ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 14 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 14

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የአንጾኪያ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #አባ_ሳዊሮስ አረፈ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #አባ_ቄርሎስ አረፈ፣ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #አባ_ያዕቆብ አረፈ፡፡


በዚህችም ቀን ሃይማኖታቸው ለቀና ምእመናን መምህራቸው የሆነ የአንጾኪያ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት ሳዊሮስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ዘመዶቹ ከሮሜ ሀገር ናቸው አባቱም ስሙ ሳዊሮስ የሚባል ኤጲስቆጶስ ነው እርሱም ስለ ንስጥሮስ በኤፌሶን ከተማ ጉባኤ በሆነ ጊዜ ከሁለት መቶ አባቶች ኤጲስቆጶሳት ጋር መጣ በዚያም እንዲህ የሚለውን ራእይ አየ ከአንተ የሚወለድ ልጅህ ስሙም እንደ ስምህ ሳዊሮስ ተብሎ የሚጠራ እርሱ የቀናች ሃይማኖትን ያጸናታል።
ይህም ኤጲስቆጶስ በአረፈ ጊዜ ልጁን ሳዊሮስ ብለው ጠሩት ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆነውን ጥበብን ሁሉ ተማረ። ከመምህሩም ወጥቶ ወደ አንድ ቦታ ሲጓዝ በዋሻ ራሱን እሥረኛ አድርጎ የሚኖር ጻድቅ ሰው ተገናኘው በእርሱም ደስ ብሎት የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሃይማኖታቸው ለቀና ምእመናን መምህራቸው የሆንክ ሳዊሮስ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው አለው ሳዊሮስም ከቶ ሳያውቀው በስሙ በጠራው ጊዜ የሚደረግለትንም ከመሆኑ አስቀድሞ በመናገሩ አደነቀ።
ከዚህም በኋላ ሳዊሮስ ትሩፋት በመሥራት አደገ መልካም ስም አጠራሩና ዜናው ተሰማ በአባ ሮማኖስም ገዳም መንኵሶ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ ለትሩፋትም ሥራ እጅግ የተጠመደ ሆነ የከበረ ወንጌል በተራራ ላይ የተሠራች መንደር መሠወር አትችልም እንዳለ ዜናው በሁሉ ዘንድ ተሰማ።
የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳትም በአረፈ ጊዜ አዋቂዎች ኤጲስቆጶሳት ይህን የከበረ ሳዊሮስን ይሾሙት ዘንድ ተስማምተው ያለ ውዴታው ወስደው በአንጾኪያ ሀገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በሹመቱም እስከ ዓለም ዳርቻ ያለች ቤተ ክርስቲያን ብርሃን ሆነላት በሀገሮች ሁሉ ወዳሉ መናፍቃን ከሀድያን ትምህርቱ በሚደርስ ጊዜ ሁለት አፍ እንዳለው ስለታም ሰይፍ ሥራቸውን ይበጥሳልና።
ከጥቂት ቀኖችም በኋላ አማኒው ንጉሥ ሙቶ በርሱ ፈንታ ስሙ ዮስጥያኖስ የሚባል መናፍቅ ነገሠ ንግሥቲቱ ሚስቱ ግን ሃይማኖቷ የቀና ነው ስሟም ቴዎድራ ይባላል። ንጉሡም የኬልቄዶን ወደሆነች ወደረከሰች ሃይማኖቱ ይህን የከበረ አባት ያስገባው ዘንድ ያስፈራራው ነበር እርሱ ግን ፈርቶ አይታዘዝለትም ቁጣውንም የሚፈራ መስሎት በእርሱ ላይ አብዝቶ ተቆጣ ቍጣውንም ባልፈራ ጊዜ በሥውር ሊያስገድለው መከረ ንግሥቲቱም አውቃ ከንጉሡ ፊት ይሸሽ ዘንድ ሊቀ ጳጳሳቱን መከረችው እርሱም በሥውር ወጥቶ ገለል አለ እግዚአብሔር የዚህን አባት ሞት አልፈቀደምና ስለ ምእመናንም ጥቅም ጠበቀው ።
በአንድ ተራ መነኵሴ አምሳል ሁኖ በቦታዎችና በገዳማት የሚዘዋወርና ምእመናንን የሚያጠናክራቸው ሆነ ስካ በሚባል አገርም ስሙ ዶርታኦስ ከሚባል ደግ ምእመን ባለ ጸጋ ሰው ዘንድ ተቀምጦ ሳለ ጌታችን በእጆቹ ብዙ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ ስካ በተባለ ሀገርም እስከ አረፈ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ሁሉንም ያስተምራቸው ነበር ከዚህም በኋላ ወደ ዝጋግ ገዳም አፈለሱት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የካቲት ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት ቄርሎስ አረፈ፡፡ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባ አምስተኛ ነው። ይህም አባት ፍዩም ከምትባል ሀገር ነው በእርሷም ቅስና ተሹሞ ኖረ ከዚህም በኋላ ከዚያ ለቆ ከምስር ከተማ ውጭ ወደ ሆነች የኢትዮጵያውያን የጕድጓድ ውኃ ወዳለበት ወደ ቅዱስ ፊቅጦር ገዳም ደረሰ በውስጡም ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ ብዙ ዘመናት ኖረ።
የዕውቀቱና የቅድስናው ዜና በተሰማ ጊዜ ያለ ውዴታው ይዘው በእስክንድርያ ሀገር ሊቀ ጵጵስና ሾሙት መንጋውንም በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ በቊርባንና በጸሎት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊሠሩት የሚገባቸውን ለካህናት ሥርዓትን ሠራ። በሹመቱም ሰባት ዓመት ከዘጠኝ ወር ከሃያ ሰባት ቀን ኑሮ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት አባ ያዕቆብ አረፈ። እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ኃምሳኛ ነው።
ይህም አባት እልመቱዝ የተባለ የግብጽ ንጉሥ በነገሠ በዐሥራ ሰባት ዓመት ተሾመ እርሱም ለመኰንኑ ለወልደ ኀሮን ረሽድ ወንድም የሆነ ነው በዚህም አባት ዘመን የአስቄጥስ ገዳማት ታድሰው መነኵሳቱ ወደሳቸው ተመለሱ።
አፎን በሚባል አገር ስሙ መቃርስ የሚባል ሰው ነበረ ወደዚህ አባት ወደ ያዕቆብ መጥቶ ወደቤቱ በመሔድ ቤቱን ይባርክለት ዘንድ ለመነው እርሱም አብሮት ሔደ።
ታሞ የነበረ ልጁም ሞተ ወደ አባ ያዕቆብም አቅርቦ እንዲህ ብሎ ለመነው ከርሱ በቀር ልጅ የለኝምና አባቴ ሆይ ራራልኝ እርሱም እነሆ ሞተ ስለርሱ ወደ እግዚአብሔር ትማልድ ዘንደ እለምንሃለሁ አለው።
አባ ያዕቆብም እንደ እምነትህ ይሁንልህ አትፍራ አለው ሕፃኑንም ከአባቱ ተቀበሎ ታቀፈውና በላዩ ጸለየ በመስቀል ምልክትም አማተበበት ስለርሱም ወደ እግዚአብሔር ለመነ ጌታችንም ልመናውን ተቀበለው የሕፃኑ ነፍስ ተመልሳ ዐይኖቹን ገለጠ ከሞትም ድኖ ተነሣ አባቱንም ልጅህን ውሰድ የሞተ አይደለም ያንቀላፋ ሁኖ ነው እንጂ አለው።
የሕፃኑም አባት ይህን ድንቅ ሥራ በአየ ጊዜ እጅግ ፈራ የገንዘቡንም እኩሌታ ለምጽዋት ብሎ ሰጠው እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ልኮ ሃይማኖታቸው ለቀና ምእመናን ሁሉ ወደርሷ በመጡ ጊዜ መጠጊያ ትሆን ዘንድ ቤተ ክርስቲያንን ሠራበት።
የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ዲዮናስዮስም ወደ ምስር በመጣ ጊዜ ከአባ ያዕቆብ ጋር ተገናኝቶ ከእርሱ ዘንድ ጥቂት ቀኖች ተቀምጦ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። ይህም አባት ያዕቆብ በሹመቱ ዐሥር ዓመት ከስምንት ወር ከሦስት ቀን ኑሮ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages