"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።
እንኳን ለክብር ባለቤት ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ ዐበይት በዓል አንዱ ለሆነው፤ ለዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት ለሆሣዕና በዓል በሰላም አደረሰን።
የሆሣዕና መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ በ፭ "ወእንዘ ሰሙን በዓለ ፋሲካ ቀርቡ አርዲኢሁ ለአምላከ ጽድቅ ኀበ ደብረ ዘይት ሙራደ ዐቀብ ሀገረ እግዚአብሔር ወተቀበልዎ ሕዝብ ብዙኀን አዕሩግ ወሕፃናት ነሢኦሙ አዕፁቀ በቀልት እንዘ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ተፅዒኖ ዲበ ዕዋል ቦአ ሀገረ ኢየሩሳሌም በትፍሥሕት ወበሐሤት ይሁቦሙ ኀይለ ወሥልጣነ። ትርጉም፦ "በፋሲካ ሰሞን የጽድቅ አምላክ ደቀ መዛሙርት የእግዚአብሔር ሀገር ወደምትኾን ወደ ደብረ ዘይት አቅራቢያ ቀረቡ፤ ብዙ ሕዝብ፣ ብዙ አዛውንትና ሕፃናት የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ሆሣዕና በአርያም እያሉ ተቀበሉት፤ ኀይልን ይሰጣቸው ዘንድ በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ በፍጹም ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው ላይ።
ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ነው፤ "ሆሻአና" ሲባል ትርጒሙም "አቤቱ አሁን አድን" ማለት ነው። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ገብቶ ቤተ መቅሱን በአህያ ግልገል ተቀምጦ በመዞር ሆሣዕና እያሉ እንዲያመሰግኑት አድርጓል። ይህም ስለርሱ እየአንዳንዳቸው በዘመናቸው ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው።
ያዕቆብ በክርስቶስ ስለ ተመሰለው ስለ ልጁ "ይሁዳ አህያውን ዘይት ዕንጨት ላይ ያሥራል ውርንጫውንም በወይን አረገ" አለ። ዘካርያስም "ጽዮን ልጅ አትፍሪ እነሆ ንጉሥሽ በአህያ ግልገል ተቀምጦ ይመጣል" አለ።
ኢሳይያስ "ንጉሥሽ ጻድቅ የዋህ የሆነ ይመጣል ዋጋውም ከእርሱ ጋራ ነው ሥራውም በፊቱ የተገለጠ ነው በአህያ ግልገልም ላይ ይቀመጣል" አለ።
አብርሃምም የሰሌን ዝንጣፊ ይዞ መሠውያውን በዞረ ጊዜ "ይችን ዕለት ተድላ ደስታ የሚደረግባት የእግዚአብሔር በዓል" ብሎ ጠራት።
ዳዊትም "ከሕፃናትና ከልጆች አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህ" አለ። ሰሎሞንም "የሕፃናት አንደበታቸው የተቃናች ሆነች" አለ። ሁለተኛም "ልጆችና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ይጫወታሉ ምርጒዛቸውም መትከያዎችሽን አስፍተሽ ድንኳኖችሽን ዘርጊ" ያለም አለ።
ይህንንም የትንቢት ነገር ለመፈጸም በከረ ወንጌል እንተጻፈ ጌታ በአህያዋና በውርንጭላዋ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ወደ ኢየሩሳሌም ሊገባ በቀረበ ጊዜ ከደብረ ዘይት አጠገብ ከምትሆን ቤተ ፋጌ ደረሰ ደብረ ዘይት ወደሚባል ቢታንያም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛመቱን ሁለቱን ላከ። "ወደ ፊታችሁ ወዳለ አገር ሒዱ በገባችሁም ጊዜ ሰው ያልተቀመጠበት አህያ ግልገል ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ለምን ትፈቱታላችሁ የሚል ሰው ቢኖር ጌታው ይሻዋል" በሉ። የተላኩትም በሔዱ ጊዜ እንደነገራቸው አገኙ። የአህያውም ግልገል ፈቱ ጌቶቹም "ለምን ትፈቱታላችሁ" አሏቸው። "ጌታው ይሻዋል" አሉ። ወደ ጌታ ኢየሱስም ይዘውት ሔዱ ልብሳቸውንም በአህያው ግልገል ላይ ጐዘጐዙ ጌታችንም አስቀመጡት። ቅጠል ቆርጠው በመንገድ ላይ የጐዘጐዙ ብዙዎች ናቸው። ልብሳቸውንም በመንገድ ላይ ያነጠፋ አሉ። በፊትም በኋላ ይሔዱ የነበሩት በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ መድኃኒት ነው ብለው አሰምተው ተናገሩ። በእግዚአብሔር ስም የምትመጣ የአባታችን ዳዊት መንግሥትም የተባረከች ናት።
ጌታ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ገባ ሕዝቡም ሁሉ አዩት በመሸም ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ። በነጋውም ከቢታንያ በወጣ ጊዜ ተራበ። በሩቅም ቅጠል ያላትን በለስ አየ። በርሷ ፍሬ ያገኝ እንደሆነ ሊያይ ሔደ ወደርሷም በደረሰ ጊዜ ከቅጠል ብቻ በቀር ያገኘው የለም የበለስ ወራት አልነበረምና "ዘላለም ካንቺ ፍሬ የሚበላ አይኑር" አላት። ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ።
ወደ ኢየሩሳሌም ደርሶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ በምኵራቡም ግቢ የሚገበያዩትን ያስወጣ ጀመረ የለዋጮችንም ሰደቃቸውን ገለበጠ ርግብ የሚሸጡትንም ወንበራቸውን። ወደ ምኵራብ ለንግድ ገንዘብ ይዘው እንዳይገቡ ከለከለ።
"ቤተ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይሁን የሚል መጽሐፍ ያለ አይደለምን እናንተ ግን የሌቦችና የወንበዴዎች ዋሻ አደራጋችሁት" ብሎ አስተማራቸው።
ቅዱስ ዮሐንስም እንዲህ አለ "አልዓዛርን ከሙታን ለይቶ ካስነሣው በኋላ። በነጋውም እሑድ ለበዓል የመጡ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ በሰሙ ጊዜ። የሰሌን ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ከኢየሩሳሌም ፈጥነው ወጡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ከአርያም የተገኘ መድኃኒት የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው" እያሉ እየጮኹ ተቀበሉት።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአህያ ግልገል አገኘ።ተቀመጠበትም እንደ ተጻፈ እንዲ ሲል። "የጽዮን ልጅ አትፍሪ እንሆ ንጉሥሽ በአህያ ግልገል ተቀምጦ ይመጣል"። አስቀድሞ ግን ደቀ መዛሙርቱ ይህን ነገር አላወቁም ነበር ጌታ ሳይሰቀል። ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ይህ የተጻፈ ስለ እርሱ እንደሆነ ያን ጊዜ አወቁት እንጂ እንዲህም አደረጉለት።
አልዓዛር አልዓዛር ብሎ ከሙታን ለይቶ እንዳስነሣው ባስነሣው ጊዜ ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መሰከሩለት። ስለዚህም ሕዝቡ አመኑበት። ያደረገውን ተአምራት ሰምተወልና የሕፃናቱንም ምስጋና ደግሞ አልዓዛርን ማስነሣቱን። የካህናቱ አለቆችና ፈሪሳውያን ግን እርስ በርሳቸው "የምታገኙት ረብሕ ጥቅም እንደሌለ አታውቁምን እንሆ ሰው ሁሉ አመነበት" አሉ።
ቅዱሳን ማቴዎስና ማርቆስ የሰሌንን ነገር አላወሱም ሌሎች ከእንጨቶች ቅጠሎችን እየቆረጡ በመንገድ ውስጥ ጐዘጐዙ አሉ እንጂ።
ቅዱስ ሉቃስም ቅጠልን ወይም ሰሌንን አላወሳም ሲሒዱ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር አለ እንጂ።
ቅዱስ ዮሐንስ ግን ለብቻው "ከኢየሩሳሌም ከሰሌን ዛፍ ላይ ዘንባባ ቆርጠው ያዙ" አለ። ሰሌንም በኢየሩሳሌም አልነበረም ጌታችን ሕፃን ሁኖ ሳለ ወደ ግብጽ በወረደ ጊዜ ከእናቱ ቡርክት ቅድስት ከሆነች ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጋር እስሙናይን ከሚባል አገር ደረሱ ከዚያም ሰሌን አገኙ። ጌታችንም ከሥርዋ ተነቅላ ሒዳ በደብረ ዘይት ላይ እንድትተከል አዘዛት ያንጊዜ ወደ አየር ወጥታ በረረች ሒዳም በዚያ በደብረ ዘይት ተተከለች ከእርስዋም ወስደው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀበሉት።
ጌታችንም የሆሣዕናን ዑደት በአሳየ ጊዜ የአይሁድ ወገን ቅናት ይዟቸው በሚገድሉት ገንዘብ ምክንያት ፈለጉ። ለእርሱም ምስጋና ይሁን በእኛ ላይም ይቅርታው ቸርነቱ ይደረግልን ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፦ የመጋቢት 22 ስንክሳር።
No comments:
Post a Comment