አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ሦስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች #እመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው፣ የሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ፋኑኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #የጻድቁ_አቡነ_ዜና_ማርቆስ ዕረፍታቸው ነው።
ታኅሣሥ ሦስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት ሲሆናት ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው ። እርሷ ለእግዚአብሔር የስእለት ልጅ ነበረችና።
እናቷ ቅድስት ሐና ልጅ የሌላት ስለሆነች በቤተ እግዚአብሔር ውስጥ ከሴቶች ተለይታ ርቃ ትኖር ነበር ሽማግሌ ከሆነ ከኢያቄም ከባሏ ጋርም እጅግ የምታዝን ሆነች ። እግዚአብሔርም ኀዘናቸውን ሰማ ቅድስት ሐናም እንዲህ ብላ ለእግዚአብሔር ተሳለች የሰጠህኝን ፍሬ ለእግዚአብሔር አገልጋይ አደርገዋለሁ ።
ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምንም በወለደቻት ጊዜ ሦስት ዓመት በቤቷ ውስጥ አሳደገቻት ከዚህም በኋላ ከደናግል ጋር ትኖር ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደቻት በቤተ መቅደስም ምግቧን ከመላእክት እጅ እየተቀበለች ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረች ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቶ ከእርሷ ሥጋን እስከ ነሣ ድረስ።
ከሴቶች ሁሉ የተመረጠች ይቺ ናት በቤተ መቅደስም በመኖር ዐሥራ ሁለት ዓመት ሲፈጸምላት እርሷ ለእግዚአብሔር የተሰጠች የስዕለት ልጅ ናትና ለሚጠብቃት ይሰጧት ዘንድ ካህናት እርስበርሳቸው ተማከሩ በሴቶች ላይ የሚደርስ በርሷ ላይም ይደርስባታል ብለው ስለፈሩ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይተዋት ዘንድ ለእርሱ ትክክል መስሎ አልታያቸውም ስለዚህም ሊጠብቃት ለሚገባው በእርሷ ላይ እጮኛ ሊአኖሩ ወደዱ።
ከዚህም አስቀድሞ ሊቀ ካህናት ዘካርያስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልጄ ማርያም ሆይ አንቺ እንዳደግሽና ለአካለ መጠን እንደደረስሽ ዕወቂ ልትታጪ ትወጃለሽን እግዚአብሔርን የሚፈራ መልካም የሆነ የተባረከ ጐልማሳ እንፈልግልሽን ወይም በሕይወትሽ ዘመን ሁሉ በቤተ መቅደስ ተቀምጠሽ እግዚአብሔርን ልታገለግዪው የምትሺ ከሆነ በሴቶች ላይ የሚደርሰው በሚደርስብሽ ወራት ወደ ቤተ መቅደስ ደጅ ከመግባት ትጠበቂ ዘንድ በኦሪቱ የተጸፈውን የርግማን ሥርዓት በአንቺ ላይ እንሠራለን አላት ።
ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምም እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋዩ በፊታችሁ ነኝ አባትና እናት የሉኝም ስሙ ቡሩክ ምስጉን ከሆነ ከእግዚአብሔር በታች በእናትና አባት ፈንታ እናንት ናችሁና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንደምታውቁ አድርጉ ብላ መለሰች።
ካህናቱና ማኅበሩም ሁሉ ዘካርያስን ወደ ቤተ መቅደስ ገብተህ ስለዚች ብላቴና ማርያም ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት ዘካርያስም ገብቶ ሲጸልይ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና እንዲህ አለው። ዘካርያስ ሆይ ወጥተህ ከዳዊት ወገን ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን ሁሉ ወንዶች ሰብስብ የየአንዳንዱንም በትር ከስሙ ጋር ውሰድ ወደ ቤተ መቅደስም በምሽት አግብተህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይበት በነጋ ጊዜም በትሮቻቸውን አውጣ እግዚአብሔርም በበትሩ ላይ ምልክት ለገለጠልህ ለዚያ ሰው ማርያምን ተቀብሎ ሊጠብቃት ይገባዋል።
ካህኑ ዘካርያስም ወጥቶ አንድነት ለተሰበሰቡት ሕዝብ የእግዚአብሔር መልአክ የነገረውን ነገራቸው በዚያንም ጊዜ ከዳዊት ወገን ጐልማሳም ቢሆን ሽማግሌም ቢሆን ሚስቱ የሞተችበት ሁሉ በኢየሩሳሌም ወደአለ ቤተ መቅደስ ይሒድ እያሉ ዓዋጅን ዙረው የሚናገሩ በእስራኤል አገር ሁሉ ላከ ።
ከዳዊት ወገን የሆነ ጠራቢው ዮሴፍም በሰማ ጊዜ በትሩን ይዞ ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ ካህኑ ዘካርያስም የሁሉንም በትሮች ተቀብሎ ስማቸውን በላያቸው ጻፈ ቁጥራቸውም አንድ ሽህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አምስት ሆነ ዘካርያስም በትሮችን ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ እንዲሁም ሰዎች ሁሉ ከቤተ መቅደስ ውጭ ቁመው ይጸልዩ ነበር ዘካርያስም ጸሎቱን በፈፀመ ጊዜ ለየአንዳንዱ በትራቸውን አውጥቶ ሰጠ ጠራቢው ዮሴፍም በትሩን ሊቀበል በቀረበ ጊዜ ከእርሷ ነጭ ርግብ የመሰለች ተገለጠች እየበረረችም ሒዳ በጠራቢው ዮሴፍ ራስ ላይ ተቀመጠች ካህናቱና ሕዝቡ ሁሉ አይተው እጅግ አደነቁ ምስጉን የሆነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ።
ዘካርያስም ዮሴፍን ዮሴፍ ሆይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እንደ ተናገረ ድንግል ማርያምን ወደ ቤትህ ወስደህ ጠብቃት አለው ዮሴፍም ቅድስት ድንግል ማርያምን ከካህናት እጅ ተቀበላት በእርሱም ዘንድ ኖረች ። ከዚህም በኋላ የመላእክት አለቃ ገብርኤል ስለ እግዚአብሔር ልጅ ከእርሷ ሰው ሁኖ ስለመወለዱ በዮሴፍ ቤት አበሠራት።
በዚችም ቀን የሊቀ መላእክት ፋኑኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።
ይህም ታላቅ መልአክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አናት እና አባት ቅድስት ሐና እና ቅዱስ ኢያቄም እግዚአብሔር አምላክ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ዘወትር ይማፀኑት ነበር፡፡ለእግዚአብሔር “ወንድ ልጅ ብንወልድ እርሱ ወጥቶ ወርዶ ያበላናል አንልም ያንተን ቤት ያገለግላል፤ ሴትም ብትሆን ጋግራ ታብላን ፈትላ ታልብሰን አንልም ሀርና ወርቅ እየፈተለች መሶበ ወርቅ እየሰፋች ቤተ መቅደስን ታገለግላለች እንጂ” ብለው ስዕለትንም ተስለው ነበር፡፡
ለአብርሀም እና ለሳራ ይስሐቅን (ዘፍ. 21፥1-8)፣ ለሕልቃና እና ለሐና ነብዩ ሳሙኤልን (1ኛ ሳሙ. 1፥1-21) የሰጠ አምላክ ዛሬም የእነዚህን ቅዱሳን እንባቸውንና ልመናቸውን ሰምቶ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሰጣቸው፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናት እና አባቷ ቤት እስከ 3 ዓመት ድረስ ከቆየች በኋላ በስእለታቸው መሰረት ለቤተ መቅደስ ሰጡ፡፡ ቤተ መቅደስ ከደረሱ በኋላ ስእለታቸውን ለሊቀ ካህኑ ለዘካርያስ በሰጡት ወቅት ሊቀ ካህኑ እና ሌሎች የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች (ካህናት) የምግቧ ነገር እንዴት ሊሆን ነው ብለው እጅግ ተጨነቁ፡፡ በዚህ ወቅት ከሰባቱ ሊቃነ መላዕክት አንዱ የሆነው መልዐኩ ቅዱስ ፋኑኤል ሰማያዊ ጽዋ አና ሰማያዊ ሕብስት ይዞ ረብቦ ታየ፡፡ ሊቀ ካህኑ ዘካርያስ ለኔ የመጣ ነው ብሎ ወደ መልአኩ ጠጋ ሲል፡፡ ያኔ ቅዱስ ፋኑኤል ወደ ላይ ከፍ አለ፡፡ የሊቀ ካህኑ ምክትል የነበረው ስምኦንም ሲቀርብ መልአኩ አሁንም ከፍ አለ፡፡ ከዛም ህፃኒቱን እስቲ ተጠጊ ብለዋት ስትጠጋው መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል ፈጥኖ ወርዶ አንድ ክንፉን አንጥፎ አንድ ክፉን ጋርዶ በሰው ቁመት ከመሬት ከፍ አድርጎ መግቧት አረገ፡፡ ይህም የሆነው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደቤተ መቅደስ በገባችበት ዕለት ነው፡፡
በተጨማሪም
✞ ድርሳነ ፋኑኤል ላይ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ሰዳዲ ሰይጣናት ወመድፍነ አጋንንት እያለ ይጠራዋል ይሕም ማለት ሰዎችን በልዩ ልዩ በሽታዎች እና እንቅፋቶች ሰዎችን የሚያሰናክሉ አጋንንትን እያሳደደ ወደ ጥልቁ የሚከታቸው መልአክ ነው ሲል ነው፡፡
✞ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል በ2ኛ ነገ. 6፥14 ላይ የሶሪያ ንጉስ ወልደ አዴር እስራኤልን በቁጥጥር ባደረገ ጊዜ ኤልሳዕንም ሆነ የእስራኤልን ልጆች ለማዳን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ሰራዊቱን አስከትሎ በከተማዋ ሰፈረ ከዛም የጠላትን ሰራዊት ዓይን አጠፋ፤ ለኤልሳዕም ሆነ ለእስራኤል ልጆች የድል ካባ በአንድ ምሽት አልብሷቸው ከአይናቸው ተሰወረ፡፡
✞ ይህ ታላቅ መልአክ በ1ኛ ነገ. 19፥5-18 በምናገኘው ታሪክ ላይ ነብዩ ኤልያስን ከተኛበት እየቀሰቀሰ እንጎቻን ብላ ሲለው የነበረው መልአክ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ነው፡፡
✞ ሌላው የአዳም 7ኛ ትውልድ የሆነው ሞትን ሳያይ የተሰወረው ሄኖክ እንዲህ ሲል ጠቅሶታል "አራተኛውም የዘላለም ሕይወትን የሚወርሱ ሰዎች ተስፋ ሊሆን ንሰሐ በሚገቡ ሰዎች ላይ የተሾመው ፋኑኤል ነው" መ.ሄኖክ 10፥15
ዳግመኛም በዚህች ቀን የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ዕረፍታቸው ነው።
አባ ዜና ማርቆስ በሃገራችን በተለይ በደቡብ ምድረ ጉራጌ ስመ ጥር ሐዋርያዊ ጻድቅ ናቸው። ምድረ ሽዋ ደግሞ እርሳቸውን ጨምሮ የብዙ ቅዱሳን መፍለቂያ ናትና ክብር ይገባታል። ነቢየ ጽድቅ ዳዊት "ትውልደ ጻድቃን ይትባረኩ" "የጻድቃን (የቅኖች) ትውልድ ይባረካል" (መዝ.111) ያለው ነገር በምድረ ዞረሬ (ጽላልሽ) ተፈጽሟል።
ሦስት ወንድማማች የተባረኩ ካህናት በስፍራው ነበሩ። ስማቸው ጸጋ ዘአብ፣ እንድርያስና ዮሐንስ ይባላል። ከእነዚህ መካከልም ጸጋ ዘአብ እግዚእ ኃረያን አግብቶ ኮከበ ከዋክብት ተክለሃይማኖትን ሲወልድ፤ ካህኑ ዮሐንስ ደግሞ ዲቦራ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ዜና ማርቆስን ወልዷል።
የአቡነ ዜና ማርቆስ ጽንሰታቸው ሚያዝያ 30 በብሥራተ ማርቆስ ወንጌላዊ ሲሆን ልደታቸው ደግሞ ኅዳር 24 ቀን በበዓለ ሱራፌል ካህናተ ሰማይ ነው። ዘመኑም 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው።
ዜና ማርቆስ በተወለዱ በ40 ቀናቸው አጐታቸው ቀሲስ እንድርያስ (የ72 ዓመት ሽማግሌ ናቸው) ሊያጠምቁ ቀረቡ። ሕጻኑ ዜና ማርቆስ ግን ከእናታቸው እቅፍ ወርደው 3 ጊዜ "እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ" እያሉ ቢሰግዱ የመጠመቂያው ገንዳ ውኃ ፈላ። ይህንን የተመለከቱት ካህኑ ደንግጠው ወጥተው ሲሮጡ ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት ተገልጦ "አትፍራ! ይልቁኑ ከጠበሉ ራስህን ተቀባ" አላቸው። እንዳላቸው ቢያደርጉ ራሰ በራ ነበሩና ጸጉር በቀለላቸው።
ሕጻኑ ዜና ማርቆስ ግን 5 ዓመት ሲሞላቸው ወደ ጉባኤ ቤት ገብተው በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ። ዲቁናን ተቀብለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱም ሽፍቶች አግኝተው በትራቸውን ቀምተው አንገላተው ሰደዋቸዋል። ወዲያው ግን ያቺ በትር እባብ ሁና ሽፍቶችን አጥፍታቸዋለች።
ጻድቁ ለቤተሰብ እየታዘዙ፣ ንጽሕናቸውንም እየጠበቁ ኑረው 30 ዓመት ሲሞላቸው ወላጆቻቸው ግድ ብለው ማርያም ክብራ ለምትባል ወጣት አጯቸው። እሳቸው ግን በሠርጉ ሌሊት ከጫጉላ ቤት ጠፍተው በርሃ ገቡ። ከዚያም በቅዱስ መልአክ መሪነት ሃገረ ምሑር ደረሱ። በቦታውም ጣዖትን ሰባብረው፣ ተአምራትንም አድርገው ሕዝቡን ወደ ክርስትና መለሱ።
መስፍኑ አውጊት ግን ተፈታተናቸው። አሠራቸው። አሥራባቸው(በረሀብ ቀጣቸው)። በጦር እወጋለሁ ሲል ግን መሬት ተከፍታ ከነ ተከታዮቹ ውጣዋለች። ከ5 ዓመታት በኋላ ግን ማልደው ከሰጠመበት አውጥተው አጥምቀውታል። ቀጥለውም ምድረ ጉራጌ ወርደው ሕዝቡን አሳምነው አጥምቀዋል።
የአዳልን ሕዝብና ንጉሡን አብደልማልን አስተምረው ያጠመቁም እርሳቸው ናቸው። ድል አሰግድ የሚባለውን መስፍንም ያሳምኑ ዘንድ ጠንቋዮቹን ድል አድርገው አጥፍተዋል።
ጻድቁ ዜና ማርቆስ ከዚህ ሐዋርያዊ ሥራቸው በተጨማሪ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምንኩስናን ከተቀበሉባት ቀን ጀምረው በጾም፣ በጸሎትና በሰጊድ ኑረዋል። ፀሐይን በምድረ ጉራጌ እስከ ማቆም ደርሰውም ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል።
አእላፍ ደቀ መዛሙርትን ሲያፈሩ 200 አንበሶች በቀኝ፣ 200 ነብሮች በግራ ይከተሏቸው ነበር። ደብረ ብሥራትን ጨምሮም ገዳማትን አንጸዋል። በመጨረሻም የምሕረት ቃል ኪዳንን ከፈጣሪ ዘንድ ተቀብለው ታኅሣሥ ሦስት ቀን በ140 ዓመታቸው ዐርፈዋል።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ይማረን፤ በመልአኩ እና በቅዱሱ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።
No comments:
Post a Comment