አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ሃያ አራት በዚህች ዕለት ጌታ ሐዲስ ሐዋርያ ብሎ የሾማቸው የኢትዮጵያ ብርሃኗ የሆኑ የደብረ ሊባኖሱ #አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት ልደታቸው ነው፣ የከበረና የተመሰገነ #ቅዱስ_አግናጥዮስ_ምጥው_ለአንበሳ ዕረፍቱ ነው፣ #አባ_ጳውሊ_ዘሰሎንቅያ ዕረፍታቸው ነው፣ የአሚናዳብ ልጅ #ቅድስት_አስቴር ዕረፍቷ ነው፣ የአንጾኪያው #አባ_ፊሎንጎስ ዕረፍቱ ነው፡፡
ታኅሣሥ ሃያ አራት በዚህች ዕለት ጌታችን በቃሉ ''ሐዲስ ሐዋርያ'' ብሎ የሾማቸው የኢትዮጵያ ብርሃኗ የሆኑ የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ልደታቸው ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ለኢትዮጵያ ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ የመረጣቸው ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል አብሳሪነት ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት 24 ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ 24 ቀን 1197 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ጻድቁ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ›› ማለትም ‹‹አንዱ አብ ቅዱስ ነው አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት የፈጠራቸውን አምላክ አመስግነውታል፡፡ ወላጆቻቸውም ስማቸውን ፍሥሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ይኸውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡ የወላጆቻቸው የቀድሞ ስማቸው ዘርዐ ዮሐንስና ሣራ ይባል ነበር፡፡
ቅዱሳን አባቶቻችን እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና እነ አቡነ ዜና ማርቆስ ሌሎቹም እነ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ ሕፃን ሞዐ፣ አቡነ አኖሪዮስ(ትልቁ)፣ አቡነ ገላውዲዮስ፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋርና አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል የትውልዳቸው መሠረት ኢያሱ ለሌዋውያን ክፍል ትሆን ዘንድ ከለያት ከኢየሩሳሌም ነው፡፡ ስማቸውን የጠቀስኳቸው እነዚህ ቅዱሳን አባቶቻችን የወንድማማቾች ልጆች ሲሆኑ ከአዳም ጀምሮ 61ኛ ትውልድ ናቸው፡፡ ይኸውም እንዴት ነው ቢሉ ትውልዱ ከአዳም ጀምሮ በካህኑ አሮን በኩል የሆነውና የሌዋዊያን ሊቀ ካህን የነበረው የሳዶቅ ልጅ አዛርያስ በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ከታቦተ ጽዮንና ከብዙ ሌዋዊያን ካህናት ጋር ሊቀ ካህን ሆኖ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አክሱም ተቀምጦ ኖረ፡፡ የኦሪትንም ሕግ እየዞረ ለኢትዮጵያ ሰዎች አስተማረ፡፡ ትውልዱም በአብርሃ ወአጽብሓና በአባ ሰላማ ዘመን እስከነበረው እንበረም የሚባለው ጻድቅ ድረስ ደረሰ፡፡ የእንበረምም ትውልድ ደገኛው ሕይወት ብነ በጽዮን ድረስ ደረሰ፡፡ ሕይወት ብነ በጽዮንም የደማስቆ ምድር ከሚሏት ከወለቃ ሀገር የመኮንን ልጅ የሆነችውን ወለተ ሳውልን አግብቶ አበይድላን ወለደ፡፡ አበ ይድላም በንጉሡ ድልዓዥን ዘመነ መንግሥት ለ150 ካህናት አለቃ ሆኖ በወለቃ ሀገር የክርስቶስን የወንጌል ሕግ እያስተማረ ብዙዎችን አጠመቀ፡፡ እስከ ሸዋ ምድር ድረስ እያስተማረ መጥቶ በሸዋ ምድር ተቀመጠ፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳነጸ፡፡ እጅግ አስደናቂ ተአምራትንም ያደርግ ነበር፡፡ ‹‹በሸዋ ጽላልሽ ተቀምጦ ሲያስተምርም በአንዲት ቀን እስከ ሁለት መቶ ሺህ ሕዝብ ያጠምቅ ነበር›› በማለት ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይመሰክርለታል፡፡
አበይድላ በመጨረሻ በፈቃደ እግዚአብሔር ከሸዋ ጽላልሽ ምድረ ዞረሬ ሚስት አግቶ ሀበነ እግዚእን ወለደ፤ ሀበነ እግዚእም በኩረ ጽዮንን ወለደ፤ በኩረ ጽዮንም ሕዝበ ቀድስን ወለደ፤ እርሱም ነገደ እግዚእ የተባለ ነው፡፡ ሕዝበ ቀድስም ብርሃነ መስቀልን ወለደ፤ እርሱም ዐቃቢነ እግዚእ የተባለ ነው፡፡ ብርሃነ መስቀልም ሕይወት ብነን ወለደ፤ እርሱም ሴትን ወለደ፡፡ ሴትም ወረደ ምሕረትን ወለደ፡፡ ወረደ ምሕረትም ዘካርያስን ወለደ፡፡ ዘካርያስም የእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት የሆኑ 6 ወንድማማች ልጆችን ወለደ፡፡ እነርሱም እንድርያስ፣ አርከሌድስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ዘርዐ ዮሐንስ ወይም ጸጋ ዘአብ፣ ቀሲስ ዮሐንስና ቀሲስ ዮናስ ናቸው፡፡ እንድርያስም ሳሙኤል ዘወገግን ወለደ፤ አርከሌድስም ሕፃን ሞዐን ወለደ፤ ዘርዐ አብርሃምም ታላቁን አኖርዮስን ወለደ፤ ዘርዐ ዮሐንስ ወይም ጸጋ ዘአብም ተክለ ሃይማኖትን ወለደ፤ ቀሲስ ዮሐንስም ዜና ማርቆስን ወለደ፣ ቀሲስ ዮናስ ደግሞ የፈጠጋሩን ማትያስንና ገላውዲዮስን ወለዳቸው፡፡ ገላውዲዮስም የመሐግሉ ቀውስጦስን ወለደ፡፡ እነዚህ ደጋግ ቅዱሳን በእናታቸውም በኩል እንዲሁ በዝምድና የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ማቴዎስ የተባለው ደገኛ ክርስቲያን የሸዋ ገዥ የነበረ ሲሆን አንድ ወንድ ልጅ መድኃኒነ እግዚእንና ሦስት ሴቶች ልጆችን ወለደ፡፡ ሶስቱ ሴቶች ልጆችም እምነ ጽዮን፣ ትቤ ጽዮንና ክርስቶስ ዘመዳ ይባላሉ፡፡ ሦስቱ እኅትማማቾችም ደጋጎቹን አባቶቻችንን ወለዱልን፡፡ እምነ ጽዮን የእነ ዜና ማርቆስን እናት ማርያም ዘመዳንና ወለደች፡፡ ትቤ ጽዮንም ሕፃን ሞዐን ወለደች፡፡ ክርስቶስ ዘመዳ ደግሞ ታላቁን አኖሬዎስን ወለደች፡፡ የፈጠጋሩ ገዥ መድኃኒነ እግዚእ ደግሞ የተክለ ሃይማኖትን እናት እግዚእ ኀረያን ወይም በሌላ ስሟ ሣራን ወለደ፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከልጅነታቸው ጀምሮ በወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በ15 እና በ22 ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ከአቡነ ቄርሎስ (ጌርሎስ) ዲቁናንና ቅስናን ተቀብለዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ያገለግሉ እንደነበር በዚህ ይታወቀል፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን አባታችን ከጓደኞቻቸው ጋር ለአደን ወደ ዱር ሄደው ሳለ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ ታያቸው፡፡ ቅዱስ አባታችንም ‹‹እንደዚህ ባለ ገናንነት የማይህ ጌታዬ ማነህ?›› ባሉት ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ዘወትር የምጠብቅህ ካንተ የማልለይ እናትህንና አባትህንም ስላንተ ከውኃ ስጥመትና ከምርኮ ያዳንኳቸው እኔ ሚካኤል ነኝ፡፡ ከእንግዲህ አውሬ አዳኝ አትሁን፤ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ሰውን በትምህርት የምታድን ሁን እንጂ፡፡ እነሆ እግዚአብሔር ጽኑዕ ሥልጣን ሰጥቶሃልና፤ ሙት ታስነሣለህ፤ ድውያንን ትፈውሳለህ፤ አጋንንትም አንተን በመፍራት ይሸሻሉ፡፡ ስምህ ፍሥሐ ጽዮን አይሁን፤ ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንጂ፡፡ ትርጓሜውም ተክለ አብ፥ ተክለ ወልድ፥ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው›› አላቸው፡፡
ቅዱስ ሚካኤል ይህን ሲነግራቸው ጌታችን በሥጋ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደነበር ሆኖ መልከ መልካም ጎልማሳ መስሎ ታያቸው፡፡ ጌታችንም ‹‹ወዳጄ እንዴት ሰነበትክ? ቸር አለህን?›› አላቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ‹‹ጌታዬ ሆይ አንተ ማነህ?›› ብለው ሲጠይቁት ጌታችንም ‹‹እኔ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ነኝ፤ በናትህ ማኅፀን ፈጥሬህ ያከበርኩህ እኔ ነኝ፡፡ በተወለድክ በሦስተኛው ቀን አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብለህ ታመሰግነኝ ዘንድ የምስጋና ሀብት ያሳደርኩብህ እኔ ነኝ፡፡ በርሃብ ዘመን በቤት የሚያሻው ምግብ ሁሉ ቅቤው፣ የስንዴው ዱቄት በእናት በአባትህ ቤት ይመላ ዘንድ በእጅህ ሀብተ በረከት ያሳደርኩብህ እኔ ነኝ፡፡ ያንን ሰው አንተን በተጣላ ጊዜ በነፋስ አውታር የሰቀለኩት በመዓት ጨንገር የገረፍኩት እኔ ነኝ፡፡ ውኃ ጠምቶህ በለመንከኝ ጊዜ ከደረቅ መሬት የጣፈጠ ውኃ ያመነጨሁልህ እኔ ነኝ፡፡ ከልጅነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ተአምራት እያደረግሁ በአንተ እጅ የታመሙትን ያዳንኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ወደፊትም አደርግልሃለሁ›› አላቸው፡፡ ይህንን ብሎ በእጆቹ ባረካቸውና ‹‹ንሣእ መንፈስ ቅዱስ›› ብሎ የሹመትን ሀብት አሳደረባቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሁን፤ በምድርም የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሁን፤ አንተን የሰማ እኔን መስማቱ ነው፤ የላከኝ አባቴንም መስማቱ ነው፡፡ አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ ማለቱ ነው፡፡ የላከኝ አባቴንም እንቢ ማለቱ ነው፡፡ ይህን ሥልጣን ቀድሞ ለሐዋርያት ሰጥቻቸው ነበር፡፡ ከሐዋርያትም ሹመትን የተቀበለ ጳጳሱ ትሾምና ትሽር፣ ትተክልና ትነቅል ዘንድ ሥልጣንን ሰጠህ፡፡ ይህንንም ያደረኩልህ የጳጳሱን ቃል በመናቅ አይደለም፡፡ የፍቅሬን ጽናት ባንተ እገልጽ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ሐዋርያት ወዳልደረሱበት ሕዝብ በመምህርነት እልክህ ዘንድ በሚካኤል ቃል አዲስ ስም አወጣሁልህ፡፡ አንተም በማናቸውም ሥራ ከእነርሱ አታንስም፣ ሐዲስ ሐዋርያ አድርጌሃለሁና፡፡ ሰውን ሁሉ በእኔ ስም እያስተማርክ ታሳምን ዘንድ፣ ሚካኤልም ባሰብከው ሥራ ሁሉ ረዳት ይሁንህ፣ ሁል ጊዜ ካንተ አይለይም፤ በምትሄድበትም ጎዳና ሁሉ እርሱ መሪ ይሁንህ፤ እኔም ባለ ዘመንህ ሁሉ አልለይህም›› ካላቸው በኋላ ሰላምታ ሰጥቷቸው ዐረገ፡፡
ብፁዕ አባታችንም እጅ ነሥተው ‹‹ለእኔ ለኀጥኡ የማይገባኝ ሲሆን ይህን ሁሉ ጸጋ የጠኸኝ ስምህ በሰማይ በምድር የተመሰገነ ይሁን›› አሉ፡፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ ሀብተ ኃይልን የተመሉ ሆኑ፡፡ ወደቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ሀብት ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጥተው ጨረሱ፡፡ ከዚያም ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ›› ብለው ቤታቸውን እንደተከፈተ ትተው ወንጌልን ለማስተማር ወጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በሀገራችን ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ኃይማኖት ስለመለሱት በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ተብለዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ይህም ቅዱስ የወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙሩ ነው በስብከተ ወንጌልም በማገልገል ከእርሱ ጋር ብዙ አገሮችን ዙሮ አስተምሮአል ከዚህም በኋላ በአንጾኪያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾመው በውስጥዋመሰ ሕይወተሰ የሆነ የወንጌልን ትምህርት አስተማረ ብዙዎችንም እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው በትምህርቱም ልቡናቸውን አበራላቸው።
ከዚህም በኋላ ጣዖትን ለሚያመልኩ ስሕተቻተውን በገለጠላቸው ጊዜ ተቆጡ። ወደ ከሀዲው ንጉሥ ወደ ጠራብዮስ ሔደው ከሰሱት እንዲህም አሉት "አግናጥዮስ የአማልክቶችህን አምልከሸ ይሽራል እኮን ሰዎችንም እያስተማረ ክርስቶስን ወደ ማመን ያስገባቸዋል"። በዚያንም ጊዜ ወታደሮች ልኮ ወደርሱ አስመጣውና "አግናጥዮስ ሆይ ለምን ይህን አደረግህ የአማልክቶቼን አምልኮስ ለምን ሻርክ ሰዎችን ሁሉ እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ አስገብተሃቸዋልና" አለው። አግናጥዮስም "ንጉሥ ሆይ ቢቻለኝስ ያክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ ክርስቶስ አምልኮት ባስገባሁህ ነበር" አለው ንጉሡም "ይህን ነገር ትተህ ለአማልክቶቼ ሠዋ አለዚያ በታላቅ ሥቃይ አሠቃይሃለሁ" አለው። "በእኔ ላይ የምትሻውን አድርግ እኔ ግን ለረከሱ አማልክቶችህ አልሠዋም ሥቃይህንም እሳትም ቢሆን አንበሳንም ቢሆን አልፈራም ከሕያው ንጉሥ ከክርስቶስ ፍቅር ልትለየኝ አትችልም" አለው። ይህንንም ሲሰማ ንጉሡ ተቆጣ ያሠቃዩትም ዘንድ አዘዘ በተለያዩ በብዙ ሥቃዮችም አሠቀሠዩት በእጆቹም ውስጥ እሳት አድርገወሰ ከእጆቹ ጋር በጉጠት ይዘው አቃጠሉት።
ከዚህም በኋላ በዲንና በቅባት እያነደዱ ጎኖቹን አቃጠሉ በሾተሎችም ሥጋውን ሠነጠቁ። ከማሠቃየትም በደከሙ ጊዜ የሚያደርጉበትን እስከመክሩ ድረስ ከወህኒ ቤት ጨመሩት ብዙ ቀኖችም በዚያ ኖረ።
ከዚህም በኋላ አስታውሱት ከወህኒቤትም አውጥተው በንጉሡ ፊት አቆሙት ንጉሡም "አግናጥዮስ ሆይ አማልክቶቼን ብታያቸው ውበታቸው ባማረህ ነበር" አለው። ቅዱሱም "ንጉሥ ሆይ አንተ በክብር ባለቤት ክርስቶስ ብታምን ሙታኖችን የምታሥነሣቸው በሽተኞችንም የምትፈውሳቸው ባደረገህ ነበር"። ንጉሡም "ለፀሐይ ከመስገድ የተሻለ የለም" አለ የከበረ አግናጥዮስም "መንግሥቱ የማያልቀውን ፈጣሪ ትተህ ለተፈጠረ ፀሐይ ትሰግዳለህን?" ብሎ መለሰ ንጉሡም "ለራስህ መልካም አልክ ግን በመተላለፍ የአንጾኪያና የሶርያን ሰዎች ስበሕ ወደ ክርስቶስ አምልኮት አስገባሃቸው እንጂ" አለው። የከበረ አግናጥዮስም ተቆጥቶ "ንጉሥ ሆይ ከንቱ የሆነ ጣዖትን ከማምለክ ሰዎችን ስለሳብኳቸውና ሰማይና ምድርን ወደ ፈጠረ ወደ ክርስቶስ አምልኮት ስለአስገባኋቸው በእኔ ላይ ትቆጣለህን ለረከሱ ጣዖቶችህስ እንድሠዋ ታዘኛለህን እኔ ግን ቃልህን ተቀብዬ ለሰይጣናት አልሠዋም ለእውነተኛ አምላክ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እሠዋለሁ እንጂ" አለው።
በዚያንም ጊዜ ንጉሥ ተቆጣ ከሥጋው ምንም ምን ሳያስቀሩ ይበሉት ዘንድ ሁለት የተራቡ አንበሶችን በላዩ እንዲሰዱ አዘዘ። የከበረ አግናጥዮስም አንበሶች ወደርሱ ሲቀርቡ በአያቸው ጊዜ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሕዝብን እንዲህ አላቸው "ከዚህ የተሰበሰባችሁ እናንተ የሮሜ ሰዎች ቃሌን ስሙ እወቁም እኔ ይህን ሥቃይ የታገሥኩት በትዕቢትና በትምክህት አይደለም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታዬና በፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንጂ። አሁንም እኒህ አንበሶች እንደ ሥንዴ ይፈጩኝ ዘንድ ነፍሴ ወደደች የክብር ባለቤት ወደ ሆነ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ልትሔድ ነፍሴ ሽታለችና"።
ንጉሡም ቃሉን ሰምቶ አደነቀ ድንጋጠረም አድሮበት እንዲህ አለ "የክርስቲያኖች ትዕግሥታቸው ምን ይብዛ ስለ አምልኮት ከአረማውያን በእንዲህ ያለ ሥቃይ ላይ የሚታገሥ ማን ነው" አለ። እነዚያ አንበሶችም ወደ ቅዱሱ ቀረብ ብለው ደንግጠው ቆሙ። ከዚህም በኋላ አንዱ አንበሳ እጁን ዘርግቶ አንገቱን ያዘው በዚያንም ጊዜ ደስ ብሎት ነፍሱን በፈጣሪው ክርስቶስ እጅ ሰጠ ልመናውንም ፈጸመለት።
ለእነዚያ አንበሶችም ሥጋውን ይዳስሡት ዘንድ አልተቻላቸውም የክብር ባለቤት ክርስቶስ ዳግመኛ እስከ ሚመጣ የተጠበቀ ሆነ እንጂ ከዚህም በኋላ በክብር በምስጋና ከከተማ ውጭ ቀበሩት እንደዚህም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመልካም ተጋድሎ ምስክርነቱን ፈጸመ ለምእመናንም ጠቃሚ ይሆን ዘንድ ገድሉን ጻፉ የበዓሉንም መታሰቢያ አደረጉለት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት አባ ጳውሊ ዘሰሎንቅያ ዐረፈ፡፡ ሰሎንቅያ በምትባል በምስር አገር ሰይጣንን ገዝተው በግልጽ ያነጋገሩትና ብዙ ምሥጢርን እንዲናገር ያደረጉት ታላቅ አባት ናቸው፡፡ የሰሎንቅያ አገር ሰዎች የሄሮድስ ወገን የሆኑ ክፉዎች ናቸው፡፡ ከዱሮ ጀምረው ሴቶችና ወንዶች ሆነው በጋራ በአንድነት ወደ አንድ ክፍል ገብተው እንስሳዊ ግብራቸውን ይፈጽማሉ፡፡ ብዙ ሆነው ገብተው በሩን ዘግተው መብራት አጥፍተው በእጃቸው የገባውን ይዘው ያድራሉ፡፡ እኅቱም ትሁን ልጁ ወደዚያ ቤት የገባ ሰው ሌላውን አይለየውም፡፡ ይህም ሰይጣናዊ ተግባራቸው ባሕላቸው ሆኖ በወር አንድ ጊዜ ያደርጉታል፡፡
አባ ጳውሊም ይህን ባየ ጊዜ ስለ ኃጢአታቸው በጣም አዝኖ "ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ?" ቢላቸው እነርሱም "አባቶቻችን ያዘዙን ትእዛዝና ባሕላችን ነው" አሉት፡፡ አባ ጳውሊም ወደዚያ ቤት ሲገቡ አይቶ እጅግ በማዘን ወደ ጌታችን ጸለየ፡፡ ጸሎቱንም እንደፈጸመ አንድ ጥቁር ሰው ከዝሙት ቤቱ ዕራቁቱን ሆኖ የእሳት ሰይፍ ተሸክሞ መጣ፡፡ አባ ጳውሊም ካማተበበት በኋላ "አንተ ማነህ? ማንንስ ትሻለህ?" አሉት፡፡ ጥቁሩም ሰው "እኔ ሰይጣን ነኝ፣ አንተ ወደ ጌታህ በለመንህ ጊዜ ላከኝ" አለው፡፡ አባ ጳውሊም "የምታስትበትን ነገር ሁሉ ትነግረኝ ዘንድ እጠይቅሃለሁ" አለው፡፡ ሰይጣንም "የምትሻውን ጠይቀኝ" አለው፡፡ አባም "ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ በሰው ላይ ታድር ዘንድ ምክንያት እንዴት ታገኛለህ?" አለው፡፡ ሰይጣንም "ሰው በእግዚአብሔር ሕግ ጸንቶ ሳለ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ስም በጠራ ጊዜና በንጽሕና ሆኖ የክርስቶስ ሥጋና ደምን በሚቀበል ሰው ላይ ለማደር ሥልጣን የለኝም" አለው፡፡ ከዚህም በኋላ የሚያስትበትን ሁሉ በዝርዝር ነገረው፡፡ ሊቀ ጳጳሳትን፣ ጳጳሳትን፣ መነኮሳትን፣ መእመናንን፣ ባለትዳሮችን፣ አዛውንቶችን፣ ወጣቶችና ሕፃናትን…ሁሉንም ነገር እያንዳንዱን በምን በምን እንደሚያስት ሁሉንም ነገር በዝርዝር ነገረው፡፡ ወዲያውም የሰይጣን መልኩ ተለውጦ እንደ እሳት ነበልባል ሲሆን አባ ጳውሊ ተመልክቶ እጅግ ደነገጠ፡፡ በዚያም ቅጽበት የታዘዘ መልአክ መጥቶ አባ ጳውሊን አበረታው፡፡
በዚያችም ሌሊት መቅሰፍት ወርዶ በዝሙት ቤት ያሉትን አጠፋቸው፡፡ ከ5 ወንዶችና ከ5 ሴቶች በቀር የተረፈ የለም፡፡ አባ ጳውሊም "ይህን ለምን ታደርጋላችሁ?" ቢላቸው "በየወሩ አንዲት ቀን ወደ ውሽባ ቤት እየገባን በሩን ዘግተን መብራት አጥፍተን ከእጃችን የገባችዋን ሴት ይዘን አንተኛለን" አሉት፡፡ "ከእናንተ ውስጥ እኅቱን ወይም ልጁን እንዴት ያውቃል?" አላቸው፡፡ "እንደ እንስሳ በመሆን እንጃ ማወቅ የለም" አሉት፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን የክርስቶስን ወንጌል ሰበከላቸውና አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ ሥጋ ወደሙንም አቀበላቸው፡፡ በሃይማኖት ካጸናቸው በኋላ ወደ በዓቱ ተመልሶ ገድሉን ፈጽሞ ታኅሣሥ 24 ቀን በሰላም ዐረፈ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የአይሁድ ወገን የሚሆን ስሙ መርዶክዮስ የሚባል የኢያኤሩ ልጅ ከብንያም ወገን የተወለደ የቄስዩ ልጅ አንድ ሰው በሱሳ አገር ነበረ፡፡ ከኢሩሳሌምም በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነጾር እጅ የተማረከ ነው፡፡ ያሳደጋት ልጅ ነበረችው፡፡ እርሷም የአባቱ ወንድም የአሚናዳብ ልጅ አስቴር ናት፡፡ ከዘመዶቿ ተለይታ በወጣች ጊዜ ልጅ ትሆነው ዘንድ አሳደጋት፡፡ እርሷም እጅግ መልከ መልካም ነበረች፡፡ በአንዲትም ዕለት ንጉሥ አርጢክስስ ብዙ ተድላ ደስታ አድርጎ መኳንንቶቹን ሁሉ ጠራ፡፡ የመኳንንቶቹንም አለቃ አማሌቃዊውን ሐማንንም ጠራው፡፡ እርሱ ከሁሉም መኳንንት የከበረ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሥ 7ቱን ባለሟሎቹን ጠርቶ ንግሥቲቱን አስጢንን አምጥተው የእቴጌነት ዘውድ ያቀዳጇት ዘንድ እርሷ መልከ መልካም ናትና ለአሕዛብም አለቆች ሁሉ መልኳንና ውበቷን ያሳዩ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ ንግሥቲቱ አስጢን ግን የንጉሡን ትእዛዝ ባለመቀበል እምቢ አለች፡፡ ከባለሟሎቿም ጋር ትመጣ ዘንድ ባለወደደች ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተናዶ ከንግሥትነቷ ሻራት፡፡ ከዚህም በኋላ 127 ከሚሆኑ ከሚገዘቸው አገሮች አንድ ሺህ ቆነጃጅቶችን ይመርጡለት ዘንድ ንጉሡ አዘዘ፡፡ ከሺህ መቶ፣ ከመቶ ዓሥር፣ ከዓሥር ሦስት መረጡ፡፡ ከሁሉም በመልክ፣ በውበት፣ በደም ግባትም አንደኛ ሆና አስቴር ተመረጠች፡፡ ንጉሡም አስቴርን አነገሣት፡፡
ንጉሡም አስቴርን እጅግ አድርጎ ወደዳት፣ በሴቶቹም ሁሉ ላይ የበላይ አድርጎ ሾማት፡፡ ከዚህም አስቀድሞ መርዶክዮስ አገሩንና አደባባዩን ከሚጠብቁት ከንጉሡ ባለሟሎች ጋር በአደባባይ ኖረ፡፡ እነርሱም ስማቸው ታራ እና ገቦታ ይባላል፡፡ እርሱም እነዚህ ሁለቱ በንጉሡ ላይ ያሰቡትን ተንኮላቸውን ሰማ፡፡ ንጉሥ አርጤክስስን ይገድሉት ዘንድ ወንጀልን እንዳዘጋጁ ባወቀ ጊዜ መርዶክዮስ ሄዶ ለንጉሡ ነገረው፡፡ ንጉሡም ነገራቸውን መርምሮ ቀጣቸውና ይህን ነገር ታሪክና ወግ በሚጻፍበት ላይ ጻፈው፡፡ ሐማ ግን አማሌቃዊ ነበረና መርዶክዮስንና እስራኤላውያንን ይጠላቸው እጅግ ነበርና የአይሁድን ወገን ሁሉ ለማጥፋት ተነሣ፡፡ መርዶክዮስም ይህንን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀዶ ማቅ ለበሰ፡፡ መርዶክዮስም የሀዘኑን መርዶ ለአስቴር እንዲደርሳት አደረገ፡፡ አስቴርም "እስከ ሦስት ቀን ጹሙ ጸልዩ እኔም ደንገጡሮቼም እንጾማለን" ብላ ላከችለት፡፡ ሱባኤዋንም እንደጨረሰች የማቅ ልብሷን አውልቃ ጥላ ወደ ንጉሡ አዳራሽ በገባች ጊዜ "እስከ መንግሥቴም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁና የሆንሽውን ንገሪኝ" አላት፡፡ በዓልንም አደረገና ሐማንና መኳንንቱን ሁሉ ጠራ፡፡ በበዓሉም ላይ ድጋሚ "ላደርግልሽ ፈቅጂውን ንገሪኝ" አላት፡፡
ንጉሡም ለመርዶክዮስ ውለታ ያደረገለትን ሲያስብ ምንም እንዳላደረገለት ዐወቀ፡፡ ወዲያውም ሐማ መርዶክዮስን በመስቀል ላይ ሰቅሎ ሊገድለው እንደሆነ ተነገረ፡፡ ንጉሡም ሐማን "ንጉሥ የወደደውን ሰው ምን ያደርግለት ዘንድ ይገባል?" አለው፡፡ ሐማም "ይህስ ለእኔ ነው" ብሎ "በክብር ይሾም ዘንድ ሹመቱም አዋጅ ይነገርለት ዘንድ ይገባዋል" አለ፡፡ ንጉሡም ለሐማ ይህን ጊዜ "መልካም ተናግረሃል፣ ለመርዶክዮስ እንዲሁ ይደረግለታል" አለው፡፡ ሐማም የንጉሡን ትእዛዝ ተቀብሎ መርዶክዮስን በፈረስ አስቀምጦ በከተማው በማዞር በክብር መሾሙን በአዋጅ አስነገረለት፡፡
ከዚህም በኋላ ንጉሡና አስቴር ለማዕድ አብረው በተቀመጡ ጊዜ ንጉሡ "ጉዳይሽን የማትነግሪኝ ለምንድነው?" አላት፡፡ እሷም ይህን ጊዜ "ንጉሥ ሆይ ዝም ባልኩ በወደድኩ ነበር ነግር ግን ወገኖቼና እኔ ለሞት ተላልፈን ተሰጥተናል" በማለት ሐማ እስራኤላውያንን በአዋጅ ሊያጠፋ መሆኑን ነገረችው፡፡ ንጉሡም "ማነው ይህን በማድረግ የደፈረኝ?" አላት፡፡ እሷም ሐማ መሆኑን ነገረችው፡፡ ንጉሡም ሐማ መርዶክዮስን ለመስቀል ባዘጋጀው መስቀል ላይ ራሱ ሐማን እንዲሰቅሉት አዘዘ፡፡ ሐማም ተሰቅሎ ሞተ፡፡ የእስራኤል ወገኖችም ሁሉ በጻድቂቱ አስቴር መዳናቸው በእርሷ ተደርጓልና ሁሉም አመሰገኗት፡፡ ምስጉን የሆነ እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ የእስራኤል ወገኖች ሁሉ ድኅነታቸው በእርሷ ተደርጓል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት አባ ፊሎንጎስ ዐረፈ፡፡ ይኽም ቅዱስ አስቀድሞ ሚስት አግብቶ አንዲት ልጅ ወለደ፡፡ ከዚህም በኋላ ሚስቱ ሞተች፡፡ እርሱም ከዚህ በኋላ የምንኩስና ልብስ ለብሶ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ ኖረ፡፡ ስለ መልካም ተጋድሎውትና ስለ ትሩፋቱ በአገልግሎትም ስለመጠመዱ በአንጾኪያ አገር ላይ ሊቀ ጳጳሳት እንዲሆን እግዚአብሔር መረጠው፡፡ በተሾመም ጊዜ የክርስቶስን መንጋዮች ምእመናንን በመልካም አጠባበቅ ጠበቃቸው፡፡ ከአርዮሳውያን ከመቅዶንዮስና ከሰባልዮስ ነጣቂ ተኩላዎች በሚገባ ጠበቃቸው፡፡ በሊቀ ጵጵስናውም የሹመት ወቅት አኗኗሩን እንደ መላእክት አደረገ፡፡ መልካም የሆነ ገድሉንም ፈጽሞ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment