ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 29 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, November 7, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 29

 

ጥቅምት 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ሳሙኤል ጻድቅ (ዘደብረ ወገግ)
2.አባ ጸቃውዐ ድንግል (ዘደብረ ዘኸኝ)
3.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሰማዕት
4.ቅዱስ ስቅጣር ሰማዕት
 
ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት
2.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
3.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
4.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
5.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ
6.ቅድስት አርሴማ ድንግል


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን አቡነ_ሳሙኤል_ዘደብረ_ወገግ አረፉ፣ በከሀዲው ንጉሥ በመክስምያኖስ ዘመን ቅዱስ_ድሜጥሮስ ዘተሰሎንቄ በሰማዕትነት አረፈ፣ የደብረ ዘኸኝ መምህር_ጸቃውዐ_ድንግል አረፈ።
 
አቡነ_ሳሙኤል_ጻድቅ (ዘደብረ ወገግ)
ጥቅምት ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ አረፉ፡፡
ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል እንድርያስና አርሶንያ ከሚባሉ የበቁ ደጋግ አባትና እናታቸው የተወለዱት በሸዋ ሀገረ ስብከት ቀድሞ ጽላልሽ ዛሬ ቡልጋ በሚባለው አውራጃ ነው፡፡ የወላጆቻቸው በጎ ምግባርና ሃይማኖት ቅዱስ ተክለሃይማኖትን ከደብረ ሊባኖስ አነሣስቶ በቤታቸው ሄደው እንዲስተናገዱ አድርጓል፡፡ ልጅ ስላልነበራቸው ያዝኑ ነበርና አቡነ ተክለሃይማኖትም በጸጋ እግዚአብሔር ተገልጾላቸው "እግዚአብሔር ጣዖታትን የሚሰብር፣ አጋንንትን በጸሎቱ የሚያርቅ፣ ሕዝብን ከኃጢአት በሽታ የሚያድን፣ ፈጣሪውን የሚያስደስት ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ" ብለው ትንቢት ነግረዋቸዋል፡፡ በትንቢቱም መሠረት አቡነ ሳሙኤል ሐምሌ 10 ቀን 1248 ዓ.ም ሲወለዱ መልካቸው በአራት ልዩ ልዩ ሕብረ መልክ እየተለዋወጠ አንድ ጊዜ እንደ በረዶ፣ አንድ ጊዜ እንደ እሳት፣ አንድ ጊዜ እንደ ልምላሜና ቢጫ ሆነው ታይተዋል፡፡
አቡነ ተክለሃይማኖትም በአባቱ እንድሪያስ በኩል የሥጋ ዘመዱ ሲሆኑ የመንፈስ ቅዱስም አባት ሆኑትና በ40 ቀን ክርስትና አንስተው ስመ ክርስትናውን "ሳሙኤል" አሉት፡፡ ትርጓሜውም "እግዚአብሔር ጸለቴን ሰማኝ" ማለት ነው፡፡ ከሕፃንነትም ጀምረው በምግባር በሃይማኖት ኮትኩተው አሳድገው ለዲቁና አብቅተው በኋላም አመንኩሰውታል፡፡ "ደብረ ወገግ" የሚለው ስያሜ የተገኘው ከመላእክት ነው፡፡ ድርሳነ ዑራኤል በሰፊው እንደሚያትተው ቅዱስ ዑራኤል የጌታችንን ደም በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ ዓለምን እየረጨ ሲቀድሳት የያዘውን ጽዋ በደብረ አስቦ ቆሞ ሳለ ነው ጨልጦ ያንጠፈጠፈው፡፡ ያንጊዜም ደብረ አስቦን የብርሃን ውጋጋን ሲያጥለቀልቀው መላእክትም "ቦታውን ደብረ ወገግ" (የብርሃን ተራራ) ብለው ሰይመውታል፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም "ወደፊት ፈጣሪውን የሚያገለግል ታላቅ ጻድቅ ይወጣባታልና ይህችን ቦታ ባርካት" ብሎ ቅዱስ ዑራኤልን በነገረው መሠረት ባርኳት እንዳረገ ድርሳነ ዑራኤል ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡
በቦታው ላይ ብዙ ጊዜ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ መታየቱን የበቁ ገዳማውያን ብቻ ሳይሆኑ በከተማ ያሉና ለመሳለም ወደ ቦታው የሄዱ ደገኛ ሰዎችም በዐይናቸው ያዩትን ይናገራሉ፡፡ በገዳሙ ዙሪያ እጅግ በጣም ብዙ ስውራን ቅዱሳን እንዳሉ በግልጽ ይታወቃል፡፡
ንጉሥ ዓምደ ጽዮን በክፉዎች ምክር የአባቱን ሚስት እንጀራ እናቱን በማግባቱ ምክንያት አቡነ ፊሊጶስ ጋር ሆነው ያወገዙትን የቅዱስ ተክለሃይማኖትን ወገኖች በየአውራጃው በተናቸው፡፡ አቡነ ፊሊጶስንም ደሙ በምድር ላይ እስከሚንጣለል ድረስ ገርፈው ወደነበረበት ቤቱ ወሰዱት፤ ፊሊጶስም በሚሄድበት ቦታ ላይ ሳይደርስ በመንገድ ሞተ፡፡ እንድርያስ፣ አኖሬዎስና ተክለ ጽዮን ሁላቸው ከተከታዮቻቸው ጋር በሰማዕትነት አርፈው እነስድስተይ በምትባል ምድር ተቀበሩ፡፡ ጳጳሱን አቡነ ያዕቆብንም ደሙ በምድር ላይ እንደውኃ እስኪወርድ ድረስ ገርፈው ወደ ሀገሩ እንዲሰደደ አደረጉት፡፡ ከዚያም በኋላ ሃይማኖቱ የቀና ደግ ጻድቅ ንጉሥ ዳዊት በነገሠ ጊዜ አባታችን ሳሙኤል ዘወገግን አገኘውና ‹‹መማጸኛ እንዲሆነኝ በእንድርያስ መቃብር ላይ ቤተክርስቲያን ሥራልኝ›› ብሎ ለመነውና የሩፋኤልን ቤተ ክርስቲያን ሠራለት፡፡ የእንድርያስንም አጽም ከመቅደሱ ስር አኖረው፡፡ ንጉሡም በዚያ በእንደግብጦን አውራጃ ሁሉ ላይ ፓትርያርክ አድርጎ ሾመው፡፡ በእነስድስታይ አገር ላሉ ሰዎችም ሁሉ አባት ሆናቸውና የመንፈስ ቅዱስ ልጁንም ታዲዮስን መምህርና አባት አድርጎ ሾመላቸውና ጽላልሽ ሄዶ እናቱን ይዞ ጽጋጋ ምድረ ወገግ ወስዶ አመነኮሳት፡፡
አቡነ ሳሙኤል ወደ ምድረ ርስቱ ደብረ ወገግ እየሄደ በዚያ ያሉ ልጆቹን እያጽናና ወደ እንደግብጦን አውራጃም እየተመለሰ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ፣ ወንጌልን እያስተማረ፣ ጣዖት አምላኪዎችን ወደ ክርስትና እየቀየረ፣ አጋንንትንና መመለኪያ ቦታዎቻቸውን እያጠፋ፣ አብያተ ክርስቲያናትን እያነጸ በብዙ ተጋድሎ ኖረ፡፡ በቅዱስ ገድሉ ውስጥ በጣም አስገራሚ በሆነ መልኩ እጅግ ብዙ ታሪኮች ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም ታሪኮች ውስጥ አቡነ ሳሙኤል በሀገራችን በጣም ብዙ ጣዖታትንና መመለኪያ ቤቶቻቸውን እያጠፉ፣ በሰዎች (በጠንቋዮች) ላይ፣ በዛፍና በባሕር ውስጥ አድሮ ይመለኩ የነበሩ ሰይጣናት አጋንንትን በሚያመልኳቸው ሰዎች ፊት እያጋለጡና እያዋረዱ ሰዎቹን አስተምረው አጥምቀው ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እየመለሷቸው ቤተክርስቲያንም በመሥራት ሐዋርያትን መሰሉ፡፡
ሰይጣን አድሮባቸው የነበሩ ጠንቋዮች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ዕቃዎችን ጻድቁ እየባረኩና እየቀደሱ ለቤተክርስቲያን መሥሪያና መጠቀሚያነት ያውሉት ነበር፡፡ ይህም ገና ሳይወለዱ በአቡነ ተክለሃይማኖት ትንቢት ተነግሮላቸው ነበር፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖት ‹‹ጣዖታትን የሚሰብር፣ አጋንንትን በጸሎቱ የሚያርቅ፣ ሕዝብን ከኃጢአት በሽታ የሚያድን፣ ፈጣሪውን የሚያስደስት ደግ ልጅ ይሆናል›› ብሎው ትንቢት እንደተናገሩላቸው አቡነ ሳሙኤል በሰዎች፣ በባሕርና በዛፍ ላይ እያደሩ ይመለኩ የነበሩ በጣም ብዙ አጋንንትን አጠፏቸው፡፡ ጠንቋዮችንም በውስጣቸው ካደረባቸው ሰይጣን እያላቀቁ የእግዚአብሔር አገልጋይ ያደርጓቸውና ያመነኩሷቸው ነበር፡፡
ጻድቁ አባታችን አባ ሳሙኤል ወንጌልን ዞረው በማስተማር ሐዋርያትን መሰሉ፣ ከዓላውያን ጋር ለመዋጋት ሰውነታቸውን ለሞት በመስጠት ሰማዕታትን መሰሉ፣ በጾም በጸሎት በስግደት በተጋድሎ ቅዱሳን ጻድቃንን መሰሉ፣ ይህን ኃላፊና ጠፊ ዓለም ንቀው በመተው ባሕታውያንን መሰሉ፣ በደልንና ኃጢአትን በማስተሠረይ ካህናትን መሰሉ፣ በጽሕናና በቅድስና መላእክትን መሰሉ እንደዚሁም ሌሎች ብዙ አስደናቂ ተአምራትንም በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ በትእምርተ መስቀል አድርገው እንደሙሴ ባሕርን ለሁለት ከፍለዋል፣ እንደ ኢያሱ በጸሎታቸው ፀሐይን አቁመዋል፡፡ አቡነ ሳሙኤል ተጋድሎአቸውን ፈጽመው ከጌታችን ታላቅ ቃኪዳን ተቀብለው በዚህች ዕለት በሰላም ዐርፈዋል፡፡

በዚህችም ቀን በከሀዲው ንጉሥ በመክስምያኖስ ዘመን ቅዱስ ድሜጥሮስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ ከተሰሎንቄ ሀገር ነው የከበረች የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ተምሮ በቀናች ሃይማኖት ጸና ሕዝቡንም የሚያስተምር ሆነ ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በመስበክ ብዙዎችን ከስሕተት መለሳቸው።
ስለዚህም በከሀዲው ንጉሥ ዘንድ ወነጀሉት ንጉሡም ወደርሱ እንዲአመጡት አዘዘ በንጉሡም ዘንድ አንድ ሥጋው የደነደነ የጸና ዐጥንቱ የሰፋ ሰው ነበረ ለሰዎችም ሁሉ እሱ ሁሉን የሚያሸንፍ እሱን የሚያሸንፈው የሌለ ይመስላቸው ነበር ንጉሡም ይወደዋል ይመካበታል እንዲህም ይል ነበር ይህን አካሉ ግዙፍ የሆነ ሰው ለሚያሸንፍ እኔ ብዙ ገንዘብ እሰጠዋለሁ።
በዚያንም ጊዜ ስሙ በስጥዮስ የሚባል አንድ ክርስቲያናዊ ሰው ተነሥቶ ወደ ቅዱስ ድሜጥሮስ ሔደ እንዲጸልይለትና በሥጋውም ሁሉ አሸናፊ በሆነ በመስቀል ምልክት እንዲአማትብበት ለመነው። እርሱም በላዩ ጸለየለት በሥጋውም ሁሉ ላይ በመስቀል አማተበበት ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሥ ገብቶ ከዚያ ሥጋው ግዙፍ ከሆነው ጋር ያታግለው ዘንድ ለመነው ንጉሡም ፈቀደለት በታገሉም ጊዜ ሥጋው የደነደነውን ያ ክርስቲያናዊ ሰው አሸንፎ ጣለው ንጉሡም አዘነ አደነቀም ሥጋው የደነደነውም በመሸነፉ አፈረ ተመክቶበት ነበርና።
ንጉሡም ስለዚህ ነገር ወታደሮቹን ጠየቀ እነርሱም ቅዱስ ድሜጥሮስ በላዩ እንደጸለየለትና በሥጋውም ላይ በመስቀል ምልክት እንዳማተበበት ነገሩት።
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ በቅዱስ ድሜጥሮስ ላይ እጅግ ተቆጣ ለአማልክትም ዕጣን እስከሚአሳርግ ድረስ እንዲገርፉት አዘዘ ንጉሡም እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉበት የንጉሡንም ትእዛዝ ባልሰማ ጊዜ እስከሚሞት በጦሮች እንዲወጉት ሁለተኛ አዘዘ።
ለቅዱስ ድሜጥሮስም ይህን ፍርድ ነገሩት ሃይማኖቱን ትቶ ለአማልክት የሚሰግድ መስሏቸው ነበርና ቅዱስ ድሜጥሮስም እኔ ከዕውነተኛ አምላክ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ አማልክት እሰግድ ዘንድ ዕጣን ማሳረግም አልፈቅድም የወደዳችሁትን አድርጉ አላቸው።
በዚያንም ጊዜ ንጽሕት ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ እስከ ሚሰጥ በጦር ወጉት ሥጋውንም በጣሉት ጊዜ ምእመናን ወደ ርሳቸው ወሰዱት የስደቱም ወራት እስከሚያልፍ በሣጥን አድርገው በቤታቸው ውስጥ ሠውረው አኖሩት።
የስደቱም ወራት ከአለፈ በኋላ እግዚአብሔር ገለጠውና ከዚያ አወጡት ያማረች ቤተ ክርስቲያንንም በተሰሎንቄ አገር ሠሩለት ሥጋውንም በውስጧ አኖሩ ድንቅ የሆነ ታላቅ ተአምርን እያደረገ እስከ ዛሬ አለ።
ሽታውም እጅግ ጣፋጭ የሆነ የሽቱ ቅባት ከእርሱ ይፈሳልና በእምነት የሚቀቡትን በሽተኞች ሁሉንም ያድናቸዋል። ይልቁንም በዕረፍቱ መታሰቢያ ቀን ከሌሎቹ ዕለታት ተለይቶ በብዛት ይፈሳል ከአውራጃው ሁሉ ብዙዎች ሰዎችም ይመጣሉ ከዚህም ቅባት ወስደው በማሰሮቻቸው ያደርጋሉ ይቺ ምልክትም እስከ ዓለም ፍጻሜ በመኖር እንደምትገኝ ደጋጎች ካህናት ምስክሮች ሆኑ።

አባ_ጸቃውዐ_ድንግል (ዘደብረ ዘኸኝ)
በዚህችም ቀን የተመሰገነና የከበረ የደብረ ዘኸኝ መምህር ጸቃውዐ ድንግል አረፈ። የዚህም ቅዱስ አባቱ ካህን ነው በጥበብና በበጎ ተግሣጽም አሳደገው መለኮታዊ ትምህርትን ሁሉ አስተማረው አድጎ አርባ ዓመትም በሆነው ጊዜ አባቱ ከአንድ ገዳም ውስጥ መነኰሰ ለመምህርነትም ተመርጦ በአባ ገብረ ማርያም ወንበር ላይ ተሾመ።
በዚያንም ጊዜ አባቱ ለልጁ የምንኵስና ልብስ አለበሰው ስሙንም ጸቃውዐ ድንግል ብሎ ሰየመው ከዚያችም ጊዜ ጀምሮ ያለ ማቋረጥ በጾም በጸሎት ብዙ በመስገድም ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ ። ከዚህም በኋላ አባቱ በአረፈ ጊዜ በአባቱ ፈንታ ተሾመ መንጋዎቹንም እንደ ሐዋርያት ሥርዓት በመልካም አጠባበቅ ጠበቃቸው።
በሌሊቱም ሁሉ ከባሕር ውስጥ ቁሞ ያድራል ከባሕሩም ሲወጣ ወዙ በምድር ላይ እስከሚንጠፈጠፍ ስግደትን ያዘወትራል ምግቡም ደረቅ እንጀራ ነው ጠጅ ወይም ጠላ አይጠጣም እግዚአብሔርም በእጆቹ ላይ ተአምራትን አደረገ በጐዳናም ሲጓዝ ከታናሽነቱ ጀምሮ ሒዶ የማያውቅ መፃጉዕን አገኘ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ የተጸለየበትን ውኃ በላዩ ረጨ በመስቀልም ምልክት አማተበው በዚያንም ጊዜ ዳነ ። ከዚህም ዓለም የሚለይበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ ጥቂት ታሞ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages