ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 6 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት 6

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ስድስት በዚህች ቀን ሊቀ ጳጳሳት የከበረ #አባት_ቅዱስ_አቡሊዲስ ሥጋው ከባሕር የወጣበት ነው፣ ጌታን ሽቱ ለቀባችው #ቅድስት_ማርያም_እንተ_ዕፍረት የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው፣ የከበሩ #አቡቂርና_ዮሐንስ_ሦስት_ደናግልም_ከእናታቸው_ከአትናስያ ጋር በሰማዕትነት ሞቱ፡፡


የካቲት ስድስት በዚህች ቀን የዓለሙ ሁሉ መምህር የሆነ የሮሜ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት አቡሊዲስ ሥጋው ከባሕር የወጣበት ነው።
ይህም የከበረ በእውቀቱም ፍጹም የሆነ ሰው ነው ከአባት አውክዮስም በኋላ ለሮም ሀገር ሊቀ ጳጳሳት ይሆን ዘንድ መንፈስቅዱስ መረጠው ይህም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ከላድያኑ በተሾመባት በመጀመሪያ ዓመት ነው ሕዝቡንም ከአረማውያን ጠባይ የሚጠብቃቸው የሚያስተምራቸውና በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት የሞያጸናቸው ሆነ።
በከሀዲውም ንጉሥ በከላድያኖስ ዘንድ ዜናው ተሰማ ይህንንም የከበረ አቡሊዲስን ይዞ በብዙ ግርፋትና ድብደባ አሠቃየው ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ በእግሮቹ ውስጥ ታላቅ ደንጊያ አሥሮ ከጥልቅ ባሕር የካቲት አምስት ቀን አሰጠመው። ማግሥትም ሲሆን የካቲት ስድስት በዛሬዋ ቀን የዚህ አባት ሥጋው በውኃ ላይ ተንሳፎ ተገኘ ደንጊያውም በእግሮቹ ውስጥ እንደታሠረ ነበር አንድ ምእመን ሰው ወስዶ በርሱ ዘንድ አኖረው በከበሩ ልብሶችም ገንዞ ሠወረው። ወሬውም በሮሜ አገሮች ሁሉ ተሰማ ንጉሡም ሊአቃጥለው ፈልጎት ነበር ግን አላገኘውም ያ ሰው ሠውሮታልና።
ይህም የከበረ አባት ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ ድርሳናትን ደርሶአል ከእርሳቸውም ስለ አካላዊ ቃል ሰው መሆንና ከኃጢአት በቀር በሥራው ሁሉ አንድ ባሕርይ ሰለ መሆኑ የደረሰው አለ። ዳግመኛም እግዚአብሔር የሚወደውን ስለ መሥራት የደረሳቸው ተግሣጻትና ትምህርቶች አሉ ስለ ቤተ ክርስቲያንም ሕግ ሠላሳ ስምንት መመሪያዎችን ሠርቷል እሊህም በሁሉ አብያተ ክርስቲያን ይገኛሉ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ጌታን ሽቱ ለቀባችው ማርያም የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው። ይችም ቅድስት አስቀድማ ኑሮዋን በዝሙት ያሳለፈች ኃጢአተኛ ነበረች። እርሷም ጐልማሶችን ወደርሷ ትማርካቸው ዘንድ በየራሱ በሆነ ሽልማትና ጌጥ ትሸለም ነበር።
በአንዲትም ዕለት እንደ ልማድዋ ተሸልማ አጊጣ ሽቱም ተቀብታ ፊቷን በመስታዋት ተመለከተች የጉንጯ ቅላትና ደም ግባቷ የዓይኗም ወገግታና ጥራት ማማሩን አይታ እያደነቀች አንድ ሰዓት ያህል ቆየች ከዚህም በኋላ በጎ ኀሳብ በላይዋ መጣ ሞትንና የዚህን ዓለም ማለፍ አሰበች።
የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስም ኃጢአተኞችን እንደሚቀበልና ኃጢኣትንም እንደሚአስተሰርይ ሰምታ ገንዘቧን ወስዳ የአልባስጥሮስን ሽቱ ገዝታ በስምዖን ዘለምጽ ቤት ለምሳ ተቀምጦ ሳለ ወደ ጌታችን ሔደች።
ከእግሩ በታችም ሰግዳ ያንን ሽቱ ቀባችው እግሮቹን በዕንባዋ አጠበችውና በራስዋ ጠጉር ወለወለችው ጌታችንም የፍቅርዋን ጽናት አይቶ ኃጢኣቷን በደሏን ተወላት የመንግሥት ወንጌልም በሚሰበክበት ይህን ያደረገችውን እንዲአስቡ አዘዘ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የከበሩ አቡቂርና ዮሐንስ ሦስት ደናግልም ከእናታቸው ከአትናስያ ጋር በሰማዕትነት ሞቱ። የእሊህም ስማቸው ቴዎድራ ትርጓሜው የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ሁለተኛዋ ቴዎፍና ትርጓሜውም የእግዚአብሔር ሃይማኖት ሦስተኛይቱም ቴዎዶክስያ ትርጓሜውም የእግዚአብሔር ምስጋና የእናታቸውም አትናስያ ትርጓሜው ሕይወት የሆነ ነው።
ይህም የከበረ አቡቂር ከታናሽነቱ በገድል ተጠምዶ የሚኖር መነኰስ ነው የከበረ ዮሐንስ ግን ከንጉሥ ሠራዊት ውስጥ ወታደር ነበር የእነርሱም ሀገራቸው እስክንድርያ ሲሆን የሚኖሩት በአንጾኪያ ነው በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም ፊት ቁመው ከእሊህ ደናግል ከእናታቸው ከአትናስያም ጋር በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ። እርሱም ከወዴት እንደሆኑ ጠየቀ ከእስክንድርያ አገር እንደሆኑ በተረዳ ጊዜ ወደዚያ ይወስዷቸው ዘንድ አዘዘ።
ወደ እስክንድርያ በደረሱ ጊዜ በመኰንኑ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ማሠቃየትንም በደከመ ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የከበረች አትናስያም ደናግል ልጆቿን በከበረ ስሙ ምስክር ሁነው ከሞቱ ለሰማያዊ ሙሽራ ክርስቶስ እነርሱ ሙሽሮቹ እንደሚሆኑ በማስረዳት ታጸናቸውና ታስታግሣቸው ነበር እንዲሁም የከበረ አቡቂር በከበረች ሐዋርያዊት ቴክላ ላይ የደረሰውን መከራ ይገልጥላቸውና ያጸናቸው ነበር።
ወታደሮችም ለባለ ሰይፍ በማከታተል አንዲቱን ከአንዲቱ በኋላ የሚያቀርቡ ሆኑ ከዚያም እናታቸውን የከበሩ አቡቂርና ዮሐንስንም ቆረጡ መኰንኑም ሥጋቸውን ለአራዊትና ለአዕዋፍ ይጥሉ ዘንድ አዘዘ ምእመናንም ሥጋቸውን በሥውር ወሰዱ በክብርም ገነዙአቸው የመከራውም ዘመን እስቲያልፍ በሣጥን አድርገው ሠወሩአቸው።
ከዚህም በኋላ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶላቸው ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከእርሳቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages