ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 4 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 4

ቅዱስ_እንድርያስ_ሐዋርያ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ አራት በዚች ቀን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ወንድም የተመሰገነ ቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስ በምስክርነት አረፈ።


ለዚህም ቅዱስ ይሰብክ ዘንድ ዕጣው በልዳ ሀገር ወጣ ከእርሷም ብዙዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት አምነው ነበር አንደበቱ የሚጥም በሥራው ሁሉና በአምልኮቱ የተወደደ ያማረ ደቀ መዝሙሩ ፊልሞና አብሮት ነበር ሐዋርያ እንድርያስም ከፍ ካለ ቦታ ላይ ወጥቶ ጣዕም ባለው አንደበቱ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንዲአነብ አዘዘው ።
የጣዖታት ካህናትም የሐዋርያ እንድርያስን መምጣት በሰሙ ጊዜ አማልክቶቻቸውን ይረግሙ እንደሆነ ሊጣሏቸው ሽተው የጦር መሳሪያቸውን ይዘው መጡ።
በዚያንም ጊዜ ፊልሞና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከወርቅና ከብር የሰው እጅ ሥራ የሆኑ የአሕዛብ አማልክቶቻቸው አፍ አላቸው አይናገሩም፣ ዐይን አላቸው አያዩም፣ ጆሮ አላቸው አይሰሙም፣ አፍንጫ አላቸው አያሸቱም፣ እጅ አላቸው አይዳስሱም፣ እግር አላቸው አይሔዱም፣ በጉሮሮአቸውም አይናገሩም፣ የሚሠሩአቸውና የሚአምኑባቸው ሁሉ እንደእነርሱ ይሁኑ እያለ ሲያነብ ሰሙት።
ስለ ቃሉ ጣዕምና ስለ ንባቡ ማማር ልባቸው ከክህደት ማሠሪያ ተፈታ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ገብተው ከሐዋርያ እንድርያስ እግር በታች ሰገዱ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አመኑ እርሱም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ከእሳቸውም ጋር ጣዖትን ከሚያመልኩ ውስጥ ብዙዎች አምነው ተጠመቁ።
በዚያ ወራትም እንዲህ ሆነ በልዳ አገር አቅራቢያ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ቄስ ነበረ ለእርሱም አንድ ልጅ አለው እርሱም ከባልንጀራው ጋር ሲጫወት በድንገት ገደለው የሟች አባትም ልጄን የገደለ ልጅህን አሳልፈህ ስጠኝ ሲል ቀሲስ ዮሐንስን ያዘው ቀሲስ ዮሐንስም የሀገር ሰዎችን ሔጄ ሐዋርያ እንድርያስን እስከማመጣው ዋስ ሁኑኝ እርሱ የሞተውን ያነሣልኛልና ብሎ ለመናቸው እነርሱም በተዋሱት ጊዜ ቀሲስ ዮሐንስ ወደ ሐዋርያ እንድርያስ ሒዶ ችግሩን ሁሉ ነገረው።
ሐዋርያ እንድርያስም ቀሲስ ዮሐንስን እንዲህ አለው ከእኔ ዘንድ የሚጠመቁ ብዙ ሕዝቦች ስላሉ ከአንተ ጋር እሔድ ዘንድ አይቻለኝም ግን ደቀ መዝሙሬ ፊልሞና አብሮህ ይሒድ እርሱ የሞተውን ያስነሣልሃል አለው።
ሐዋርያ እንድርያስም ከቄሱ ጋር ሒዶ የሞተውን ያስነሣለት ዘንድ ፊልሞናን አዘዘው ወደ ከተማውም ሲቀርቡ ቄሱንና ፊልሞናን ሰዎች በከተማው ውስጥ ሁከት ሁኗልና አገረ ገዥው እንዳይገድላችሁ ወደ ከተማ አትግቡ አሏቸው ። ፊልሞናም እንዲህ አለ እኔ የመምህሬን ትእዛዝ መተላለፍ አልችልም የሞተውን ለማንሣት እሔዳለሁ እንጂ መኰንኑ ቢገድለኝም መምህሬ እንድርያስ መጥቶ እኔንም አስቀድሞ የሞተውንም ያስነሣናል።
ሲገባም መኰንኑን ኒቆሮስን ተገናኘውና ፊልሞና እንዲህ አለው ሀገርን ለምን ታጠፋለህ የሾሙህ ከክፉ ነገር ሁሉ ሀገርን ልትጠብቅ አይደለምን መኰንኑም ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ይመስላል አለ ወታደሮችንም ይዛችሁ ሰቅላችሁ ግረፉት አላቸው ወታደሮችም ይገርፉት ዘንድ ይዘው ሰቀሉት።
ፊልሞናም ኒቆሮስ የተባለውን መኰንን እንዲህ አለው የበደልኩት በደል ሳይኖር ለምን ሰቅለህ ትገርፈኛለህ እኔ ታናሽ ብላቴና ስሆን ደቀ መዝሙሩን እኔን ሰቅለው ሲገርፉኝ ይመለከት ዘንድ ለመምህሬ እንድርያስ ማን በነገረው አለ ። ወደ ወታደሮችም ፊቱን መልሶ እንዲህ አላቸው ከውስጣችሁ የሚራራና የሚያዝንልኝ የለምን በመሰቀልና በመገረፍ እንዳለሁ ሒዶ ለመምህሬ እንድርያስ ስለ እኔ ይነግረው ዘንድ አለ ከቃሉ ጣዕም የተነሣ ወታደሮች ተሰብስበው መጥተው አለቀሱ።
በዚያንም ጊዜ አዕዋፍ ሁሉ መጥተው እኛን ላከን ብለው ተናገሩት ድምቢጥ ቀርባ እኔ በአካሌ ቀላል ነኝና እኔን ላከኝ አለችው አንቺስ አመንዝራ ነሽ ከወገንሽ በመንገድ አንዱን ያገኘሽ እንደሆነ ከርሱ ጋር ትጫወቺአለሽ ፈጥነሽ አትመለሽም አላት ከዚህም በኋላ ቁራ ቀርቦ እኔን ላከኝ አለው ፊልሞናም እንዲህ አለው አንተም በቀድሞ ዘመን በተላክህ ጊዜ ለአባታችን ኖኅ የመልእክቱን መልስ አልመለስክም አለው።
ፊልሞና ግን ርግብን ጠርቶ እንዲህ አላት እግዚአብሔር የዋሂት ብሎ ስም ያወጣልሽ ከአዕዋፍ ሁሉ የተመረጥሽ ወገን አንቺ ለአባታችን ኖኅ በመርከብ ውስጥ ሳለ መልካም ዜና አድረሰሽለታልና አባታችን ጻድቅ ኖኅም ባርኮሻልና አሁንም ወደ ልዳ ከተማ ወደ መምህሬ እንድርያስ ሔደሽ ንገሪው ሰቅለው እየገረፉኝ ነውና ወደ እኔ ወደ ደቀ መዝሙሩ ፊልሞና ይመጣ ዘንድ። በዚያን ጊዜ ርግብ ሒዳ ለሐዋርያ እንድርያስ ነግራ የመልእክቱን መልስ ይዛ ተመለሰች የተባረከች ርግብም ለፊልሞና መምህርህ እንድርያስ እኔ እመጣለሁና አይዞህ በርታ ብሎሃል አለችው።
በዚያንም ጊዜ ርግብ በሰው ቋንቋ ለፊልሞና ስትነግረው ኒቆሮስ መኰንን ሰማት እጅግም አደነቀ ፈጥኖ ተነሥቶም ራሱ በእጁ ፊልሞናን ፈትቶ ከተሰቀለበት አወረደው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አመነ።
ሰይጣን ግን ቀና በመኰንኑ ሚስት ልቡና አድሮ አሳበዳትና ልጅዋን ገደለች አገልጋዮቹም ሒደው የሆነውን ሁሉ ለመኰንኑ ነገሩት ፊልሞናም አትፍራ አይዞህ አለው ። ከዚህም በኋላ ርግብን ጠርቶ ወደ መኰንኑ ቤት ሒጂ እንዳይሸበሩ በጸጥታ እንዲቆዩ ንገሪያቸው አላት ርግቢቱም ሒዳ ፊልሞና እንዳዘዛት ለሕዝቡ ነገረቻቸው ሕዝቡም ርግቢቱ በሰው ቃል ስትናገር በሰሙ ጊዜ እጅግ አድንቀው ፊልሞና ወዳለበት ተሰበሰቡ።
በዚያንም ጊዜ ሐዋርያ እንድርያስ ደረሰ አስቀድሞ የሞተውን ያስነሣው ዘንድ ደቀ መዝሙሩ ፊልሞናን አዘዘው እርሱም ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን በመጸለይ ከሞት አስነሣው ሁለተኛም ወደ መኰንኑ ቤት ሔዱ ሐዋርያ እንድርያስም የመኰንኑን ልጅ እናቱ የገደለችውን አስነሣው የመኰንኑንም ሚስት አዳናት ከእርሷ የወጣውንም ያንን ጋኔን ይዞ በሰው ሁሉ ፊት ምድርን ከፍቶ ወደ ጥልቅ አዘቅት አሰጠመው።
ከዚህም በኋላ ሐዋርያ እንድርያስ ርግብን ጠርቶ ዕድሜሽ ስንት ነው አላት እርሷም ስምንት ዓመት ነው አለችው ። እርሱም ለደቀ መዝሙሬ ስለታዘዝሽ ወደ ዱር ሒጂ ለዓለም ሰዎች ከመገዛት ነጻ ሁኚ አላት ወዲያውኑ ሔደች ሕዝቡም ይህን ድንቅ ሥራ አይተው አምነው ሁሉም የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ።
ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው ዘንድ ወጥቶ አክራድ አክሲስ አክሳስያ ሴኒፎሮስም ወደ ተባሉ አገሮች ሒዶ አስተማረ ከሐዋርያ በርተሎሜዎስም ጋር ተገናኝቶ ጋዝሪኖስ ወደ ሚባል አገር በአንድነት ሔዱ የሀገር ሰዎች እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እስከተመለሱ ድረስ ረዳት ከተደረገላቸው ገጸ ከልብ ጋር ገብተው ወንጌልን ሰበኩ ድንቅ ተአምራትንም አደረጉ።
ከዚህም በኋላ ሐዋርያ እንድርያስ ወደ ሌሎች አገሮች ሒዶ አስተማረ በፍጻሜውም ወደ አንዲት አገር ገብቶ ቅዱስ ወንጌልን ሰበከ የዚያች አገር ሰዎች ግን እጅግ የከፉ ስለሆኑ ትምህርቱን አልተቀበሉትም።
ከቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስም ድንቅ ተአምራትን ስለአዩ ያመኑ አሉ ያላመኑ ግን ወደእነርሱ እንዲመጣና እንዲገድሉት በቅዱስ እንድርያስ ላይ ክፉ ምክርን መክረው በተንኩል ወደርሱ መልእክተኞችን ላኩ መልእክተኞችም ወደ ቅዱስ እንድርያስ ሲደርሱ ማራኪ የሆነ ትምህርቱን ሰሙ ፊቱንም ብርሃን ሁኖ አዩትና ክብር ይግባውና በጌታችን አመኑ ደቀ መዝሙሮችም ሆኑት ወደላኳቸውም አልተመለሱም።
ሁለተኛም በእሳት ሊአቃጥሉት ተማከሩና ተሰብስበው ወደርሱ ሔዱ እርሱ ግን የልባችሁን ክፋት ትታችሁ ትድኑ ዘንድ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እመኑ ይህ ካልሆነ ግን ለእኔ ያላችኋት ይቺ እሳት እናንተን ትበላለች አላቸው ። ቃሉንም ባልሰሙ ጊዜ ከሰማይ እሳት ወርዳ እንድታቃጥላቸው ክብር ይግባውና ጌታችንን ለመነው ወዲያውኑ እሳት ወርዳ አቃጠለቻቸው በዚያች አገር አውራጃዎች ሁሉ ዜናው ተሰማ እጅግም ፈርተው ብዙዎች ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።
የጣዖታት አገልጋዮች ግን ይህን ሁሉ ድንቅ ተአምራት አይተው አላመኑም ቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስን ሊገድሉት ፈለጉት እንጂ። ከዚህም በኋላ ተሰብስበው መጡና ቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስን ይዘው ወሰዱት ታላቅ ግርፋትንም ገርፈው በከተማው ሁሉ ራቁቱን አዙረው ከወህኒ ቤት ጨመሩት በማግሥቱ የሚሰቅሉትን ሰው ልማዳቸው እንዲሁ ነውና ሰው ሊገድሉ በሚሹ ጊዜ ወስደው በእንጨት ላይ ይሰቅሉታል እስከሚሞትም ድረስ በደንጊያዎች ይወግሩታል።
በዚያችም ሌሊት የተመሰገነ ሐዋርያ አባታችን እንድርያስ እንደ ፊተኞቹ እሳት ወርዳ እንድትበላቸው ክብር ይግባውና ጌታችንን ክርስቶስን ለመነው ክብር ይግባውና ጌታችንም ተገለጠለትና ከዚህ ዓለም የምትለይበት ጊዜ ደርሷልና አትዘን አለው ሰላምታም ሰጥቶት ከእርሱ ተሠወረ የተመሰገነ የሐዋርያ እንድርያስም ልቡናው ፈጽማ ደስ አላት።
ንጋትም በሆነ ጊዜ ወስደው በዕንጨት ላይ ሰቀሉት እስከ ሞተ ድረስም በደንጊያዎች ወገሩት አማንያን ሰዎችም መጥተው ሥጋውን ወስደው ገንዘው ቀበሩት ከእርሱም ታላላቅ የሆኑ አስደናቂዎች ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ በሐዋርያ እንድርያስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages