ጥቅምት 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ)
3.ቅድስት ማርያም (እናቱ)
4.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
5.አባ አብርሃም ገዳማዊ
6 ቅዱስ ይስሐቅ ንጉሥ
ወርኃዊ በዓላት
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
2.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
3.አባ ሣሉሲ ጻድቅ
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሠላሳ በዚህች ቀን ወንጌልን የጻፈ ሐዋርያው ቅዱስ_ማርቆስ የተወለደበት ነው፣ የመጥምቁ_ዮሐንስ ቅድስት ነፍሱ ከተቆረጠች ራሱ ጋራ በግልጽ የታየችበት ነው፣ በገድል የተጸመደ ቅዱስ_አባት_ባሕታዊ_አብርሃም ያረፈበት ነው።
ጥቅምት ሠላሳ በዚህች ቀን ለእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት አለቃ የሆነ ወንጌልን የጻፈ ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ የተወለደበት ነው።
የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አርስጦቡሎስ ነው እርሱም ከአምስቱ አገሮች የሆነ የእናቱም ስም ማርያም ነው እርሷም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ተጽፋለች እርሱም አስቀድሞ ስሙ ዮሐንስ ነው። በግብረ ሐዋርያት ማርቆስ በተባለ በዮሐንስ እናት ቤት ሐዋርያት ይጸልዩ ነበር ተብሎ እንደ ተጻፈ። እርሷም ባለጸጋ ነበረችና የዮናናውያንን የሮማይስጥን የዕብራይስጥን ትምህርት ለልጅዋ ለማርቆስ አስተማረችው።
በአደገም ጊዜ በርናባስ ወንጌልን ለመስበክ ከጳውሎስ ጋራ ሲሔድ ይዞት ሔደ በእነርሱም ላይ የሚደርስባቸውን መከራ አይቶ በጵንፍልያ ከተማ ሳሉ ትቷቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
ሐዋርያትም በተመለሱ ጊዜ የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን አሕዛብ እንደ ተመለሱ እግዚአብሔርም በእጆቻቸው ላይ ድንቅ ተአምራትን እንዳደረገ ተናገሩ። ይህ ብላቴና ማርቆስም ከእርሳቸው ስለ መለየቱ አዘነ ተጸጸተ።
ከዚያም አብሮአቸው ሊሔድ ፈለገ አስቀድሞ ትቷቸው ስለተመለሰ ጳውሎስ ሊአስከትለው አልወደደም በርናባስ ግን ወሰደው አጎቱ ነውና። በርናባስም ከአረፈ በኋላ ወደ ሮሜ አገር ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ሒዶ ለእርሱ ደቀ መዝሙሩ ሆነ በዚያም ቅዱስ ጴጥሮስ የተረጐመለትን ወንጌልን ጻፈ በሮሜ አገርም አስተማረበት። ከዚያም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝና በሐዋርያትም ትእዛዝ ወደ እስክንድርያ አገር ሔደ። በውስጥዋም የከበረ ወንጌልን አስተማረ ደግሞም በአፍራቅያና በአምስቱ አገሮች በርቃ በሚባልም አገር ወደ እስክንድርያ ከተማ በገባ ጊዜ ጫማው ተቆረጠ።
በዚያም በከተማው መግቢያ ጫማ ሰፊ ነበረ። ቅዱስ ማርቆስም እንዲሰፋለት ለርሱ ሰጠው ሲሰፋም ጣቱን ወግቶ ሰነጠቀው ከእርሱም ደም ፈሰሰ በዮናኒም ቋንቋ ኢታስታዖስ አለ ትርጓሜውም አንድ እግዚአብሔር ማለት ነው። ቅዱስ ማርቆስም ስሙን የምትጠራው አውቀኸው ነውን አለው እንጠራዋለን እንጂ አናውቀውም አለ።
እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ አባታችን አዳም ትእዛዙን እንደተላለፈ የጥፋት ውኃም እንደ መጣ ሙሴንም እንደላከውና እስራኤልን ከግብጽ እንዳወጣቸው ሕግንም እንደ ሠራላቸው ናቡከደነጾርም ወደ ባቢሎን ማርኮ እንደወሰዳቸውና ከሰባ ዓመት በኋላ ወደ አገራቸው ኢየሩሳሌም እንደ ተመለሱ ክርስቶስ ሥጋ በመልበስ ወደ ዓለም ስለ መምጣቱ ነቢያት ትንቢት እንደ ተናገሩ ያስተምረው ዘንድ ጀመረ።
ከዚያም በኋላ ወደ ምድር ምራቁን ትፍ ብሎ ጭቃ አድርጎ ጣቱን ቀባው ወዲያው ዳነ በጌታችንም አመነ። ያም ሰፊ ስሙ አንያኖስ ነው። ቅዱስ ማርቆስንም ወደ ቤቱ ወስዶ ልጆቹን ዘመዶቹንም ወደ ርሱ አቀረበ እርሱም አስተምሮ አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው።
በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሰዎች በበዙ ጊዜ የቅዱስ ማርቆስን ዜና ሰምተው የአገር ሰዎች ሊገድሉት ተሰበሰቡ እርሱም አንያኖስን ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሹሞ ልጆቹን ቄሶችና ዲያቆኖች አድርጎ ከዚያም ወደ በርቃ ወደ አምስቱ አገሮችም ወጥቶ አስተማረ። በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው በእርሳቸውም ዘንድ ሁለት ዓመት ኖረ ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው።
ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ተመለሰ ምእመናንም ተጨምረው በዝተው በታወቁ ቦታዎች ሁሉ በባሕሩም ዳር በላሞች መካበቢያ በሚባለውም አብያተ ክርስቲያን ሠርተው አገኛቸው።
ከሀድያንም የከበረ ሐዋርያን ይገድሉት ዘንድ በብዙ ድካም ፈለጉት እርሱም አምስቱን አገሮች ሲጐበኝ በሥውር ወደ እስክንድርያ ከተማ ይገባ ይወጣ ነበር። በአንዲትም ዓመትም ከአምስቱ አገሮች ተመልሶ ሚያዝያ ዐሥራ ሰባት ቀን በመድኃኒታችን የትንሣኤ በዓል ወደ ቤተክርስቲያን ገባ ሕዝቡም ሁሉ በዙሪያው አሉ። ከሀድያንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው በአንገቱ ውስጥ ገመዶችን አድርገው በከተማው ሁሉ ጎተቱት። እነርሱም ገና እንደፍየል ሙክት እንጎትተዋለን እያሉ ይጮኹ ነበር ። በላሞች መካበቢያና በሀገሪቱ አደባባይ በከተማውም ዙሪያ በየቀኑ ሲጎትቱት ኖሩ።
ሌሊትም በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያት ጋራ በነበረበት አርአያ ሁኖ ተገለጠለት ሰላምታም ሰጥቶ አጽናናው ቃል ኪዳንም ሰጠው። እነሆ አንተ ከወንድሞችህ ሐዋርያት ጋር ተካከልህ አለው። እርሱም በልቡናው ፈጽሞ ደስ አለው። በማግሥቱም ሁለተኛ ገመዶችን በአንገቱ አድርገው በአገሮች ሁሉ ጎተቱት በቀኑም መጨረሻ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።
ከሀዲዎችም ታላቅ እሳትን አንድደው የቅዱስ ማርቆስን ሥጋ ከውስጡ ጨመሩ ። በክብር ባለቤት ጌታችን ፈቃድም ንውጽውጽታ ጨለማ ቀዝቃዛ ነፋስ መብረቅና ነጐድጓድ ሆነ። ፀሐይም ጨለመ ከሀዲዎችም ሸሹ ምእመናንም መጥተው የሐዋርያ ቅዱስ ማርቆስን ሥጋ ወሰዱ ምንም ጥፋት ሳይደርስበት ደኀና ሆኖ አገኙት በመልካም ልብስም ገንዘው በጥሩ ቦታ አኖሩት መታሰቢያውንም አደረጉ።
ዳግመኛም በዚህች ቀን የመጥምቁ ዮሐንስ ቅድስት ነፍሱ ከተቆረጠች ራሱ ጋራ በአየር ውስጥ እየበረረች 15 ዓመት ስታስተምር ከኖረች በኋላ በዐረቢያ ምድር በግልጽ ታይታለች፡፡
ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡- ሄሮድያዳ ልጅ ርጉም የሆነ ንጉሥ ሄሮድስን በዘፈኗ በጣም አድርጋ ስላስደሰተችው እርሱም በተራው ሊያስደስታት ፈለገና እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ይሰጣት ዘንድ በሕዝቦቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት እንዳይከዳት በፅኑ ቃልኪዳን ማለላት፡፡ እርሱም አስቀድሞ "የፈለግሽውን ጠይቂኝ፣ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁ ምን ላድርግልሽ?" እያለ በመሐላ ባላት ጊዜ በእናቷ ምክር የዮሐንስን አንገት ቆርጦ ይሰጣት ዘንድ ለመነችው፡፡ እርሱም ስለማሐላው የዮሐንስን አንገት እንድትቆረጥ አደረገ፡፡ በመጀመሪያም የሄሮድስ ወታደሮች ሠይፍ ይዘው የዮሐንስን አንገት ይቆርጡ ዘንድ ወደ መኅኒ ቤት ሲሄዱ ቅዱስ ዮሐንስም የሄሮድስ ጭፍሮች ሊገድሉት እንደመጡ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ስላወቀ ከጨለማው ቤት ውስጥ አንገቱን በመስኮት አውጥቶ እንደሚመቻቸው አድርጎ ጠበቃቸው፡፡ የንጉሡም ጭፍሮች የመጥምቁን ራስ በወጪት አድርገው ለንጉሣቸው ሄሮድስ ሰጡት፡፡ ሄሮድስም ለሄሮድያዳ ልጅ ሰጣት፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ ግን በወጪት ላይ ሆና ሕዝቦቹና የመንግሥቱ ታላላቅ ሰዎች እየሰሟት በየመኳንንቱ ፊት ንጉሥ ሄሮድስን "የወንድምህን የፊሊጶስን ሚስት ማግባት አይገባህም" እያለች መጀመሪያ ትዘልፈው እንደነበረው ሁሉ አሁንም ዘለፈችው፡፡ መዓዛዋም እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነበር፣ ዐይኖቹም እንደፀሐይ ያበሩ ነበር፡፡
የሄሮድያዳም ልጅ የመጥምቁን ራስ ወስዳ ለእናቷ ልትሰጣት ስትል ዐይኖቹ እንደፀሐይ ሲያበሩ ብታየው "ንጉሡን አትፈራውምን?" በማለት ተቆጣች፡፡ በመቀጠልም "እነዚህን ዐይኖቹን በወስፌ እያወጣሁ እጥላቸዋለሁ፣ ምላሱንም ደግመኛ እንዳይገሥጽ ቆርጨ እጥላቸዋለሁ" በማለት ፊቱን በጥፊ ለመምታት እጇን ስታነሣ ያንጊዜ የዮሐንስ ራስ ክንፍ አውጥታ በረረች፡፡ በአየር ላይ ሳለችም ዳግመኛ "የተረገምሽ ሄሮድያዳ የባልሽን ወንድም ሄሮድስን ማግባት አይገባሽም፣ ቀድሞ የምዘልፍሽ አሁንም የምዘልፍሽ እኔ ነኝ" እያለች የዮሐንስ ራስ የቤቱን ጣሪያ ሰንጥቃ እንደንሥር በአየር በራ ሄደች፡፡
ከዚህም በኋላ ለጥፊ የዘረጋቻቸው የሄሮድያዳ እጆቿ ከትከሻዋ እየተቆረጡ መሬት ላይ ወደቁ፤ እውነቷንም መሬት አፏን ከፍታ ዋጠቻት፡፡ ዘፋኟ ልጇም አብዳ የቤተ መንግሥቱን ዕቃ ሁሉ መሰባበር ጀመረች፡፡ የንጉሡ አንዱ ጭፍራም የሄሮድያዳን በእሳት እንደተለበለበ የግንድ እሳት የመሰለና የተቆረጠ እጇን አምጥቶ ለሄድሮስ ሰጠውና የሆነውን ነገረው፡፡ ንጉሡም ነገሩ እውነት መሆኑን ሄዶ ባየ ጊዜ በሀፍረት እጅግ ተሸማቀቀ፡፡ ዘፍና በማስደሰት የዮሐንስን ራስ እንዲያስቆርጠው ያደረገችው የሄሮድያዳ ሴት ልጅም አብዳ በቤተ መንግሥቱ ስትለፈልፍ አገኛት፡፡ ሄሮድስም መኳንንቶቹን "በቤተ መንግሥቴ የተደረገውን ይህን ነገር ለማንም አትንገሩ" ብሎ አማላቸው ነገር ግን ያበደችው የሄሮድያዳ ሴት ልጅ ራሷ ሄዳ ሄሮድስን "የወንድምህን የፊሊጶስን ሚስት ማግባት ፈጽሞ አይገባህም" እያለች በመኳንንቶቹ ፊት ገሠጸችው፡፡ ንጉሥ ሄሮድስም ይህን ቃል ከእርሷ በሰማ ጊዜ እጅግ ተናደደና "ቀደሞ ያልሆነ ሥራ ታሠራ በኋላ ደግሞ ምሥጢር ታወጣ ንሣ በሰይፍ ቁረጣት" ብሎ አንገቷን በሰይፍ አስቆረጣት፡፡ ሥጋዋንም ዓሣ አንበሪ ተቀብሎ ዋጣት፡፡ ሄሮድም የወንደሙን ሚስት ሲያገባ አስቀድሞ አግብቷት የነበረችውን ሚስቱን በግፍ አባሯት ነበር፡፡ እርሷም ይህንን ሄሮድስ ያደረሰባትን ግፍ ለአባቷ አርጣ ብትነግረው አባቷ ብዙ ጦር ሰብስቦ መጥቶ ምድረ ገሊላን በኃይል አፈራረሳት፡፡ የበላዩ ንጉሥ ቄሳርም የገሊላን መፍረስና መውድም ሲሰማ ምክንያቱን ቢጠይቅ ሄሮደስ ባደረገው ግፍ ምክንያት መሆኑን ነገሩት፡፡ ቄሳርም ሄሮድስን ከሥልጣኑ ሽሮ አጋዘውና በወህኒ ጣለው፡፡ ሄሮድስም በወህኒ ቤት ሳለ አብዶ ራሱን ስቶ የገዛ አካሉን እየነጨ እየበላ ቷ ብሎ ፈንድቶ ተልቶ ሸቶ እጅግ ክፉ አሟሟት ሞተ።
ከዚህም በኋላ ጌታችን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ራስ መለስ ብሎ እንዲህ በማለት ሥልጣን ሰጣት፡- "እነሆ መንፈስሽን በራስሽ ውስጥ አድርጌልሻለሁ በሰማይም የምትበሪበት እንደ ንሥር ክንፍ ሰጥቼሻለሁና እንደንስር በሰማይ እየበረርሽ በዓለም ሁሉ እየዞርሽ የሄሮድስንና የሄሮድያዳን ኃጢአት ግለጭባቸው፤ እስከ 15 ዓመት ድረስ ገቢረ ተአምራት የምታደርጊበት ኃይሌን መንፈሴን በእራስሽ ውስጥ አድርጌልሻለሁ" አላት፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ዮሐንስን "እኔም ከ3 ዓመት በኋላ ለአዳም የሰጠሁትን ተስፋ ፈጽሜ በሞቴ ወደ ሲኦል ወርጄ ነፍሳትን ከዲያብሎስ እጅ ማርኬ በ3ኛው ቀን ከሙታን ተለይቼ ተነሥቼ ወደ ባሕርይ ክብሬ ተመልሼ ወደ ሰማይ አርጌ ባባቴ ቀኝ በተቀመጥኩኝ ጊዜ ከ15 ዓመት በኋላ ርጉም ሄሮድስ ካስፈጃቸው ከትንንሾቹ ሕፃናት ጋራ ትሆን ዘንድ በአባቴ ፈቃድ እራስህን ተሸክመው ወደ አባትህ ወደ ዘካርያስ ያመጧት ዘንድ እኔ መላእክትን አዛቸዋለሁ፡፡ ዛሬ ግን ነፍስህን በእኔ ቀኝ ባባትህ በዘካርያስ አጠገብ አኑሬያታለሁ መንፈስህንም እስከ 15 ዓመት በእራስህ ውስጥ እንድትኖር አዝዣታለሁ፣ ሥጋህም ከነቢዩ ከኤልሳዕ ጋር እንዲቀመጥ አድርጌያለሁ" አለው፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን እንዳዘዛት የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እራስ እንደንስር በአየር ላይ እየበረረች የምታስተምር ሆነች፡፡ በምሥራቅ በኩል ሄዳ በዐረብ አገር ውስጥ በሰማይ ላይ ስታስተምር በዚህች ዕለት ጥቅምት 30 ቀን በግልጽ ታየች፡፡ ነጋዴዎች ድምጹዋን ሰምተውና አይተዋት እጅግ ተደስተው ገንዘባቸው ሁሉ ጥለው የቅዱስ ዮሐንስን እራስ ለመያዝ ሰውነታቸውን ብዙ አደከሙ፡፡ ነገር ግን ለመያዝ አልተቻላቸውም፡፡ ከዚህም በኋላ ከሰማይ "የምትያዝበት ጊዜ ስላልደረሰ ሰውነታችሁን አታድክሙ" የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣላቸው፡፡ መፈለጋቸውንም ተው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስም እራስ 15 ዓመት ስታስተምር ኖራ ሚያዝያ 15 ቀን በዐረብ ሀገር ዐረፈች፡፡ የታዘዙ ቅዱሳን መላእክትም መጥተው ከቅዱስ ዮሐንስ እራስ ከተባረኩ በኋላ በታላቅ ዝማሬ እያመሰገኑ የቅዱስ ዮሐንስን አንገት ወስደው በነቢዩ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ አብረው ቀበሯት፡፡ ቅድስትን ነፍሱንም እያመሰገኑ ወደ ሰማይ አሳረጓት፡፡ በዚያም በሥሉስ ቅዱስ ዙፋን ፊት ወድቃ ከሰገደች በኋላ አባቷ ዘካርያስንና እናቷ ኤልሳቤጥን እጅ ነሳቻቸው፡፡ ከዚህም በኋላ በ3ኛው ሰማይ ውስጥ ተቀመጠች፡፡ ጌታችን ሦስቱን ሰማየ ሰማያት ርስት ጉልት አድርጎ ሰጥቶታልና፡፡
በዚህች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር በገድል የተጸመደ ቅዱስ አባት ባሕታዊ አብርሃም አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚያመልኩ ናቸው በዚህም ዓለም ገንዘብ እጅግ ባለጸጎች ነበሩ።
ይህም ቅዱስ በአደገ ጊዜ የምንኵስናን ልብስ ሊለብስ ሽቶ በላዕላይ ግብጽ ወደሚገኝ ወደ ሀገረ አክሚም በመርከብ ተጭኖ ሔደ ወደ አባ ጳኵሚስም ደረሰ እርሱም የምንኲስና ልብስን አለበሰው በገድልም በመጸመድ ሥጋውን አደከመ በአባ ጳኵሚስም ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ሃያ ሦስት ዓመት ያህል በማገልገል ኖረ።
ከዚህም በኋላ በዋሻ ውስጥ ብቻውን ይኖር ዘንድ እንዲአሰናብተው አባ ጳኵሚስን ለመነው እርሱም ፈቀደለት ዓሣ የሚያሠግሩበትን መረብ የሚሠራ ሆነ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ ሰውን አመጣለት ያም ሰው መረቡን ሽጦ ምግቡን አተር ይገዛለታል የተረፈውንም ለድኆች ይሰጣል የምግቡም መጠን ሁልጊዜ ማታ ማታ አንዲት እፍኝ ከጨው ጋር በውኃ የራሰ አተር ነው።
እንዲህም እየተጋደለ በዚያች ዋሻ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ ልብሱም ከገዳም ሲወጣ የለበሰው ከዘመን ርዝመት የተነሣ አርጅቶ ተበጣጠሰ ሥጋውንም በጨርቅ የሚሸፍን ሆነ። በየሁለት ዓመትም ወደ መነኰሳቱ ገዳም በመውጣት ሥጋውንና ደሙን ተቀብሎ ወደ በዓቱ ይመለስ ነበር። በዚያችም ዋሻ መኖር በጀመረባት ዓመት ሰይጣናት ወደ ርሱ በመምጣት ምትሐት እየሠሩ ተፈታተኑት እርሱ ግን ውሻን እንደሚአበር ሰው አበረራቸው።
ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ያን ሕዝባዊ ሰው ልኮ የአባ ጳኵሚስን ረድእ አባ ቴዎድሮስን አስጠራው በመጣም ጊዜ ሰግዶ ሰላምታ ሰጠው እንዲጸልይለትና በጸሎቱም እንዲአስበው ለመነው። ከዚህም በኋላ ሁለቱም በአንድነት ጸለዩ በዚያንም ጊዜ አባ አብርሃም በርከክ ብሎ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ አባ ቴዎድሮስም ወደ መነኰሳቱ ላከ እነርሱም መጥተው ከሥጋው በረከትን ተቀበሉ ሥጋውንም ወሰደው ከቅዱሳን ሥጋ ጋር በአንድነት አኖሩት።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።
No comments:
Post a Comment