ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 1 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 1

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ አንድ በዚህች ቀን በእስራኤል ፊት #ነቢይ_ቅዱስ_ኤልያስ የተገለጠበት ነው፣ የእስራኤላዊ #ቅዱስ_ናቡቴ ዕርፍቱ ነው፣ ቅዱስ አባት የጋዛ #ኤጲስቆጶስ_ጴጥሮስ አረፈ፣ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_ዮሐንስ አረፈ።


በዚህችም በታኅሣሥ አንድ ቀን በእስራኤል ፊት ነቢይ ኤልያስ የተገለጠበት ነው። ይህ ቀናኢ ኤልያስ ከሌዊ ወገን የሆነ የአባቱ ስም ኢያስኑዩ የእናቱም ስሟ ቶና ነው።
ስለርሱም እንዲህ ተነገረ በተወለደ ጊዜ ብርሃንን የለበሱ አራት ሰዎች ሲሰግዱለትና ሕፃናት በሚጠቀለሉበት ጨርቅ ፈንታ በእሳት ሲጠቀልሉት አባቱ አየ። እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ይህን ለካህናቱ ነገራቸው እነርሱም ማደሪያው በብርሃን ውስጥ ይሆን፣ በቃሉም የሚቆርጥ ይሆን፣ ወይም እስራኤልን በሰይፍና በእሳት እየቀጣ ይገዛቸው ይሆን ተባባሉ።
በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብና በሚስቱ በኤልዛቤል በልጁም በአካዝያስም ዘመን ያደረገው የተአምራቱ ዜና በመጽሐፈ ነገሥት ተጽፎአል ። ወደ ሰማይ ያረገበት ዜናው ግን በጥር ወር በስድስት ቀን ተጽፎአል።
በኋላ ጊዜም ስለሚሆነው ሞቱ ራእይን በሕይወቱ ያየ ዮሐንስ ከኄኖክ ጋር እንደሚመጣና ሐሳዊ መሲሕን እንደሚቃወሙት ተአምራትንም እንደሚያደርጉ ተናግሮአል። ሁለቱ የዘይት ዕንጨቶች በምድር ላይም የተሾሙ በእግዚአብሔር ፊት የሚያበሩ ሁለት መብራቶች ናቸው አለ።
ከጠላቶቻቸውም ወገን ሊጣላቸው የወደደውን እሳት ከአፋቸው ወጥታ ታጠፋቸዋለች የሚጠሏቸው እንዲህ ይጠፋሉ። ትንቢት በሚናገሩበት ወራት በምድር ላይ ዝናም እንዳይዘንም ይዘጓት ዘንድ በሰማይ ላይ ሥልጣን አላቸውና ዳግመኛም ደምን ያደርጉት ዘንድ በውኃው ላይ ሥልጣን አላቸው የፈለጉትን ያህል በመቅሠፍቱ ሁሉ ምድርን ያስጨንቋታል።
ምስክርነታቸውንና ትንቢታቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከባህር የወጣው አውሬ ከእሳቸው ጋር ይጣላል ድል ነስቶም ይገድላቸዋል ። አስከሬናቸውንም ፍጥሞ በምትባል በታላቂቱ አገር ያስጥለዋል ይችውም በምሥጢር ሰዶም ግብጽ የተባለች ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።
አስከሬናቸውንም ሕዝብና አሕዛብ በሀገርም ያሉ ነገዶች ሦስት ቀን ተኩል ያዩታል አስከሬናቸውንም በመቃብር ይቀብሩት ዘንድ አያሰናብቱም። በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በእነርሱ ሞት ደስ ይላቸዋል እርስበርሳቸውም በደስታ እጅ መንሻ ይሰጣጣሉ እሊህ ሁለቱ ነቢያት በምድር በሚኖሩ ሰዎች መከራ አጽንተውባቸዋልና ይላሉ።
ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወት መንፈስ መጥታ ታድርባቸዋለች ተነሥተውም በእግራቸው ይቆማሉ በሚያዩዋቸው ላይም ጽኑ ፍርሀት ይሆናል።
ከወደ ሰማይ ቃል መጥቶ ወደዚህ ውጡ ይላቸዋል ከዚህ በኋላ ጠላቶቻቸው እያዩአቸው በደመና ያርጋሉ። በዚያችም ሰዓት ጽኑ መነዋወጥ ይሆናል የዚያችም አገር ዐሥረኛ እጅዋ ይጠፋል በዚያም መነዋወጥ ሰባት ሽህ ሰዎች ይሞታሉ የቀሩት ግን ደንግጠው የሰማይ አምላክን ፈጽመው ያመሰግናሉ።

በዚህችም ዕለት የእስራኤላዊ ናቡቴ ዕርፍቱ ነው ይህ ናቡቴ በሰማርያው ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን አትክልት ቦታ ነበረው። አክዓብም ናቡቴን ለቤቴ ቅርብ ነውና የተክል ቦታ ይሆነኝ ዘንድ ይህን የወይን ቦታህን ስጠኝ ከሱ የሚሻል ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ ዋጋውንም ትሻ እንደሆነ የዚህን የወይን ቦታህን ሽያጭ ወርቅ እሰጥሃለሁ የተክል ቦታ ይሁነኝ አለው።
ናቡቴም አክዓብን የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እንዲህ ያለ ነገር እግዚአብሔር አያምጣብኝ አለው። አክዓብም አዝኖ ሔደ ፊቱንም ተከናንቦ በመኝታው ተኛ እህልንም አልበላም። ሚስቱ ኤልዛቤልም ወደርሱ ገብታ እህል የማትበላ ምን ሆንክ የሚያሳዝንህስ ምንድን ነው አለችው። የኢይዝራኤል ሰው ናቡቴን የውይንህን ቦታ በዋጋ ሽጥልኝ ትወድም እንደሆነ ስለርሱ ፈንታ ሌላ ቦታ እሰጥሃለሁ ብዬ ብናገረው የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም ብሎኛልና ስለዚህ ነው ያዘንሁት አላት።
ሚስቱ ኤልዛቤልም ዛሬ እንዲህ የምታደርግ አንተ የእስራኤል ንጉሣቸው ነህን አሁንም ተነሥተህ እህል ብላ ራስህንም አፅና ልቡናህም ደስ ይበለው የኢይዝራኤል ሰው የናቡቴን ቦታ እኔ እሰጥሃለሁ አለቸው።
በአክዓብ ስም ደብዳቤ ጽፋ በማኅተሙም አትማ ያቺን ደብዳቤ ከናቡቴ ጋር ወደሚኖሩ ወደዚያ አገር አለቆችና ወደዚያች አገር ሽማግሌዎች ላከቻት።
የዚያችም ደብዳቤ ቃል እንዲህ የሚል ነው ጾምን ጹሙ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀምጡት የሐሰት ምስክሮችንም ሁለት ሰዎችን አስነሡበት እግዚአብሔርን ሰደብከው ንጉሥንም ረገምከው ብለው ይመስክሩበት ከከተማም ወደ ውጭ አውጥታችሁ በደንጊያ ውገሩትና ይሙት የሚል ነው። እንዲህም በግፍ ኤልዛቤል አስገደለችው።
በዚህችም ቀን ቅዱስ አባት የጋዛ ኤጲስቆጶስ ጴጥሮስ አረፈ። ይህም ሮሀ ከሚባል አገር ክብር ካላቸው ወገን ነው ይሾመውም ዘንድ ወላጆቹ ለንጉሥ ቴዎዶስዮስ ሰጡት እርሱ ግን ሹመትንና ክብርን ይጠላ ነበር በንጉሡም አዳራሽ ውስጥ በጾም በጸሎት በሰጊድ ተጠምዶ ኖረ ከርሱም ጋር የፋርስ አገር ሰማዕታት ሥጋ አብሮት አለ በዚያንም ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነው።
ከዚህም በኋላ ከገዳማት ወደ አንዱ ገዳም ሔዶ መነኰሰና ጽኑ ተጋድሎንም ተጋደለ የቅድስናውና የተጋድሎው ዜና በተሰማ ጊዜ ያለ ፈቃድ ወስደው ጋዛ በምትባል አገር በአውራጃዋም ሁሉ ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት። ስለርሱም የቊርባንን ቅዳሴ በሚቀድስ ጊዜ ኅብስቱን ሲፈትት ጻሕሉን እስቲ መላው ድረስ ብዙ ደም እንደሚፈስ ተነገረ።
የቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድን ሥጋ ወደርሱ ወስዶ ከኢየሩሳሌም ገዳማት በአንዱ ገዳም ኖረ በከሀዲው መርቅያን ዘመንም ወደ ግብጽ አገር ሸሸ የቅዱስ ያዕቆብም ሥጋ ከእርሱ ጋር አብሮ ነበር በዚያም ጥቂት ጊዜ ኖረ።
በአንዲትም ዕለት መሥዋዕት አዘጋጅቶ እርሱ ሲቀድስ ቁመው የነበሩ ሕዝብ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር በቅዳሴ ቊርባን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስም አልገሠጻቸውም የእግዚአብሔርም መልአክ አይቶ ወደታች ሊወረውረው ወዶ ከመካከላቸው አንሥቶ ያዘው ግን ታግሦ ተወው እርሱ እነርሱን መገሠጽ አፍሮ አክብሮአቸዋልና።
የከሀዲው መርቅያን ዘመን በተፈጸመ ጊዜ ወደ ፍልስጥዔም ምድር ተመልሶ አብያተ ክርስቲያናትን አጠናከረ ከግብጻዊ አባ ኢሳይያስም ጋር ተገናኘ ዜናውም በንጉሥ ዘይኑን ዘንድ በተሰማ ጊዜ ንጉሡም ሊያየው ወደደ እርሱ ግን አልወደደም ከዚህ ከኃላፊው ክብር እጅግ ይሸሽ ነበርና።
ከዚህም በኋላ ጋውር ከሚባል አገር ዳርቻ ደርሶ በዚያ ተቀመጠ የተመሰገነ የሰማዕታት ፍጻሜ የሆነ የሊቀ ጳጳሳት ጴጥሮስ በዓሉ በደረሰ ጊዜ የቊርባንን ቅዳሴ ሠራ ቅዱስ ጴጥሮስም ተገለጸለትና ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ ትመጣ ዘንድ ይጠራሃል አለው። ከዚያችም ቀን ወዲህ የዕረፍቱ ጊዜ እንደ ደረሰ አውቆ ሕዝቡን ጠራቸውና በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ አዘዛቸው ከዚህም በኋላ እጆቹን ዘርግቶ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

በዚህችም ቀን የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዮሐንስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳኛ ነው።
ይህም የከበረ ቀሲስ የሆነ የገምኑዲ አገር ሰው ነው በዘመኑም የቅዱሳን ሰማዕታት የሰርጊስና የባኮስ ቤተ ክርስቲያናቸው ተሠራች ዳግመኛም የአቡቂርና የዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በምስር መሰብሰቢያ ቅጽር አጠገብ ተሠራች ያነፃቸውም ስሙ እንድርያስ የሚባል እግዚአብሔርን የሚፈራ ያዕቆባዊ አንድ የግብጽ ሰው ነው። እርሱም ለመርዋን ልጅ ለገዢው ለንጉሥ አብደል ጸሐፊው ነው።
ይህም አባ ዮሐንስ የወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስን ቤተ ክርስቲያን በእስክንድርያ አገር በታወቀ ቃምስ በሚባል ቦታ የሠራ ነው።
በዚህ በንጉሥ አብደል ዘመንም ሦስት ዓመት ያህል ጽኑ ረኃብ ሆነ ይህም አባት ለድኆች ለጦም አዳሪዎችና ለችግረኞች የሚያስብ ሆነ በየሳምንቱም አራት ጊዜ ወርቅና ብር እንጀራም ይሰጣቸዋል አብዝቶ የሚራራ መመጽወትን የሚወድ በጎ ሥራዎችን የሚሠራ ነውና።
በዘመኑም ንጉሥ ይዜድ ሙቶ በርሱ ፈንታ መርዋን ነገሠ ይህም አባት በማርቆስ ወንበር ዘጠኝ ዓመት ኖረ በሰላምም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages