ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 30 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 30

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ሠላሳ በዚህች ቀን ጻድቁ #ንጉሥ_አፄ_ገብረ_መስቀል ዕረፍቱ ነው፣ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_አባት_አካክዮስ አረፈ፣ የቅዱሳን_ቆዝሞስና_ድምያኖስ ቤተ ክርስቲያናቸው የከበረችበት ነው።


አፄ_ገብረ_መስቀል_ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
ኅዳር ሠላሳ በዚህች ቀን ጻድቁ ንጉሥ አፄ ገብረ መስቀል ዕረፍቱ ነው።
ዐፄ ካሌብ የናግራንን ሰማዕታት ደም ተበቅሎ በድል ከተመለሰ በኋላ በአቡነ ጰንጠሌዎን እጅ መንኩሶ ገዳም ከገባ በኋላ ልጁ ገብረ መስቀል ነገሠ፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል በእውነትና በቅንነት ከነገሠ በኋላ አመራሩ ከአህጉሪቷ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ደረሰ፡፡ በዘመኑም ሁሉ መንግሥቱን የሚቃወም አልተነሣም፤ እርሱም ቤተ ክርስቲያንን ከመሥራት በቀር ወደ ጦርነት የሄደበት ጊዜ የለም፡፡ መንግሥቱንም ይባርክለት ዘንድ ሠራዊቱን ይዞ ወደ አባታችን ወደ አቡነ አረጋዊ ዘንድ ደብረ ዳሞ ሄደና በፊቱ ሰግዶ ‹‹አባቴ ሆይ! እኔን ባሪያህን፣ መንግሥቴንና ሕዝቤን ሠራዊቴንም ሁሉ ባርክ›› እያለ አጥብቆ ማለደው፡፡ አባታችን አረጋዊም ‹‹የአባቶችህን የዳዊትንና የሰሎሞንን መንግሥት የባረከ፣ የአባትህን የካሌብንም መንግሥት የባረከ እግዚአብሔር የአንተንም መንግሥት ይባርክ…›› ብለው ባረኩት፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሥ ዐፀ ገብረ መስቀል አቡነ አረጋዊን የት ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን እንደሚሠራ ጠይቋቸው ካሳዩት በኋላ ሲሠራ ሁለት ዓመት የፈጀበት ግሩም ቤተክርስቲያን ሠራላቸውና 12 የወርቅና የብር መስቀሎችን ጨምሮ ብዙ ንዋያተ ቅድሳቶችንና ሥጦታዎችን ሰጣቸው፡፡ ጳጳስም አስመጥቶ አስባረካትና ከማኅበረ በኩር ያመጣውን በወርቅ በብር የተለበጠች የእመቤታችንን ታቦት በውስጧ አስገባ፡፡ ጳጳሱና ንጉሡ ዐፄ ገብረ መስቀልም አቡነ አረጋዊን ‹‹ቀድሰህ አቁርበን›› ብለውት ይቀድስ ዘንድ በገባ ጊዜ መላእክት ሙቀት ያልተለየው ኅብስትና ወይኑን በጽዋ ለቅዳሴው የሚያስፈልገውንም ሁሉ ከሰማይ አወረዱለትና ቀድሶ ሲያበቃ ሁሉንም አቆረባቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ንጉሡ ዐፄ ገብረ መስቀል ከተራራው ጫፍ በሚወርድበት ጊዜ አባታችንን ‹‹ይህን የተራራውን መውጫ መሰላል ላፍርሰው ወይስ ልተወው?›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹ለልጅ ልጅ መታሰቢያ እንዲሆን ይህን ድንቅ ሥራ እያየ በፍጥረቱ ሁሉ አንደበት እግዚአብሔር ይመሰገን ዘንድ የደረጃውን መሰላል አፍርሰው፣ ነገር ግን ስለዘንዶው ጅራት ፋንታ ገመድ አብጅ›› አለው፡፡ ንጉሡም እንደታዘዘው የደረጃውን መሰላል አፈረሰውና ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፡፡ ጻድቁ ንጉሥ በዐፄ ገብረ መስቀል ካበረከተልን ትልቅ ውለታው ውስጥ አንዱ ዛሬ በዩኔስኮ የተመዘገበውን የመስቀል በዓልን በአደባባይ እንዲከበር ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ በዘመኑም ካህናቱ ሕዝቡ ሁሉ አደይ አበባ ይዘው ወደ አደባባይ በመውጣት በያሬዳዊ ዝማሬ የመስቀልን በዓል ያከብሩ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ብርሃኗ የሆነ ነገር ግን እርሷ እንደሚገባው መጠን ያላከበረችው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ጻድቅ ንጉሥ በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት የነበረ ነው፡፡ አብረውም ብዙ ታሪኮችን ፈጽመዋል፡፡ ገዳማትን ላይ በመዟዟር ቅዱስ ያሬድ ዜማን ሲያስተምር ንጉሡ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ያስፋፉና ቋሚ መተዳደሪያ ይሰጡ ገዳማቱን ያጠናክሩ ነበር፡፡ አቡነ አረጋዊ ደግሞ አብረው ምኩስናን ያስፋፉ ነበር፡፡ ሦስቱም ይህን ተግባራዊ እንዳደረጉ ለማሳያ ይሆን ይሆን ዘንድ ቅዱስ ያሬድ 3 ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት ያስተማረባትንና ዛሬም ድረስ ማስመስከሪያ የሆነችውን እጅግ ጥንታዊቷን ዙር አባ ጽርዓ አርያም አቡነ አረጋዊ ገዳምን እንደምሳሌ ማየት እንችላለን፡፡ አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ያሬድ በዘንዶ ታዝለው ዓምባው ላይ ከወጡ በኋላ ለንጉሡ ለዐፄ ገብረ መስቀል ደግሞ ተራራውን ባርከው ከፍለው መንገድ አበጅተውላቸው ወደ ዓምባው ወጥተው ሦስቱም በዚያ በጋራ ኖረው ብዙ መንፈሳዊ ሥራን ሠርተዋል፡፡
ጻድቁ ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል ከተስዓቱ ቅዱሳን ጋር ሆኖ ብዙ መንፈሳዊ ሥራን ሠርቷል፡፡ ሌላው በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ከነበሩት ቅዱሳት አንስት ውስጥ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዋነኛዋ ናት፡፡ ይኽችውም ቅድስት ከልጅነቷ ጀምራ በምግባር በሃይማኖት፣ በተጋድሎ በትሩፋት ያጌጠች ናትና ንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ገብረ መስቀል በሁለመናዋ የተመሰገነች መሆኗንና ዝናዋን ስለሰማ ‹‹በጸሎትሽ አስቢኝ›› በማለት ከአገልጋዮቹ ውስጥ እርሷን እንዲያገለግሏት 174 አገልጋዮችን ልኮላታል፡፡ ለነገሥታት ሚስቶች የሚደረገውን በሐርና በወርቅ የተሠሩ ልብሶችና ጫማ ልኮላታል፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል በጽድቅ ሕይወት እየተመላለሱ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የዋሉት ውለታ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ገርዓልታ አካባቢ ከዱጉም ሥላሴ በእግር የ2 ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ የቅዱስ ዐፄ ገብረ መስቀል አስደናቂ ፍልፍል ቤተ መቅደስ ይገኛል፡፡

በዚህች ቀን የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት አካክዮስ አረፈ።
ይህም ቅዱስ ቸር የሆነ ምሁር ነው አምላክ ያጻፋቸውንም መጻሕፍት ቃላቸውን አሳምሮ የሚተረጉም አዋቂ ነው በቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያንም ቅስና ተሹሞ ነበር ። በኬልቄዶንም ስብሰባ በሆነ ጊዜ ይህ አባት በጉባኤው ውስጥ በሆነው ሁሉ ደስ አላለውም ስለ እውቀቱም እንዲመጣ በፈለጉት ጊዜ እርሱ አሞኛል ብሎ ስለራሱ ምክንያት ሰጠ።
በእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት በቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላይ ስለ ደረሰበት ሥቃይ በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ሃይማኖታቸው የቀና እንደሆነ በሚያውቃቸው ባልንጀሮቹ በሆኑ በወዳጆቹ በወታደር አለቆችና በመኰንኖች ፊት የአንድነት ጉባኤያቸውን ረገመ ከእሊህም ክፉዎች ከጉባኤያቸው አንድ ያላደረገኝ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ አለ ።
የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት እንጣልዮስም በአረፈ ጊዜ ሃይማኖቱ የቀና እንደ ሆነ ስለ አወቁ የአገሩ ሊቃውንትና መኳንንት ይህን አባት አካክዮስን መረጡት። እርሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሆነው መጣላትና መለያየትን ያስወግዳል በማለት ተስፋ አድርገው በቁስጥንጥንያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።
በተሾመ ጊዜም ከብቻው እግዚአብሔር በቀር ማንም ሊአስወግደው የማይችል የጥልና የመለያየት የማይድን በሽታ አገኘ በልቡም አስቦ መጀመሪያ ራሴን አድን ዘንድ አይሻለኝምን አለ የቅዱሳን አባቶችን የቄርሎስንና የዲዮስቆሮስን የቀናች ሃይማኖት የተማረና በእርሷ የጸና መሆኑን እየታመነለት ከዚህም በማስከተል በክህነት ሥራ በመሳተፍ ይቀበለው ዘንድ ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ሦስተኛው ጴጥሮስ መልእክትን ላከ።
አባ ጴጥሮስም መልእክቱን በአነበበ ጊዜ ደስ ብሎት ታላቅ ክብርን አከበረው ያቺንም መልእክት በጉባኤ ፊት አስነባባት ከዚህም በኋላ አባ ጴጥሮስ ለመልእክቱ መልስ ጽፎ ከሦስት ኤጲስቆጶሳት ጋር ወደ አካክዮስ ላከ እነርሱም ወደ ቁስጥንጥንያ ከአባ አካክዮስ ዘንድ በደረሱ ጊዜ የአባ ጴጥሮስን ደብዳቤ ሰጡት እርሱም ሃይማኖታቸው በቀና በወዳጆቹና በሀገሩ መኳንንት ፊት አነበባት።
ሁሉም ደስ አላቸው አባ አካክዮስም እሊህን ኤጲስቆጶሳት ታላቅ ክብርን አከበራቸው ወደ አንድ ገዳምም ወሰዳቸው መሥዋዕትንም አዘጋጅቶ የቁርባን ቅዳሴ በመቅደስ ከእሳቸው ጋር አንድ ሆነ ከእሳቸውም ቡራኬ ተቀበለ።
ዳግመኛም ከአባ አትናቴዎስ፣ ከአባ ጢሞቴዎስ፣ ከአባ ቄርሎስ፣ ከአባ ዲዮስቆሮስ ከሃይማኖታቸው የሚተላለፈውን እያወገዘ ጻፈ ያቺንም የመልእክት ደብዳቤ ሰጣቸውና በፍቅር በሰላም አስናበታቸው።
ወደ አባ ጴጥሮስም በደረሱ ጊዜ አባ አካክዮስ ያደረገውን ሁሉ ነገሩት የመልእክቱንም ደብዳቤ ሰጡት እርሱም ደስ አለው ስሙንም በማዕጠንትና በቁርባን ጊዜ እንዲጠሩ አዘዘ።
ዜናውም በሮማውያን ኤጲስቆጶሳት ዘንድ በተሰማ ጊዜ አባ አካክዮስን ከቁስጥንጥንያ መንበር አሳደዱት በቀናች ሃይማኖት እንደ ፀና በደሴት ውስጥ አረፈ።

በዚችም ቀን የቅዱሳን ቆዝሞስና ድምያኖስ ቤተ ክርስቲያናቸው የከበረችበት ነው። እሊህም ቆዝሞስ፣ ድምያኖስ ወንድሞቻቸውም አንቲቆስ፣ ዮንዲኖስ፣ አብራንዮስ ድዮማ ከምትባል ከተማ ስለ እግዚአብሔር ልጅ የታነፀች ግምብ ከአለችበት አረምያ ከምትባል አገር ናቸው።
እናታቸውም ቴዎዳዳ እግዚአብሔርን የምትፈራና የምትራራ መጻተኞችንና ዶኆችን የምትወዳቸው የምትረዳቸው ናት አባታቸውም ከሞተ በኋላ ልጆቿን እያስተማረች አሳደገቻቸው ። እሊህም ሁለቱ ቆዝሞስና ድምያኖስ የሕክምና ጥበብን ተምረው በሽተኞችን ያለ ዋጋ የሚፈውሱአቸው ይልቁንም ድኆችን አብዝተው የሚረዷቸው ሆኑ።
ወንድሞቻቸው ሦስቱ ግን ወደ ገዳም ሒደው መነኰሱ በጾምና በጸሎትም ተጠመዱ ። ከአባ አጋግዮስ አደራ በአስጠበቀው በንጉሠ ቊዝ ልጅ ምክንያት ዲዮቅልጥያኖስ ክዶ የረከሱ ጣዖታትን በአመለከ ጊዜ በምእመናን ላይ መከራ ሆነ ገንዘብ ወዳጅ አጋግዮስ ብዙ ወርቅን ተቀብሎ የንጉሠ ቊዝን ልጅ ወደ አባቱ ልኮታልና ከዚህም በኋላ የንጉሠ ቊዝን ልጅ ዲዮቅልጥያኖስ ዳግመኛ ከጦር ሜዳ አግኝቶ ማረከው እርሱንም የንጉሡን ልጅ ሠውሮ አባ አጋግዮስን ጠራው ያንንም አደራ የሰጠውን የንጉሠ ቊዝን ልጅ እንዲአመጣ አዘዘው አጋግዩስም ሙቶ ተቀብሮአል ብሎ በሐሰት ተናገረ በዚያንም ጊዜ በመሠዊያው ፊት አማለው እሳትም ከሰማይ ወርዳ እንደምታቃጥለው ጠበቀ የእሳትም መውረድዋ በዘገየ ጊዜ ወርቅን በእሳት አቅልጦ አጠጣውና አቃጠለው ስለዚህም ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጣዖታትን አመለከ ።
ቆዝሞስና ድምያኖስ በሀገሩ ሁሉ ስለ ክርስቶስ እነርሱ እንደሚያስተምሩ ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ ወደርሱ እንዲአቀርቧቸው አዘዘ በደርሱም ጊዜ ለአገረ ገዢው ለሉልዮስ እንዲአሠቃያቸው ሰጠው ። እርሱም በብዙ ሥቃዮች ማሠቃየትን ጀመረ በእሳት የሚያቃጥልበት ጊዜ አለ በግርፋት የሚገርፍበትም ጊዜ አለ ሦስት ወንድሞችም እንዳሏቸው ሰምቶ እነርሱንም ወደርሱ አስመጣቸውና አምስቱንም በመኰራኲር ውስጥ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ። ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጨመሩዋቸው በውስጡም ሦስት ቀኖችና ሌሊቶች ኖሩ ያለ ጥፋትም በጤንነት ወጡ ዳግመኛም ከብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቻቸው እሳትን አነደዱ እግዚአብሔርም ያለ ጥፋት ጠበቃቸው።
መኰንኑም እነርሱን ማሠቃየት በሰለቸ ጊዜ ወደ ንጉሥ መለሳቸው ንጉሡም ዳግመኛ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው ቴዎዳዳ እናታቸውም የምታስታግሣቸው ንጉሡንና የረከሱ ጣዖቶቹን የምትረግም ሆነች።
በዚያንም ጊዜ አንገቷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትንት አክሊልንም ተቀበለች ሥጋዋ ግን በምድር ላይ ወድቆ ነበር ቆዝሞስም እንዲህ ብሎ ጮኸ የዚች አገር ሰዎች ሆይ ይችን አሮጊት መበለት ሥጋዋን አፈር አልብሶ ይሠውራት ዘንድ ከውስጣችሁ ርኅራኄ በልቡ ያደረበት የለምን የህርማኖስ ልጅ ቅዱስ ፊቅጦርም በሰማ ጊዜ ተደፋፍሮ ሥጋዋን ገንዞ ቀበራት።
ንጉሡም እነርሱን ማሠቃየት በሰለቸ ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። ከመከራውም ዘመን በኋላ ቤተ ክርስቲያን ተሠርታላቸው ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከእርሳቸውም ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages