ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 2 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 2

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ሁለት በዚህች ቀን ቅዱሳን_ሠለስቱ_ደቂቅ (አናንያ፣ አዛርያ፣ ሚሳኤል) መታሰቢያ ነው፣ በላይኛው ግብጽ ከሚኖሩ ሰዎች ወገን የሆነ ቅዱስ_አባት_አባ_ሖር አረፈ።


ቅዱሳን_ሠለስቱ_ደቂቅ (አናንያ፣ አዛርያ፣ ሚሳኤል)
ታኅሣሥ ሁለት በዚህች ቀን ናቡከደነፆር ከአባታቸው ጋር ለማረካቸው ሦስት ለሆኑ ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮአቄም ልጆች ለአናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል እግዚአብሔር ኃይልን አደረገላቸው።
እሊህም ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮአቄም ልጆቹ ናቸው። ዳንኤልም የእኅታቸው ልጅ ነው። በምርኮ ጊዜም ከእስራኤል ልጆች ጋራ ተማርከው ወደ ባቢሎን ወረዱ።
ከእስራኤል ልጆች ምርኮ ውስጥ በመብልና በመጠጥ እያስተማረ አሳድጎ በሠራዊቱ መካከል ጭፍሮቹ ያደርጋቸው ዘንድ ነውር ነቀፋ የሌለባቸውን ወጣቶች ንጉሥ መረጠ። እሊህም ከተመረጡት ውስጥ የተቆጠሩ ሆኑ የእኅታቸው ልጅ ዳንኤልም ነበር። ምግባቸውን በሚሰጧቸው ጊዜ አረማውያን ከአረዷቸው ውስጥ መብላትን አልወደዱም። ከንጉሥ ማዕድም ከሚመጣ ከሥጋው እንዳያበላቸውና እንዳያጠጣቸው አለቃውን ለመኑት።
እግዚአብሔርም በባለሟሎች አለቃ ፊት ቸርነቱን አደረገላቸው። የባለሟሎች አለቃም ንጉሡ ጌታዬን እፈራዋለሁ የምትበሉትንና የምትጠጡትን ምግባችሁን ስለ አዘዘ ከባልንጀሮቻችሁ እናንተን ከስታችሁ ቢያያችሁ ንጉሥ ራሴን ይቀጣኛል አላቸው።
በእነርሱ ላይ የተሾመ አሚሳድን እንዲህ አሉት እኛን ባሮችህን ዐሥር ቀን ፈትነን ከምድር ዘር ሽምብራን ይስጡን እንበላ ዘንድ ውኃንም እንጠጣ ዘንድ። ቃላቸውንም ሰምቶ ዐሥር ቀን ፈተናቸው ዐሥር ቀንም ከአለፈ በኋላ የንጉሡን ማዕድ ከሚመገቡ ከእነዚያ ልጆች ይልቅ ሰውነታቸው ወፍሮ መልካቸውም አምሮ ታየ።
ከዚህ በኋላ አሚሳድ የሚበሉትን ምግብ የሚጠጡትን ወይን እየወሰደ ለአራቱ ሁሉ ልጆች ሽምብራ ይሰጣቸው ነበር። እግዚአብሔርም ዕውቀትንና ጥበብን መጻሕፍትን በማንበብ ሁሉ ማስተዋልን ሰጣቸው። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ያዘዘው ቀን በተፈጸመ ጊዜ ወደርሱ አመጡአቸው የባለሟሎችም አለቃ ወደ ንጉሡ ወደ ናቡከደነፆር አገባቸው።
ንጉሡም ጠየቃቸው በሰው ሁሉ ዘንድ እንደ አናንያና እንደ ዳንኤል እንደ ሚሳኤልና እንደ አዛርያ ያለ አልተገኘም። በንጉሡም ፊት ቆሙ። ንጉሡም የፈለገውን የምክርና የጥበብን ነገር ሁሉ በግዛቱ ካሉ ጠንቋዮችና አስማተኞች ሰዎች ሁሉ ይልቅ በነሳቸው ዘንድ ዐሥር እጥፍ አገኘ። ንጉሡም እጅግ ወደዳቸው በባቢሎን አገር ሁሉ ላይ ገዢዎች አድርጎ ሾማቸው።
ንጉሥም ጣዖትን ከወርቅ ባሠራ ጊዜ ሰዎችን ሁሉ እንዲሰግዱለት አዘዛቸው። ሦስቱ ልጆችም ለዚያ ጣዖት ባልሰገዱ ጊዜ የሚቀኑባቸው ወደ ንጉሥ ነገር ሠርተው በንጉሥ ፊት አቀረቧቸው። ስለ አልሰገዱለትም ጠየቃቸው። እነርሱም "እኛስ ለሠራኸው ለወርቅ ምስል አንሰግድም" አሉት። ንጉሥም ተቆጥቶ ከምትነድ የእሳት ምድጃ ውስጥ ይጨምሩአቸው ዘንድ አዘዘ።
እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ የእሳቱን ነበልባል አጠፋው በጥዋት ጊዜ እንደሚቀዘቅዝ በእሊህ በሦስቱ ልጆች ዘንድ እንደ ጥዋት ውኃ ቀዝቃዛ አደረገው። ከዚያም የእሳቱ ነበልባል አርባ ዘጠኝ ክንድ ያህል ከፍ ከፍ ብሎ በውጪ ያሉትን አቃጠላቸው። እሊህን ሠለስቱ ደቂቅን ግን ምንም አልነካቸውም።
ንጉሥም ይህን ድንቅ ሥራ አይቶ በፊታቸው ሰገደ። የሰማይና የምድር ፈጣሪ እግዚአብሔርንም አመነ። ለእሊህም ልጆች ሹመታቸውን ከፍ ከፍ አድርጎ ክብርን ጨመረላቸው። ከዚህም ዓለም የሚወጡበት ጊዜ ሲደርስ በበዐታቸው እየጸለዩ ሳሉ ሰግደው ነፍሳቸውን በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ።
ወዲያውኑ ታላቅ ንውጽውጽታ በባቢሎን አገር ሆነ። ንጉሡም ፈርቶ ስለ ምን ይህ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ ብሎ ዳንኤልን ጠየቀው። ነቢይ ዳንኤልም "ይህ ሦስቱ ልጆች ስለ አረፉ ከዓለም ለመውጣታቸው ምልክት ነው።" ብሎ ነገረው። ንጉሡም ወደርሳቸው ደርሶ ታላቅ ኀዘንን አዘነ። ከዝሆን ጥርስም ሦስት ሣጥኖችን እንዲሠሩላቸው፣ በሐር በግምጃ ልብሶች ገንዘው ቅዱሳኑን በሣጥኑ ውስጥ እንዲያኖሩአቸው አዘዘ። ንጉሡ እንዳዘዛቸውም አደረጉ።
ሁለተኛም የወርቅ ሣጥን ሠርተው እርሱ በሚሞት ጊዜ ሥጋውን በውስጡ አድርገው በከበሩ ሠለስቱ ደቂቅ መካከል እንዲያኖሩት አዘዘ እንዲሁም አደረጉለት።

በዚችም ቀን በላይኛው ግብጽ ከሚኖሩ ሰዎች ወገን የሆነ ቅዱስ አባት አባ ሖር አረፈ ።
ደግነት ያለው መነኰስ በመሆን ጽኑዕ ገድልን ተጋደለ በአምልኮቱና በተጋድሎው ከቅዱሳን ሁሉ ተለይቶ በብዙዎች ላይ ከፍ ከፍ አለ ለብቻ መኖርን ስለወደደ ወደ በረሀ ወጥቶ በገድል ተጠምዶ ብዙ ዘመናት ኖረ። የበጎ ሥራ ጠላት የሆነ ሰይጣንም ቀንቶበት በግልጥ ታየውና በበረሀ ውስጥ ግን አንተ ድል ትነሣናለህ በዚህ ሰው የለምና ጽኑ ኃይለኛ ከሆንክ ወደ እስክንድርያ ከተማ ና ብሎ ተናገረው።
አባ ሖርም ይህን በሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኃይል ተማምኖ ወደ እስክንድርያ ከተማ ሒዶ ለእሥረኞችና ለችግረኞች ደካሞች ውኃ የሚቀዳ ሆነ በአንዲት ዕለት ሦስት ፈረሶች በከተማው ውስጥ እየዘለሉ ሲያልፉ አንዱ ፈረስ አንዱን ሕፃን ረገጠውና ወዲያውኑ ሞተ ሰይጣንም በሰዎች ልብ አደረና ይህን ሕፃን ያለዚህ አረጋዊ መነኵሴ የገደለው የለም ብለው አሰቡ አባ ሖርም መጣና ሕፃኑን አንሥቶ ታቀፈው በልቡም በመጸለይ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ማለደ በመስቀል ምልክትም በላዩ አማተበ የሕፃኑም ነፍስ ተመለሰች ድኖም ተነሣ ለአባቱም ሰጠው ወደ ከተማ ውጭ ሸሽቶ በመሔድ ወደ በዓቱ ገባ ፈልገውም አላገኙትም ጽድቅንና ትሩፋትንም በመሥራት ብዙ ዘመናት በገድል ተጠምዶ ኖረ።
የሚሞትበት ጊዜ ሲቀርብ ብዙዎች ቅዱሳንን ሲጠሩት አያቸው እጅግም ደስ አለው ልጆቹንም ሰብስቦ በምንኲስና ሥርዓት ጸንተው ትሩፋትን እንዲሠሩ አዘዛቸው ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እርሱ እንደሚሔድ ነገራቸው እነርሱም እጅግ አዘኑ ጥቂት ቀንም ታሞ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages