(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 10 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 10

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ዐስር በዚህች ዕለት የአንጾኪያው ሊቅ #ቅዱስ_አባት_አቡነ_ሳዊሮስ ፍልሠተ ሥጋው ነው፣ #ቅዱስ_አባት_አባ_ኒቆላዎስ አረፈ፣ #አባ_ጥዋሽ ዕረፍቱ ነው፣ የከበረች #ቅድስት_ሱርስት ዐረፈች፣ ቅዱሳን ሰማዕታት #ቅዱስ_ተላስስና_ቅዱስ_አልዓዛር በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡


ታኅሣሥ ዐስር በዚህች ዕለት እጅግ የከበሩ አቡነ ሳዊሮስ የፍልሥተ ሥጋቸው ሆነ፡፡ እርሳቸውም በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ቤተ ክርስቲያንን እንደፋና አብርተውላት በዓለም መድረክ አንድ ያደረጓት ናቸው፡፡ (የዕረፍታቸውን ዕለት የካቲት ዓሥራ አራትን ይመለከቷል፡፡)
እጅግ ክቡር የሆኑት የአንጾኪያው ታላቁ አባት የአቡነ ሳዊሮስ ትውልዳቸው ከሮሜ ሀገር ሲሆን አባታቸው ሳዊሮስ የሚባሉ ኤጲስ ቆጶስ ናቸው፡፡ አባታቸው ሳዊሮስ ስለ ንስጥሮስ የከፋ ክህደት በኤፌሶን ከተማ ጉባኤ በተደረገ ጊዜ ከሁለት መቶው እጅግ ከከበሩት ሊቃውንት ቅዱሳን አባቶች ጋር ተሰብስበው ሃይማኖትን አቅንተዋል፡፡ ንስጥሮስንም በቃላቸው ትምህርትና የተለያዩ ተአምራትን እያሳዩ አስተምረው ሊያሳምኑት ቢሞክሩ ሰይጣን በልቡ ስላደረ ከክህደቱ ሊመለስ አልቻለም ነበርና ቤተ ክርስቲያንን እንዳያውክ ምእመናንም በክህደት በመርዙ እንዳይበክል ብለው ቅዱሳኑ በኅብረት አውግዘው ለዩት፡፡
ታላቁ አቡነ ሳዊሮስም ለጉባኤው በኤፌሶን ከተማ እንደመጡ ‹‹ከአንተ የሚወለድ ልጅህ ስሙም እንደ ስምህ ሳዊሮስ ተብሎ የሚጠራ ልጅህ የቀናች ሃይማኖትን ያጸናታል›› የሚል ታላቅ ራእይን ተመለከቱ፡፡ ይህም ታላቁ አቡነ ሳዊሮስ ባረፉ ጊዜ ልጃቸውን ሳዊሮስ ብለው ጠሩት፡፡ እርሱም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆኑትን የጥበብና የፍልስፍና ትምህርቶቸን በሙሉ ጠንቅቆ ተማረ፡፡ በአንዲት ዕለትም ከመምህሩ ዘንድ ወጥቶ በመንገድ ሲጓዝ በዋሻ ውስጥ የሚኖርና ራሱን እስረኛ ያደረገ አንድ ታላቅ ጻድቅ ሰው አገኘ፡፡ ያም ጻድቅ ሰው ሳዊሮስን ‹‹የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሃይማኖታቸው ለቀና ምእመናን መምህራቸው የሆንክ ሳዊሮስ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው›› አለው፡፡ ያም ጻድቅ ሰው ሳዊሮስን ከነጭራሹ ሳያውቀው በስሙ ስለጠራውና የሚደረግለትንም ከመሆኑ አስቀድሞ ትንቢት በመናገሩ በጣም ተደነቀ፡፡
ከዚህም በኋላ ሳዊሮስ የትሩፋት ሥራዎችን መሥራት ጀመረ፡፡ ወደ አቡነ ሮማኖስ ገዳም ገብቶ መነኮሰና በጾም በጸሎት በእጅጉ ይተጋ ጀመር፡፡ በገዳሙም ጽኑ በሆነ በመንፈሳዊ ተጋድሎ እየበረታ ሲሄድ ዜናው በሁሉ ዘንድ መሰማት ጀመረ፡፡ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት በሞት ባረፉ ጊዜ የከበሩ ሊቃውንት ኤጲስቆጶሳት በአንድ ሀሳብ ሆነው ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቀው አቡነ ሳዊሮስን የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ይሾሙት ዘንድ ወደዱ፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔርም ያለ ፈቃዱ በግድ ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት፡፡
በአቡነ ሳዊሮስ በሹመታቸው ዘመን እስከ ዓለም ዳርቻ ያለች ቤተ ክርስቲያን ብርሃን ሆኑላት፡፡ የመለኮት ነገር የሚናገሩት ድርሰቶቻው እጅግ ድንቅ ናቸው፡፡ በየሀገሩ ወዳሚገኙ መናፍቃን ከሃድያን ትምህርታቸው በሚደርስ ጊዜ ሁለት አፍ እንዳለው ስለታም ሰይፍ ሥራቸውን ይበጥሳልና፡፡ የአቡነ ሳዊሮስን ትምህርታቸውን የሰማ መናፍቅ በውስጡ ያደረበት የጥርጥር መንፈስ መድረሻ ያጣል፡፡ አቡነ ሳዊሮስ በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ቤተ ክርስቲያንን እንደፋና አብርተውላት በዓለም መድረክ አንድ አድርገዋታል፡፡
አቡነ ሳዊሮስ በቀናው ተጋድሎአቸው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ከመናፍቃን ተኩላዎች በመጠበቅ ሲተጉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደጉና አማኙ ንጉሥ ሞቶ በእርሱ ፈንታ ስሙ ዮስጥያኖስ የሚባል መናፍቅ ነገሠ፡፡ ይህም ከሃዲ ንጉሥ ዮስጥያኖስ ‹‹በውሾቸ ጉባኤ›› የተወሰነውን የኬልቄዶንን ሃይማኖት የሚያምን መናፍቅ ከሃዲ ነው፡፡ ንግሥቲቱ ሚስቱ ቴዎድራ ግን ሃይማኖቷ የቀና ምግባሯ ያማረ ነው፡፡ አቡነ ሳዊሮስ በጣም ትወዳቸውና ታከብራቸው ነበር፡፡ ይህም ከሃዲ ንጉሥ አቡነ ሳዊሮስን ወደ ረከሰች ሃይማኖቱ ያስገባቸው ዘንድ ግድ አላቸው፡፡ በብዙ ማስፋራራትና ቁጣ ሊያስገድዳቸው ቢሞክርም አቡነ ሳዊሮስ ግን ቁጣውንና ማስፈራራቱን አልፈሩም፡፡ ንጉሡም አስገድዶ ወደረከሰች ሃይማኖቱ ሊያስገባቸው እንዳልቻለ ባየ ጊዜ አቡነ ሳዊሮስን በስውር ሊገድላቸው ፈለገ፡፡ ንግሥቲቱም ከሃዲው ንጉሡ ባሏ አቡነ ሳዊሮስን በሥውር ሊገድላቸው እንደሆነ ስትሰማ አባን ከአንጾኪያ አገር ወጥተው በመሄድ ራሳቸውን እንዲያድኑ ነገረቻቸው፡፡ አቡነ ሳዊሮስ ግን መሸሽ አልፈለጉምና ‹‹ክብር ይግባውና ስለ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሞት የተዘጋጀሁ ነኝ›› ብለው ለንግሥቲቱ መለሱላት፡፡ ነገር ግን ብዙ ምእመናንና ንግሥቲቱ አጥብቀው ስለለመኗቸው ጻደቁ ወጥተው ወደ ግብፅ አገር ተሰደዱ፡፡ ከምእመናንም አብረዋቸው የተሰደዱ አሉ፡፡
ከሃዲውም ንጉሥ አቡነ ሳዊሮስን በስውር ሊገድላቸው አስቦ ይዘው እንዲያመጧቸው ወታደሮቹን ላካቸው ነገር ግን አላገኟቸውም፡፡ አቡነ ሳዊሮስን ጌታችን ስለሰወራቸው የንጉሡ ጭፍሮች ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ እሳቸው በጭፍሮቹ አጠገብ እየተጓዙ ጭፍሮቹ ግን አያዩአቸውም ነበር፡፡ ጭፍሮቹም በፍለጋ ሲጓዙ ከአቡነ ሳዊሮስ ጋር በአንድ ቦታ የሚያድሩበት ጊዜም አለ ነገር ፈጽሞ አላዩአቸውም፡፡ እግዚአብሔር አቡነ ሳዊሮስን ለምእመናን ጥቅም ሲል አሁን እንዲሞቱ አልፈቀደም ነበርና ጭፍሮቹም ፈልገው ባጧቸው ጊዜ ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡
አቡነ ሳዊሮስም ግብፅ አገር ከደረሱ በኋላ ከአንደኛው ገዳም ወደ አንደኛው ገዳም አንድ ተራ መነኩሴ መስለው በስውር የሚዘዋወሩ ሆኑ፡፡ በየሄዱበትም በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ምእመናንን የሚያጠነክሩ ሆኑ፡፡ እግዚአብሔርም በእጆቻቸው ድንቅ ድንቅ የሆኑ ብዙ ተአምራትን አደረገ፡፡ በአንዲት ዕለት አባታችን ወደ አስቄጥስ ገዳም በደረሱ ጊዜ በመጻተኛ መነኩሴ አምሳል ወደ አቡነ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ገቡ፡፡ በዚያም ቄሱ ዕጣንንና ቁርባንን ሊያሳርግ ጀመረና እንደ ሥርዓቱ እየዞረ አጠነ፡፡ ሐዋርያት የጻፏቸውን ቅዱሳት መጻሕፍትና መልዕክቶቻውን የከበረ ወንጌልንም ካነበቡ በኋላ ቄሱ እጆቹን ታጥቦ ማኅፈዱን በገለጠው ጊዜ በጻሕሉ ውስጥ የቁርባኑን ኅብስት አላገኘውም፡፡ ደንግጦም መሪር ልቅሶን አለቀሰ፡፡ ከዚያም ወደ ሕዝቡ ተመልሶ ‹‹ወንድሞቼ እነሆ የቁርባኑ ኅብስት ተሰውሮ በጻሕሉ ውስጥ አላገኘሁትምና ይህ የሆነው በእኔ ኃጢአት ወይም በእናንተ ኃጢአት እንደሆነ ዐላወቅሁም›› አላቸው፡፡ ያንጊዜም የእግዚአብሔር መልአክ ለቄሱ ተልጦለት ‹‹ይህ የሆነው በአንተ ኃጢአት ወይም በሕዝቡ ኃጢአት አይደለም ነገር ግን ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስ እያለ መሥዋዕትን ለማሳረግ በመድፈርህ ነው›› አለው፡፡
ቄሱም በጣም ደንግጦ መልአኩን ‹‹ጌታዬ ሆይ! ሊቀ ጳጳሳት መኖሩን ዐላወቅሁም›› አለው፡፡ መልአኩም ተራ የመነኩሴ ልብስ ለብሰው ወደቆሙት ወደ አባ ሳዊሮስ አመለከተው፡፡ ቄሱም ወደ አቡነ ሳዊሮስ ሄዶ ከእግራቸው በታች ሰገደና ቡራኬ ተቀበለ፡፡ አባታችንም የጀመረውን ቅዳሴውን እንዲፈጽም ቄሱን አዘዙት፡፡ እርሳቸውንም በታላቅ ክብር ወደ ቤተ መቅደሱ አስገቧቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ቄሱ ወደ መሠዊያው በወጣ ጊዜ ተሰውሮበት የነበረውን የቁርባኑን ኅብስት በጻሕሉ ውስጥ መልሶ አገኘው፡፡ በዚህም ካህናቱና ሕዝቡም ሁሉ ምስጉን የሆነ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡
የቁርባኑም ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ካህናቱና ሕዝቡ ከአቡነ ሳዊሮስ ቡራኬ ተቀበሉ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባታችን አቡነ ሳዊሮስ ከአንደኛው ገዳም ወደ አንደኛው ገዳም አንድ ተራ መነኩሴ መስለው በስውር እየተዘዋወሩ በየሄዱበትም ምእመናንን እያጠነከሩ በእጆቻቸውም ብዙ ተአምራትን እያደረጉ ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡
በመጨረሻም ስካ ወደሚባል አገር ሄደው ስሙ ዶራታዎስ ከሚባል ደግ ምእመን ባለጸጋ ሰው ዘንድ ተቀምጠው ሳለ ጌታችን በእጆቻቸው ብዙ አስገራሚ ተአምራትን አደረገ፡፡ በመጨረሻም በዚህች ስካ በምትባል አገር የካቲት 14 ቀን እስካረፉ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ሁሉንም አስተማሯቸው፡፡ በኋላም ታኅሣሥ 10 ቀን ምእመናን ቅዱስ ሥጋቸውን ዝጋግ ወደምትባል ገዳም አፍልሰውታል፡፡ ጥቅምት 2 ቀን ደግሞ አባታችን ተሰደው ወደ ግብፅ አገር የመጡበት ዕለት ነው፡፡ ከእስክንድርያ ውጭ ወደሆነቸ ደብረ ዝጋግ ገዳም ቅዱስ ሥጋቸው በፈለሰበት ወቅት እንዲህ ሆነ፡- ቅዱስ ሳዊሮስ ስሓ በምትባል አገር አምላክም በሚወድ ደገኛ ክርስቲያን ባለጸጋ ስሙ ዱራታዎስ በሚባል ሰው ዘንድ ባረፉ ጊዜ ከምእመናን ሰዎች ጋር ወደ በመርከብ አሳፍሮ ላከው፡፡ ወደ ደቡባዊ ባሕረ ቅርጣስ በደረሱ ጊዜ ግን መርከባቸውን ማንቀሳስ ፈጽሞ አልተቻላቸውም፡፡
ከዚያም ወደ ደብረ ዝጋግ አድርሰው ያ ባለጸጋ ዱራታዎስ በሠራለት ቦታ ውስጥ አኖሩት፡፡ በግብጽ አገርም ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡ እግዚአብሔርም ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራቶችን ከሥጋቸው ገለጠ፡፡ ቅዱሱ በሕይወት ሳሉ የወለቀች አንዲት ጥርሳቸውን አንዱ መነኮስ አግኝቶ በጨርቅ ጠቅልሎ በገዳሙ አስቀምጧት ነበርና እርሷም ለሕሙማን ሁሉ ፈውስን የምትሰጥ ሆነች፡፡ እነርሱም ወደ እስክንድርያ ያመጧትና በሕሙማን ላይ ሲያኖሯት ሕሙማኑ ፈጥነው ይድናሉ፡፡ እግዚአብሔርም ቅዱስ ሳዊሮስን በሕይወታቸው ካሉበት ጊዜ ይልቅ በሞት ካረፉ በኋላ እጅግ ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል፡፡

ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባት አባ ኒቆላዎስ አረፈ፡፡ አባቱ ኤጲፋንዮስ እናቱ ዮና ይባላሉ፡፡ እርሱም ሜራ በምትባል አገር እጅግ ባለጸጎች ሆነው የሚኖሩ ደጋግ ሰዎች ናቸው፡፡ እጅግ ባለጸጎች ቢሆኑም ልጅ ስላልነበራቸው እያዘኑ እግዚአብሔርን በመለመን ብዙ ዘመን ኖሩ፡፡ የመውለጃ ጊዜአቸውም ባለፈ ጊዜ ስለ ልጅ መለመናቸውን አቆሙ፡፡ እግዚአብሔር ግን በመጨረሻ ዘመናቸው የተባረከ ይህን ኒቆላዎስን ሰጣቸው፡፡ እግዚአብሔርም በልጃቸው ላይ የጽቅን ሥራ ገለጠ፡፡ ልጁ ገና እንደተወለደ ተነሥቶ በእግሮቹ ቆሞ በሰዎች መካከል ለሁለት ሰዓት ያህል ቆመ፡፡ ይህም ለመንደሳዊ ሥራ የተነሣ ቅዱስ መሆኑን ያጠይቃል፡፡ በሕፃንነቱም የሐዋርያትን ትምህርት ፈጽሞ ረቡንና ዓርብን በመጾም እስከ ዘጠኝ ሰዓት የእናቱን ጡት አይጠባም ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ወላጆቹ ለመምህር ሰጥተውት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ ተማረ፡፡ ወደ ገዳምም ገብቶ ማንም እንደ እርሱ ሊሠራው የማይችለውን ጽኑ ገድል ተጋደለ፡፡ ዘጠኝ ዓመትም በሆነው ጊዜ ቅስና ተሾመና ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ማድረግ ጀመረና ሕመምተኞችን ሁሉ የሚፈውሳቸው ሆነ፡፡ አንድ ባለጸጋ በሀገሩ ነበር፡፡ እርሱም የዕለት እራት እስኪያጣ ድረስ ፈጽሞ ድኃ ሆነ፡፡ አራት ሴት ልጆችም ነበሩትና እነርሱን ስለድኅነቱ የሚያገባቸው ጠፋ፡፡ ባለጸጋ የነበረውም ሰው የዝሙት ሙት ሠርቶ በዚያ ልጆቹ እያመነዘሩ በዝሙት ዋጋ ይኖሩ ዘንድ ይህንን የረከሰ ሀሳብ ሰይጣን አሳሰበው፡፡
እግዚአብሔር ግን የዚያን ባለጸጋ የነበረ ሰው ክፉ ሀሳብ ለአባ ኒቆላዎስ ገለጠለት፡፡ አባ ኒቆላዎስም ከአባቱ ገንዘብ ላይ መቶ የወርቅ ዲናር ወስዶ በሌሊት ማንም ሳያየው ወደዚያ ባለጸጋ ወደነበረው ሰው ቤት ሄዶ በበሩ ሥር አስቀምጦለት ተመለሰ፡፡ ባለጸጋ የነበረውም ሰው ወርቁን ወስዶ እጅግ ደስ ብሎት ታላቂቱን ልጁን አጋባት፡፡ አሁንም ለ2ኛ ጊዜ አባ ኒቆላዎስ መቶ የወርቅ ዲናር አስቀመጠለትና ሰውየውም ሌላኛዋን ታላቅ ልጁን ዳራት፡፡ አባ ኒቆላዎስም ለ3ኛ ጊዜ እንዲሁ አደረገ፡፡ ባለጸጋውም በስተመጨረሻ ‹‹ይህን የሚያደርግልኝ የእግዚአብሔርን ሰው ማየት አለብኝ›› ብሎ ቁጭ ብሎ እያደረ በሌሊት የሚመጣውን መጠበቅ ጀመረ፡፡ አባ ኒቆላዎስም ለ4ኛ ጊዜ ወርቁን ሲያኖርለት አገኘውና ወድቆ ሰገደለት፡፡ ‹‹ከገንዘብና በኃጢአት ከመውደቅ አድነኸኛልና ዋጋህ ፍጹም ነው›› ብሎ አመሰገነው፡፡ አባ ኒቆላዎስ በአካባቢው ባለው ዛፍ ላይ አድረው በሰውየው ላይ መከራ ያመጡበትን አጋንንት አባረራቸው፡፡ በዚያ የነበሩ ሕመምተኞችንም አዳናቸው፡፡ ዳግመኛም ጥቂት እንጀራን አበርክቶ ብዙ ሕዝቦችን አጠገባቸው፡፡ እጅግ የበዛ ትራፊም ተመልሶ ተነሣ፡፡
ከዚህም በኋላ አባ ኒቆላዎስ ኤጲስቆጶስነት ከመሾሙ አስቀድሞ የክህነት ልብስንና ብርሃንን የለበሰ ሰው በዙፋን ላይ ተቀምጦ በራእይ አየና ‹‹ይህንን የክህነት ልብስ ለብሰህ በዙፋኑ ተቀመጥ›› የሚል ድምጽ ሰማ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜም እመቤታችን ተገልጣለት የክህነትን ልብስ ስትሰጠው ጌታችንም የከበረች ወንጌልን ሲሰጠው አየ፡፡ ከዚህም በኋላ የሜራ አገር ኤጲስቆጶስ በሞት ባረፈ ጊዜ የታዘዘ መልአክ ለሮሜው አገር ሊቀ ጳጳስ ተገለጠለትና ስለ አባ ኒቆላዎስ መልኩንና ስሙን በዝርዝር ነገረው፡፡ እርሱም ለሕዝቡ ሁሉ ነገራቸው አባ ኒቆላዎስን ወስደው በሜራ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት፡፡
ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ አምለኮ ጣዖትን በግዛቱ ሁሉ ሲያውጅና የክርስቲያኖችን ደም እንደውኃ ሲያፈስ አባ ኒቆላዎስ ደግሞ ክርስቲያኖችን ያስተምራቸውና በሃይማኖት ያጸናቸው ነበር፡፡ ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ አባ ኒቆላዎስን ይዞ እጅግ ብዙ አሠቃየው፡፡ ነገር ግን ጌታችን ከመከራው ሁሉ እያዳነው ከቁስሉም ይፈውሰው ነበር፡፡ ንጉሡም እጅግ ቢያሠቃየውም ቅዱሱ ደግሞ መልሶ ጤነኛ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ በዚህም ማሠቃየት ቢሰለቸው ወደ እሥር ቤት ጨመረው፡፡ እግዚአብሔርም ዲየቅልጥያኖስን አጥፍቶት ጻደቁን ቆስጠንጢኖስን እስካነገሰው ድረስ አባ ኒቆላዎስ በእሥር ቤት ብዙ ዓመታት ኖረ፡፡ ቆስጠንጢኖስም የታሰሩትን ቅዱሳን ሁሉ በፈታቸው ጊዜ አባ ኒቆላዎስ ከእሥር ወጥቶ ወደ መንበረ ጵጵስናው ተመለሰ፡፡ ሕዝቡንም ስለቀናች ሃይማኖት አስተማራቸው፡፡ ሃይማኖታቸው የቀና እጅግ የከበሩ 318 ቅዱሳን በአርዮስ ጉዳይ በተሰበሰቡ ጊዜ ይህ ቅዱስ አባት አባ ኒቆላዎስ ከእነርሱ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እርሱም ከሌሎቹ ቅዱሳን ጋር ሆኖ አርዮስን አሳዶ የቀናች ሃይማኖትን ደነገገልን፣ ሥርዓትን ሠራልን፡፡ እርሱም ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡

ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባት አባ ጥዋሽ አረፈ፡፡ ይኽም ቅዱስ ከልጅነቱ ጀምሮ ድንግል ሆኖ በምንኩስና በታላቅ ተጋድሎ የኖረ ነው፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ወደ እስክንድርያ ሲጓዝ በመንገድ ላይ አንዲት አይሁዳዊት ሴት ስታለቅስ አገኛትና ምን እንደሆነች ጠየቃት፡፡ እርሷም ‹‹ክርስቲያን መሆን እሻ ነበር›› አለችው፡፡ አባ ጥዋሽ የነፍሱን ጥቅም አስቦ ሊተዋት ነበር ግን ሴቲቱ መዳን እየፈለገች ቢተዋት በእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ በደል እንዳይሆንበት ከእርሱ ጋር ወሰዳትና የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃት፡፡
ከዚህም በኋላ አባ ጥዋሽ ከሴቲቱ ጋር ሆኖ በየገበያው ቦታ ሁሉ እየዞሩ ለነዳያን ይመጸውቱ ጀመር፡፡ የእስክንድርያ መነኮሳትም እርሷ ሚስቱ እንደሆነች አስበው በዚህ ተሰነካከሉበት፡፡ ይዘውትም ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ዮሐንስ ዘንድ አቀረቡት፡፡ አባ ዮሐንስም ሁለቱን ተያይተው እንዲታሰሩ አዘዙ፡፡ በዚያችም ሌሊት ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ዮሐንስ በሕልማቸው አባ ጥዋሽ የቆሰለ ጀርባውን እያሳያቸው ‹‹ያለበደሌ ለምን አቆሰልከኝ?›› ሲላቸው ተመለከቱ፡፡ አባ ዮሐንስም በነቁ ጊዜ አባ ጥዋሽን አስመጥተው በግርፋት ብዛት የቆሰለ ጀመርባውንና ፍጹም ድንግል መሆኑን አይተው እጅግ አዝነው አለቀሱ፡፡ ‹‹ይቅር በለኝ›› ብለው በፊቱ ወደቁ፡፡ ከዚያም አባ ጥዋሽን ያመጡትንና የደበደቡትን ሰዎች ከማዕረጋቸው አውርደው ለ3 ዓመታት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከመቀበል ከለከሏቸው፡፡ ካሳ ይሆነውም ዘንደ ለአባ ጥዋሽ ብዙ ገንዘብ ቢሰጡት እርሱ ግን ምንም ሳይቀበል ወደ በዓቱ ተመልሶ ሄዶ ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ዕለት ዐረፈ፡፡

ይኽችም ቅድስት ከቁስጥንጥንያ አገር እጅግ ከከበሩ ወገኖች የአንዱ ልጅ ናት፡፡ ለአንድ ለከበረ ሰው ልጅ በታጨች ጊዜ አባቷን ‹‹አባቴ ሆይ! አስቀድሜ ወደ ቤተ መቅደስ ሄጄ እሰግድ ዘንድ ፍቀድልኝ በምመለስበት ጊዜ እግዚአብሔር እንደፈቀደ ይሁን›› አለችው፡፡ አባቷም ‹‹አስቀድመሽ ወደ ባልሽ ግቢ፣ ሠርግሽ ከተፈጸመ በኋላ ከእርሱ ጋር ወደ ወደድሽው ሄደሽ ስዕለትሽን ትፈጽሚያለሽ›› አላት፡፡ እርሷም መልሳ ‹‹በድንግልናዬ ሳለሁ ወደዚያች የከበረች ቦታ ሄጄ ልጸልይ ለእግዚአብሔር ቃል ገብቻለሁና ቃሌን ብዋሽ ፈጣሪ በእኔ ላይ ይቆጣል›› ስትለው አባቷ ከሚያገለግሏት ወንዶችና ሴቶች አሽከሮች ጋር ለምጽዋትም የምትሰጠው 300 የወርቅ ዲናር ሰጥቶ ላካት፡፡
ሱርስትም እዚያ በደረሰች ጊዜ የከበሩ ቦታዎችን ሁሉ እየዞረች ተሳለመች፣ ወደ ግብጻውያን ገዳምም በደረሰች ጊዜ አንድ አረጋዊ መነኩሴ ማቅ ለብሶ አገኘችውና የልቧን ሀሳብ ሁሉ ማለትም ልትመነኩስ እንደምትፈልግ ነገረችው፡፡ እርሱም ‹‹የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን›› አላት፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሊሄዱ በተዘጋጁ ጊዜ ወደ ስውር ቦታ ገብታ ለወላጆቿ ‹‹እኔ ሰውነቴን ለእግዚአብሔር አቅርቤያለሁ አታገኙኝምና አትፈልጉኝ›› ብላ ደብዳቤ ጻፈች፡፡ ደብዳቤውንም በልብሷ አሥራ ከዕቃ ውስጥ አኖረችው፡፡ ሰዎቹም ከእነርሱ ጋር አብራ የምትሄድ መስሏቸው ዕቃ ጭነው በቀደሟት ጊዜ አንዱን አገልጋይ ይዛ አስቀረችውና ‹‹ወደ ጎልጎታ ገብቼ ልጸልይ እሻለሁና›› ብላ ምሥጢሯን እንዲጠብቅ ነገረችው፡፡
ከዚህም በኋላ ወደዚያ ሽማግሌ መነኩሴ ዘንድ ተመልሳ የያዘችውን 300 የወርቅ ዲናር ለድኆችና ጦም አዳሪዎቸ እንዲያከፋፍለው ሰጠችውና ያመነኩሳት ዘንድ ለመነችው፡፡ እርሱም ጽናቷን አይቶ ፈቃደ እግዚአብሔርም መሆኑን ዐውቆ ራሷን ላጭቶ የምንኩስና ልብስ አለበሳት፡፡ እርሷም እግዚአብሔር ወደፈቀደላት ወደ አንዲት ዋሻ ሄዳ በዚያ በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመረች፡፡ በዚህም ጊዜ ዕድሜዋ ገና 12 ዓመት የነበረ ቢሆንም የሰውን ፊት ሳታይ በዚያች ዋሻ ውስጥ ለ27 ዓመታት በተጋድሎ ኖረች፡፡
ቃህራ ከሚባል አገር በገድል ሥራ የሚኖር ሲላስ የሚባል መነኮስ ነበር፡፡ በቀልሞን ዋሻ የሚኖር አንድ ጓደኛ መነኮስ አለውና ፋሲካ በደረሰ ጊዜ እርሱን ጎብኝቶ በረከት ለመቀበል ሄደ፡፡ በሄደም ጊዜ አላገኘውምና እርሱን ፍለጋ ተራራ ለተራራ ዞረ፡፡ በዚያም የእግር ዱካ አገኘና ዱካውን ተከትሎ በመሄድ መግቢያው ላይ ሲደርስ ‹‹የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ ባርከኝ›› አለ፡፡ ከውስጥም ያለው ድምጽ ስሙን ጠርቶት ‹‹ሲላስ ሆይ አንተ ካህን ነህና ልትባርከኝ ይገባል›› አለው፡፡ ሲላስም ወደ ውስጥ እንደገባ ቅድስት ሱርስትን አገኛት፡፡ እርሷም ምሥጢሯን ሁሉ በዝርዝር ነገረችው፡፡ ወዲያውም በሰላም ዐረፈች፡፡ ሲላስም በዚያች ዋሻ ውስጥ በክብር ገንዞ ቀበራት፡፡ ገድሏንም ጻፈላት፡፡

ቅዱስ ተላስስ ከነነዌ አውራጃ ከባቢሎን ሰዎች ወገን ነው፡፡ ጌታችንን በማመኑ ምክንያት ከሃዲው የፋርስ ንጉሥ ሳቦር ይዞት ብዙ አሠቀየው፡፡ ለአማልከቱም እንዲሠዋ ተላስስን ባስገደደው ጊዜ ቅዱሱ ግን አማልክቱን ረገመበት፡፡ ንጉሡም በተለያዩ የማሠቃያ መሣሪያዎች አሠቃየው፡፡ መቶ ጊዜ ካስገረፈው በኋላ ‹‹ተላስስ ሆይ! ከዚህ ሥቃይ እንድታርፍ ለአማልክት ሠዋ›› አለው፡፡ ቅዱስ ተላሰስስም ‹‹ፈጣሪዬ ስለሚጠብቀኝ ሥቃይህ ለእኔ አልታወቀኝም›› አለው፡፡ በዚህም ጊዜ ንጉሡ ቅዱስ ተላስስን ሁለት መቶ ጽኑ ግርፋትን ካስገረፈው በኋላ በዓይኖቹ ወስጥ የብረት ችንካሮችን ተክለው እጅግ አሠቃዩት፡፡ መናገር እስከማይችል ደረስ ምላሱንም ቆርጠው ካሠቃዩት በኋላ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነት ፍጻሜው ሆኖ የክብርን አክሊል ተቀዳጀ፡፡ ከዚህም በኋላ አልዓዛርን በንጉሥ ሳቦር ፊት አቀረቡት፡፡ ንጉሡ እርሱንም ‹‹ለአማልክት ሠዋ›› አለው፡፡ አልዓዛርም ‹‹ለረከሱ አማላክትህ አልሠዋም እኔስ ጌታዬን ፈጣሩዬን ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ እንጂ›› አለው፡፡ ንጉሡም ወዲያው ተናዶ ቅዱስ አልዓዛርን ወደ እቶን እሳት ውስጥ ወረወረው፡፡ ቅዱሱም በዚያው ሰማዕትነቱን ፈጸመ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages