ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 19 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, April 2, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 19

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ዐሥራ ዘጠኝ በዚች እለት #ሐዋርያ_አርስጥቦሎስ ሐዋርያ አረፈ፣ #ቅዱስ_አስከናፍርና የሚስቱ ማርታ የልጆቹ አርቃድዮስና ዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ፣ #የሰባቱ_ሰማዕታት መታሰቢያቸው ሆነ፡፡


መጋቢት ዐሥራ ዘጠኝ በዚች እለት የሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር አርስጥቦሎስ ሐዋርያ አረፈ። እርሱም ጌታችን ከመረጣቸውና ከመከራው በፊት እንዲሰብኩ ከላካቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የተቆጠረ ነው።
በሃምሳኛው ቀን በዓልም መንፈስ ቅዱስ በላዮ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋራ ጸጋንና ኃይልን ተመልቶ ሕይወት በሚገኝበት በወንጌል ትምህርት ሐዋርያትን ተከትሎ በመሔድ አገለገላቸው።
ብዙዎችንም ወደ ድኀነት መንገድ መልሶ የክብር ባለቤት ወደ ሆነ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት አስገባቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጥምቆ የአምላክን ሕግና ትእዛዝ ከማስጠበቁ የተነሣ ነፍሳቸውን አዳነ።
አባቶቻችን ሐዋርያትም ይህን ቅዱስ አብራጣብያስ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት። ወደርሷም ሒዶ በውስጥዋ ወንጌልን ሰበከ ብዙዎቹንም በቀናች ሃይማኖት እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሳቸው።
በፊታቸውም ድንቆች ተአምራትን በማድረግ በሃይማኖት አጸናቸው ነገር ግን ከአይሁድና ከዮናናውያን ብዙ መከራ ደረሰበት።
ብዙ ጊዜም ወደ ፈረጆች አደባባይ ወስደው በደንጊያ ወገሩት ጌታችንም ከመከራው ሁሉ ጠብቆ አዳ ነው መልካም ተጋድሎውንም በፈጸመ ጊዜ በሰላም በፍቅር አረፈ። እነሆ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ሐዋርያ ጳውሎስ አስታውሶታል።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ደግሞ ቅዱስ አስከናፍርና የሚስቱ ማርታ የልጆቹ አርቃድዮስና ዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ። ይህም አስከናፍር ብዙ ገንዘብ ያለው ባለጠጋ ነው ለእግዚአብሔርም ሕግ የሚጠነቀቅ ነበር ልጆቹንም መንፈሳዊ ምክርና ተግሣጽ በማስተማር አሳደጋቸው።
በአደጉም ጊዜ የጥበብንና የተግሣጽን ትምህርት እንዲማሩ ተይሩት ወደምትባል አገር ሰደዳቸውና ትምህርታቸውን በፈጸሙ ጊዜ ሊድራቸውና በሰርጋቸው ደስ ሊለው ሽቶ ያመጡአቸው ዘንድ ላከ በመርከብም ሁነው ሲመጡ ማዕበል ተነሥቶ መርከቡ ተሰበረ። እግዚአብሔርም ከስጥመት አድኖ በየብስ አወጣቸው ዮሐንስ የተባለውን በአንድ ቦታ ማዕበሉ አውጥቶ ጣለው።
ዮሐንስም ተስፋ በቆረጠ ጊዜ ወደ ቅዱሳን ገዳም ሒዶ መነኰሰ። ስለ ወንድሙ ስለአርቃድዮስም እንደሞተ ተጠራጥሮ በጸም በጸሎትና በስግደትም ሥጋውን አደከመ። አርቃድዮስም ወደ ዮርዳኖስ ገዳም ገብቶ ከአንድ ቅዱስ አረጋዊ ሰው ዘንድ መንኲሶ እየተጋደለ ሦስት ዓመት ኖረ።
አስከናፍር ግን ልጆቹ በማዕበል እንደሰጠሙ በሰማ ጊዜ ከሚስቱ ጋራ ማቅ ለብሰው አመድ አንጥፈው እያለቀሱ ተቀመጡ። በአንዲት ሌሊትም አስከናፍር በሕልሙ ልጁ ዮሐንስን በራሱ ላይ ከዕንቊ የተሠራ አክሊል ተቀዳጅቶ መስቀል ይዞ አየው።
አርቃድዮስንም በኮከብ አምሳል የሆነ አክሊል በራሱ ላይ ደፍቶ አየ ከእንቅልፉም ነቅቶ ለሚስቱ ያየውን ነገራት። ከዚያም በኋላ በየአድባራቱና በየገዳማቱ የልጆቻችንን ወሬ እንመረምር ዘንድ ተነሺ እንሒድ አላትና ወደ ዮርዳኖስ ሒደው ከመጥምቁ ዮሐንስ ገዳም ደረሱ።
ልጃቸውን አርቃዴዎስን ያመነኰሰውን አረጋዊ አባትን አገኙት ችግራቸውን ነገሩት እርሱም የክርስቶስ ወዳጆች አትዘኑ ወደ ቤተ መቅደስ ስትመለሱ ልጆቻችሁን በሕይወት ታገኛላችሁ አላቸው ደስ እያላቸውም ተመለሱ።
ዮሐንስም በመስቀል በዓል ሊሳለም መጣ አረጋዊውም ጠርቶ ከአርቃድዮስ ከወንድሙ አገናኘው ተያይዘውም አለቀሱ። ደግሞ አስከናፍርን ከሚስቱ ጋራ ጠርቶ ከልጆቻቸው ጋራ አገናኛቸውና በላያቸው ወድቀው እየሳሟቸው አለቀሱ።
ከዚህ በኋላ ከዚያ አረጋዊ ዘንድ የምንኲስና ልብስ ለበሱ ሚስቱን ማርታንም ከሴቶች ገዳም አስገባት አገልጋዮችንም ነፃ አውጥቶ አሰናበተ። ገንዘቡንም ለድኆችና ለችግረኞች በተነ ከገዳምም ገብቶ በጾም በጸሎት ተወሰነ እንዲሁም የተባረኩ ልጆቹ በገደል በትሩፋት የተጠመዱ ሁነው ኖሩ ጌታችንንም ደስ አሰኙት በፍቅር አንድነትም አረፉ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን ደግሞ የሰባቱ ሰማዕታት መታሰቢያቸው ሆነ፡፡ እንርሱም የግብጽ ሰው እለእስክንድሮስና እስክንድሮስ ከጋዛ መንደር አጋብዮስ ከቡንጥስ ከተማ ኒሞላስ ከጠራልብስ ዲዮናስዮስ ሮሜሎስና ተላስዮስ ከግብጽ አውራጃዎች የሆኑ ናቸው።
እነርሱም በመንፈሳዊ ፍቅር ጸንተው ስለ ሃይማኖት ምስክሮች ሊሆኑ ተስማሙ። በፍልስጥዔም ውስጥ ወደ አለው ቂሣርያ ደርሰው በመኰንኑ ፍት ቆሙ።
በከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማመናቸውን ገለጡ መኰንኑም በጽኑዕ ሥቃይ አሠቃይቶ ገደላቸው። የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages