ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥ 11 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥ 11

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ዐስራ አንድ በዚህች ዕለት ታላቁ አባት #ቅዱስ_አባ_በኪሞስ ዐረፈ፣ ታላቁ ሰማዕት #ቅዱስ_ገላውዲዮስ ልደቱ ነው፡፡


ታኅሣሥ ዐስራ አንድ በዚህች ዕለት ታላቁ አባት ቅዱስ አባ በኪሞስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይኸውም ቅዱስ ከደቡባዊ ግብጽ መጺል ከምትባል አውራጃ የተገኘ ታላቅ አባት ነው፡፡ እርሱም የአባቱን በጎች የሚጠብቅ እረኛ ነበር፡፡ ዕድሜውም 12 ዓመት በሆነው ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ በሰው አምሳል ተገለጠለትና ‹‹በአንድነት ሄደን እንመነኩስ ዘንድ ትሻለህ?›› አለው፡፡ በኪሞስም በዚህ ደስ ተሰኝቶ ሁሉቱም ተስማምተው አብረው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ገቡ፡፡ በዚያም ሦስት አረጋውያን መነኮሳት አገኙና አባ በኪሞስ ከእነርሱ ጋር 24 ዓመታትን ኖረ፡፡
ከዚህም በኋላ አባ በኪሞስ ከዚያ ተነሥቶ የሦስት ቀን ጎዳና ተጓዘና ሩቅ ወደሆነ በረሃ ሄደ፡፡ በዚያም ሰይጣናት በእሪያዎችና በዘንዶዎች አምሳል ሆነው መጡበት፡፡ ሊነክሱትም አፋቸውን ከፍተው በከበቡት ጊዜ እርሱ ግን የአጋንንት ሥራ መሆኑን ዐውቆ በእግዚብሔር ኃይል እፍቢልባቸው እንደትቢያ ተበተኑ፡፡ እርሱም ወንዝ አግኝቶ ሰባት ሰባት ቀን እየጾመ በዚያ ሦስት ዓመት ኖረ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ ላይ በእጁ ቴምር በተአምራት መልቶ ስለሚገኝ እርሱን ይመገባል፡፡ ቅዱሱም በሌሊት ሁለት ሺህ አራት መቶ ጊዜ በቀንም እንዲሁ ሁለት ሺህ አራት መቶ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ይጸልያል፡፡ ከዚህም በኋላ 40 40 ቀን እየጾመ 24 ዓመታትን በታላቅ ተጋድሎ ኖረ፡፡ አርባውም ቀን ሲፈጸም አንድ ጊዜ ይመገባል፡፡ ከዚህም በኋላ ቆዳው ከአንጥንቱ እስኪጣበቅ ድረስ አንድ ጊዜ እስከ ሰማንያ ቀን ጾመ፡፡ በዚህም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ አባ በኪሞስ የሚበላውንና የሚጠጣውን ሰማያዊ የሕይወት ምግብና መጠጥ አምጥቶ መገበው፡፡ ያንንም መልአክ ያመጣለትን ምግባ መጠጥ አባ በኪሞስ እስካረፈበት ጊዜ ድረስ ብዙ ዓመታት ሲመገበው ኖረ፡፡
በአንደኛውም ቀን በሌሊት ጌታችን ለአባ በኪሞስ ተገልጦለት ወደ አገሩ እንዲመለስ ነገረው፡፡ እርሱም ወደ ሀገሩ ተመልሶ በዚያች ትንሽ በዓት አበጅቶ መኖር ሲጅር ብዙዎች ወደ እርሱ መጥተው ፈውስን የሚያገኙ ሆኑ፡፡ እርሱም ጣዕም ባለው አንደበቱ ወንጌልን እያስተማራቸው ድውያንንም ሁሉ የሚፈውሳቸው ሆነ፡፡ በአንዲት ዕለትም የታዘዘ መልአክ መጥቶ አባ በኪሞስን ነጥቆ ወስዶ ወደ ኤፍራጥስ ምድር አደረሰው፡፡ የዚያች አገር ሰዎች ሕግን በመተላለፍ ከእውነተኛ ሃይማኖት ወጥተው ነበርና፡፡ አባ በኪሞስም አስተምሮ ወደ ቀናች ሃይማኖትና ወደ በጎ ምግባር መለሳቸውና ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ በአንዲት ዕለትም ሸጦ የዕለት ምግቡን ያገኝ ዘንድ አገልግሎችን ተሸክሞ ወደ ከተማ ሲሄድ በጎዳና ላይ ደክሞት አገልግሎቹን አስቀምጦ ያርፍ ዘንድ ተቀመጠ፡፡ ወዲያውም ከአገልግሎቹ ጋር የእግዚአብሔር ኃይል ተሸክሞ ወስዶ ከሚሸጥበት ቦታ አደረሰው፡፡
በአንደኛውም ቀን ታላቁ አባት አባ ሲኖዳ ከፍተኛ የዕንቁ ባሕርይ ምሰሶ በራእይ አየና ‹‹ይህ ታላቅ ግሩም የሆነ ምሰሶ ምንድነው?›› ብሎ ደነገጠ፡፡ የታዘዘ መልአክ ተገለጠለትና ‹‹ይህ አባ በኪሞስ ነው›› አለው፡፡ አባ ሲኖዳም አባ በኪሞስን ያገኘው ዘንድ ወደ እርሱ አገር በእግሩ ተጓዘ፡፡ ከዚያም በፊት ከቶ አላየውም ነበር፡፡ ሄዶም ባገኘው ጊዜ ሁለቱ ቅዱሳን ሰላምታ ተሰጣጡና የእግዚአብሔርን ነገር እየተነጋገሩ አብረው እየጸለዩ ጥቂት ቀን ቆዩ፡፡ በአንዲት ዕለት አብረው ሲጓዙ አንድን የሞተ ሰው ራስ ቅል አገኙና አባ ሲኖዳ በበትሩ ነቅነቅ አደረገውና ‹‹ምውት ሆይ! ያየኸውን ትነግረን ዘንድ በጌታችን ስም ተነሥ›› አለው፡፡ ወዲውም ነፍሱ ወደ ዐፅሙ ተመልሳ ሥጋ ለብሶ ተነሣና ሰገደላቸው፡፡ በሲኦል ያየውንም ሁሉ በዝርዝር ነገራቸው፡፡ በየወገናቸው በሲኦል ውስጥ የሚሠቃዩትንና እርሱም የማያምን አረማዊ መሆኑን ነገራቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ክብር ይግባውና በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያመኑ ትእዛዙን ግን ያልጠበቁ በአሕዛብ ሥራባ በአረማውያን ርኩሰት የኖሩ በሲኦል ከእኛ በታች የሚኖሩ ክርስቲያኖች አሉ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ቅዱሳኑም ‹‹በል ተመልሰህ ተኛ›› አሉትና እንቀድሞው ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ሲኖዳ አባ በኪሞስን ተሰናብቶ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡
አባ በኪሞስም የዕረፍቱ ጊዜ ሲደርስ አገልጋዩን ጠርቶ የሥጋውን መቅበሪያ ቦታ አሳየው፡፡ ወዲያውም በሆድ ዝማ ሕመም ጥቂት ታመመና፡፡ ቅዱሳንም ከተለያየ ቦታ በአንድነት ወደእርሱ ሲመጡ በመንፈስ ተመለከተ፡፡ቅዱሱ 58 ዓመት በገዳም በምንኩስና ሥራ ተጠምዶ ኖሮ በሰባ ዓመቱ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ፡፡ ቅዱሳን መላእክትም በዝማሬ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም አሳረጓት፡፡

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዲዮስ ልደቱ ነው፡፡ ገላውዴዎስ ማለት ‹‹ዕንቈ ጳዝዮን›› ማለት ነው፡፡ የመላእክት አርአያ ያለቅ ቅዱስ ገላውዴዎስ አባቱ አብጥልዎስ የሮሙ ንጉሥ የኑማርያኖስ ወንድም ነው፡፡ አባቱን የአንጾኪያ ሰዎች እጅግ ይመኩበትና ይወዱት ነበር፡፡ በሕይወት እያለም በጦርነት ድል ሲያደርግ የሚያሳይ ሥዕሉን በከተማው ላይ አሠርተው ያከብሩት ነበር፡፡ ልጁ ቅዱስ ገላውዴዎስ ግን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየተማረ አደገ፡፡ የሮሙ ንጉሥም ዜናውን ሰምቶ ሊያየው ወደደና ልጁን እንዲልክለት መልእክት ላከ፡፡ ሄዶ ሲያየውም ንጉሡ ከነሠራዊቱ ወጥቶ በክብር ተቀበለው፡፡
ጣዖት አምላኪ የሆኑ የቁዝና የሌሎችም ሀገሮችን ቅዱስ ገላውዴዎስ ድል እያደረጋቸው ጣዖቶቻቸውንም ይሰባብርባቸው ነበር፡፡ ወደ አንጾኪያም በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስ ጌታችንን ክዶ ጣዖት ማምለክ መጀመሩን ባየ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ ከቅዱስ ፊቅጦርም ጋር ሆነው የመጻሕፍትን ቃል ዕለት ዕለት ያነቡ ነበር፡፡ ሁለቱም ስለ ጌታችን ክብር ሰማዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሱ ዘንድ በምክር ተስማሙ፡፡ ሰይጣንም በሽማግሌ አምሳል ተገልጡ ያዘነላቸው በመምስል ‹‹ልጆቼ ሆይ መልካም ጎልማሶች ናችሁ፣ የነገሥታት ልጆችም ናችሁ፣ እኔ ስለ እናንተ አዝንላችኋለሁ ስለዚህም ከንጉሡ ጋር ተስማምታችሁ አማልክቶቹን እያጠናቸሁ ትእዛዙንም እየፈጸማችሁ ኑሩ፡፡ ነገር ግን ክርስቶስን በቤታችሁ አምልኩት ይህ ዲዮቅልጥያኖስ ግን እጅግ ጨካኝና ኃይለኝ ነው›› እያለ መከራቸው፡፡ እግዚአብሔርንም ይህን የሚናገራቸው ሰይጣን መሆኑን ገለጸላቸውና ‹‹አንተ የሐሰት አባት ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ሀሳብ ትቃረናለህ›› ብለው በገሠጹት ጊዜ መልኩን ለውጦ ጥቁር ባሪያ ሆነ፡፡ ‹‹እነሆ ከንጉሡ ጋር አጣልቼ ደማችሁን እንዲፈስ አደርገዋለሁ›› ብሎ ወደ ከሃዲው ንጉሥ ወደ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ ሄዶ ‹‹ፊቅጦርንና ገላውዴዎስን ካልገደልካቸው በአንተ ላይ ይነሱብሃል፣ አንተንም ገድለው መንግሥትህን ይወስዳሉ፣ እነርሱም የመንግሥት ልጆች መሆናቸውን ዕወቅ›› አለው፡፡
ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም ቅዱስ ገላውዴዎስን አስጠርቶ የአባቱን ሹመት እንደሚሾመው ቃል ከገባለት በኋላ ለጣዖቱ እንዲሠዋ አዘዘው፡፡ ቅዱስ ገላውዴዎስ ግን በድፍረት ጣዖቱንና ንጉሡን ሰደባቸው፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር አባት ኅርማኖስ የተባለው ባለሟሉ ‹‹እንደ ልጄ ፊቅጦር ዐመፀኛ ነውና ወደ እስክንድርያ ልከነው በዚያ እንዲገድሉት እናድርግ›› ብሎ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስን መከረው፡፡ አሠቃይተው እንዲገድሉትም ከደብዳቤ ጋር አድርገው ወደ እንዴናው ሀገር ገዥ ወደ ጨካኙ አርያኖስ ላኩት፡፡
አርያኖስም ቅዱስ ገላውዴዎስን ባየው ጊዜ ደንግጦ በክብር ተቀበለው፡፡ እጅ ነሥቶም ከሳመው በኋላ ‹‹ጌታዬ ስለምን የንጉሡን ትእዛዝ ትተላለፋለህ?›› እያለ መከረው፡፡ ቅዱስ ገላውዴዎስም ‹‹ንጉሡ ያዘዘህን ትእዛዝ ልትፈጽም እንጂ በነገርህ ልታስተኝ አልተላኩም›› አለው፡፡ መኮንኑም እስኪቆጣ ድረስ ብዙ ጊዜ እያባበለው ተነጋገሩ፡፡ ከዚህም በኋላ አርያኖስ እጅግ ተቆጣና በያዘው ጦር ወግቶ ቅዱሱን ገደለው፡፡ ቅዱስ ገላውዴዎስም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጀ፡፡ ምእመናንም የመከራው ዘመን እስኪፈጸም ቅዱስ ሥጋውን ወስደው ከቅዱስ ፊቅጦር ጋር በሣጥን አኖሩት፡፡ የቅዱስ ፊቅጦርም እናት ቅድስት ሶፍያ ወደ እንዴና ሀገር መጥታ የሁለቱን ቅዱሳን ሥጋቸውን ወደ አንጾኪያ ወስዳ በክብር አኖረችው፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት አና ጻድቃን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages