አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ሃያ ሦስት በዚች ቀን የመቶ አለቃ የነበረ #ጻድቁ_ቅዱስ_ቆርኔሌዎስ አረፈ፣ #የነቢይ_አብድዩ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
ጻድቁ_ቅዱስ_ቆርኔሌዎስ (የመቶ አለቃው)
ከዚህም በኋላ የሚጾም የሚጸልይ ለድኆችና ለችግረኞች የሚመጸውት ሆነ በጸሎቱም ጊዜ እንዲህ ይል ነበር አቤቱ አምላክ ሆይ እኔ አንተን ከማወቅ ጎደሎነኝና አንተ ግን የቀና መንገድህን ምራኝ።
ቸር ይቅር ባይ እግዚአብሔርም ይቅር ብሎት መልአኩን ላከለት ወደርሱም አይቶ ቆርኔሌዎስ ፈራ አቤቱ ምን ትላለህ አለ ጸሎትህ ምጽዋትህ መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጓል አሁንም በጫማ ሰፊው በስምዖን ቤት የሚኖረውን ስምዖን ጴጥሮስን ይጠሩልህ ዘንድ ሰዎችን በባሕር አቅራቢያ ወደአለች ኢዮጴ ከተማ ላክ አለው።
በዚያንም ጊዜ መልአኩ እንደነገረው ሰዎችን ላከ ጴጥሮስም በመጣ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀብሎ ከእግሩ በታች ሰገደለት ጴጥሮስም አነሣውና ተነሥ እኔም እንዳንተ ሰው ነኝ አለው። ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ ወደርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ።
ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው ለአይሁዳዊ ሰው ሒዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ እኔን ግን ማንንም ማን ቢሆን እንዳልጸየፍ እግዚአብሔር አሳየኝ። አሁንም እንደላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ የጠራችሁኝ ለምን እንደሆነ እስቲ ንገሩኝ።
ቆርኔሌዎስም ዛሬ አራተኛ ቀን ነው አለ በቤቴ ውስጥ በዘጠኝ ሰዓት ስጸልይ አንድ ሰው ብርሃን ለብሶ ታየኝ። እንዲህም አለኝ ቆርኔሌዎስ ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም በእግዚአብሔር ፊት ታሰበልህ ። አሁንም ከባሕር አቅራቢያ ወዳለችው ወደ ኢዮጴ ከተማ ላክና በጫማ ሰፊው በስምዖን ቤት የሚኖረውን ጴጥሮስ የተባለ ስምዖንን ይጥሩልህ እርሱ አንተ የምትድንበትን ወገኖችህም ሁሉ የሚድኑበትን ይነግርሃል።
ያን ጊዜም ስለዚህ ወዳንተ ላክሁ ወደእኛ መምጣትህም መልካም አደረግህ አሁንም እግዚአብሔር ያዘዘህን ሁሉ ልንሰማ እነሆ ሁላችን በፊትህ አለን።
ጴጥሮስም አንደበቱን ገልጦ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለሙ ሁሉ ድኅነት ሰው መሆኑን መከራ ተቀብሎም ተሰቅሎ ስለ መሞቱ ስለ መነሣቱና ወደ ሰማይ ስለማረጉ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ ስለ መምጣቱ አስተማራቸው።
የከበረ ቆርኔሌዎስም ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ከዚያ የነበሩ ብዙዎች አሕዛብም አመኑ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም እንደተጻፈ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ።
ከዚህም በኋላ ቆርኔሌዎስ ይህን ዓለም ለመግዛት የተሾመውን ሹመት ተወ ቅዱስ ጴጥሮስ ለክርስቶስ ጭፍራ የመሆንን ሹመት በመስጠት ለእስክንድርያ አገር ኤጲስቆጶስነት ሹሞታልና ወደ ርሷም ሒዶ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከ ጣዖታትንም ለሚያመልኩ ስሕተት መሆኑን ገለጠላቸው ልባቸውንም እግዚአብሔርን በማወቅ ብሩህ አደረገላቸው በፊታቸውም ተአምራትን አደረገ ብዙዎችም አምነው ተጠመቁ ከእነርሱም በኋላ መኰንኑን ድሜጥሮስን አጠመቀው። እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት ዳግመኛ የስሙ ትርጓሜ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነ የነቢይ አብድዩ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ።
በመጽሐፍ ቅዱስ 1ኛ ነገ. 18፥3 ላይ "አብደዩ እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ነበር" ተብሎ የተነገረለት እውነትም "የእግዚአብሔር አገልጋይ" የሆነ የነቢዩ ኤልያስ ደቀመዝሙር የነበረ ታላቅ ነቢይ ነው፡፡
ነቢዩ አብድዩ ነገዱ ከነገደ ኤፍሬም ሲኾን አባቱ አኪላ እናቱም ሳፍጣ እንደሚባሉ የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ያስረዳል፡፡ ይህም ቅዱስ ነቢይ ከጠረፍ በረሃ አቅራቢያ ካለች ሱሳም በምትባል አገር ካሉ ሰዎች ወገን ነው፡፡ ለነቢዩ ኤልያስ ደቀ መዝሙሩ ሆኖ በንጉሡ በአክዓብምና በንግሥቲቱ በኤልዛቤል ምክንያት በእርሱ ላይ የመጣውን መከራ ሁሉ ታግሷል፡፡ ታላቁ ነቢይ ኤልያስ ከእነ ኤልዛቤል ሸሽቶ ወደ ተራራ ላይ ወጥቶ በዋሻ ተሸሽጎ ምግቡን አሞራ እያመጣለት በኖረበት ጊዜ እንኳን አብድዩ ግን ብቻውን የእግዚአብሔርን ነቢያት ይንከባከብ ነበር፡፡ አብድዩ የንጉሥ አክዓብ የቤቱን አዛዥ የነበረ ቢሆንም ንግሥት ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ አብድዩ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውኃ ይመግባቸው የነበረ ታላቅ ባለውለታ ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ታሪኩ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው፡- "ከብዙ ቀንም በኋላ በሦስተኛው ዓመት "ሂድ ለአክዓብ ተገለጥ፥ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ" የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ፡፡ ኤልያስም ለአክዓብ ይገለጥ ዘንድ ሄደ፤ በሰማርያም ራብ ጸንቶ ነበር፡፡ አክዓብም የቤቱን አዛዥ አብድዩን ጠራ፤ አብድዩ እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ነበር፡፡ ኤልዛቤልም የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ እርሱ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውኃ ይመግባቸው ነበር፡፡ አክዓብም አብድዩን "በአገሩ መካከል ወደ ውኃው ምንጭ ሁሉና ወደ ወንዝ ሁሉ ሂድ፤ እንስሶችም ሁሉ እንዳይጠፉ ፈረሶችንና በቅሎችን የምናድንበት ሣር ምናልባት እናገኛለን" አለው፡፡
ሁለቱም የሚመለሱበትን አገር ተካፈሉ፤ አክዓብም ለብቻው በአንድ መንገድ አብድዩም ለብቻው በሌላ መንገድ ሄዱ፡፡ አብድዩም በመንገድ ሲሄድ እነሆ ኤልያስ ተገናኘው፤ አብድዩም አወቀው፣ በግምባሩም ተደፍቶ "ጌታዬ ሆይ! ኤልያስ አንተ ነህን?" አለ፡፡ ኤልያስም "እኔ ነኝ ሄደህ ለጌታህ ‹ኤልያስ ተገኝቶአል› በል አለው፡፡ አብድዩም "እኔን ባሪያህን እንዲገድል በአክዓብ እጅ አሳልፈህ ትሰጠኝ ዘንድ ምን ኃጢአት አድርጌአለሁ? አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! ጌታዬ ይፈልግህ ዘንድ ያልላከበት ሕዝብ ወይም መንግሥት የለም፤ ሁሉም 'በዚህ የለም' ባሉ ጊዜ አንተን እንዳላገኙ መንግሥቱንና ሕዝቡን አምሎአቸው ነበር፡፡ አሁንም እነሆ 'ሂድ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር' ትለኛለህ፡፡ እኔም ከአንተ ጥቂት ራቅ ስል የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደማላውቀው ስፍራ ይወስድሃል፤ እኔም ገብቼ ለአክዓብ ስናገር ባያገኝህ ይገድለኛል፤ እኔም ባሪያህ ከትንሽነቴ ጀምሬ እግዚአብሔርን እፈራ ነበር፡፡ ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ መቶውን የእግዚአብሔር ነቢያት ወስጄ አምሳ አምሳውንም በዋሻ ውስጥ ሸሽጌ እንጀራና ውኃ የመገብኋቸው ነበር፡፡ ይህ ያደርግሁት ነገር በውኑ ለጌታዬ አልታወቀህምን? አሁንም 'ሄደህ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር ትላለህ' እርሱም ይገድለኛል" አለው፡፡
ኤልያስም ''በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ ዛሬ ለእርሱ እገለጣለሁ" አለ፡፡ አብድዩም አክዓብን ሊገናኘው ሄደ፣ ነገረውም፤ አክዓብም ኤልያስን ሊገናኘው መጣ፡፡ አክዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ "እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን?" አለው፡፡ ኤልያስም "እስራኤልን የምትገለባብጡ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፣ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም" አለው፡፡ 1ኛ ነገ.18፥1-20፡፡
ቅዱስ አብድዩ የንጉሥ አክዓብ የቤቱን አዛዥነቱን ትቶ የኤልያስ ቀደ መዝሙሩ ሆኖ በነቢይነት እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኖሮ የትንቢቱ ወራት ሲፈጸም በዚህች ዕለት ዐርፏል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment