ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 1 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 1

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት አንድ በዚህችም እለት የከበሩ መቶ ሃምሳ ኤጲስቆጶሳት የአንድነት ስብሰባ #በቍስጥንጥንያ_ጉባኤ አደረጉ፣ #አቡነ_እንድርያስ ዘደብረ ጽጌ ሰፍኣ አረፉ፣ የሰማዕታትም ፍጻሜ የሆነ የሊቀ ጳጳሳት #የቅዱስ_ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው።


የካቲት አንድ በዚህችም እለት የከበሩ የመቶ ሃምሳ ኤጲስቆጶሳት የአንድነት ስብሰባ በቍስጥንጥንያ ከተማ በታላቁ ቴዎዶስዮስ ዘመነ መንግሥት ተደረገ።
ስብሰባቸውም የሆነው በቍስጥንጥንያ አገር ላይ ሊቀ ጳጳሳት ስለ ሆነው የክብር ባለቤት የሆነ መንፈስ ቅዱስን በከፋች ሃሳቡ ፍጡር ነው ብሎ ስለ ካደው ስለ መቅዶንዮስ ሁለተኛም አንድ ገጽ ስለሚሉ ስለ ሰባልዮሳውያን ሦስተኛ ወልድ ከብቻው ሥጋ በቀር ነባቢት ለባዊት ነፍስን አልነሣም መለኮቱ በነፍስና በልቡና ፈንታ ሆነው ስለሚሉ ስለ አቡሊናርዮሳውያን ነው።
የእሊህ ከሀድ**ያንም ስሕተት ግልጽ በሆነ ጊዜ አሰባስቦ የአንድነት ጉባኤ ያደርግላቸው ዘንድ ንጉሥ ቴዎዶስዮስን ለመኑት እርሱም ቃላቸውን ተቀብሎ ወደ ሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ኢየሩሳሌምም ኤጲስቆጶስ ወደ እስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳትም መልእክትን ላከ ምሁራን የሆኑ ኤጲስቆጶሶቻቸውንም ይዘው እንዲመጡ አዘዛቸው።
እሊህም አባቶች በቍሰጥንጥንያ ከተማ ተሰበሰቡ የሮሜው ሊቀ ጳጳሳት ግን አልመጣም ምሁራን የሆኑ ሰዎችን ላከ እንጂ ከእሳቸውም ጋር በእጁ የጻፉትን ደብዳቤ ላከ።
የጉባኤውም ሊቀ መንበር የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጢሞቴዎስ ነው መቅዶንዮስንም ጠርቶ የረከሰች ሃይማኖቱን ይናገር ዘንድ አዘዘው ያ ከሀ*ዲም እንደ ፍጥረቶች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ የተፈጠረ ነው አለ። ጢሞቴዎስም መልሶ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሕይወቱ እንደሆነ አታውቅምን የእግዚአብሔርን ሕይወት እንዴት ፍጡር ታደርገዋለህ አሁንም ከዚች ከረከሰች ሃይማኖትህ ተመለስ ወደ ዘላለማዊ እሳተ ገሃነም ከመግባትህ በፊት ንስሓ ግባ አለው። እርሱ ግን ሰምቶ አልተመለሰም እነርሱም አወገዙት ከሹመቱም ሻሩት ከቤተ ክርስቲያንም አሳደዱት።
ከዚህም በኋላ ሰባልዮሳውያንን ጠርቶ እናንተስ ስለ ሃይማኖታችሁ ምን ትላላችሁ ተናገሩ አላቸው እነርሱም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ገጽ አንድ ህላዌ ነው በምንም በምን ሦስት አይሆንም አሉ።
አባት ጢሞቴዎስም መልሶ እንዲህ አላቸው በዮርዳኖስ ውስጥ ወልድ ቁሞ ሳለ በፀዓዳ ርግብ አምሳል መንፈስ ቅዱስ ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ አብም ከደመና ውስጥ ሁኖ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ብሎ አሰምቶ ተናገረ ያለው የወንጌል ቃል ተሻረን። እናንተ እንደምትሉት ከሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቃችሁት የክርስትናችሁ ጥምቀት ተሽሮአል አሁንም ክህደታችሁን ተዉ ብትመለሱም ይሻላችኋል። አርዮስም አስቀድሞ ወልድን ካደው ይህ መቅዶንዮስም መንፈስ ቅዱስን ካደው እናንተም የእነርሱ ተሳታፊዎች ሆናችሁ። እነርሱም ሰምተው አልተመለሱም የአንድነት ጉባኤም አውግዞ ከምእመናን አንድነት ለያቸው።
ከዚህም በኋላ ደግሞ ወልድ ነባቢት ለባዊት የሆነች ነፍስን አልነሣም ሥጋን ብቻ እንጂ የሚለውን የአቡሊናርዮስን ትምህርት አወገዙ።
እሊህ መቶ ኃምሳ የሆኑ ኤጲስ ቆጶሳት አባቶቻችንም በጸሎተ ሃይማኖት ላይ ጌታ አዳኝ በሚሆን ከአብ በሠረፀ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን እንሰግድለት እናመሰግነውም ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋራ በነቢያት አድሮ የተናገረ የሚለውን ጨመሩ።
ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እናምናለን። ኃጢአትን ለማስተሰረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን። የሙታንንም መነሣት የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ ተስፋ እናደርጋለን።
ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ አባቶቻችን የተናገሩት ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም እስከሚል ነው። እሊህ መቶ ኃምሳው አባቶች የተሰበሰቡት ስለ መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ስለርሱ የእርሱን ነገር አብራሩ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ መንግሥት ፍጻሜ በሰማዕትነት የሞተ ከሀ**ዲ አርዮ*ስንም ያወገዘ የሰማዕታትም ፍጻሜ የሆነ የሊቀ ጳጳሳት የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው።
ጻድቁ ቈስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ የጣዖታትን ቤቶች ሁሉ አፈረሰ ይችንም ቤተ ክርስቲያን ከእስክንድርያ ከተማ በምዕራብ በኩል በቅዱስ ጴጥሮስ ስም አነፃት በዛሬዋም ዕለት ከበረች በውስጧም ብዙ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ያቺም ቤተ ክርስቲያን እስ**ላሞች በግብጽ እስከ ነገሡበት ዘመን ኖረች ከዚያም በኋላ ቢሆን የታወቀች ሁና ትኖር ነበር ከዚህም በኋላ ፈረሰችና ምድረ በዳ ሆነች። የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ግን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጅ የተያዘችና የተጠበቀች ናት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም እለት አቡነ እንድርያስ ዘደብረ ጽጌ ሰፍኣ አረፉ፡፡ የእናታቸው ስም ቅድስት፡ዓመተ፡መንፈስ ቅዱስ የአባታቸው ስም ቅዱስ፡ ዘአማኑኤል ይባላል። የተወለዱትም ትግራ እንደርታ አካባቢ ነው። እናትና አባታቸው ልጅ ስሌላቸው ዘወትር ወደ እግዚአብሔር እየጸልዩ እናታቸውም "አንተ ደስ የሚያሰኝ ልጅ ካልሰጠኸኝ ማኅፀኔን ዝጋ" ይሉ ነበር። የእመቤታችንንም ዝክር በየወሩ ይዘክሩ፡ ነበር። እመቤታችንም አንድ ቀን ተገልጻ "ደስ የሚያሰኝ ልጅ ትወልዳላችሁ የሚወለደውም እኔ በተወለድኩበት ቀን ነው" አለቻቸው። አባታችን ልክ ግንቦት አንድ ቀን ሲወለዱ በእናት በአባታቸው ቤት ብርሃን ወረደ። አርባ ቀን ሲሞላቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ክርስትና ሊያስነሷቸው ወሰዷቸው ሲጠመቁም አባታችን "በአብ ስም አምናለሁ በወልድ ስም አምናለሁ በመንፈስ ቅዱስ አምናለሁ" አሉ። ስመ ክርስትናቸውም መሐረነ እግዚእ ተባሉ።
አቡነ እንድርያስ የስለት ልጅ ስለ ነበሩ 3ዓመት ሲሆናቸው ወደ ቤተ ክርስቲያም አስገባቸው። እርሷቸው ቀን ቀን እያገለገሉ እየተማሩ ሌሊት ሌሊት እየጸለዩ ይሆሩ ነበር እመቤታች በሌሊት ሲጸልዩ ተገልጻ በክንፍ ጋረደቻቸው። ከዚያም እድምያቸው ለጋብቻ ሲደርስ እናትና አባታቸው "እናጋባህ" አላቸው እርሳቸው ግን "አልፈልግም" ብለው በሌሊት ተነስተው ወደ ደብረ ፀሎላ ገብተው በአባ ገብረ ክርስቶስ እጅ 12ዓመታቸው መነኰሱ። የምንኲስና ስማቸውም አባ እንድርያስ ተባሉ። በዚያ ጊዜ ዲቁንና ክህነት የሚሰጥ ጳስስ በኢትዮጵያ ስላልነበረ አበምኔቱሙ አባ ገብረ ክርስቶስ ዲቁንናንና ክህነት እንድትቀበል "ወደ ግብጽ እንሒድ" አሏቸው። አባታችን "አይሆኑም" ሲሉ፡ ጌታችን በሌሊት ተገልጾ "እንድርያስ ወዳጄ ለምን እቢ አልክ፡እኔ ምርጬሃለሁና" አላቸው አባታችን ጠዋት ተነስተው "ኑ እሒድ" አሏቸው። ከዚም ወደ ግብጽ ሒደው ዲቁንናንና ክህነት ተቀብለው ወደ ገዳማቸው፡ ተመለሱ።
አንድ ቀን አባታችን ሲቀድሱ ከምድር አንድ ሜትር ከፍ ብለው እርሳቸው የቆሙበት ቦታ ውሃ አፈለቀ። ይህን ያዩ መነኰሳት ለአበምኔቱ ለአባ ገብረ ክርስቶስ ነገራቸው አበምኔቱ መጥተው የፈለቀው ውሃ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ አቡነ እንድርያስ አስጠርተው "አንተ ከዛሬ ጀምሮ ከእኛ ጋር ለሥራ መውጣት የለብህ ስእኛ ጸልይን እንጂ" አሏቸው እርሳቸው አይሆኑም ብለው ከእዛ ገዳም ወጥው "ወደ ኢየሩሳሌም ሔጄ ጌታ የተጠመቀበትን ማየ ዮርዳኖስ አያለው" ብለው ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ኤርትራ አዲ ሞገስ ወደሚባል አካባቢ ሲደርሱ አንድ ታምነ በእግዚእ የሚባል ገበሬ "አባቴ የንስሐ አባት ሁኑኝ" አላቸው። አባታችን "በአገራችሁ ካህን የለም እንዴ? አሉት እርሱም "አዋ የለም" አላቸው አባታችንም ሕዝቡ አስተምረው አጥምቀው ጉዞ ወደ ኢየሩሳሌም ጀመሩ። ደብረ ጽጌ ሰፍኣ ሲደርሱ ጌታ ተገልጾ,"ይህን ቦታ ዳግማዊ፡ ኢየሩሳሌም አድርጌልሀለው ውሃውም የዮርዳኖስ ውሃ ይሆንልሃል እና ከዚህ አትህድ" አላቸው።
አባታችንን አቡነ እንድርያስ ተከትለው ወደዚህ ገዳም ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ተማሪዎች ወደ እሳቸው መጡ፡እነዚህ ልጆቻቸውን አመነኰሷቸው። ለእነዚህ ልጆቻቸው፡ ቀድሞ በመንገድ ላይ አስተምረው ካጠመቁት ገበሬው ከታምነ በእግዚእ እንደ ሰው እየተላላከ እህል የሚጭልላቸው የሚያገለግላቸው ገብረኄር የሚባል አህያ ነበራቸው ሰይጣንም ቀንቶ ይህንን አህያ ብገለው ልጆቹ በርሃብ ምክንያት ይበተናሉ ብሎ አስቦ በአንበሳ አድሮ ገደለው። አንበሳው ደግሞ አቡነ እንድርያስ በአንድ መርገም ቃል ገደሉት። ልጆቻቸውም ምግብ ሲያጡ ጥለው ሊሆዱ ሲሉ አባታችን ትዕግስት ይኑራችሁ አላቸው። እነርሱም እንቢ፡ ብለው ወደ ታምነ በእግዚእ ሆዱ። ታምነ በእግዚእ ባለቤቱን "ምግብ አዘጋጅላቸው" አላት እሷም "አቡነ እንድርያስ ሳይመጦ አላዘጋጅ" አለችው እነርሱም እቢ ስላለቻቸው ልጆቹም "እኛ የአባታችን ምክር ስልሰማን ነው የከለከለችን" ብለው ወደ ገዳማቸው ተመለሱ።
አቡነ እድርያስም ልጆቹ ከተመለሱ በኋላ ውሃ የሞሉ፡እንስራዎች ነበሩና ቢባርኩት የወይን ጠጅ ሆነ። እንደ ገናም እግዚአብሔር ዘላለም ብለው ሲጸልዩ ከሰማይ አርያም ስንዴ ዘነበላቸው ያንን ለ14ዓመታት ተመገብ ይህ ሲያልቅ ደግሞ ወርቅ አዘነቡላቸው ወርቁ በእህል እየለወጡ ተመገበሩ። አባታችን ልጆቻቸውን "እኔ ወደ እግዚአብሔር የምሄድበት ቀን ደርሷል" አሏቸው። ልጆቹም "አንተ ከሆድክ ማን ከሰማይ ስንዴና ወርቅ እያዘነበ ውሃው ወይን እያደረገ ይመግበናል" አሏቸው እሷቸው "እኔ ከሞትኩ በኋላ እናተም ከዐሥር ቀን፡ በኋላ ወደ ትመጣላች እኔ ቦታ ላዘጋጅላችሁ ነው የምሆደው" ብለዋቸው በ126 ዓመታቸው የካቲት1 ዐርፈዋል። ልጆቻቸውም እንዳሏቸው በአንድ፡ቀን በአረማውናን ሰማዕትነት በመቀበል የካቲት10፡ ቀን ዐርፈዋል። ከአባታች ከአቡነ እንድርያስ ረድኤትና በረከትን በጸሎታቸውም ይማረን!።
(ምንጭ፦ ከደብረ ጽጌ ሰፍኣ ገዳም የተገኘ ማስታወሻ።)
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages