ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 29 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 29

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ሃያ ዘጠኝ በዚች ቀን የአቡነ_እጨጌ_ዮሐንስ ዘጠገሮ ልደታቸው ነው፣ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን የቅዱሳን_ሰማዕታተ_ክርስቶስ መታሰቢያቸው ነው፣ የሰማዕታት መፈጸሚያ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_ጴጥሮስ በሰማዕትነት አረፈ፣ የሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ_ቀሌምንጦስ_ሐዋርያ በሰማዕትነት አረፈ።


ኅዳር ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን የአቡነ እጨጌ ዮሐንስ ዘጠገሮ ልደታቸው ነው።
ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ተወለዱ፡፡ አባታቸው ድላሶር እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል፡፡ ወላጆቻቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡ አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ ‹‹በምን አውቀኸኝ ነው?›› ብላ አቅፋ ሳመችውና ‹‹ከእንግዲ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 ትኖራለህ" ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡
ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዩሐንስ ለክርስቶስ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ 50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኃላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኩስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በድብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ አባ ዩሐንስ ወደ ተዘጋቸላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኃላ ይገኛል፡፡
ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው፡፡ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል፡፡ በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል፡፡ እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል፡፡ ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡
አባታችን በታላቀ ተጋድሎ ሣሉ ሰይጣን የሀገሩን ሰዎች በጠላትነት እንዲነሡባቸው አደረገ፡፡ ሰዎቹም አባታችንን እንዴት እንደሚያጠፏቸው ይማከሩ ጀመር፡፡ ሊገድሏቸው ፈልገው ቅድስናቸው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ፈሩ፡፡ ከዚኽም በኋላ ‹‹ለምን ከመንደራችን ከወንድ ያረገዘች ሴት ፈልገን እሳቸው አስረገዟት ብለን በሐሰት እንከሳቸው?›› ብለው ተማከሩ፡፡ ብዙ ወርቅና ብርም ለአንዲት ሴት ሰጥተው በሐሰት ከእርሱ አርግዣለሁ ብላ እንድትመሰክር አደረጓት፡፡ አባታችንም በሕዝብ ፊት በሐሰት ተከሰሱ፡፡ ጻድቁም ‹‹አንቺ ሴት ከእኔ ነው ያረገሽው?›› አሏት እርሷም ‹‹አዎ ከአንተ ነው ልትክድ ነው እንዴ?›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝነው ‹‹በአንቺና በእኔ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ›› ሲሉ ያች ሴት ወዲያው ለሁለት ተሰንጥቃ ሞተች፡፡ የአገሩ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ አባታችንም ምድሪቱን እረገሟት፡፡ ‹‹የተዘራው ዘር አይብቀልብሽ፣ የተተከለው አይፅደቅ፣ ብርድና ውርጭ ይፈራረቅብሽ›› ብለው እረግመዋት በደመና ተጭነው ወደ ሰሜን ጎንደር እስቴ ጉንደ ተክለተሃማኖት ሔዱ፡፡
አቡነ ዩሐንስ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እየተዘዋወሩ ያስተማሩ ሲሆን ከቅድስናቸው የተነሣ በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 የኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በይፋት ጠግሮ በዓለወልድ፣ በአፋር አዘሎ፣ በመንዝ ፍርኩታ ኪዳነምሕረት፣ በደብረ ሊባኖስ፣ በጎንድ ተክለ ሃይማኖት በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ አባታችን ከሰማይ መስቀል የወረደላቸው ሲሆን ዛሬም በገዳማቸው የሔደ ሰው በወረደው በእጃቸው መስቀል እየተዳበሰ ቆመው በጸለዩበት ባሕር በጠበላቸው ይጠመቃል፡፡ በተጨማሪም ይይዙት በነበረውም መቋሚያቸው በመዳበር በረከትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቆመው ከጸለዩበት ባሕር ውስጥ ደረቅ አሸዋ ይወጣል፡፡ አባ ዩሐንስ 500 ዓመት ከኖሩ በኃላ እረፍተ ዘመናቸው ሲደርስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከ15 ነቢያት፣ ከ12 ሐዋሪያት፣ ሄሮድስ ያስፈጃቸው ከመቶ አርባ አራት ሺ ሕፃናት፣ ከአብርሃም ከይስሐቅ፣ ከዕቆብ ጋር ሁሉንም ነገደ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ "ስምህን የጠራ ገዳምህን የረገጠ፣ መባ የሰጠ፣ ቤተ ክርስትያንህን የሠራ ያሠራ የረዳ፣ ገድልህን የሰማ ያሰማ ያስተረጎመ፣ መታሰቢያን ያደረገ እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለው፤ ንስሀ ሳይገባ አይሞትም፣ ልጅ መውለድ ባይችል እኔ ልጅ እሰጠዋለሁ፤ ገድልህን በቤትህ ያስቀመጠ እርኩስ መንፈስ፣ ክፉ አጋንንት ቸነፈር ወባ መልአከ ጽልመት አይነካውም፡፡ በገዳምህ መነኩሴ ቢቀበር በሰማይ ክንፍ አበቅልለታለሁ፤ አይሁድም አረማዊም ያላመነ ያልተጠመቀ በገዳምህ መጥቶ ቢያርፍ ይቅር እልልሃለሁ፣ እንደ መቃብሬ ጉልጎታ እንደተቀበረ አድርጌ እቆጥርልሃለሁ…" የሚል ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኃላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
ቅዱስ አባታችንም በ500 ዓመታቸው ሐምሌ 29 ቀን ዐርፈው በጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚገኘውን ይህንን ገዳም ጻድቁ ራሳቸው ናቸው የመሠረቱት፡፡ ነገር ግን የገዳሙን ስያሜ በአባታቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም አድርገውታል፡፡ አቡነ ዮሐንስ ካረፉ በኋላ በእርግማናቸው መሠረት በመንዝና በይፋት ብርዱ ድርቁ ስለበዛባቸው አንድ ብቁ ባሕታዊ ከበዓታቸው ወጥተው ‹‹በሐሜታችሁ ምክንያት እጨ ዮሐንስ ስለረገማችሁ ነው የእርሱን ዐፅም ካላመጣችሁ ብርዱ ውርጩ ድርቁም አይጠፋላችሁም›› አሏቸው፡፡ ሕዝቡም አባታችን በጉንድ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሩ ከ134 ዓመት በኃላ በቅዱሳን እየተመሩ ሄደው በሌሊት ግማሽ ዐፅማቸውን አምጥተው በሀገራቸው አምጥተው ስላስቀመጡ ብርዱና ውርጩ በመንዝ እየቀነሰላቸው መጥቷል፡፡ ዛሬም በሀገሩ ብርዱና ውርጭ ሲበዛ የጻድቁን ታቦት ሲያወጡ ውርጩ ይጠፋል፡፡ ጠገሮ በሚባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘው ጠበላቸው እጅግ አስደናቂ ነው፡፡
ግማሽ ዐፅማቸውን ከጉንደ ተክለሃይማኖት አምጥተው አርባ ሐራ መዳኒዓለም አጠገብ በላይ በፍሩክታ ኪዳነምሕረት መጋቢት 18 ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡ ምድሪቷም ተባረከች፣ የዘሩትንም አበቀለች፣ ውርጩም ብርዱም ቀነሰ፣ ዝናብ አልዘንብ ሲል ወይም ሰብል የሚጨርስ አንበጣ ሲመጣ ታቦታቸው ወጥቶ ምህላ ይያዛል። ወድያውም መቅሰፍት ይርቃል፣ ዝናብም ይዘንባል፡፡ ጻድቁ ደመናን፣ ጨረቃንና ፀሐይን በእጃቸው እየያዙ ይጸልዩ ነበር፡፡ በጠገሮ፣ በአዘሎ፣ በፍርኩታና በሌሎቹም ታላላቅ ቦታቦዎች ላይ በእያንዳንዱ ገዳም ሃምሳ ሃምሳ ዓመት በጸሎት ኖረው በአጠቃላይ በ500 ዓመታቸው ነው ያረፉት፡፡ ዐፅማቸው መንዝ ከአርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ ፍርኩታ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡

ኅዳር ሃያ ዘጠኝ በዚች ቀን በዚችም ዕለት በከሀዲው ንጉሥ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት የሞቱ የአርባ ሰባት አእላፋት መታሰቢያቸው ነው።
ቤተ ክርስቲያን ዛሬ (ኅዳር 29) የሁሉንም ሰማዕታት በዓል ታከብራለች። አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቅዱሱ ሊቅ) በመጽሐፈ ሰዓታት ሰማዕታትን:-
"መስተጋድላን ከዋክብት ብሩሃን።
ማኅትዊሃ ለቤተ ክርስቲያን።" ይላቸዋል።
በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሮም መንግስት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር። የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግስቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ:- ፋሲለደስ፣ ገላውዴዎስ፣ ፊቅጦር፣ መቃርስ፣ አባዲር፣ ቴዎድሮስ (ሦስቱም)፣ አውሳብዮስ፣ ዮስጦስ፣ አቦሊ ሌሎቹም ነበሩ።
ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ:- ማርታ፣ ሶፍያ፣ ኢራኢ፣ ታኡክልያ ሌሎቹም ነበሩ። ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር። ወቅቱ ከፋርስ፣ ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ (ሞተ)።
የሮም መንግስትም ባዶ ሆነች። ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር። ግን እነሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ።
በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪጳዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር። ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪጳዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው። ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው።
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም። የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው። ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው። ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች።
ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ። የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ። ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው። ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግስት እንምረጥ" አላቸው። ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ።
ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ ይጸልዩ ገቡ። ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር። ከሃዲውም ይህንን ሲያይ የልብ ልብ ተሰማው። ከድሮ ያሰበውንና ክርስቲያኖችን የማጥፋቱን እቅድ ሊፈጽም ምክንያት አገኘ።
አባ አጋግዮስ በሚባል መነኩሴ ምክንያት "አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ አብያተ ጣዖታት ይትረኀዋ" "ቤተ ክርስቲያኖች ይዘጉ ቤተ ጣዖቶችም ይከፈቱ" አለ። አጵሎን፣ አርዳሚስ የሚባሉ ጣዖቶችንም አቆመ።
በዚህ አዋጅ ምክንያትም የክርስቲያኖች ሰቆቃ ጀመረ። ምድር በደም ታጠበች፣ ቅዱሳኑ ቀባሪ አጡ፣ እኩሉ ተገደለ፣ እኩሉ ተቃጠለ፣ እኩሉ ታሠረ፣ እኩሉም ተሰደደ።
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈው በብራናና በብዕር አይደለም። ይልቁኑ እንደ ቀለም የሰማዕታት ደማቸው፣ እንደ ብዕር አጥንታቸው፣ ቆዳቸው እንደ ብራና ሆኖ ተጽፏል እንጂ። ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው።
ስለዚህም "ተጋዳዮች የሚያበሩ ኮከቦች፣ የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች" ተብለው እነሱ እየቀለጡ አብርተዋል። ሰማዕትነት በብሉይ ኪዳን የጀመረና እስከ ዳግም ምጽዐተ ክርስቶስም የሚቀጥል ቢሆንም "ዘመነ ሰማዕታት" የሚባለው ከ150 እስከ 312 ዓ.ም ድረስ ያለው ዘመን ነው።
በተለይ ግን ከ270ዎቹ እስከ 312 ዓ.ም ድረስ ያሉ ዓመታት እጅግ የከፉ ነበሩና የአርባ ሰባት ሚሊየን (47,000,000) ክርስቲያኖች ደም በምድር ላይ ፈሷል። የሰማዕታት ምሥጢራቸው ቃለ ወንጌል፣ የጌታ ስብከትና ሕይወት እንጂ ሌላ አይደለም። (ማቴ.10፥16, ማር.13፥9, ሉቃ.12፣4, ዮሐ.16፥1, ሮሜ.8፥35, ራዕይ.2፥9)
የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ነው።

በዚህች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ ሰባተኛ የሆነ የተመሰገነና የከበረ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ጴጥሮስ በሰማዕትነት አረፈ እርሱም የሰማዕታት መፈጸሚያ በመሆን ነው።
የዚህ አባት ወላጅ አባቱ በእስክንድርያ አገር ሊቀ ካህናት ነው ስሙም ቴዎድሮስ ነው የእናቱም ስም ሶፍያ እነርሱም እግዚአብሔርን እጅግ የሚፈሩ ጻድቃን ናቸው ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም። በሐምሌ ወር በአምስት የቅዱሳን ሐዋርያት የጴጥሮስና የጳውሎስ በዓላቸው በሆነ ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች ያማሩ ልብሶችን ከልጆቻቸው ጋር ተሸልመው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ የዚህ ቅዱስ እናት ሶፍያ አየች። በከበረ መሠዊያውም አንጻር ቁማ ልጅን ይሰጣት ዘንድ በብዙ እንባ ክብር ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነችው።
በዚያችም ሌሊት ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ ተገለጡላትና እነሆ ክብር ይግባውና እግዚአብሔር የተባረከ ልጅን ይስጥሽ ዘንድ ልመናሽን ተቀበለ ስሙንም ጴጥሮስ በዪው አልዋት ከዚህም በኋላ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎናስ እንድትሔድና እንዲጸልይላት አዘዙዋት።
እርሷም ወደ አባ ቴዎናስ ሔዳ ጸለየላት ከዚህም በኋላ ፀንሳ ይህን ቅዱስ ወለደችው ስሙንም ጴጥሮስ ብላ ሰየመችው ዕድሜውም ሰባት ዓመት ሲሆነው ነቢይ ሳሙኤል እንደ ተሰጠ ለሊቀ ጳጳሳት ቴዎናስ ሰጠችው። ለርሱም ተወዳጅ ልጅን ሆነው አስተምሮም አናጉንስጢስነት ሾመው ከዚህም በኋላ ዲቁና ደግሞም ቅስና ሾመው በሊቀ ጵጵስናው ሥራ የቤተ ክርስቲያንም በሆኑ በብዙ መልካም ሥራዎች ሁሉ የሚረዳው ሆነ።
የሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎናስ የሚያርፍበት ጊዜ ሲደርስ በእርሱ ፈንታ አባ ጴጥሮስን ሊቀ ጵጵስና እንዲሾሙት ኤጲስ ቆጶሳቱንና ካህናቱን አዘዛቸው እርሱም በሞተ ጊዜ ይህን አባ ጴጥሮስን ሾሙት እርሱም ለአብያተ ክርስቲያን ካህናትን ሾመ።
እንዲህም ሆነ በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በአንጾኪያ ከተማ አንድ መስፍን ነበረ የሚስቱም ስም ሣራ ይባላል እርሱም ከከሀዲው ንጉሥ ጋር ተስማማ እርሷ ግን በሃይማኖቷ ጸናች በአንድነትም ሳሉ ሁለት ልጆችን ወለደች። ነገር ግን በአንጾኪያ አገር የክርስትና ጥምቀትን ልታስጠምቃቸው አልተቻላትም ስለዚህም ወደ እስክንድርያ ትሔድ ዘንድ ልጆቿን ይዛ በመርከብ ተሳፈረች።
በጉዞ ላይም ሳሉ ጽኑዕ የሆነ ማዕበል ተነሣባቸው እርሷም ልጆቿ የክርስትና ጥምቀትን ሳይጠመቁ እንዳይሞቱ ፈራች ጡቷንም በምላጭ ሠንጥቃ በደሟ ግምባራቸውን በመስቀል ምልክት ቀብታ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቀቻቸው በዚያንም ጊዜ ታላቅ ጸጥታ ሆኖ ከመሥጠም ዳኑ።
ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰች ጊዜ ያጠምቃቸው ዘንድ ልጆቿን ከሀገር ልጆች ጋር ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ አቀረበች ይህም አባት ያጠምቃቸው ዘንድ ወደ ልጆቿ በደረሰ ጊዜ ውኃው እንደ ሰም ሁኖ ረጋ ወደ ሌሎች ሲሔድ ግን ይፈሳል ወደዚች ሴት ልጆች ሲመለስም እንደ ሰም የረጋ ይሆናል እንዲህም ሦስት ጊዜ አደረገ አደነቀም ከእርሷም ስለሆነው ነገር ጠየቃት እርሷም የባሕር ማዕበል እንደተነሣባት ጡቷንም ሠንጥቃ በደሟ የልጆቿን ግምባራቸውን እንደቀባችና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳጠመቀቻቸው ነገረችው። ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስም ሰምቶ እጅግ አደነቀ አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ትላለች እንዲህ ትሠራለች ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነው።
በዚህም አባት ጴጥሮስ ዘመን ከሀዲ አርዮስ ተነሣ ከክህደቱም ይመለስ ዘንድ ይህ አባት ብዙ ጊዜ መከረው ገሠጸው ቃሉንም ባልሰማው ጊዜ ረግሞ አወገዘው።
ከዚህም በኋላ የንጉሥን አማልክት እንዳያመልኩ በሁሉ ቦታ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደሚያስተምር ዜናውን ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ ስለዚህ ይዘው እብዲአሥሩት መልእክተኞችን ላከ። የሀገር ሰዎችም በአወቁ ጊዜ የንጉሥ መልእክተኞችን ይወጓቸው ዘንድ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ተሰበሰቡ።
ቅዱስ አባት ጴጥሮስም ስለርሱ ታላቅ ሁከት እንደሚሆን በአየ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሊሰጥ ወደደ ሕዝቡንም ሁሉ ወደርሱ አቅርቦ በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ አዘዛቸው አጽናንቶ አረጋግቶ ወደ ቤቶቻቸው እንዲገቡ አሰናበታቸው።
አርዮስም ቅዱስ አባት ጴጥሮስ ከዓለም በሞት እንደሚለይ በአወቀ ጊዜ ይህ አባት ጴጥሮስ ከውግዘቱ እንዲፈታው ያማልዱት ዘንድ አኪላስንና እለእስክንድሮስን ለመናቸው እነርሱም እንዲፈታው በለመኑት ጊዜ በውግዘት ላይ ውግዘትን ጨመረ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀደደ ልብስ ለብሶ እንዳየው ልብስህን ማን ቀደዳት ባለውም ጊዜ ልብሴን አርዮስ ቀደዳት እንዳለው አስረዳቸው። ይህም ማለት ከአባቴ ለየኝ ማለት ነው ሁለተኛም ከእርሱ ተጠበቁ በክህነት ሥራም አትሳተፉት እርሱ ለክብር ባለቤት ክርስቶስ ጠላቱ ነውና አላቸው ። አንተም አኪላስ ከእኔ በኋላ ሊቀ ጵጵስና ትሾም ዘንድ አለህ አንተም አርዮስን ትቀበለዋለህ ፈጥነህም ትሞታለህ አለው።
ከዚህም ነገር በኋላ ቅዱሳ አባት ጴጥሮስ ከንጉሥ መልክተኞች ጋር በሥውር ተማከረ በእሥር ቤት ከውስጥ ሲያንኳኳላቸው እነርሱ ወደ መስኮት እንዲቀርቡ እርሱም ራሱን ሊሰጣቸው ንጉሡ እንዳዘዛቸው ይፈጽሙ ዘንድ በዚያንም ጊዜ የወንጌላዊ ማርቆስ መቃብር ወዳለበት ከከተማው ውጭ ይዘው ወሰዱት በዚያም ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደሜ መፍሰስ ለጣዖታት አምልኮ መጨረሻ ይሁን ከሁሉ ዓለምም ይጥፋ ብሎ ጸለየ። ከሰማይም አሜን ይሁን ይደረግ የሚል ቃል መጣ።
ለዚያ ቦታም በአቅራቢያው የነበረች አንዲት ብላቴና ድንግል ይህን ቃል ሰምታ ተናገረች።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባት ጴጥሮስ ወታደሮችን የታዘዛችሁትን ፈጽሙ አላቸው በዚያንም ጊዜ የከበረች ራሱን ቆረጡ በድኑም ሁለት ሰዓት ያህል ቆመ ሕዝቡም ከከተማ ፈጥነው በመውጣት ወደ እሥር ቤት መጡ እስከ ነገሩአቸውም ድረስ የሆነውንም አላወቁም ነበር ከዚህም በኋላ የቸር ጠባቂያቸውን ሥጋ አንሥተው ወደ ከተማ አመጡ አክብረውም ገነዙትና ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አግብተው በወንበሩ ላይ አስቀመጡት።
ከዚህ አስቀድሞ በወንበሩ ላይ ሲቀመጥ ከቶ ማንም አላየውም በወንበርህ ላይ የማትቀመጥ ለምንድን ነው ብለው በጠየቁት ጊዜ እኔ የእግዚአብሔር ኃይል በወንበር ላይ ተቀምጦ አያለሁና ስለዚህ በዚህ ወንበር ላይ መቀመጥን እፈራለሁ ብሎ መለሰላቸው።
ግንዘቱንም አከናውነው ከተመረጡ ሊቃነ ጳጳሳት ከሥጋቸው ጋር ሥጋውን አኖሩ እርሱም በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር በሹመት የኖረው ዐሥራ አራት ዓመት ነው የተሾመውም ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ በሃያ ስድስት ዓመት ነው ከሥጋውም ብዙ ድንቅ ተአምር ተገለጠ።

በዚህች ቀን ለሮሜ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት የሆነ የሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ ደቀ መዝሙሩ ቀሌምንጦስ በሰማዕትነት አረፈ።
ይህም ቅዱስ ከመንግሥት ልጆች ወገን የሆነ ለሮም ንጉሥ የጭፍራ አለቃ ለሆነ ለቀውስጦስ ልጁ ነው ደጎች የሆኑ አባትና እናቱም ቅዱስ ጴጥሮስ የወንጌልን ትምህርት በሰበከ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ገንዘባቸውንም ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋት አድርገው ሰጡ።
ከዚህም በኋላ መኰንኑ ቀውስጦስ ወደ ንጉሥ ሒዶ በዚያው በዘገየ ጊዜ ወንድሙ የመኰንኑን የቀውስጦስን ሚስት ሊአገባት አሰበ እርሷም በአወቀች ጊዜ አባታቸው እስቲመለስ ወደ አቴና ሔዳ ጥበብን ታስተምራቸው ዘንድ ቀሌምንጦስንና ታናሽ ወንድሙን ይዛ በመርከብ ተሳፈረች።
በዚያንም ጊዜ ብርቱ ነፋስ በመንፈሱ ማዕበል ተነሥቶ መርከቡ ተሰበረ ቀሌምንጦስም በመርከቡ ስባሪ ተንጠለጠለ የባሕሩም ሞገድ ወደ እስክንድርያ አገር አደረሰውና በዚያ ጥቂት ቀኖች ኖረ። በዚያንም ወቅት የከበረ ሐዋርያ ጴጥሮስ ቃል ጠራውና ወደ እስክንድርያ ሀገር እንዲሔድ አዘዘው በሔደም ጊዜ በውስጥዋ የወንጌልን ቃል ሰበከ ከዚህ ከቅዱስ ቀሌምንጦስ በቀር ከሀገር ሰው አንድ እንኳን ያመነ የለም እርሱ የቅዱስ ሐዋርያ ጴጥሮስን ትምህርት በሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የክርስቶስን ጥምቀትን ተጠመቀ።
ሐዋርያ ጴጥሮስም የጌታችንን የመለኮቱን ምሥጢር ለሚያመልኩትም የሚሰጣቸውን ብልጽግናውንና ክብሩን በስሙም ኃይል ድንቅ ተአምራትም እንደሚደረግ ገለጠለት። ከዚችም ዕለት ጀምሮ ቀሌምንጦስ ቅዱስ ጴጥሮስን ተከተለው ደቀ መዝሙሩም ሆነ እርሱም የሐዋርያትን ገድላቸውን ከዐላውያን ነገሥታትና መኳንንት የደረሰባቸውን ሥቃይ ሁሉ ጻፉ።
ከዚህም በኋላ በብዙ አገሮች ውስጥ አስተማረ ሐዋርያትም በጉባኤ ተነጋግረው የሠሩአቸውን የሥርዓት መጻሕፍትን ለርሱ ሰጡት። ከዚህም በኋላ በሮሜ አገር ሊቀ ጵጵስና ተሾመ በትምህርቱም ከሰዎቿ ብዙዎችን እግዚአብሔርን ወደማወቅ መለሳቸው።
ስለርሱም ከሀዲ ንጉሥ ጠራብሎስ ሰምቶ ጭፍራ ልኮ ወደርሱ አስመጥቶ ክርስቶስን ክደህ ለአማልክት ስገድ አለው ትእዛዙንም ባልሰማ ጊዜ በዚያ ያሠቃዩት ዘንድ ወደ አንዲት አገር ሰደደው እርሱ በላዩ እንዳይነሡበት ከሀገር ሰዎችና ከዘመዶቹ የተነሣ ፈርቷልና መኰንኑንም ጽኑዕ ሥቃይን እንዲአሠቃየው አዘዘው።
የዚያችም አገር መኰንን በመርከቦች ውስጥ የሚኖር እግሮች ያሉት ከባድ ብረት በአንገቱ ውስጥ አንጠልጥሎ ከባሕር ውስጥ አሠጠመው ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ወንጌልን እንደ ሰበኩ ሐዋርያትም በመንግሥተ ሰማያት የምስክርነት አክሊልን ተቀበለ።
እንዲህም ሆነ አንዲት ዓመትም ስትፈጸም ባሕሩ ተገልጦ እንደተኛ ሁኖ የቅዱስ ቀሌምንጦስ ሥጋ በጥልቁ ባሕር ውስጥ ታየ። እርሱም ሕይወት ያለው ይመስል ነበር ሰዎችም ገብተው ከእርሱ ተባረኩ የከበረ የደንጊያ ሣጥንም አምጥተው ሥጋውን በውስጡ አድርገው አንሥተው ከባሕር ውስጥ ሊአወጡት ፈለጉ ግን ከቦታው ሊአንቀሳቅሱት አልቻሉም ከባሕር ውስጥ መውጣትን እንዳልፈለገ አወቁ በዚያም ትተውት ወደ ቤቶቻቸው ሔዱ። ከዚህም በኋላ በመታሰቢያው ቀን በየዓመቱ ያቺ ባሕር ከቅዱስ ቀሌምንጦስ ሥጋ ላይ የምትገለጥ ሆነች ምእመናንም ሁሉ ገብተው ከእርሱ ይባረካሉ መታሰቢያውንም በማድረግ በዓሉን ያከብራሉ ከዚያም በኋላ ወጥተው ወደቤታቸው ይገባሉ።
ከአስደናቂዎች ተአምራቶቹም ከተጻፉት ያዩ ይህን ተናገሩ በአንዲት ዓመት ከሥጋው ሊባረኩ በገቡ ጊዜ የቅዱስ ቀሌምንጦስ ሥጋው ካለበት ሣጥን ዘንድ ሲወጡ ታናሽ ሕፃን እንደረሱ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚወዱት ቅዱሳኑ ክብራቸውን ከርሱ የተቀበሉትንም ጸጋ ይገልጥ ዘንድ ወዷልና ። ወላጆቹም ከወጡ በኋላ ሕፃኑን ፈለጉት ግን አላገኙትም ባሕሩም በላዩ ተከድኖ ነበር ሙቶ በባሕር ውስጥ ያሉ አራዊት የበሉት መስሏቸው አለቀሱለት እንደ ሥርዓቱም በማዕጠንትና በቁርባን ቅዳሴ መታሰቢያውን አደረጉ።
በዳግመኛውም ዓመት ያቺ ባሕር ተገልጣ እንደ ልማዳቸው ገቡ ሕፃኑንም በሕይወት ሁኖ በቅዱስ ቀሌምንጦስ የሥጋ ሣጥን ዘንድ ቁሞ አገኙት በዚህ ባሕር ውስጥ አኗኗርህ እንዴት ነበር ምን ትበላ ነበር የባሕር አራዊትስ እንዴት አልበሉህም ብለው ጠየቁት። እርሱም ቅዱስ ቀሌምንጦስ ያበላኝ ነበር እግዚአብሔርም በባሕር ካሉ አራዊት ይጠብቀኝ ነበር ብሎ መለሰ ሰምተውም እጅግ አደነቁ በቅዱሳኑና ስለ ከበረ ስሙ ደማቸውን በአፈሰሱ ሰማዕታት የሚመሰገን ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages