንም በዚህ ረገድ የበኩሏን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን እየገለፅን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የጥቅምቱ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተከፈተ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናበስራለን።
 
እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ !!
                  ወስብሐት ለእግዚአብሔር !!!
                               አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት ፲፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

 


No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages