ስንክሳር_ዘወርኀ ኅዳር 1 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, November 9, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ ኅዳር 1

 

ኅዳር 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
2.ቅዱሳን መክሲሞስና ባልንጀሮቹ (ሰማዕታት)
 
ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር
 
 
 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
 
ኅዳር አንድ በዚችም ቀን የጻድቁ የኢትዮጵያ ንጉሥ_ነአኵቶ_ለአብ መታሰቢያው፣ ቅዱሳን_መክሲሞስማንፍዮስ#ፊቅጦርና #ፊልጶስ በሰማዕትነት አረፉ።


ቅዱስ_ነአኩቶ_ለአብ_ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
ኅዳር አንድ በዚችም ቀን የጻድቁ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነአኵቶ ለአብ መታሰቢያው።
ሃገራችን ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ቅድስና ያላቸው ቅዱሳን ባለቤት ናት። በዘመኑ ያለን ወጣቶችም ሆነ ጐልማሶች ከቤተ ክርስቲያንና ከቅድስና ሕይወት ለምን እንደራቅን ስንጠየቅ ከምንደረድራቸው ምክንያቶች አንዱ ሥራችን ነው።
ነገር ግን ሥራው በራሱ ኃጢአት እስካልሆነ ድረስ በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ቢሆን ቅድስናን ማስጠበቅ እንደሚቻል አበው አሳይተውናል። ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም ከእነዚህ ቅዱሳን አንዱ ነው።
¤እርሱ ንጉሥ ነው። ግን ገዳማዊ ሕይወትን በቤተ መንግስቱ ውስጥ ያሳየ ጻድቅ ነው።
¤ሁሉ በእጁ ነው። እርሱ ግን ንጹሕና ድንግል ነው።
¤እርሱ የጦር መሪ ነው። ግን በእጁ ደም አልፈሰሰም።
¤እርሱን "ወደድንህ ሞትንልህ" የሚሉ ብዙ ሰዎች በአካባቢው ነበሩት። ለእርሱ ግን ፍቅር ማለት ክርስቶስ ነበር።
¤የሃገር መሪ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እንደ መሆኑ እጅግ ባተሌ (busy) ነው። ግን ደግሞ ለክርስትናው ጊዜ ያጣ ሰው አልነበረም።
እኛ ቤተ ክርስቲያንን "በሐኪ" ለማለት (ለመሳለም) እንኳ "ጊዜ የለኝም" ስንል እርሱ ግን አብያተ ክርስቲያናትን ይፈለፍል፣ ያንጽ፣ በክህነቱ ያገለግል፣ ማዕጠንት ያጥን፣ ለረጅም ሰዓትም ይጸልይ ነበር።
እኛ "ሥራ ውያለሁና ደክሞኛል" ብለን ከስግደት ስንርቅ እርሱ ግን ንጉሥ ሆኖ ሳለ ...ጦር በፊት በኋላ በቀኝና በግራ ተክሎ ይሰግድ ስለ ነበር ደሙ እንደ ውኃ በምድር ላይ ፈሷል። ይህንን ሁሉ ያደረገው ቅዱሱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ነአኩቶ ለአብ ነው።
 
ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በዛግዌ ሥርወ መንግስት ከነገሡ 11 ነገሥታት አንዱ ሲሆን ከመጨረሻውም ሁለተኛ ነው። እርሱን በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን የወለዱት ቅዱሱ ንጉሥ ሐርቤ (ገብረ ማርያም) እና መርኬዛ ናቸው። ዘመኑ ቅድስና በላስታ ዙሪያ የመላበት በመሆኑ ቅዱስ ሐርቤ ከመመነኑ በፊት ነበር ነአኩቶ ለአብን የወለደው።
እናቱ መርኬዛ እርሱን ልትወልድ ምጥ ተይዛ ሳለ ጀሮዋ ቅዳሴን ይሰማ ነበር። ቅዳሴው ሲጀመር የጀመራት ምጥ ድርገት ሲወርዱ (ሥጋ ወደሙ ሲሰጥ) ተፈታላትና ልጇን ተገላገለች። ሕጻኑን አንስታ ስትታቀፈው ዲያቆኑ ማቁረቡን ፈጽሞ "ነአኩቶ" እያለ ሲዞር ሰማችው።
እዚያው ላይም "ነአኩቶ ለአብ" (አብን እናመስግነው) ስትል ስም አወጣችለት። ወዲያው ግን አባቱ ቅዱስ ሐርቤ መንግስቱን ለቅዱስ ላሊበላ ሰጥቶ በርሃ በመግባቱ ቅዱሱ ሕጻን ወደ አጐቱ ላሊበላ ቤተ መንግስት ውስጥ ገባ።
የቅዱስ ላሊበላ ቤት ደግሞ በቅድስና ያጌጠ ነውና ከርሱና ከሚስቱ (ቅድስት መስቀል ክብራ) ሕጻኑ ነአኩቶ ለአብ ምናኔና ፍቅረ ክርስቶስን ተማረ። በዘመኑ ብዙ ሊቃውንት ስለ ነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በደንብ አጠና። ክህነት ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግልም እድሜው 30 ደረሰ።
በወቅቱ ቅዱስ ላሊበላና ባለቤቱ መስቀል ክብራ ልጃቸው ይትባረክ እያለ ንግሥናቸውን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አወረሱ። ቅዱሱ ነአኩቶ ለአብም ምን እንደሚሠራ ሲያስብ አንድ ነገር ተገለጠለት። ቤተ መንግስቱን እንደሚገባ ካደራጀ በኋላ በቤት ውስጥ አንድ ጉድጓድን በቁመቱ ልክ አስቆፈረ።
በውስጡም በ4 አቅጣጫ ጦሮችን ተከለባቸው። ድንግል ካህን ነበረና ቀን ቀን ሃገር ሲያስተዳድር ቅዳሴ ሲቀድስ በጾም ይውላል። ሌሊት ደግሞ ወዳስቆፈረው ቦታ ገብቶ ያለማቋረጥ እየጸለየ ይሰግዳል።
ወደ ምድር ሲሰግድ በፊቱ ያለው ጦር ይወጋዋል። ቀና ሲል ደግሞ የጀርባው ይቀበለዋል። እንዲህ እያለ የፈጣሪውን ሕማማት ይካፈላል። በተለይ ዐርብ ዐርብ ሲሆን ደሙ፣ እንባውና ላበቱ ተቀላቅሎ ይፈስ ነበር። እርሱ መስቀሉን ተሸክሞ ጌታውን ይከተል ዘንድ መርጧልና።
ከተጋድሎው ጐን ለጐን ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አብያተ ክርስቲያናትንም ያንጽ ነበር። በተለይ በ1211 አካባቢ ያነጻት አሸተን ማርያም ልዩ ናት። እርሷን ካነጸ በኋላ ከቤተ መንግስቱ በደመና ሠረገላ ተጭኖ እየሔደ ያጥናት ይቀድስባትም ነበር።
ታዲያ አንድ ቀን አጥኖ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ብዙ ሥውራን ቅዱሳን መቅደሱን ከበው ተመለከተ። እርሱም "ወገኖቼ! ከወዴት መጣችሁ?" ቢላቸው "መዐዛ እጣንህን አሽተን መጣን" ሲሉ መለሱለት። በዚህ ምክንያትም እስከ ዛሬ ድረስ "አሽተን (አሸተን) ማርያም" ስትባል ትኖራለች።
ዛሬ ታቦቱ ያለበት ገዳሙም በእርሱ የታነጸ ሲሆን እጅግ ተአምረኛ ቦታ ነው። ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የነገሠ በ30 ዓመቱ ነው። ለ40 ዓመታት በእንዲህ ያለ ቅድስና ኑሮ 70 ዓመት ሞላው። በዚህ ጊዜም ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ እርሱ ዘንድ መጣ። ሰላምታንም ሰጠው።
"ወዳጄ ነአኩቶ ለአብ! አንተ ስለ እኔ ፍቅር ለ40 ዓመታት መከራን ተቀብለሃልና ሞት አያገኝህም። ክፍልህ ከነ ኤልያስ ጋር ነውና። የሚያከብርህን አከብረዋለሁ። ደጅህን የሳመውን፣ ይህ ቢያቅተው በሩቁ ሆኖ በአድናቆት የተመኘህን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እምርልሃለሁ" አለው።
ቀጥሎም "ይሕች ቤት አንተ ስትደማ እንደኖርክባት እርሷም እስከ ምጽዓት ድረስ ለመታሰቢያህ ስትደማ ትኑር" አለው። እነሆ ዛሬም ድረስ ከመቅደሱ ጠበል ይንጠበጠባል። ለዚህም ደግሞ እኛ ኃጥአን ምስክሮች ነን። ሳይገባን የቅዱሱን ደጅ ተመልክተናልና።
ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም የዚህን ዓለም ተጋድሎውን ፈጽሞ ወደ ብሔረ ሕያዋን መላእክት ወስደውታል። የተሰወረበትን ዕለት ስንክሳር ሕዳር 1 ሲያደርገው አንዳንድ መዛግብት ደግሞ በ3 ነው ይላሉ። በዙፋኑም ላይ የአጐቱ የላሊበላ ልጅ አፄ ይትባረክ ተተክቷል።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages